በጥር 4 ቀን 2003 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ‹‹በምን እየሠሩ ነው›› ዓምድ ከሻምበል ገብረ መድኅን ቢረጋ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ማቅረባችሁ ይታወሳል፡፡
በቃለ መጠይቁ መግቢያ ግለሰቡ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ‹‹ከ10 ዓመታት በፊት ለተቋቋመው ‹‹የኢትዮጵያን ኮንስዩመር ፕሮቴክሽን አሶሴሽን›› በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ አሁን አዲስ ስያሜ ላገኘውና በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፎች ለከፈተው የኢትዮጵያ ሸማቾች ማኅበር ዳይሬክተር ናቸው፤›› የሚል አረፍተ ነገር ሰፍሯል፡፡
በእርግጥ ግለሰቡ ቀድሞ ‹‹አሃ የኢትዮጵያን ኮንስዩመር ፕሮቴክሽን አሶሴሽን›› የሚል ስያሜ ለነበረው ማኅበር እስከ 1998 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ፍትሕ ሚኒስቴር በጠራው የማኅበሩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ከመስከረም 4 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከማኅበሩ አመራር ተወግደው በተራ አባልነት ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን፣ ማኅበሩም በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ስሙን እንደገና ቀይሮ ‹‹ኢትዮጵያን ኮንስዩመርስ ፕሮቴክሽን አሶሴሽን›› /ኢኮፓ/ በሚል ስያሜ በፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራት ምዝገባና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ዳግም ምዝገባ በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኢኮፓ ባለው መረጃ ግለሰቡ በሸማቾች ጉዳይ ላይ የሚሠራ ሌላ ማኅበር ከአንድ ዓመት በፊት ማቋቋማቸውን ያውቃል፡፡
ይሁንና በተጠቀሰው ቀን በወጣው ቃለ መጠይቅ ግለሰቡ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ የሰፈረው ሐረግ ኢኮፓ ስሙን እንደለወጠና የሚመሩትም እሳቸው እንደሆኑ የሚያስመስል ነው፡፡ ይኼው አገላለጽ በመላው የማኅበራችን አባላትና አብረውን በሚሠሩ የለጋሽ ድርጅቶች ላይ ብዥታን ፈጥሮ ለጽሕፈት ቤታችን ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ኮንስዩመርስ ፕሮቴክሽንስ አሶሴሽን ስሙን ሳይለውጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ማኅበር ሲሆን፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ተከራይቶ ለተከታታይ ሳምንታት በምግብ ዘይት ጥራት ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያደረጉትን ውይይት ማዘጋጀቱና ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡ ምስክር ነው፡፡
ማኅበሩ የዓለም አቀፉ የሸማቾች ማኅበር (Consumer International) አባል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እየገለጸ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ የፀደቀው የሸማቾች መብት ጥበቃ ሕግ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ለተግባራዊነቱም የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ያስታውቃል፡፡ በመሆኑም የተፈጠረው ስህተት እንዲስተካከል ይጠይቃል፡፡
ዶ/ር ምናለ አረጋ፣
የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ
*****************************
መፍትሔው ይቀየር
በሕዝቡ ላይ የደረሰውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ በአንዳንድ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ መንግሥት የዋጋ ተመን በማውጣቱ ጊዜያዊ የዋጋ ግሽበትን ሊያረግብ ቢችልም፣ ሸማቹና ነጋዴው እንዲፋጠጡ ማድረጉ አልቀረም፡፡
መንግሥት ዕርምጃውን የወሰደው ዘግይቶ ቢሆንም የችግሩን መንስዔ ወደ ነጋዴው እንደሆነ የሰሞኑ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እያደረጉት ያለው ቅስቀሳ አመላካች ነው፡፡ መንግሥት አስቀድሞ ችግሩ ሳይባባስ ወይም በእንጭጩ የትንበያ ጥናት በመውሰድ ሊከላከል ለምን አልቻለም? በተለይ የሸቀጦች ብቻ ሳይሆን የእህል ዋጋ እያሻቀበ የመጣው ከ1997 ምርጫ በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ገበሬው ሚሊዬነር የተባለበትና ምርቱን ሳይጨምር ዋጋው የጨመረበት ምክንያት በመንግሥትም ተበረታትቶ ነበር፡፡
ዛሬ ችግሩ ሲባባስ ግን መንግሥት መንስዔውን ሳይሆን የችግሩን ውጤት ለመግታት ቀስቱን ወደ ነጋዴው እንዲገትር አድርጐታል፡፡
በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ግን መንግሥት ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የወሰዳቸው አንዳንድ ዕርምጃዎች ለሸቀጦችም ሆነ ለእህልና አገልግሎቶች ዋጋ መናር ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እነዚህም በተለይ በብር ላይ ከፍተኛ የምንዛሬ ዋጋ ቅነሳ፣ በነዳጅ ላይ የነበረን ድጐማ በማንሳት በየጊዜው ያልተቋረጠ ጭማሪ ማድረግ፣ የስኳርን የጨረታ ዋጋ ከፍ ማድረግን፣ በተለይ በሚሌኒየም የበዓል ሰሞን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለድግስ መርጨት እንዲሁም ሸቀጦች መሸከም የማይችሉትን ከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ በጀት (ገንዘብ በማተም) መመደብ፣ ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ግሽበት መንስዔ ስለመሆናቸው የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ነጋዴው የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝቡን ለከፍተኛ ብሶት ዳርጐታል፡፡
ስለሆነም ለችግሩ ተጠያቂ ላለመሆን መንግሥት ሳልቀደም ልቅደም ዓይነት ሆኖ ነጋዴውን ‹‹ከስረህም ቢሆን ሽጥ›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ኢሕአዴግ በ2002 ምርጫ እንዳሸነፈ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች ቢኖሩም፣ ሕዝቡ ችግሩ ይቀረፍልኛል ብሎ ስለመረጠኝ ሌት ተቀን ሠርቼ ሕዝቡን ከድኅነት አላቅቃለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ሕዝብን በኑሮ ውድነት የሚገርፉ ዕርምጃዎች መወሰዱ ነው፡፡
መንግሥት የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለማስተንፈስ አሁን እየወሰደ ያለው የዋጋ ተመን ግዳጅ አሉታዊ ውጤት ስለሚኖረው ቀጥሎ የተመለከቱት የመፍትሔ ሐሳቦች አቀርባለሁ፡፡
1ኛ. የብርን የምንዛሪ ዋጋ ከ2002 ምርጫ በፊት ወደነበረበት መመለስና አዝጋሚ ጭማሪ እንዲኖረው ማድረግ፣
2ኛ. እንደቀድሞው የነዳጅ ዋጋን መደጐም፣
3ኛ. የስኳር የጨረታ ዋጋን ከብር 10 በታች አድርጐ የችርቻሮንና የማከፋፈያን ዋጋ መተመን (መገደብ)፣
4ኛ. ገንዘብ በአገር ውስጥ ከመጠን በላይ እንዲሰራጭ የፊሲካል ፖሊሲውን መቆጣጠር፡፡
መንግሥት ከዚህ በላይ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ለልማት የሚውለው የካፒታል በጀት እጥረት ሊገጥም ይችላል፡፡ ሆኖም ልማትና እድገት ሕዝብን በማስቀደም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሕዝብ ያላመነበት ዕድገትና ልማት እንደ ጥፋት ሊቆጠር ይችላልና፡፡ አገርን ማልማት የሕዝብ እንጂ የመንግሥት መሆን የለበትም፡፡
ማቴዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ
************************
ማረሚያ
እሑድ ጥር 15 ቀን 2003 ዓ.ም. እትም ላይ ‹‹ግብፅ የኒውክሌር ማመንጫ ለመገንባት ጨረታ ልታወጣ ነው›› በሚል ርዕስና ‹‹ኢትዮጵያ ስለኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ማሰብ እንዳለባት ተጠቆመ›› በሚል ንዑስ ርዕስ የወጣው ዘገባ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ኢንጅነር አስተራይ ጽጌ የሚሠሩበትን መሥሪያ ቤት እንደማይወክል ለመግለጽ እንወዳለን፡፡


