(በፍሬው አበበ)
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እሑድ ኅዳር 20 ቀን 2002 ዓ.ም. በኢምፔሪያል ሆቴል ሲያካሂድ ያሰበው የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ "በዲስፒሊን ጉድለት ከፓርቲው በተባረሩ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው" ከተጨናገፈ በኋላ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ በፓርቲው ጽ/ቤት ስብሰባውን በማካሄድ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ፓርቲውን በአባልነት የተቀላቀሉትን ሁለት ግለሰቦች ለብሔራዊ ምክር ቤት አባልነት መረጠ፡፡
አንድነት ሰኞ ዕለት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጋዊ ፈቃድ ወስዶ የጠራው ጉባዔ ከፓርቲው በዲስፒሊን ጉድለት ተባረዋል ባላቸው ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ሲስተጓጎል ሠላም የማስከበር ተልዕኮ ያለው ፖሊስ በቦታው አለመገኘቱን፣ የተፈጠረውን ሁኔታ በዕለቱ ለቦሌ እና ለገርጂ ፖሊስ ጣቢያዎች ቢያሳውቁም እርምጃ አለመወሰዱ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የአንድነት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ዕለቱን "የሕግ የበላይነት የተሸነፈበት" ሲሉ ገልፀውታል፡፡
ከአስተዳደሩ የስብሰባ ፈቃድ ሲወስዱ የፖሊስ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በተሰጣቸው ደብዳቤ ላይ መገለፁን ያወሱት ኢ/ር ግዛቸው "በሕጋዊ መንገድ የጠራነው ስብሰባ ሲታወክ ፖሊስ ምንም ሊረዳን አልቻለም" ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ በቦታው መገኘቱን ነገር ግን በፓርቲው የውስጥ መግባት እንደማይችል በመግለፅ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል፡፡
ጉባዔ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ በፓርቲው ጽ/ቤት 235 ተሳታፊዎች ለአራት ሰዓታት ቆመው ማከናወናቸውን ኢ/ር ግዛቸው ጠቅሰው በዚሁ ስብሰባ ላይ ባለፈው ሣምንት ሐሙስ ዕለት በግዮን ሆቴል በተካሄደ ዝግጅት ፓርቲውን በይፋ መቀላቀላቸው የተነገረላቸው የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የቀድሞ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ የፓርቲው የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲሠሩ በሙሉ ድምፅ መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ስዬ እና ዶ/ር ነጋሶ ባደረጉት በዕለቱ ንግግርም ፓርቲው የሰጣቸውን ኅላፊነት በብቃት ለመወጣት ተግተው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ብሐራዊ ም/ቤት 60 ቋሚ አባላት እና 15 ተለዋጭ አባላት ያሉት ሲሆን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ብዛት 18 መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኅዳር 20 በኢምፔሪያል ሆቴል
የአንድነት ፓርቲ የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ኅዳር 20 ቀን 2002 ዓ.ም. በኢምፔሪያል ሆቴል ስብሰባ የጠራ ሲሆን ስብሰባው በቁጥር አአ/ከፀ/10/30-4/45 በ15/03/2002 በአቶ ማርቆስ ብዙነህ የሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ኦፊሰር ፊርማ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡
እንደ ኢ/ር ግዛቸው ገለፃ ከሆነ የልዩ ጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች የመጡት በውክልና ነው፡፡ ፓርቲው ካደራጃቸው አራት ቀጠናዎች ማለትም የደቡብ፣ የሰሜን፣ የምዕራብና ምሥራቅ እንዲሁም የመሃል ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተወከሉ 235 ያህል የስብሰባው ተካፋዮች በውክልና እንዲገኙ ተደርጓል፡፡
በዕለቱ ስብሰባው በሚጀመርበት የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከፓርቲው በዲስፒሊን ችግር የተባረሩና ተባባሪዎቻቸው ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ወደ ስብሰባው እንገባለን በሚል በተነሳ አለመግባባት ስብሰባውን ለማካሄድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡
አንድነት ከትላንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ላይ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡፡
"ኅዳር 20 ቀን 2002 ዓ.ም. ከፓርቲው የተባረሩ ግለሰቦችና አባሪዎቻቸው የስብሰባው ሰዓት ከመድረሱ በፊት ወደ ሆቴሉ በመግባት የስብሰባ አዳራሹን በር በመያዝ እንዲሁም በዋና በር በኩል በጉልበት በመግባትና በማወክ ስብሰባው እንዳይጀመር አድርገዋል፡፡ የአንድነት አመራር አባላትና የሆቴሉ አስተዳደር በየደረጃው ላሉ የፖሊስ ቢሮዎች ስልክ በመደወል በአካልም በመሄድ ሥነስርዓት የሚያስከብር የፖሊስ ኃይል እንዲመጣ ቢማፀኑም በቦታው አልተገኘም" ብሏል፡፡
የአለመግባባቱ ጭብጥ
ከፓርቲው የተሰናበቱትና "የአንድነት መርህ ይከበር" የሚሉ ወገኖች አሁን በአመራር ላይ ያሉትን ግለሰቦች "አምባገነን ሆነዋል፣ የፓርቲው ሕግና ደንብ አያከብሩም" በሚል በተደጋጋሚ ይወቅሳሉ፡፡ አያይዘውም "መርህ ይከበር" በማለታችን ተባርራችኋል ተብለናል በማለት ድርጊቱን አጥብቀው እንደሚቃወሙ ያስረዳሉ፡፡
አቶ አንተነህ ማስረሻ የመርህ ይከበር የሚለው ቡድን አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ስለሁኔታው ከሪፖርተር ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የአንድነት አመራር አባላት አባረናል የሚሏቸው ሰዎች በጋዜጣ ላይ ከመመልከት ውጪ የደረሰን ደብዳቤ የለም ብለዋል፡፡
እሑድ ዕለት በተጠራው ጉባዔ ላይ እንደማንኛውም አባል ለመገኘት ሄደናል ያሉት አቶ አንተነህ የአንድነት አመራሮች እኛን በር ላይ ሲያዩ እነሱ ዞር ካላሉ አንሰበሰብም በሚል ሁከት ፈጥረዋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
"አናስገባም ብለው የአዳራሽ በር ዘግተው ያዙ" የተባለውም ሐሰት መሆኑን በመግለፅ የሄድነው በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመሳተፍ በመሆኑ አናስገባም የምንልበት ምክንያት የለንም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
የአንድነት አመራር በበኩሉ ከተባረሩት ግለሰቦች ጋር ቀደም ሲል ውይይት ለማድረግ ሞክሮ አለመሳካቱን፣ ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተደርገው አለመሳካቱን፣ ጉዳያቸው በዲስፒሊን ኮሚቴ መታየቱን፣ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት እርምጃ መውሰዱን፣ ሒደቱም ሕጋዊ መሆኑን በመግለፅ የተፈፀመ ስህተት አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡


