በምሕረት አስቻለው
የተለያዩ ፈጠራዎችን በመሥራት ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝተዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ በሁለትና ሦስት የተለያዩ ሥራዎች የተቋሙን ማረጋገጫ ማግኘት ችለዋል፡፡ ተቋሙ በየዓመቱ ፕሮፖዛሎችን (ትልማሳቦችን) በመቀበል በልጦ ለተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ብዙዎቹ የፈጠራ ሥራዎቻቸው ተግባራዊ መሆን የሚችልበትን መንገድ በመቀየስ ረገድ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳልፈጸመ ይናገራሉ፡፡
ፍሬወይኒ መብራቱ በዝቅተኛ ዋጋ በገበያ ላይ መዋል የሚችልና እየታጠበ በተደጋጋሚ ሊያገለግል የሚችል የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ (ፓድ) በመሥራት ከመሥሪያ ቤቱ የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝታለች፡፡ የፈጠራ ሥራዎቻቸው የሚገባውን ያህል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዳልተጠበቁ ታምናለች፡፡
‹‹ሥራዎቻችን በተመሳሳይ መልኩ ሲሠሩ እንመለከታለን፡፡ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን በራሳቸው ወይም በሚደረግላቸው ጥቆማ መሠረት ክትትል በማድረግ የባለቤትነት ማረጋገጫ ለሰጧቸው የፈጠራ ሥራዎች ጥበቃ ሲያደርጉ አይታይም፤›› በማለት ከጥበቃው በተጨማሪ ልዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው የሚወጡ ወጣቶች ከባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ውጭ ለሥራቸው ተግባራዊነት ማበረታቻ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡
እንደ ፍሬወይኒ አባባል፣ ማበረታቻው የግድ የገንዘብ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የፈጠራ ባለቤቶች በተለያየ መልኩ በኅብረተሰቡ ዘንድ እውቅናን እንዲያገኙ፤ ከባለሀብቶችና ከተለያዩ ተቋማትም ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹም ሆነ የባለቤቶቹ እውቅና ማግኘት ደግሞ ባለቤትነትን ለማስጠበቅ አስተዋጾአቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ጥቂት የማይባሉ የፈጠራ ሥራዎቻቸው በወረቀት ላይ መቅረቱን ይናገራሉ፡፡ የፍሬወይኒስ? የገንዘብ አቅም ስለነበራት፣ ድጋፍ ሊያደርግላት ከሚችል ተቋም ጋር የነበራት ግንኙነትም መልካም ስለነበር የፈጠራ ሥራዋን ፍሬ መመልከት ችላለች፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫውን ያገኘችው በ1998 ዓ.ም. ሲሆን እንደታለመለት ዛሬ የንጽሕና መጠበቂያው መቀሌ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሴቶች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በስፋት ለገበያ ለማቅረብ በመሥራት ላይ ነች፡፡
ወጣት አካሉ ገብረ ሕይወት በ1994 ዓ.ም. በሦስት ሥራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫዎችን አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ያለቀና እያሠራቸው ያሉ ሌሎች ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ይዞ ወደ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለመሔድ የማመንታት ነገር ይታይበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሦስቱም ሥራዎቹ እንዲተገበሩ ብዙ ቢደክምም አንዱ እንኳ ተግባራዊ ሆኖ ፍሬውን መመልከት አለመቻሉ ነው፡፡
‹‹ተቋሙ በየዓመቱ ትልማሳቦችን (ፕሮፖዛሎችን) እየሰበሰበ የበለጠ ነው ላለው ሥራ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህ እድል ግን የባለቤትነት ማረጋገጫ ላገኙ ብቻ ሳይሆን፣ ለማንም ክፍት ነው፡፡ ገንዘቡም ለአንድ የፈጠራ ሥራ በቂ የማይሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ገንዘቡ በቀጥታ የፈጠራ ባለቤቱ እጅ አለመድረሱም ሌላ ነገሮችን የሚያጓትትና የሚያወሳስብ ነው፡፡››
መሥሪያ ቤቱ የሚያደርገው ይህ የገንዘብ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ለፈጠራ ባለቤቶች የተለየ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት፣ ገንዘቡም ለሥራው ተግባራዊነት በሚረዳ መልኩ መውጣት እንዳለበት ይናገራል፡፡ እንደ ወጣት አካሉ እምነት፣ የሚደረገው ድጋፍ የገንዘብም ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የመሥሪያ ቦታ ማመቻቸት የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ሊደግፉ ከሚችሉ ባለሀብቶች ወይም ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ባለቤቶቹ ከሥራቸው፣ ኅብረተሰቡም ከፍሬው እንዲጠቀም መሥሪያ ቤቱ የባለቤትነት የማረጋገጫ ከመስጠት በዘለለ መሥራት እንዳለበትም ገልጿል፡፡
‹‹የመሥሪያ ቦታ ተመቻችቶ፣ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጐ፣ ደጋፊው አካልና የፈጠራ ባለቤቱ የተግባራዊነቱን ውጤት በእኩል ወይም እንደ ስምምነታቸው ሊካፈሉ ይችላሉ፡፡›› የሚለው አካሉ፣ ከቤንዚንና ከናፍጣ ውጭ በራሱ ኃይል መሥራት የሚችል ጀነሬተር በመሥራት ላይ መሆኑን ነግሮናል፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት፣ የፓተንት ፍለጋና ሥረ ነገር ምርመራ ቡድን መሪ አቶ ግርማ በጅጋ፣ ወጣቶቹ የፈጠራ ባለቤቶች ያነሧቸው ቅሬታዎች እውነትና መሠረት ያላቸው መሆኑን ተቀብለዋል፡፡ ቀደም ሲል መሥሪያ ቤቱ የነበረው አወቃቀር ተቀይሮ የሰው ኃይልም እየተጠናከረ በመሆኑ እነዚህ ነገሮች እንደ ችግር ተለይተው በመታወቃቸው ስትራቴጂዎች መነደፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን በማውጣት እውቅና እንዲያገኙ ቀደም ሲልም የተሠራ ሥራ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የፈጠራ ሥራዎችን በሚመለከት ግን ለፈጠራ ሥራዎቹ እውቅና ከመስጠት ባሻገር የሚያደርጉት ነገር ባለመኖሩ ሥራዎቻቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት የሚወድቀው በባለቤቶቹ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


