ክረምትም ይበርዳል ዝናብ እየጣለ፤
ሌሊት ያበራሉ ከዋክብት በሰማይ፤
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
ፈሳሽ ውኃ ሁሉ ቁልቁለትን ይሻል፤
የእሳት ጠባይ ሲሆን መሄድ እየጋለ፣
ጨለማ በባሕሪው ብርሃንን ይሸሻል፤
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
ዐዋቂ ያስባል ልጆች ሲጫወቱ፤
ውጊያ ይፈልጋል መሣሪያ የሳለ፤
ጐበዝ ያሸንፋል ደካሞች ሲረቱ፣
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
ጠቢብ ይጠቀማል ሆኖ የዓለም ጌታ፤
ሰነፍ ይዋረዳል ሳይሠራ የዋለ፡፡
ሰው ሁሉ ይይዛል የምግባሩን ቦታ፣
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
አዲስ ትውልድ ሁሉ አላፊን ይንቃል፤
በሁሉም የምበልጥ እኔ ነኝ እያለ፣
ባባቱ ተግባሮች ልጅ ሁሉ ይስቃል፤
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
ልጃገረድ ሁሉ ትሻለች እጮኛ፣
ባሕሪው የሚስማማት እሷን የመሰለ፣
ጥሩ ነገር ማየት አይወድም ምቀኛ፣
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
እናት ስለ ልጅዋ አንጀቷ ይባባል፤
ቅብዝብዝ ይሆናል ነፍስን የገደለ፤
ከክፉም ከደጉም የሰው ዘር ይረባል፤
ኑዋሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
ሁሉም እንደ ባሕሪው ሁሉም እንደ ባህሉ፣
ተፈጥሮ ጠባዩን እየተከተለ፣
ዘለዓለም ያው ሆኖ ሁሉም እንዳመሉ፣
ኗሪ ነገር ሁሉ ይኖራል እንዳለ፡፡
(ከበደ ሚካኤል፤የቅኔ ውበት፣1999)
* * * *
አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል
በናይሮቢ በቆየሁበት ረጅም ዘመን ብዙ ዓይነት ኢትዮጵያውያን አጋጥመውኛል፡፡ አብዛኞቹ በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው ተሰድደው የሄዱ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ለመሥራት የሥራ እድል አጋጥሟቸው በተለያዩ ጊዜ የሄዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በኬንያ መንግሥትና ሕዝብ መካከል ጥሩ የሆነ መግባባት ስላለ ኢትዮጵያውያን ወደዚች የኬንያ ምድር ከቀድሞ ጀምሮ ይሄዳሉ፡፡
በአስከፊው የጣሊያን ወረራ ዘመን ብዙ ኢትዮጵያኖች ወደ ኬንያ ተሰደው ይሄዱ እንደነበር ሰምተናል፡፡ በበኋላውም በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና ከዚያም በደርግ አስተዳደርና ከዚያም በኋላ በኢሕአዴግ አስተዳደር በኢኮኖሚና በፖለቲካው ሁኔታ ያልተደሰቱና ያልተመቻቸላቸው ወገኖቻችን ወደ ኬንያ በመሰደድ ኑሮአቸውን ይመሠርታሉ፡፡ አብዛኞቹም ስደተኞች አስከፊ የሆነውን በኬንያ የሚያጋጥማቸውን የሕይወት ውጣ ውረድ ተቋቁመው በመጨረሻም እድላቸው የተስተካከለላቸውና ሕይወታቸውን ያሻሻሉ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከነኝህ መካከል አንዲት ኢትዮጵያዊት እህታችን በተባበሩት መንግሥታት መ/ቤት ውስጥ በጸሐፊነት ለመሥራት እድል አጋጥማት ኑሮዋን አመቻችታ ትኖር ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ግን ያላሰበችው መጥፎ እድል አጋጠማት፡፡ ይኸውም ከአንድ ሕንድ ነጋዴ ጋር ተዋውቃ ሕንዱም አንድ ሻንጣ ወደ እንግሊዝ አገር ይዘሽልኝ ከናይሮቢ ሎንዶን በተረርሽ የነፃ ደርሶ መልስ ትኬት ናይሮቢ ሎንደን የሆነ ገዝቼ እሰጥሻለሁ ብሎ ቃል ይገባላታል፡፡
ሴትዮዋም ከ600 ፓውንድ የማይበልጥ ነፃ ትኬት ማግኘቷ ስለአስደሰታት በሐሳቡ ተስማማች፡፡
ወደ ሎንዶን ለዕረፍት ለመሄድ ናይሮቢ ጆሞ ኬኒያታ አየር ማረፊያ እንደደረሰች ከላይ የተጠቀሰው ሕንድ ሻንጣውን ያስረክባታል፡፡ እሷም ትኬቷን በነፃ ስላገኘች ተደስታ ለበረራው ቼክ ለማድረግ ሰልፍ ትገባለች፡፡ በሰልፉ ውስጥም እንዳለች የሠራችው ሥራ ወንጀል ነክ ሊሆን ይችላልና ከዚያ አስከፊ ሁኔታ ይደርስብኛል ብላ መጨነቅ ጀመረች፡፡ ከጭንቀቷም የተነሣ እጀግ በጣም ተረበሸች፡፡ በመጨረሻም ጭንቀቷ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እያለ ሻንጣዋን አስመዝግባ የበረራ ማረጋገጫ ኩፖኗን በሚያዘጋጁላት ቅጽበት ራሷንስታ (ፌንት አድርጋ) ከመሬት ወድቃ ተዘረጋች፡፡ በዚህም ጊዜ ከፍተኛ ግርግር በአካባቢዋ ተፈጠረ፡፡
በአየር ጣቢያው ወደሚገኘው የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ክሊኒክ ተወስዳ ከታየች በኋላ ወደ ናይሮቢ ሆስፒታል በአንቡላንስ እንድትወሰድና ተከታታይ ሕክምና እንዲሰጣት ሐኪሞቹ አዘዙ፡፡
በዚህ መካከል በዚያን ወቅት ለመብረር ባለመቻሏ ሻንጣዋ ብቻውን ገቢ ሆኖ በረራው ቀጠለ፡፡ ከዚያም አይሮፕላኑ በረራውን ወደ ሞምባሳ ቀጥሎ ለአጭር ጊዜ እንዳረፈ ለበረራ አስተናጋጆቹ የሴትዬዋ ሻንጣ ሞምባሳ ላይ እንዲቀር ከሕዝብ ደኅንነት ትዕዛዝ ስለተሰጠ የሷን ሻንጣ አውጥተው ለፖሊስ አስረከቡ፡፡
የሞምባሳ ፖሊሶችም በውስጥ ያለውን ነገር ለማየት ሻንጣውን ሲከፍቱቱ እጅግ በጣም ብዙ የአሜሪካ ዶላርና የእንግሊዝ ፓውንድ እንደታጨቀበት ያያሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ሴትዮዋ ወንጀለኛ ሆና ስለተገኘች ባለችበት ሆስፒታል በፖሊስ ተጠብቃ ሕመሟ ሲሻላት ወደ እስር ቤት እንድትገባ ይወሰናል፡፡
በሻንጣው ውስጥም የተገኘው ከሚሊዮን በር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለመንግሥት ውርስ ሆና እንዲገባ ተደረገ፡፡
ሕንዱም ሻንጣው በፖሊስ እጅ መግባቱን ሲረዳ የእኔ አይደለም በማለትና ሴትየዋንም አላውቃትም ብሎ ካደ፡፡
ይህችም ያልታደለች ወዳጃችን ከሕመሟ ተሽሏት ከሆስፒታል ወጥታ በናይሮቢ እስር ቤት ተከረቸመች፡፡ ለስድስት ወር ያህል እስር ቤት ከቆየች በኋላ በዋስ ተፈትታ ጉዳዩዋን ከእስር ቤት ውጪ ሆና እንደትከራከር ተፈቀደላት፡፡
በዚህ በእስር ቤት ውስጥ በስቃይ ባሳለፈችው የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ልጆቿና ቤተሰቦቿ የሚበሉት ስላልነበራቸውና የቤት ኪራይ መክፈል ስላልቻሉ በናይሮቢ የምንኖር ወዳጆቿ ገንዘብ በማዋጣት ጊዜያዊ ችግሯ እንዲፈታ ጠበቃም ይዛ እንድትከራከር ትብብር አደረግንላት፡፡
እህታችንም በዋስ ከተፈታች በኋላ ባጋጠማት መጥፎ እድልና ሀፍረት በመጸጸት የፍርድ ቤቱም ጉዳይ እልባት ሳያገኝ በታንዛንያ በኩል ድንበር ተሻግራ ከአፍሪካ ምድር ወደ አልታወቀ አገር መጥፋቷን ሰማን፡፡
(ሰሎሞን ኃ/ማርያም፤ደስታን ያሳደደች ሕይወት፣2003)
* * * *
ገንፎ በቅቤ
አንዲት ሚስት ከልጆቹ ለይታ ለባለቤቷ ጥሩ ምግብ /ገንፎ በቅቤ/ አዘጋጀች፡፡ ይህንን ምግብ በጓዳ ጨለማ ሥፍራ ውስጥ ባልዬው ሲበላ አንዱ ትንሹ ልጅ ከልጆቹ ሁሉ ጋር ለከብት ጥበቃ ሜዳ ሳይሄድ ቤት ቀርቶ ነበርና በቅቤ የተዘጋጀው የገንፎ ሽታ አወደው፡፡ ወደ ጓዳው አባቱ እንዳለ ያውቅ ነበርና አባቱን ጠርቶ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ‹‹አባዬ›› አለው፣ ‹‹አቤት›› አለ አባት፡፡ ‹‹ምን እየበላህ ነው?›› አለው፤ እርሱ ጠዋት ከወንድሞቹ ጋር እንደ ነገሩ ስለ ተሸኘ በመቆጨት፡፡ አባትም፣ ‹‹አፈር እየበላሁ ነው›› አለው፡፡ ልጅም አፈር እንዳልሆነ በሽታው ስላወቀና የእናቱም እንዲህ ዓይነት መሠሪነት ስላናደደው ድምፁን ከፍ አድርጐ፣ ‹‹አባዬ፣ አፈር ከሆነ የምትበላው እኔም መጥቼ ልብላ›› አለው፡፡ አባትየውም የልጁ ተከታታይ ጥያቄ ገንፎውን እንዳይበላ እያወከው ስለሆነ ተናዶ ለልጁ እንዲህ አለው፡፡ ‹‹ልጄ፣ አፈር ለመብላት ትፈልጋለህ?›› አለው፡፡ ‹‹አዎን›› አለ ልጁ፡፡ ‹‹ጥሩ አፈር ለመብላት ከፈለግክ እዚያው ያለህበት ጀምር፡፡ አፈር ሁሉም ቦታ አለና ከግድግዳው ጀምር›› አለውና አረፈው፡፡
አዎ፣ እውነተኛ ፍቅር ከራሱ ይልቅ ሌላውን ያስበልጣል፣ የሌላውን ጥቅም ያስቀድማል፡፡ ዛሬ በየቤታችን ለልጆቻችን ያለን ፍቅር ምን ያህል ይሆን? ይህ ከላይ ያለው አባት ልጁን አፈር ብላ ነው የሚለው፡፡ እኛስ? እናቱም የጐላ አድልዎ እያሳየች ነው፡፡ እርስዎስ?
(ደመወዝ አበበ፤የሰባኪው ምሳሌ 2ኛ መጽሐፍ፣1998)
* * * *
‹‹ሁለቱ አገሮች ከጥንት ጀምሮ የቆዩ ጠላቶች ናቸው የሚባለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያስወግዳል››
ኢትዮጵያም እስከ ከ1928 1933 ዓ.ም. በኢጣሊያ ሥር ቆየች፡፡ በ1928 ዓ.ም. ከዚያ ስድስት ዓመት በፊት በዙፋን የተቀመጡት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለዓለም ማኅበር ታሪካዊ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ የዓለም ማኅበር የኢትዮጵያን ወረራ ባያቆም፣ ማኅበሩ በራሱ ላይ ውድቀት ማስከተል ብቻ ሳይሆን የዓለም ጦርነትን ያስከትላል በማለት ንጉሠ ነገሥቱ ያስጠነቀቁት በዚያው አቤቱታቸው ነበር፡፡ ኢጣሊያ ከአንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታት ጋር ካደረገችው መግባባት የተነሣ የዓለም ማኅበር አንዳችም ዕርምጃ ሳይወስድባት ቀረና ከዚያ በኋላ ስለደረሱት ሁኔታዎች የንጉሠ ነገሥቱ ትንቢታዊ ንግግር ቁልጭ ያለ ማስረጃ ነው፡፡
ግርማዊነታቸው ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. በእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ዕርዳታ ወደአገራቸው ሲመለሱ፣ የኢጣሊያ 30ሺሕ ጦር ኃይሎች መመታት ተጀመረ፡፡ የቅኝ ተገዢነትን ቀንበር ተሸክማ ለማታውቀው በነፃነት ለ3ሺሕ ዓመታት ለኖረችው አገር የአምስት ዓመት ስቃይ የማይሽር ቁስል ሊፈጥር ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ የመንፈስ በላይነት የፋሺስቶችን ጭካኔና ዓረማዊነት በመርሳትና ይቅርታ በማድረግ በፋሺዝም ላይ ያልታሰበ ድንገተኛ ሞት ከደረሰ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ግንኙቶች ከኢጣሊያ ጭምር አዲስ ምዕራፍ ከፈቱ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በ1962 ዓ.ም. ኢጣሊያንን በጐበኙበት ወቅት ጉብኝታቸው ሁለተኛ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ለኢጣሊያው ፕሬዚዳንት ጁሴፔ ሳራጋት አስገንዝበዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ከሁሉ አስቀድሞ ‹‹ሁለቱ አገሮች ከጥንት ጀምሮ የቆዩ ጠላቶች ናቸው የሚባለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያስወግዳል›› ብለው ንጉሠ ነገሥቱ ንግግራቸውን በመቀጠል ‹‹የኢጣሊያ ሪፒብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር የመሠረታቸውን ልዩ ልዩ ግንኙቶች ለማጠንከር›› ምኞታቸው መሆኑን ገለጡ፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ የወሰዱት እርምጃ የዚያን ያህል ትክክል ከመሆኑ የተነሣና የተደረገላቸውም አቀባበል በጣም የጋለ ስለነበር የኢትዮጵያንና የኢጣሊያን የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የካልቸር፣ የቴክኒክና የመተባበር ግንኙቶችን በይበልጥ ለማጠንከር መሠረታዊው ስምምነት ተፈረመ፡፡
(የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል፤ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች አስተያየት፣1966 ዓ.ም.)
* * * *
ፀሐይን እንዲህ አላት
‹‹ዛራቱስትራ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አገሩንና የአገሩንም ወንዞች ትቶ ወደ ተራራ ሄደ፡፡ በዚያም የገዛ ራሱን መንፈስና ብቸኝነቱን በመደሰት ምንም ስጋት ሳይሰማው አሥር ዓመት ኖረ፡፡ በመጨረሻ ልቡ ተመለሰ፡፡ አንድ ቀን ማለዳ ተነሣ፡፡ በፀሐይዋ ፊለፊት ቆሞ እንዲህ ሲል ተናገራት፡፡
ትልቅ ኮከብ ሆይ፤ ብርሃንሽን የምታድያቸው ባይኖሩሽ ኖሮ ደስታሽ ምን ይሆን ነበር፡፡ አሥር ዓመት ሙሉ በየዕለቱ እስከዋሻዬ ድረስ ትመጭ ነበር፡፡ እኔና አብረውኝ ያሉት ንስርና እባብ ባንኖር ኖሮ ስለብርሃንሽና ስለጉዞሽ ሐሳብ ይገባሽ ነበር፡፡ ግን እኛ በየጧቱ እንጠባበቅሽ ነበር፡፡ ተትረፍርፎ ካንቺ የሚፈሰውን ወሰድን፤ ስለሱም መረቅንሽ፡፡
እነሆ፤ ስለጥበቤ ሐሳብ ገባኝ፤ ብዙ ማር እንዳከማቸች ንብ ለመውሰድ የተዘረጉ እጆች አስፈለጉኝ፡፡ ወዲያ ለመስጠትና ለማደል እፈልጋለሁ፡፡ በሰዎች መካከል ያሉት ጠቢባን በሞኝነታቸው፤ ድሆችም በሀብታቸው እስኪደሰቱ ድረስ፡፡ በዚህ ዓላማ ምክንያት አሁን ቁልቁል መውረድ አለብኝ፡፡ ሁልጊዜ በየምሽቱ እንደምታደርጊው፣ በባሕሩ ማዶ አልፈሽ በታችኛው ዓለም ላሉት ብርሃን ለመስጠት እንደምትሄጅ፣ እጅግ ባለፀጋዋ ኮከብ ሆይ፡፡
እኔም እንዳንቺ ወደታች ‹‹መጥለቅ›› አለብኝ፤ የምወርድላቸው ሰዎች እንደሚሉት፡፡ ከመጠን በላይ የሆነውን ደስታ እንኳ ያለቅናት የምታይ፣ ሰላምን የተመላሽ ዓይን ሆይ፣ እንግዲህ መርቂኝ፡፡
ተርፎ ለመፍሰስ የሚፈልገውን ዋንጫ መርቂ፣ ውኃው ከሱ እንደ ወርቅ ይፈስ ዘንድ፤ የደስታሽንም ማንፀባረቅ (ሪፍሌክሽን) ወደመላው ዓለም ይሸከምልሽ ዘንድ፡፡ እነሆ ይህ ዋንጫ እንደገና ባዶ ለመሆን ፈለገ፤ ዘራቱስትራም ዳግመኛ ሰው ለመሆን ተመኘ፡፡
(እጓለ ገብረ ዮሐንስ፤የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣1956 ዓ.ም.)
* * * *
ከእኔ ለእናንተ
ወሲብ ጥበብ ነው - ታላቅ ኃይል፡፡ ሰውም ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ታዲያ በተፈጥሮ ሁላችንም ይህን ጥበብ ገና ስንፈጠር ተቸረነዋል፡፡ በግብር ለማዋል ስንነሣ ተሰጥኦአችንን እንተረጉመዋለን፡፡ ኃይሉ ምን ያህል ከባድ እንደሆነም የምንረዳው በፍቅር - በግብረገብነት በሌሎች ሕይወት ውሰጥ አስርጸነው ነፋሪቱ እነሱን ለውጦ እነሱም እኛን ሲለውጡ ነው፡፡ የሰጠነው ኃይል ሳይባክን ሲመለስ፡፡ ኃይሉ ከባከነ ሕይወት ትናወጣለች - ትናጣለች፡፡ መንፈስም ሕብረ - ሚዛን ያጣል፡፡ ሕግም ይዛባል፡፡ ይህ ሲሆን ኃየሉን ማንነታችንን ለመፈተሽ ወደ እራሳችን ውስጥ ማስረጽ ይገባል፡፡ በእዚህም ጊዜ ቋጠሮው ይገኛል፡፡ መፍታታም አዳጋች አይሆንም፡፡
ሕይወት እንደገና ታንሰራራ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዋንም ታንሣ፡፡ ቅኝቷንም ትግፋበት፡፡ ዝማሬዋ ይሰማ፡፡ ይህ ሲሆን የሰጠችው ምስጢር ተተርጉሟል፡፡ የዘራችው አጎንቁሏል፡፡ መከርንም ይናፍቃል፡፡
ቅኝቱ ከተዛባ ሙዚቃው ከተሳከረ ሕይወት ትርጉም ያጣል፡፡ ቅሬውም ይወይባል፡፡ ቃናውም ይማልጋል -ምቱ፡፡ ፍቅር ይናኝ ይሰጥ ገኖ፡፡ ፈጽሞ አይቀርም ባክኖ- ኳትኖ፡፡ እሱም በእሷ እሷም በእሱ ይሰርጻሉ፡፡ እኔነትን በማስቀረት በአንድነት ይነግሣሉ፡፡ በመግባባት ይከንፋሉ - ያርጋሉ፡፡ ወሲብ ፍቅር - ፍቅርም ወሲብ ነው ይላሉ፡፡ ልዩ ጸጋን ተጎናጽፈው አንዱ የሌላው እስትንፋስ እና ሕይወት ሆነው በፍጹምነት እኔነትን ድል ነስተው፡፡ የምድርን ሁሉ በሽታ - ዝገት ፍቀው . . . ይኖራሉ አዲስ የህሊና ዓለም አዋቅረው . . . እኔነትን ሰርዘው . . .
(አሸናፊ ዘድባብ፣ ፍቅር እና ወሲብ፣ ለማወቅ የሚሹት መጠየቅ የሚያፍሩት፣1992)
* * * *
ገራገር
ሌቦቹ በስህተት የሰው ቅሪት ሰረቁ
ሌቦች አደንዛዥ እፅ መስሏቸው፣ ከአንድ ሰውና ከሁለት ውሾች አካል ተቃጥሎ የተቀረውን አመድ መስረቃቸውን የፍሎሪዳ ፖሊስን በመጥቀስ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አመዱን የያዘው ኮንቴነር የተወሰደው ፍሎሪዳ ሲልቨር ስፕሪንግ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የአንዲት ሴት ቤት መሆኑን፤ ሟቹ አባቷ ሲሆን ሁለቱ ውሾችም የሷ እንደነበሩ ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከሴትዬዋ ቤት አመድ ከያዙት ኮንቴነሮች በተጨማሪ ጌጣጌጦችና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችም ተወስደዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ አመዱን በስህተት ከመውሰዳቸው በተጨማሪ ኮኬይን ወይም ሔሮይን እንደሆነ በማመን ሲስቡት መቆየታቸውም ሊታወቅ ችሏል፡፡ ስህተት እንደፈጸሙ ሲገባቸው ግን ቀሪውን አመድ ለመመለስ ቢወስኑም፣ አሻራቸው እንዳይገኝ በመፍራት አመድ የያዘውን ኮንቴነር ወደ አንድ ሐይቅ መወርወራቸውን የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ሚስተር ኮችረን ተናግረዋል፡፡
* * * *
በባቡር ሐዲድ ላይ ተኝቶ ባቡር ሲሔድበት ራሱን የቀረጸው ሰው
አንድ ሰው ለ56 ሴኮንድ ክሊፕ ብሎ በባቡር ሐዲድ ላይ ተኝቶ ባቡሩ ሲሔድበት ራሱን መቅረጹን ዴይሊ ሚኒር ዘግቧል፡፡ በዚህ መልኩ የተቀረጸው ክሥተትም በዩቲዩብ ላይ ሲለቀቅ 270,0000 ሰዎች ፊልሙን ተመልክተውታል፡፡
ፊልሙ በእንግሊዝ ውስጥ ስለመቀረፁ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፣ ብዙዎች ሁኔታውን ከአንድ አእምሮ ካለው ሰው የማይጠበቅ እንደሆነ እየገለጹ ነው፡፡
ማንነቱ ባልታወቀው በዚሁ ራሱን በቀረፀው ሰው አካል ላይ ባቡሩ ጉዳት ቢያደርስ፣ የባቡሩ አሽከርካሪ ሰው እንደገጨ ቢያስብ የሚፈጠረው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ይሆን እንደነበር ተገልጿል፡፡ ማንም ለራሱ ደህንነት የሚያስብ ለሌሎችም ስሜት የሚጨነቅ እንዲህ ያለውን ተግባር ሊሞክረው አይገባም እየተባለም ነው፡፡


