በምሕረት አስቻለው
ባለቤታቸው የመጀመርያ ልጃቸውን አርግዛ በነበረበት ወቅት በተደጋጋሚ ይታመሙ ነበር፡፡
ሕመማቸው ከባድ ሊሆን ይችላል ብለው ባይገምቱም የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው አሰቡ፡፡ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል የሔዱት ለብቻቸው ሳይሆን ነፍሰ ጡር ሚስታቸውንም ይዘው ነው፡፡
ዕድሜያቸው በአርባዎቹ መጨረሻ የሚገኘውና በንድፍ ዲፕሎማ ያላቸው እኚህ ሰው ለስምንት ዓመታት በምሕንድስናው ዘርፍ ሠርተዋል፡፡ ባለቤታቸው ግን ያልተማረች በመሆኗ ስለኤችአይቪ፤ የጥንዶች ውጤት ሊለያይ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን አታውቅም ነበር፡፡ ለእሳቸው ግን ደም ከመስጠታቸው በፊት የተሰጣቸው ምክር ሙሉ ለሙሉ እንግዳ አልነበረም፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አልፎ አልፎ የሚከሠት ቢሆንም የጥንዶች ውጤት መለያየት (Discordance) ያጋጥማል፡፡ እኚህ ሰውና ባለቤታቸው በ1998 ዓ.ም. የኤችአይቪ ምርመራ ባደረጉበት ጊዜ የታየውም ይኸው ነበር፡፡ ባለቤታቸው ከኤችአይቪ ነፃ፤ እሳቸው ደግሞ በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስ ተገኘ፡፡ እንዴት ልያዝ ቻልኩ? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመው ለራሳቸው በማንሣት ከራሳቸው ጋር ብዙ ተወዛገቡ፤ ደነገጡ፤ አዘኑም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የባለቤታቸው ነፃ መሆን አስደሰታቸው፡፡
ባለቤታቸው አልለይህም በማለቷ ዛሬም በአንድ ላይ ናቸው፡፡ እሳቸውም ለባለቤታቸው በማሰብ እንጂ አብሮነታቸውን አልጠሉትም ነበር፡፡ ያለኮንዶም ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይፈጽሙ ምክር ቢሰጣቸውም ባለቤታቸው አሻፈረኝ በማለቷ ምርመራ አድርገው ውጤታቸውን ካወቁ በኋላ ሁለት ልጆችን ወልደዋል፡፡ እሳቸው ግን ከጊዜ በኋላ ብትያዝስ? ብለው ይሰጋሉ፡፡ የመጀመሪያዋ ልጅ የአራት፣ ሁለተኛው የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆኑ ሁለቱም በተደጋጋሚ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየሠሩ ባለመሆኑ የሚተዳደሩት በሚያገኙት ዕርዳታ ብቻ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትም በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡ ችግር፣ ሕመምና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ አንዳንድ ማኅበራዊ ጫና ኑሮውን ቢያከብድባቸውም፣ ከአንደበታቸው ጽናት ጥንካሬአቸውን መገመት ይቻላል፡፡ በ2000 ዓ.ም. በሕንፃ ሥራ ሰርተፊኬት አግኝተዋል፡፡ ባለቤታቸውን ወደ ዐረብ አገር ለመላክ ፓስፖርት አውጥተው ነገሮችን በማጤን ላይ ናቸው፡፡ የተለያዩ የሥራ ማስታወቂያዎችን እየተከታተሉ ሥራ ለማግኘት ደፋ ቀና ቢሉም እስካሁን አልተሳካላቸውም፡፡
በመቅድም ኢትዮጵያ ጥንድ ሆነው የኤችአይቪ ምርመራ ያደረጉና ውጤታቸው የተለያየ ግለሰቦች ማኅበር አባል ናቸው፡፡ በ1995 ዓ.ም. ምርመራ ካደረጉ በኋላ በመቅድም ኢትዮጵያ አባል ሆነዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉን፣ ሃያ ሁለቱ የማኅበሩ አባላት በየወሩ አንድ ጊዜ እየተገናኙ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያልተገኘ ኮንዶም መጠቀም አለመፈለግ፤ ልጆች ማፍራት መፈለግና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ለውይይት ይቀርባሉ፡፡
‹‹ከጥንዶች ውጤት መለያየት ጋር በተያያዘ ብዙ እንቆቅልሽ አለ፡፡ አንዳንዱ ፍጹም አልያዝም ብሎበማሰብ ኮንዶም አልጠቀምም ብሎ ያስቸግራል፡፡ በአንዳንዶች በመጀመርያ ልጅ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ተገኝቶ የሁለተኛው ውጤት የተለየ ይሆናል፡፡ በኮንዶም ካልተጠቀሙ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የሌለው ሰው በሒደት ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ያልተያዙ ሰዎችንም እየተመለከትን ነው፤›› በማለት እሳቸው ዘወትር ግንኙነት የሚፈጽሙት በኮንዶም እንደሆነ፤ ከጊዜ ብዛት ባለቤታቸው ተጋላጭ ይሆናሉ ብለው ስለሚሰጉም በየሦስት ወሩ እንደሚያስመረምሯቸው ገልጸውልናል፡፡
የጥንዶች የኤችአይቪ ምርመራ ውጤት መለያየት የሚከሠተው በዚህ ምክንያት ነው ተብሎ በግልጽ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ፣ ይልቁንም በዚህ ረገድ የሚሰነዘሩት መላምቶች መሆናቸውን በዘውዲቱ ሆስፒታል የኤችአይቪ የፈቃደኝነት ምርመራ ማዕከል ባለሙያ ሲስተር አልማዝ ነዲ ነግረውናል፡፡
እንደ እሳቸው አባባል፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጥንድ ሆኖ የመመርመር ሁኔታ አነስተኛ ስለነበር የጥንዶች ውጤት መለያየቱም አነስተኛ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥንዶች አንድ ላይ እየተመረመሩ ስለሆነ የውጤት መለያየት ጨምሮ እየታየ ነው፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኅንም ስለዚሁ መለያየት ሽፋን እየተሰጠ መሆኑ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ እያሰፋ ነው፡፡ እ.ኤ.አ 2007 ላይ በሁለት የፈቃደኝነት ምርመራ ማዕከሎች ላይ በተደረገ ጥናት ከአሥር ሺሕ ጥንዶች አንድ ሺዎቹ ውጤታቸው የተለያየ መሆኑ ሊታወቅ ችሏል፡፡
ውጤታቸው የተለያየ ጥንዶችን ያለኮንዶም ግንኙነት ማድረግንና ፍሬ ማፍራትን በማስመልከት ሲስተር አልማዝ እንዳሉት፣ ያለ ኮንዶም ግንኙት ማድረግ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የሌለውን ሰው ለቫይረሱ እንዲጋለጥ ያደርጋል፡፡ አባት ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ቢኖርና እናት ነፃ ብትሆን የሚወለደው ሕፃን ከቫይረሱ ነፃ ይሆናል፡፡ አባት ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ባይገኝ እና እናት ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ያለ ብትሆን የቫይረሱ ከእናት ወደ ጽንስ የመተላለፍ እድል አርባ በመቶ በመሆኑ ይህንንም በሕክምና መከላከል ስለሚቻል ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ ይወለዳል፡፡
‹‹የውጤት መለያየት የአንደኛው ታማኝ መሆን ወይም የሌላው አለመሆን አይደለም፡፡ ስለሁኔታው መከሠት እስካሁን እየተሰጠ ያለው መላምት ነው፡፡ ይህ እርግጥ ያልሆነ መላምት ደግሞ ለሚመረመሩም ሆነ ተመርምረው ውጤታቸው የተለያየ መሆኑን ላወቁ አይነገርም፤›› በማለት አክለዋል፡፡
በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የፈቃደኝነት ምርመራ ማዕከል ሥራውን ከጀመረበት ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዘንድሮው መስከረም ድረስ 22,413 ጥንዶች ተመርምረው፣ 1,643ቱ ውጤታቸው መለያየቱን ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡


