Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ኤጋ ቆርቆሮ በአንድ ወኃ ቀለም

E-mail Print PDF
User Rating: / 3
PoorBest 

በናታን ዳዊት

ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ አንድ አውሮፓዊት አገር ሔዶ የነበረ የቅርብ ጓደኛዬ ሰሞኑን ወደ አገር ቤት ተመልሶ ተገናኘን፡፡ የመጣው ለወንድሙ ሠርግ ነበር፡፡ የቆይታ ጊዜው አጭር ቢሆንም ሥራ ፋታ ሲሰጠኝ፤ እርሱም የወንድሙን ሠርግ ለማሰማመር ወዲያ ወዲህ ብሎ ሲያበቃ ተገናኘን፡፡

ወደ አገር ቤት የመጣበት ወቅት መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተወሰኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ጥሎ ተግባራዊ መሆን የጀመረበት የመጀመሪያ ሳምንት ስለነበር ስለጉዳዩ እንዳስረዳው ጠየቀኝ፤ የምችለውን ያህል አስረዳሁት፡፡

ከቀናት ቆይታ በኋላ ምሳ ለመብላት ተቃጠርን፡፡ ጥሩ ምሳ እናገኝበታለን ወዳልነው አንድ ምግብ ቤት ገባን፡፡ ምግብ ቤቱ ከምግብ አዳራሹ ሌላ በረንዳው ላይም አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ወደ ምግብ አዳራሹ ከምንገባ ውጭ መስተናገድን መረጥን፡፡

እንደተቀመጥን አስተናጋጅዋ የምግብ ዝርዝር የያዘውን ‹‹ሜኖ›› ይዛልን መጣች፡፡ እኔ የምፈልገውን ምግብ አዘዝኩ፡፡ ጓደኛዬ ግን ዓይኑን ምግብ አዳራሹ መግቢያ በር ላይ ወደ ተለጠፈው ማስታወቂያ ላይ ተክሎ፣ ‹‹እኔ የምፈልገው አንድ ኤጋ ቆርቆሮ ነው፤›› ሲል ሰማሁት፡፡

አስተናጋጅዋም ግር ሲላት ተመለከትኩ፡፡ ለቅስፈት ያህል ምን ማዘዝ ፈልጐ ይሆን ብዬ ማሰቤ አልቀረም፡፡ ኤጋ የምትለውን ቃል ስለሰማሁ እንቁላል ማለት ፈልጐ ይሆንም ብዬ አሰብኩ፡፡

እንዲህ ማሰቤ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ እርሱም እንደ አንዳንድ ዲያስፖራዎች የሚፈልገውን ምግብ በእንግሊዝኛ ለማዘዝና ቀምጠል ለማለት ፈልጐስ ቢሆን ብዬ ነው፡፡ ለማንኛውም ምን እንደሚፈልግ አስተናጋጅዋ በድጋሚ ስለጠየቀችው ቀደም ብሎ ያየዘውን ለማወቅ ቻልኩ፡፡ ‹‹አንድ ኤጋ ቆርቆሮና አንድ የውኃ ቀለም . . . የሚለውን ትዕዛዙን ልቅም አድርጌ ሰማሁ፡፡ የፈጠረው ግርታ ሁላችንንም ማደናገሩ ስለገባው ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ይኼኔ የምግብ ቤቱ አዳራሽ ላይ ወደነበረው ማስታወቂያ አንጋጠጥኩና ምን ለማለት እንደፈለገ ገባኝ፡፡ አስተናጋጅዋም የጓደኛዬ ያልተጠበቀ ትዕዛዝ ቢያስገርማትም ለምን እንደዚያ እንዳለ ገባትና እርሷም ፈገግ አለች፡፡

ከሜኖ ላይ የሚፈልገውን አዘዘና አስተናጋጅዋ ሄደች፡፡ እኔም ነገሩና ትኩረቱ ገርሞኝ ማስታወቂያውን ልቅም አድርጌ ሳነብ፣ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያ መለጠፍ አግባብ ነው? አይደለም? የሚለውን መጠየቅ ይዘን የየራሳችንን አስተያየት ሰጠንበት፡፡

በእርግጥም ማስታወቂያው ላይ ከተዘረዘሩት የዕቃዎች የዋጋ ዝርዝር ውስጥ በምግብ ቤቱ ሊገኝ የሚችል ዕቃ ቢኖር ለስላሳና ቢራ ብቻ ነበር፡፡ ሌሎቹ ፍጹም ከምግብ ቤቱ አገልግሎት ጋር የማይገናኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የጓደኛዬ የመጀመሪያ ትዕዛዝ የነበረው ኤጋ ቆርቆሮ፣ ዘይት፣ ሳሙና የመሳሰሉ የዋጋ ዝርዝሮች አንድ ምግብ ቤት ውስጥ ለምን መለጠፍ እንዳስፈለገ ሊገባኝ አልቻለም፡፡

ለማንኛውም እኔና ጓደኛዬ ለሁለተኛ ጊዜ በዋጋ ተመኑ ዙሪያ የምናወጋበት ሌላ አጋጣሚ ፈጠረልን፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የዋጋ ተመን ሲጥል በየቀበሌው ባሉ አስፈጻሚዎች የዋጋ ዝርዝሮቹን ይዘው በየመደብሩና ይመለከታቸዋል በተባሉ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ በመሄድ በአገልግሎት መስጫው ግድግዳ፣ በራፍ ወይም መስኮት ላይ ሲለጥፉ፤ ለሆቴል ቤቶችና ለመደብሮች የሚሆነውን መለየት አለመቻላቸውን ያሳያል፡፡

በነገራችን ላይ ከዚያም በኋላ በአንዳንድ ምግብ ቤት፣ ኬክ ቤትና መሰል አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ተመሳሳይ የሆነ ማስታወቂያ አይቻለሁ፡፡ ለነገሩ ድርጊቱ ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም የመጀመሪያው የዋጋ ተመን ሥራ ላይ እንዲውል ከተደረገ በኋላ በአንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡

የዋጋ ተመኑ ይፋ ከተደረገበት የመጀመሪያው የሕዝብ ማስታወቂያ ወዲህ በተከታታይ ወደ አራት የሚሆኑ ማስታወቂያዎች ወጥተዋል፡፡ በነዚህ ተከታታይ ማስታወቂያዎች መረዳት እንደሚቻለው አንዳንድ ምርቶች ዋጋቸው እየተለዋወጠ መምጣቱን ነው፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው ማስታወቂያ አንድ ዘይት ሊትር ዘይት ይሸጥበታል የተባለው ዋጋ 16.50 ብር ነበር፡፡ በሁለተኛው ማስታወቂያ ደግሞ 21.50 ብር ተደርጎ ለቀናት ከተሠራበት በኋላ ሰሞኑን በወጣው ማስታወቂያ ደግሞ የአድን ሊትር ዘይት ዋጋ 24.50 ብር ነው ሲባል፣ ገበያ ውስጥ የሚፈጥረው ብዥታ ቀላል አለመሆኑን እንረዳለን፡፡

በሌሎች ምርቶች ላይም ተመሳሳይ የሆነ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ይህ ድርጊት አንዳንድ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ መንግሥት ወደ እርምጃው ከመግባቱ በፊት ዋጋ እንዲተመንላቸው ስላደረጋቸው ምርቶች ጥናት አላደረገም ማለት ነው? የሚለው ዋነኛ መጠይቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን እንዲህ ያሉ የዋጋ አተማመኖች በገበያ ውስጥ ሊፈጥሩት የሚችሉት ተጽእኖ ሸማቹንና ነጋዴውን ላያግባባ ይችላል፡፡ ወደፊትም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የዋጋ ተመን የሚወጣላቸውን ምርቶች አሁን ባለው አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ እንደማይገባ ትምህርት ሊወሰድለት ይገባል፡፡

ከዚህ ከዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ አንድ ዓይነት ምርቶች በአንዳንድ ክልል ከተሞች ያለ ቫትና በቫት እየተባለ የተጣለው ዋጋ፣ መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ካስተላለፈበት አሠራር ጋር የሚጣረስ መሆኑ ነው፡፡

የዋጋ ተመኑን አተገባበር በሚመለከት የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁትም በአንድ ከተማ የተለያየ ዋጋ ሊኖር ካለመቻሉም በላይ በቫትና ያለቫት የሚል መመሪያ አለመተላለፉን ነው፡፡

ምናልባት የዋጋ ልዩነት ሊኖር የሚችለው መንግሥት ከተመነው ዋጋ በታች ለመሸጥ ፍቃደኛ ከሆነ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት አንድ ቢራ ሰባት ብር ከ10 ሳንቲም ይሸጥበት ሲል ዋጋው ቫትንም አጠቃሎ ነው፡፡ ነገር ግን ቫት ሳይቀር ሰባት ብር ከ10 ሳንቲም በታች ለመሸጥ የሚችል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

አሁን በአንዳንድ የክልል ከተሞች ግን አንድ ቢራ በአምስት ብር ከ27 ሳንቲም እንዲሸጥ ማስታወቂያ ወጥቷል፡፡ በሌሎችም ምርቶች ላይ ተመሳሳይ የሆነ ተመን ስላለመውጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

እንዲህ ዓይነቱን ክፍተቶች ለመድፈን መንግሥት የተጠናና እንደክልሉ ርቀትና ተጨባጭ ሁኔታ ተስማሚ የሆነ አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ኃላፊነቱ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

የእርምጃው መዘግየት ገበያው የተረጋጋ እንዳይሆን ማድረጉ የማይቀር በመሆኑ በየክልሉ የዋጋ ትመናን የሚያስተባብሩ መሥሪያ ቤቶችንና የፌዴራል ንግድ ሚኒስቴር በቅርብ ሊከታተሉት ይገባል፡፡