በኃያል ዓለማየሁ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፊልም ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረውን 3D የተባለውን የፊልም ቴክኖሎጂ ለፊልም አፍቃሪው ኅብረተሰብ ዕይታ ያበቃው ኤድና ሞል ሕንጻ ላይ የሚገኘው ማቲ መልቲፕሌክስ ሲኒማ፣ ከወራት በፊት ቴክኖሎጂውን በማስመጣት 3D ፊልሞችን ማሳየት መጀመሩ ይታወቃል፡፡
በተሻለ ሁኔታ በፊልሙ ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያትን በተመልካቹ አካባቢ እንዳሉ አስመስሎ የሚያሳየው የ3D ፊልም ጥበብ፣ በአገራችን መታየት ከጀመረ ከስድስት ወራት በኋላም አግራሞት መፍጠሩ ቀጥሏል፡፡
ይህንኑ በመገንዘብ ይመስላል የ3D የፊልም ወረት ሳያበቃ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ዕድገት ወደ አዲስ መልክ የቀየረውን 4D የተባለውን የሲኒማ ቴክኖሎጂ በአገራችን ለማስተዋወቅ፣ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ዋዜማ ከቻይና ወደ ቀዬው የተመለሰው ቴዎድሮስ ሽፈራው ቆርጦ የተነሳው፡፡
የ4D የሲኒማ ጥበብ በ3D ቴክኖሎጂ በመታገዝ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ወደ አዲስ መልክ የቀየረው ሲሆን፣ በ4D ሲኒማ ቤት ፊልም ሲመለከቱ በፊልሙ ውስጥ የሚከሰተውን ክስተት በነባራዊው ዓለም በአምስቱ የስሜት ህዋሳት ስሜቶች ይሰማዎታል፡፡ ለምሳሌ በፊልሙ ዝናብ ሲዘንብ ዝናቡ የወረደብዎት ይመስልዎታል፣ ቅዝቃዜም ይሰማዎታል፡፡ በፊልሙ ውስጥ መልካም መዓዛ ወይም መጥፎ ሽታ ያለው ነገር ከታየ፣ መልካም መዓዛ ወይም መጥፎ ሽታ ይሸትዎታል፡፡ ከዚህም በላይ በፊልሙ ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያትን ሁሉ በዙሪያዎ ሆነው ይታይዎታል፡፡
ሮዜታ ሜትሮ ፕላዛ የተሰኘውና በቅርቡ ግንባታውን ከፍሬንድሺፕ ሕንጻ ፊት ለፊት የሚጀመረው ባለ 16 ፎቅ ሕንጻ ዲዛይን፣ በአዲስ አበባ ከሚገነቡትና በአብዛኛው የአራት መአዘን ቅርጽ ያላቸው ሕንጻዎች የተለየ ነው፡፡ ሕንፃው የ4D ሲኒማ ቤትንም ያካትታል፡፡
ሕንጻው ከመሬት በታች ባለሦስት ደረጃ መኪና ማቆሚያ የሚኖረው ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ወለል እስከ አምስተኛው ፎቅ ክፍት የሆነ የገበያ አዳራሽ ይኖረዋል፡፡ ሕንጻው በውስጡ ሦስት ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶችን ያካትታል፡፡ ከአምስተኛው ፎቅ በላይ በኮከብ ደረጃ አገልግሎት የሚሰጥ 150 ክፍሎች ያሉት ሆቴል ይኖረዋል፡፡
የአየር ትራንስፖርት፣ የእምነበረድ አምራች ኩባንያ፣ የሪል ስቴት ግንባታና የተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን የሚመሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከሮዜታ ሜትሮ ፕላዛ ግንባታ በስተጀርባ ሰፊ ዕቅድ አንግበዋል፡፡
‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቦሌ አየር ማረፊያ ወደ ሌላ አገር ለመብረር እዚህ በጊዜያዊነት የሚያርፉት ተጓዦች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የስታር አሊያንስ አባል በመሆኑ የእነዚሁ ተጓዦች ቁጥር የባሰ እየጨመረ ነው የሚሄደው፤›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ 150 ክፍሎች የሚኖሩትና በሜትሮ ፕላዛ ላይ የሚገነባው ሆቴል እነዚህን ተጓዦችና ሌሎች ቱሪስቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
አየር መንገዱ እነዚህን ተጓዦች ለማስተናገድ የራሱን ሆቴል በመሥራት ላይ ቢሆንም፣ ሁሉንም በማስተናገድ አቅም እንደሚያንሰው የሚገልጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ እነዚህ ተጓዦች በምቹ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚችሉ አውቶቡሶችና ታክሲዎችን ሆቴሉ የሚያሰማራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሆቴሉም ከቦሌ አየር ማረፊያ ሁለት ደቂቃ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑም፣ ለእነዚሁ ተጓዦች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አቶ ቴዎድሮስ ይገልጻሉ፡፡
ወለሉን ጨምሮ በአምስቱ ፎቆች ላይ የሚኖሩት እያንዳንዳቸው አንድ ሺሕ ካሬ የሚኖራቸው የገበያ አዳራሾች ብዙ ገንዘብ ይዘው፣ ነገር ግን የያዙትን ገንዘብ ማጥፋት የሚችሉበት ቦታ ባለመኖሩ ገንዘቡን ይዘው የሚመለሱትን ተጓዥ መንገደኞች ቀልብ የሚስቡ እንደሚሆኑ ከአቶ ቴዎድሮስ ገለጻ መረዳት ይቻላል፡፡
እነዚህኑ ተጓዥ መንገደኞችና ቱሪስቶችን በሮዜታ ሜትሮ ፕላዛ ቆይታቸው የሚያዝናኑ ሰባት ሲኒማ ቤቶች ሲኖሩ፣ ከሰባቱ ትልቁን ሲኒማ ቤት የ4D ሲኒማ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ሌሎቹም እንደ ሁኔታው የዘመኑን የላቀ የሲኒማ ቴክኖሎጂ የያዙ ሲኒማ ቤቶች እንደሚሆኑ የሜትሮ ፕላዛው ዕቅድ ያሳያል፡፡
እነዚሁ ሲኒማ ቤቶች በአንድ ጊዜ እንደ ደንበኞች ምርጫ የተለያዩ ፊልሞች የሚያሳዩ ይሆናሉ፡፡
የሮዜታ ሜትሮ ፕላዛ ዲዛይን የተሠራው ከአሜሪካን አገር በተመለሱ ኢትዮጵያውያን አርክቴክቸሮች ሲሆን፣ ግንባታውም በቻይና ኩባንያ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በዕቅዱም መሠረት ሕንጻ እ.ኤ.አ. በ2012 አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡
ሮዜታ ሜትሮ ፕላዛ እራሱን የቻለ በውስጡ የተለያዩ የንግድ ዓይነቶችን ያካተተ ሰፊ የንግድ መስክ ቢሆንም፣ አቶ ቴዎድሮስ ከዚሁ የንግድ መስመር ውጪ የአየር ትራንስፖርት፣ የሪል ስቴት፣ የእመነበረድ ማምረቻና በቻይና አገር የሚገኝ የንግድ ማዕከልን የሚመሩ ዲያስፖራ ናቸው፡፡
‹‹እዚህ አገር በመካሄድ ላይ ያሉትን የሪል ስቴት እንቅስቃሴዎችን በማይበት ወቅት በቻይና አገር ቆይታዬ ከተገነዘብኩት ሁኔታ በመነሳት የተሻለ ነገር መሥራት እንደምችል በማመኔ 101 ቪላ ቤቶችን ሰርቻለሁ፤›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከእነዚሁ ውስጥ 30 የሚሆኑትን መሸጣቸውን አልሸሸጉም፡፡
እኚሁ ግለሰብ የሚያስተዳድሩት የእምነበረድ ኩባንያ በዓመት እስከ አራት ሺሕ ካሬ እምነበረድ የሚያመርት ሲሆን፣ ፋብሪካውም በዓመት እስከ 10 ሺሕ ካሬ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡
ቴዲ አየር በመባል የሚታወቀውና በአቶ ቴዎድሮስ የሚተዳደረው ኩባንያ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን በሁለት አነስተኛ አይሮፕላኖች የአየር ትራንስፖርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ይኸው ኩባንያ ሴስና ከተባለው የአሜሪካ አነስተኛ አይሮፕላን አምራች ኩባንያ ሁለት ተጨማሪ አነስተኛ አይሮፕላኖች ለመግዛት በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡
አቶ ቴዎድሮስ የሚመሩትንና በቻይና የሚገኘውን የንግድ ማዕከል ተመልክቶ ከመረመረ በኋላ ለአውሮፕላኖቹ መግዣ የሚሆን የባንክ ብድር ለማግኘት የሚያስችል ዋስትና ለመስጠት የአሜሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የተስማማ ሲሆን፣ ይህንኑ ዋስትና ለማግኘት ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስለ ቴዲ አየር የንግድ እንቅስቃሴ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም አቶ ቴዎድሮስ አይሮፕላን ለማብረር የሚያስችላቸው ትምህርት ለመውሰድ በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡


