(ሀ) ኮንዶምና ማስታወቂያው
ምሽት ላይ በቴሌቪዥን የሚታይ የኮንዶም ማስታወቂያ ነው፡፡ ማስታወቂያውን የምትሠራው እንስት ቡና እየቆላች የኮንዶሙን ስም ስትጠራ ያስተዋለችው እናቴ፣ ‹‹ይሄ ነገር እንዴት ነው የቡና ቅመም ሆነ እንዴ!›› ብላ ተችታለች፡፡
(ሁ) ሦስቱ ‹‹መ››ዎች
አንዳንድ ጊዜ በአንዳንድ መምህራን ተሠሩ ተብሎ የምንሰማቸው ስህተቶች አሉ፡፡ ስለ ጾታ ግንኙነት፣ ስለአባላዘር በሽታና ስለመሰል የጤና ጉዳዮች ሲያስተምሩ ለማን፣ ምን ማስተማር እንዳለባቸው፣ ምን ዓይነት የማስተማርያ ዘዴ መጠቀም እንዳለባቸው ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡
ለሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ስለ ሦስቱ የ‹‹መ›› ሕጎች የሚያስተምሩ መምህራን አሉ ተብለው ይታማሉ፡፡ ከሚታሙ መምህራን መካከል አንዱ ታዲያ ስለ ሦስቱ የ‹‹መ›› ሕጎች ሲያስተምር የሚከተለው ነገር ገጠመው አሉ፡፡
‹‹ተማሪዎች ሦስቱን የ‹መ› ሕጎች ታውቋቸዋላችሁ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ተማሪዎቹም ‹‹ቲቸር! ተሳስተዋል፤ ሦስት ‹ሀ› እንጂ ሦስት ‹መ› የሚባል የለም›› ብለው እርፍ፡፡
(ሂ) መሪ ቃል
በታላቁ ሩጫ ላይ የሆነ ነገር አለ፡፡ አንዱ ወጣት ከሩጫ መልስ ሜዳልያውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ መንገድ ላይ አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ያገኘዋል፡፡
‹‹እሺ! በቅድሚያ ስምህን ብትነግረን?›› ይለዋል፤ ወጣቱ ይናገራል፡፡
‹‹የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ መሪ ቃል ምን እንደሆነ ብትነግረኝ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣
‹‹እኔንጃ! እኔ መሃል አካባቢ ነበርኩ፡፡ መሪው ማን እንደሆነ አላየሁም›› ብሎ መለሰ፡፡
(ሃ) ምሥጢር ብሎ ዝም
ሰውየው መጠጥ ቢጤ እየወሳሰደ ከመሥርያ ቤት ባልንጀሮቹ ጋር እየተዝናና ለመጫወት መሸታ ቤት ጎራ ይላል፡፡ ከባልንጆሮቹ ጋር ብርጭቆ ጨብጦ እየተጫወተ ሳለ፣ መቼም ሥጋ ደካማ ነው፤ ከአንዲት አስተናጋጅ ሞንዳላ ሰውነት ላይ ዓይኑ ያርፋል፡፡ ቀልቡም ከባልንጀሮቹ ጨዋታ ላይ እንቢኝ ብሎ ወደ ሴቲቱ ይሸፍታል፡፡ ሥጋ ሲፈጠር ደካማ አይደል!?
ባልንጀሮቹ የሚያውቁት በመሥርያ ቤቱ በሚያሳየው የሥራ ትጋት እንጂ ይህ አመሉን ባለመሆኑ፣ የሥጋውን ጥያቄ በገሃድ ከውል እንዳያደርስ ክፉ ደንቃራ ሆነበት፡፡ ምን ያድርግ? ምንስ ብልሃት ይፍጠር? አሰበ፣ አሰበ፣ አሰበ፡፡ ማሰብ መቼም ደግ ነው አንድ ብልሃት መጥቶ አእምሮው ደጃፍ ላይ ግትር አለለት፡፡ ድራፍት ቀጂውን በጥቅሻ ጠራው፡፡ ቀልጣፋው ድራፍት ቀጂ ከተፍ አለ፡፡ ባልንጀሮቹ በማይሰሙት፣ ዝግ ባለ ድምፅ ‹‹ያቺን መልከ መልካም ሴት አነጋግርልኝ፤ ቀስ ብለህ በኮድ (በምሥጢር) ለኔ ትነግረኛለህ፤›› አለው፡፡ ሴቲቱን የሚገኛኝበት ጊዜ እየናፈቀው፡፡ ድራፍት ቀጂው እሺ ብሎ ወደ መጣበት ሔደ፡፡
ሰውየው ከባልንጀሮቹ ጋር እየተጫወተ የድራፍት ቀጂውን መልዕክት በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ድራፍት ቀጂው ካለበት ሆኖ ‹‹ጋሽዬ!›› ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተጣራ፡፡ ‹‹አቤት!›› አለ ሰውዬው እሱን መሆኑን ሳይጠራጠር፡፡ ድራፍት ቀጂው ድምፁን ዘለግ አድርጎ፣ ‹‹ያሉኝን አነጋግሬው እርጉዝ ነኝ! አልሠራም፤›› ብሏል ብሎ እርፍ፡፡ በእርሱ ቤት በምሥጢር መናገር ነው፡፡ ሰውዬው ምን ይዋጠው!
(ሄ) ተረት ተረት
‹‹እኔ በዚህ ወንዝ ተሰላችቻለሁ፤›› አለች አንድ ትንሽ ዓሣ ለታላቋ እየተማረረች፡፡ ‹‹እዚህ ያለው ሕይወት ለውጥ አይታይበትም፤ ውኃው ያው፣ ጓደኞቼ እነኛው፣ የዕለት ከዕለት ምግቤም ያው ነው፤ . . . ሳስበው ሌላው ወንዝ የሚያስደስት ይመስለኛል፡፡››
ትልቋ ዓሣ ልብ ብላ ካዳመጠች በኋላ መለሰች፤ ‹‹ሌላው ወንዝ ማስደሰቱን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እዚህ ብዙ ጓደኞች አሉን፡፡ የምግብም ሆነ የውኃ እጥረት የለብንም፤›› ትንሿ ዓሣ ለታላቋ መልስ ቁብ ሳትሰጥ፣ በአቅራቢያው ያለውን ኩሬ ለማየት ጓጉታ ወደ ወንዙ ዳርቻ እመር ብላ ወጣች፡፡ ‹‹ይኸዋ! በሕይወቴ ሙሉ ስመኘው የቆየሁት ይህን ነበር፤›› እንዳለች አዳለጣትና አፉን በከፈተ ግዙፍ ዓሣ አፍ ውስጥ ተከረቸመች፡፡
(መላ ጤና ይስጥልኝ፣ኅዳር 2003)
* * * * *
ሒልተንን በ15 ብር
ለአንድ መንገደኛ እውነተኛ የሆነውን የኢትዮጵያን ምግብ በያይነቱ ለማግኘት አዲስ አበባ በጣም ተስማሚ ሥፍራ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ገበታው ዓይን የሚስብና ከፍታው ጉለበት የሚደርስ ከፍ ያለና ከሸንበቆ የተሠራ ነው፡፡ በዚህም ላይ ነጣ ያለ የተነባበረ እንጀራ ይዘረጋል፡፡ ይህም በአንድ ፊት የለሰለሰ በሌላ ፊት ደግሞ በሙሉ ጠቃጠቆ ዓይን ያለው እንደመሆኑ ዘወትር የሚያስታውሰኝ ጊዜ ያለፈበትን የፒንግ ፖንግ መጫወቻ ነው፡፡ በእንጀራውም ላይ በብዙ ዓይነት ቅመም የተሠራ ወጥ በያይነቱ ይጨመርበታል፡፡ ቀጥሎም እንጀራው እየተቆረሰ በወጥ ይጠቀሳል፡፡ ለመጠጥም የሚቀርበው ወርቅማ ቀለም ያለውና ከማር የሚጣል ጠጅ ነው፡፡
በአዲስ አበባም በየትም ዓለም የሚገኘው ሒልተን አለ፡፡ የሒልተንን ሆቴል የማይፈቅዱት ቀድሞ ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት የነበረውንና ከኦሊምፒክ ጋር የሚመጣጠን መዋኛ፣ እንዲሁም ሰፊ መስክ ያለውን የግዮንን ሆቴል ይመርጣሉ፤ ለአልጋና ቁርስ 15 ብር ያህል ይከፈላል፡፡ ከዚህም ሌላ በማዕከላዊ ሥፍራ የሚገኘውና በአዲስ አበባ ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የምግብ አዳራሽ ያለው ዋጋውም መለስ የሚለው የኢትዮጵያ ሆቴል ነው፡፡ እንዲሁም ሆቴል አፍሪካና ዋቢ ሸበሌ ተመሳሳይ ዋጋ የሚጠይቁና ጥሩ ሆቴሎች ናቸው፡፡ የቀድሞው የራስ ሆቴል ደግሞ ለገንዘብ አወጣጥ ለአልጋና ቁርስ 7 ብር እንደመከፈሉ እጅግ ጥሩ ሲሆን፣ በእንግዳ ማረፊያውም ክፍል ሞላው አዲስ አበባ ይሰበሰብበታል፡፡
በአሥመራ የሚገኘውና ቻዎ የሚባለው ሆቴል በአዲስ አበባ ከሚገኘው ከራስ ሆቴል ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢምፔሪያልና የኒያላ ሆቴሎች ሁለቱም እጅግ ተስማሚ ናቸው፡፡ ለአልጋና ቁርስ የሚከፈለው 11 ብር ነው፡፡
ይሁንና ሌላ ሥፍራ በሚጐበኝበት ጊዜ የሆቴሎች ምርጫ ለማድረግ አይቻልም፡፡ በርግጥ በአሜሪካውያን የኑሮ ደረጃ ሲታይ ለአንድ ሰው በቀን የሚደረገው ማዕከላዊ ወጭ ወደ 14 ብር የሚጠጋ እንደመሆኑ የሚከፈለው ዋጋ ቀለል ያለ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በጣም በሚያምረውና ብቻውን በላሊበላ በሚገኘው ይኸውም ‹‹በሰቬን ኦሊቭስ ሆቴል›› ውስጥ ውኃና የኤሌክትሪክ መብራት ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ግን ምግቡ ጥሩ ነው፡፡ ጐንደር የሚገኘው የእቴጌ ሆቴል ደግሞ ያማረ የመዋኛ ኩሬ ቢኖረውም፣ በዚሁ ኩሬ ውስጥ ውኃ ፈጽሞ ታይቶ አያውቅም፤ ጐንደር ካመት ዓመት የሚቆይ የውኃ ችግር አለባት፡፡
(የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል፤ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች አስተያየት፣1966)
* * * * *
ደሴ
‹‹አረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ
አለቀልሽ ልቤ ተንዶ ተንዶ
ደሴ ደረቅ ወይራ ገራዶ ቢለን
የስንቱ መወከል ለከፈኝ እኔን፡፡››
በማለት ስንኝ የተቋጠረላት ደሴ ከተማ በሰንሰለታማ ተራራና ጉብታዎች የተከበበች ከተማ ስትሆን፣ በ1875 ዓ.ም. በንጉሥ ሚካኤል ተቆረቆረች፡፡ ንጉሡ ከተማዋን የቆረቆሩበት ዋና ምክንያት ለስትራቴጂክ ቦታነት በመጠቀም ጠላቶቻቸውን ለመከላከል አስበው እንደሆነ ከታሪክ ድርሳናት እንረዳለን፡፡ ደሴ ከተማ 395.7 ጋሻ ወይም 15829 ሔክታር የቆዳ ስፋት ያላት ለአዲስ አበባ፣ ለትግራይ፣ ለአፋር፣ ለጎንደርና ለጎጃም መተላለፊያ በርና የንግድ ማዕከል ናት፡፡ ከባህር ጠለል በላይ በ2500 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ደሴ የአየር ንብረቷ ደጋማና በተፈጥሮ ውኃዋ ጥራትና ጣዕም የታደለች ለኑሮ ተስማሚ የውበት የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት ከተማ ነች፡፡
(የደሴ ማስታወቂያ ጽ/ቤት፣ደሴ ከተማ በለውጥ ጎዳና፣2002)
* * * * *
የውጤታማ ጋብቻ ልዩ ባሕርያት
ፍቅር - ፍቅር የጋብቻ ሞተር ዘይት፣ ነዳጅ ከመሆንም አልፎ ሞተሩ ራሱ ነው፡፡ ፍቅር የሌለበት ጋብቻ ዕድሜ አይኖረውም፡፡ ውኃ እንዳጣ አትክልት ይጠወልጋል፤ - ይደርቃል፡፡ ፍቅር ያለበት ጋብቻ በዕድሜው እረጅም፣ በጉልበቱ ጠንካራ በመሆኑ ይዘልቃል፡፡
ስለራስ ያለ ዕውቀት - ራስን ማወቅ - ስሜትን መረዳት - ፍላጎትና ዓላማን በግልጽ ማወቅ ጥንካሬና ድክመትን መለየት፣ ሰብዕናችንን እና ለሥራ ያለንን ፍላጎት ለራሳችን ተረድተን ለሌሎችም ግልጽ እንዲሆን ማድረግ፡፡
ትክክለኛ ተጓዳኝ - ለጋብቻ የምንመርጣቸውን በደንብ ካወቅናቸውና ጥምረታችንን ከመሠረትን ጋብቻችን ይሰምራል፡፡ ስንመርጥ ግን የምንመርጠውን ማወቅ ይገባናል፡፡
ጓደኝነት - አንዱ ሌላውን መውደድ አለበት፡፡ ጥሩ ጓደኝነት ካለ ፍቅር እንኳ ቢቀንስ ትስስሮሹ ያለመከዳዳት እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ መግባባት - መናበብ ይኖራል፡፡ መበለጥም አለ፡፡
መነጋገር - በትንሹም በትልቁም ነገር ሳያሰልሱ መነጋገር፡፡ ቀጥተኛ መቀራረብን የሚያስገኝ መነጋገር ቅሬታና ቅራኔ እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡ ጨዋነት የተሞላበት፣ ሐቅ ላይ የተመረኮዘ መነጋገር ልብን ከልብ፣ አእምሮን ከአእምሮ ያቆራኛል፡፡ ሁለቱም (ባልና ሚስቱ) ለንግግር ተዘጋጅተው መገኘት አለባቸው፡፡ ቀጥተኛ በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሁለት በኩል መነጋገር ትዳርን ከብረት ያጠነክራል - ችግሮች በጊዜ ስለሚቀነሱ ስለሚወገዱ፡፡ መነጋገር በጋብቻም ሆነ በሌላ ሕይወት የመጀመሪያ ደረጃን ይዞ ቢገኝ ለውጤት ያበቃል፡፡
(አሸናፊ ዘድባብ፤ፍቅር እና ወሲብ፣1992 ዓ.ም.)
* * * * *
የመንፈስ ውድድር
ከውድድር ዓይነቶች መካከል አንዱ በሥነ ጽሑፍ የሚገለጸው የመንፈስ ውድድር ነው፡፡ የው መንፈስ የቱን ያህል ፈጣሪና ወላድ (Creative, Productive) መሆኑን ለማወቅ የሚቻለው በውድድር ነው፡፡ ‹‹ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደሳት›› አለ ደራሲ፡፡ የሰውን መንፈስ እንደ እሳት የሚያጋግለው የሚያሟሙቀው ውድድር ነው፡፡ ውድድር ከሌለ ቆሞ መቅረት ይመጣል፡፡ መንፈስ ወደ ብቸኝንት፣ ወደ ብሕትውና ከተመለሰ በራሱ ክበብ ውስጥ ተወስኖ ይቀራል፡፡ መካን ይሆናል፡፡ ምንም ሊያስገኝ አይችልም፡፡ እርስ በርሱ የሚፋጭ ብረት እንኳ ስለት ያስገኛል፡፡ በዚህ ሐሳብ በመመራት የቀድሞ ዘመን ግሪኮች ውድድርን በመንፈስም ረገድ በመቀጠላቸው በመላው ዓለም ሥልጣኔ ውስጥ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው የሥነ ጽሑፍ ድርሰቶች ወይም በተለይ ስማቸው ትረጀዲዎችና ኮመዲዎች አስገኝተዋል፡፡ ወደ ቀድሞ ዘመን ሁናቴ እንዛወርና እስኪ በዓይነ ልቡናችን እንመልከት፡፡
ቴአትሮን ይባላል፡፡ የትዕይንት ቦታ ማለት ነው፡፡ በአንድ በኩል ዘቅዘቅ ያለ ክብ ቦት ነው፡፡ ከላይ እስከታች ድረስ ከአሥር እስከ ሃያ ሺሕ ሰዎች የሚያስቀምጡ የእብነ በረድ ደረጃዎች አሉ፡፡ በማለዳ ገና ጎሕ ሲቀድ ብዙዎች ተመልካቾች ቦታ ለማግኘት ይሽቀዳደማሉ፡፡ የመጨረሻው የቅኔ ወይም የድራማቲክ ጥበብ ውድድር የሚደረግበት ቀን ነው፡፡ ሦስት ባለቅኔዎች ቀርበዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ ኤስሂሎስ፣ ሶፎክሊስ፣ ወይም ኤቭሪፒዲስ ሊሆን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ አራት አራት ድርሰቶች ወይም ድራማዎች ይዘዋል፡፡ ሃያ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ይመለከታሉ፡፡ በትያትሩ መጀመሪያ ወንበሮች ላይ ሊቃውንት፣ ከፍተኞች የከተማ ባለሥልጣኖች ካህናት ተቀምጠዋል፡፡ እነ ኢፊጌንያን፣ ኤሌክትራን፣ ኢዲፑስን የሚያካክሉ አሥራ ሁለት ድራማዎች ለዚህ ቀን ቀርበዋል፡፡ በነዚህ በድራማዎች ውስጥ የሰው ትልቅነትና ትንሽነት፤ የሐሳቡ ርቀትና ስህተት፣ የስሜቱ ንጹሕነትና ርክሰት፣ ድቀቱ፣ ትንሣኤው፣ ደስታው፣ ኀዘኑ፣ ልቅሶው፣ ሳቁ፣ ተስፋው፣ ናፍቆቱ፣ ማግኘቱ፣ ማጣቱ፣ ባንድ ቃል የሰው ነፍስ የምትዋኝበት ባሕር እንደመነጽር በሚያጎላው በባለ ቅኔው ዓይን ተመርምሮ ይቀርባል፡፡ እነዚህን የሐሳብና የስሜት ዓለማት በመመልከት ቀኑን ሙሉ ሳይደክሙ ያሳልፋሉ፡፡ በመጨረሻ የትኛው ደራሲ ይበልጥ አስደስቶአቸው፣ ማርኮአቸው ይሆን፡፡ ነገሩ ቀላል አይሆንም፡፡ ግን ላንዱ ግድ መወሰን አለባቸው፡፡ ከብዙ ወዲያና ወዲህ በኋላ ወደ አንዱ ያዘነብላሉ፡፡ ‹‹ብዙኀን ይመውዑ፡፡›› (ብዙኃን ያቸንፋሉ) ነገሩ በድምፅ ብልጫ ይወሰናል፡፡ አንዱ ባለቅኔ ያቸንፋል፡፡ የቱን ያህል ክብር ያገኛል፡፡ የጥበብ ቤዛዎች የሆኑ አማልክት አሉ፡፡ ሙሴ ይባላሉ፡፡ የነዚህ አማልክት እንደራሴ የምትሆን አንዲት የተዋበች ድንግል በተመልካቾች ፊለፊት ትቀርባለች፡፡ በቅኔውና በጣዕመ ዝማሬው ሰዎችም፣ እግዜሮችም የተደሰቱ መሆናቸውን ለመግለጽ አቸናፊውን ደራሲ ጠርታ በራሱ ላይ ከአበባ የተሠራ አክሊል ትደፋለች፡፡ ከዘውድ፣ ከራስ ቁር የበለጠ ነገር ነው፡፡ በዚያን ዘመን ክብር ሲባል የመጨረሻው ይህ ነበር፡፡ የሚደነቅ ነው፡፡
(እጓለ ገብረ ዮሐንስ፤የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣1956)


