በምሕረት አስቻለው
‹‹የተፈራረምን ዕለት ምንም ዓይነት ዝግጅት አልነበረንም፡፡ በባለቤቴ በኩል ምስክር የሆኗት ሁለት ጓደኞቿ ነበሩ፡፡
እኔ እንዲያውም በአጋጣሚ ያገኘኋቸው ጓደኞቼ ናቸው ምስክር የሆኑኝ፡፡ ተፈራርመን ከማዘጋጃ ቤት ከወጣን በኋላ እንኳን ከምስክሮቻችን ጋር ሻይ አልጠጣንም፡፡ እንዲያውም ምስክር ወረቀት እስከምንቀበልም አልጠበቁም ሔደዋል፡፡ ዕለቱ ለኛ ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም፤ ፎቶ የለም፤ እወቁልን ካርድ መበተን የለም፤›› በማለት ያለ አንዳች ሻይ ቡና እንዲሁ በባዶ ጋብቻ መፈጸሙን የነገረን አቶ ሳሙኤል ሉሌ ነው፡፡
ከቀድሞ ፍቅረኛው ከዛሬ ባለቤቱ ጋር የተዋወቁት በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡ ጋብቻቸውን በ1997 ዓ.ም. ፈጽመዋል፡፡ የሁለት ዓመት ሕፃንም አላቸው፡፡ ሠርግ ከወንድ ልጅ በተለየ መልኩ በሴት ልጅ ሕይወት አንድምታው ትልቅ እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል፡፡ በማኅበረሰባችን ሴት ልጅ ከቤቷ መውጣት ያለበት ተኩላ ተውባ በሠርግ ነው የሚለው አቋምም ጠንካራ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ‹‹ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ…››፣ ‹‹ካባ ልበሽ ምንድነው፤ ሠርግና ሞት አንድ ነው…›› እና ሌሎችም ተመሳሳይ የሠርግ ዘፈኖች ይህንን የማኅበረሰቡ አቋም ያንጸባርቃሉ፡፡
ሠርግ መደገስ በቀጣይ የተጋቢዎች ሕይወት በተጨባጭ የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ያምናል፡፡ ስለዚህም ይነስም ይብዛ ሠርግ መደገስ ለሱ ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ይህንን አቋሙን ለጓደኛው ቀደም ብሎ በግልጽ አሳውቆ ነበር፡፡ መቼ እንጋባለን? እንጂ እንዴት ወይም ምን በሚመስል ዝግጅት ጋብቻችንን እንፈጽማለን አንድም ቀን በመካከላቸው አጀንዳ ሆኖ አያውቅም ነበር፡፡
ይህን አቋሙን ጓደኛው እንዲሁም ቤተሰቦች እንዴት ተቀበሉት? ጓደኛው ሠርግ ተደግሶ ነው እንጂ እንዲሁ ከቤቴ አልወጣም አላለችም፡፡ ይልቁንም ለነገ ሕይወታቸው አንድም ተጨባጭ ውጤት በማያስገኝ የሠርግ ዝግጅት ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን ማፍሰስ ተገቢ እንዳልሆነ ታውቅ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ እሱ የራሱን ሐሳብ ነጥብ በነጥብ አስረድቶ ስላሳመናት ሳይሆን፣ ከሷ ከውስጧ የመጣ እንደሆነ ሳሙኤል ይናገራል፡፡
ቤተሰቦቿ ግን ሐሳቧን በቀላሉ አልተቀበሉትም፡፡ ባይበዛም ቀለል ብሎ ምሳ ወይም ራት ማድረግ አለብን፤ ወጪውንም እኛ እንሸፍናለን በማለት አነስተኛም ቢሆን የግድ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ አቋማቸውን አሳወቁ፡፡ ጥንዶቹ ግን እሺ አላሉም፡፡ ‹‹በወቅቱ ፍላጎት ቢኖረኝ የተወሰነ ነገር አድርጌ ዝግጅት ማድረግ እችል ነበር፡፡ ግን ሠርግ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሒደቱ ደንብና ሥርዓቱ ራሱ ይጨንቀኛል፡፡ ስለዚህ የማላምንበትንና የሚያስጨንቀኝን ነገር ለምን አደርጋለሁ?››
ጓደኛው የተወሰነ ዝግጅት ሳይደረግ በማለት ሐሳቡን አልቀበል ብትል ኖሮ የአብሮነታቸው ጉዳይ ያበቃ እንደነበር የሚናገረው ሳሙኤል፣ ማኅበረሰቡ የሠርግ አስፈላጊነት ላይ ምን ያህል ቢያተኩር፣ ባህሉም ምን ጥብቅ ቢሆን፣ ተጓዳኞቹ ካመኑበት ሳይደግሱ ጋብቻን መፈጸም ከባድ አይደለም ይላል፡፡ እሱም ሆነ ባለቤቱ ከተሜ ባለመሆናቸው በአካባቢያቸው ኅብረተሰብ ሠርግ መደገስና መዳር ምንም ጥያቄ አልነበረውም፡፡ እንዲያውም አንድ ቤተሰብ ልጅ ሲድር ጎረቤት፣ የቅርብም የሆነ የሩቅ ዘመድ እንደ አቅሙ እንጀራና በግ ለደጋሹ ይወስዳል፡፡ ደጋሹም በተራው ያመጣለት ሰው ልጅ ሲድር ተመሳሳይ ነገር ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ልጅ እንዲሁ ካለ ሠርግ ላገባ ነው ቢል እኔ የሰው ሠርግ ስበላ ኖሬና ስንቱ ሲድር የዋልኩት ውለታስ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡ ሳሙኤልና ባለቤቱ ግን ይህን ሁሉ ተቋቁመው ያለ አንዳች ዝግጅት ጋብቻቸውን ፈጽመዋል፡፡
በተቃራኒው ከስድስት ወር በፊት የባለቤቱ ጓደኛ ምንም እንኳ የወንድ ጓደኛዋ ሠርግ መደገስ አስፈላጊ አለመሆኑን በመግለጽ ቢወተውትም እንዴት ካለ ሠርግ አገባለሁ፤ የሙሽርነት ወግስ እንዴት ይቀርብኛል? በማለት ያላትን ገንዘብ ጨምሮ እሱም እሷም በየበኩላቸው ተበድረው መደገሳቸውን እንዳስተዋለ አጫውቶኛል፡፡
ወይንሸት ይላቅ ለሰባት ዓመታት ፕሮቶኮል በመሆን በርካታ ሠርጎችን ታድማለች፡፡ በቅርብ የምታውቃቸው ሰዎችን ሠርግ ጭምር ሠርታለች፡፡ በዚህም ፕሮቶኮል ሆና በሠርጉ ዝግጅቶች ላይ ከመሥራት ባሻገር ስለተጋቢዎቹና ስለቤተሰቦቻቸው ብዙ ነገሮችን የማወቅ አጋጣሚም ነበራት፡፡ ፕሮቶኮል በሆነችባቸው ሠርጎች ላይ በአብዛኛው ሠርግ እንዲደረግ ግፊት ያደረጉት ሴቶች መሆናቸውን አስተውላለች፡፡
‹‹ጥንዶቹ ጋብቻቸውን የፈጸሙት ‹‹ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ወንዱ ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ሴቷ ደግሞ ሠርጌ አንድ ጊዜ ነው፤ አይደገምም፤ እንዴትስ ሆኖ ይቀራል የምትል ነበረች፡፡ በመጨረሻም ለሷ ብሎ ይስማማል፡፡ ተጀምሮ እስኪያልቅ እያንዳንዱ ነገር ያጨቃጭቅ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ አንቺ ነሽ ከእንዲህ ያለ ጣጣ ውስጥ ያስገባሽኝ እያለ ይማረር ነበር፡፡ በዕለቱም ገጽታው ላይ ይነበብ የነበረው ደስ የማይል ነገር ነበር፡፡ አድርግ የሚባለውን ነገርም አያደርግም ነበር፤›› በዚህ የተጀመረው የጥንዶቹ አለመግባባት በርትቶ የመጀመርያ ልጃቸውን ወልዳ ለመታረስ ወላጆቿ ቤት እንደገባች ሚስት በዚያው መቅረቷንና ትዳራቸውም እንደተቋጨ ከወይንሸት ተረድተናል፡፡
ሠርግ በመደገስ ላይ ያላት አቋም ምን እንደሆነ ጠየቅናት፡፡ ‹‹ሴት ዓለሟ አንድ ነው፡፡ ወንድ ሁለት ሦስቴም ሊያገባ ይችላል፡፡ ፈቶ አገባ ብሎ ጉዳይ የሚለው የለም፡፡ ሴቷ ግን ፈትታ ደግማ ስታገባ ኅብረተሰቡ ይገረማል፡፡ ስለዚህ ለሴት ልጅ ሠርጓ ዓለሟ ነው፡፡ ይህም አንዴ ነው፡፡ ተሞሽሮና ተኩሎ ለመውጣትም ጉጉት ያድርባታል፡፡›› በማለት አቅምን ያገናዘበ ይሁን እንጂ፣ ሠርግ በሴት ልጅ ሕይወት ልዩ ቦታ እንደሚሰጠውና አስፈላጊ እንደሆነ ትናገራለች፡፡
መጀመርያ ሠርግ እንደሚያስፈልግ በሴቶች ግፊት ሲደረግባቸው አሻፈረን ብለው የቆዩ፣ በመጨረሻም የተጓዳኛቸውን ሐሳብ ለመሙላት እሺ ብለው ሠርግ የደገሱና በሠርጋቸው ዕለት ግን ከሙሽራዋ ይበልጥ ደስተኛ ሆነው ሲቦርቁ የተመለከተቻቸው ባሎች እንዳሉም ትናገራለች፡፡ ጋብቻውን ከፈጸሙ ከዓመታት በኋላ ፕሮቶኮል ሆና ከምትሠራበት ሠርግ ላይ ታዳሚ ሆነው ያገኘቻቸው፤ የሠርጋቸውን ዕለት አስታውሰው በደስታ ያወጓት ወንድ ሙሽሮችም ጥቂት አይደሉም፡፡
አሁን ከሠርግ ጋር በተያያዘ ጥሎሽ፣ መልስና ቅልቅል መቅረቱን፤ ግብዣም ራትም ምሳም መሆኑ ቀርቶ ወደ ራት ወይም ምሳ ማዘንበሉን በመጥቀስ የድግስ ነገር እየቀነሰ መምጣቱን ተመልክታለች፡፡ ይህ ሰው ያለውን አውጥቶም ይሁን ተበድሮ በሰፊው ከመደገስ፣ በአቅም ማድረግን መምረጡ እንደሚያሳይ ታምናለች፡፡
ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ አይደለም፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው፣ አሁንም እየሠራች ያለችው ግን በአዲስ አበባ ነው፡፡ ያለምንም ዝግጅት ጋብቻዋን በማዘጋጃ ቤት የፈጸመችው በቅርብ ነው፡፡ ለሷ ተወልዳ ካደገችበት አካባቢ መራቅ ሠርግ ባለመደገሷ ሊደርስበት ይችል ከነበረ የቤተሰብና የአካባቢ ጫና እንዳስጣላት ታስባለች፡፡
እንደ እሷ እምነት፣ ሠርግ መደገስ ከታይታ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ተጓዳኞቹ አቅም ቢኖራቸው እንኳ ባለው የኑሮ ውድነት መደገስ በማንኛውም መንገድ አዋጭ አይደለም፡፡ ይልቁንም ውጥረትንና ጭንቀትን ይጨምራል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመቼውም በተለየ መልኩ ያለምንም ዝግጅት በማዘጋጃ ቤት ተፈራርሞ ጋብቻን መፈጸም በብዛት እየተስተዋለ መምጣቱን በማስመልከት አንዳንዶች መደገስ አስፈላጊ እንዳልሆነ፤ ለተጋቢዎቹ ጥምረትም የሚጨምረው አንዳች ነገር እንደማይኖር በማመን እንደሚወስኑ ትገምታለች፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በኑሮ ጫና ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ይሰማታል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ጋብቻን ከመፈጸም ጋር በተያያዘ፣ ሴቶች ሠርግ መደገስ ይኖርበታል፤ በእልልታም ከቤት ተኩለንና ተውበን መውጣት አለብን፤ የሚል አቋም የሚያንጸባርቁት ኅብረተሰቡ ከሰጣቸው የሴትነት ሚና፤ ሠርግ በህብረተሰቡ ዘንድ ካለው ተቀባይነት በመነሣት እንደሆነ የገለጹልን አቶ መሳይ ገ/ማርያም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፒ.ኤችዲያቸውን በመሥራትና በሶሻል ወርክ ዲፓርትመንት በማስተማር ላይ የሚገኙት አቶ መሳይ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀላሉ በማዘጋጃ ቤት ጋብቻን የማድረጉ አዝማሚያ ከሴቶች በኩል አንድም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመረጃ ሐሳብን የመለወጥ፣ የባሕርይ ለውጥ የማምጣት ውጤት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ እንደ እሳቸው አባባል፣ የኢኮኖሚ አቅምም አንድ ተጽእኖ አሳዳሪ ነው ፡፡ በተለያየ መልኩ ምሳሌ የሚደረገው የጋብቻ ዓይነትም በቀላሉ በማዘጋጃ ቤት መፈራረም መሆኑም በዛሬው የሴቶች ምርጫ ላይ ተጽእኖ አለው፡፡


