በይስማው መንግስቱ
ለዚህ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በሚዲያ ሰፊ ሽፋን አግኝቶ የመወያያ ርዕስ ሆኖ የሰነበተው የሸቀጦች ዋጋ ቁጥጥርን አስመልክቶ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጠራ ስብሰባ ላይ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታ አቅርበውት የነበረው የጥናት ጽሑፍ ነው፡፡
መንግሥት ከተለመደው አካሄዱ ወጣ ብሎ ወደ እዝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዘው ብሎ እንደገባ ያስቆጠረውን ዕርምጃ ለመውሰድ የተገደደበትን ሁኔታ ዋና ዳይሬክተሩ በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ በጥናታቸው የአገሪቱ የግብይት ሰንሰለት በጥቂት ነጋዴዎች ተፅዕኖ ሥር መውደቁ፤ የሸቀጦች መሸጫ ዋጋ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የሚወሰንበት ሁኔታን እንደፈጠረና፤ መንግሥትም ከመስመር ‹‹ያፈነገጠውን›› የግብይት ሥርዓት በማረቅ የሸማቹን መብት የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ገበያው በጥቂት ነጋዴዎች ሥር ለመውደቁ ማሳያ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት ምግብና ምግብ ነክ ካልሆኑ ሸቀጦች 57 በመቶ የሚሆነው ከ3ዐ በማይበልጡ ነጋዴዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሒደት በአገሪቱ ጤናማ ያልሆነ የግብይት ሥርዓት እንዳይሰፍን እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ጣልቃ መግባቱ ተገቢ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከላይ ያነሱትን የመከራከሪያ ነጥብ በተወሰነ ደረጃ እጋራለሁ፡፡ የአንድ አገር የገበያ ሥርዓት በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ሥር ከወደቀ አገሪቷን የከፋ ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይታወቃል፡፡ እናም ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር መንግሥት የገበያውን መጫወቻ ሜዳ መደላድል በመፍጠር ጤናማ የነፃ ገበያ ሥርዓት እንዲዳብር የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡
የግብይት ሥርዓቱ በጥቂት ነጋዴዎች መዳፍ ሥር መውደቅ የሚፈጥረው አደጋ አንድ ነገር ሆኖ፤ የእኔ ችግር ይህንን ለመታደግ መንግሥት የወሰደው የዋጋ ቁጥጥር ዕርምጃ በራሱ የታለመለትን ግብ ከማሳካት አኳያ በቂ አይደለም የሚል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንግሥት ለችግሩ መፈጠር አስተዋጽኦ ያደረጉ መሠረታዊ ምክንያቶችን (Root causes) ለይቶ ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ ካልወሰደ በስተቀር፤ የሸቀጦች ዋጋ ተመን መወሰን የመሳሰሉ የችግሩ መገለጫዎችን (Symptoms) ለማስታገስ የሚወሰደው ዕርምጃ መሠረታዊ ለውጥ አያስገኝለትም፤ እንደውም ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት ዋና ዳይሬክተሩ ያሠመሩበት የግብይት ሰንሰለቱ በጥቂት ነጋዴዎች ቁጥጥር ሥር መውደቅ እንዴት ሊከሰት እንደቻለና ይህንን የተወላገደ አካሄድ ከማቃናት አኳያ መንግሥት ራሱን ጨምሮ ሊፈትሻቸው ከሚገባቸው መሠረታዊ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን ለመንሳት እሞክራለሁ፡፡
ወደጽሑፌ ጭብጥ ከመሸጋገሬ በፊት በጽሑፌ ርዕስ የተጠቀምኩበት ‹‹3ዐዎቹ›› የሚለው ቃል በአጭሩ ‹‹ጥቂቶች›› የሚለውን የሰለቸ አጣጣይ አገላለጽን በቁጥር በመተካት ለጽሑፌ ማጣፈጫነት ለመጠቀም መሆኑ ታውቆልኝ፤ ዋና ዳይሬክተሩ በጥናታቸው ካመላከቷቸው ግለሰቦች ወይንም ድርጅቶች ጋር በምንም መልኩ እንዳይያያዝብኝ አደራ እላለሁ፡፡
የፋይናንስ ወይም የገንዘብ አቅም የአቅሞች ሁሉ ንጉሥ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ የአገሬ ሰው ‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› የሚለው ገንዘብ /ወይም ሀብታም ገንዘቡን ተጠቅሞ/ መፍጠር የማይችለው ነገር እንደሌለ አጉልቶ ለማሳየት ሲፈልግ ነው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ጠቀስ አድርገው ያለፉት የ"Oligarchy" /በጥቂት ሰዎች ተጽእኖ ሥር የወደቀ ሥርዓት/ ጉዳይ ባልዳበረ የፋይናንስ አቅም ሊያብብ ቀርቶ ሊያቆጠቁጥ ከቶም አይቻለውም፡፡ ስለሆነም የአንድ አገር የግብይት ሠንሠለትን በመቆጣጠር ትርጉም ያለው ተጽእኖ ለማሳረፍ ከሁሉም በላይ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የግድ ይላል፡፡
ከዚህ በመነሳት መንግሥት ገበያውን በመቆጣጠር ያለአግባብ ዋጋ በማናር የሚከሳቸው ጥቂቶቹ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የካፒታል መጠን ያላቸው ባለሀብቶች መፈጠር እንደመልካም ውጤት የሚታይ በመሆኑ እኔም እንደዜጋ በዚህ መሠረታዊ አስተሳሰብ ላይ ችግር የለብኝም፡፡
የእኔ ቅሬታ የ‹‹3ዐዎቹ›› የፋይናንስ አቅም ‹‹በብርሃን ፍጥነት›› እየጎለበተ ሄዶ የግብይት ሰንሰለቱን ለመጨምደድ የበቃበት አካሄድ ላይ ነው፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚል ዘይቤ የተቀረፀ በሚመስለው አካሄድ የዳበረ የፋይናንስ ጡንቻ በጽኑ ሊወገዝና ተገቢው ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባ አካሄድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጤናማ ያልሆነው አካሄድ በመንግሥት በኩል ገደብ ሳይበጅለት እስካሁን እንዲቀጥል የተደረገበት ሁኔታ ዛሬ መንግሥትን በእጅጉ ላሳሰበው የአገሪቷ ገበያ በጥቂት ሰዎች እጅ መወድቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
በአገራችን ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉት ባንኮች ናቸው፡፡ እናም በንግድ ሥራ የተሠማሩ ዜጎች ሥራቸውን ለማካሄድ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ በአብዛኛው የሚያገኙት ከነዚህ ተቋማት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያበቡ የመጡት የአክሲዮን ማኅበራት ከዚህ በተለየ መልኩ ከኅብረተሰቡ ካፒታል በማሰባሰብ የንግድ ሥራቸውን የሚያካሂዱበት ሁኔታን ለመፍጠር የቻሉ ቢሆንም፤ ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ፍላጎት በማሟላት ረገድ የባንኮች ሚና አሁንም የጎላ ሆኖ ይታያል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሦስተኛው የሩብ ዓመት ሪፖርቱ እንደጠቆመው፣ እ.ኤ.አ በመስከረም 2ዐ1ዐ መጨረሻ በባንኮች በኩል ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በብድር መልክ የተለቀቀው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከብር 58.9 ቢሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፤ በተመሳሳይ መልኩ ባንኮቹ ከኅብረተሰቡ ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ብር 95 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
ሪፖርቱ የግል ባንኮች በተጠቀሰው የሪፖርት ጊዜ ከብር 36.4 ቢሊዮን በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰባቸውንና ከዚህ ውስጥ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ለብድር አገልግሎት ማዋላቸውን ይገልጻል፡፡ /ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድህረ ገጽ የተወሰደ/
ከላይ ከቀረበው መረጃ ለመረዳት የሚቻለው የግል ባንኮች በአገሪቷ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ሚና እየጎለበተ መምጣቱን ነው፡፡ ይህ አበረታች ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት በጥንቃቄ ሊወስዳቸው ከሚገባው ዕርምጃዎች አንዱና ዋንኛው ባንኮች ጤናማ በሆነ የፋይናንስ አሠራር ታንጸው የሚጎለብቱበት መንገድን ማመቻቸት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ባንኮች በአብዛኛው በሕዝብ ሀብት ሥራቸውን የሚያካሂዱ እንደመሆኑ መጠን ተገቢው ቁጥጥር ካልተደረገባቸው የጥቅማቸውን ያህል የሚያስከትሉት አደጋ ከፍተኛ ሊሆን በመቻሉ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት የግል ባንኮች ለአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ያደረጉት አስተዋጽኦ ሚዛን የሚደፋ ቢሆንም፤ ጥቂት የማይባሉ ባንኮች ከባለቤትነት ይዞታ ጋር በተያያዘ እንደግብይት ሥርዓቱ ሁሉ በ‹‹3ዐዎቹ›› ተጽእኖ ሥር መውደቃቸው በተወላገደ የባንክ አሠራር እንዲያልፉ አስገድዷቸዋል፡፡ እንዲሁም አልፎ ተርፎ ለሚታየው ጤናማ ያልሆነ የገበያ ሥርዓት መፈጠር፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ ተስተውለዋል፡፡ ይህ ጤናማ ያልሆነ አካሄድ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለና ከዚህ አሠራር ‹‹3ዐዎቹ›› እንዴት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደቻሉ ለማሳየት ልሞክር፡፡
ከላይ በጥቂቱ ለመነካካት እንደሞከርኩት በአንዳንድ ባንኮች ሥር በሰደደ መልኩ ለሚታየው የተወላገደ አሠራር ዋነኛው መነሻ ከባለቤትነት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ባንኮቹ በጥቂት ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ባለቤትነት ይዞታ ሥር መውደቃቸውና ባለቤቶቹም ባንኮቹን የራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ መሳሪያ አድርገው መጠቀማቸው ነው፡፡
በግልጽ እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የግል ባንኮች ለበርካታ ዓመታት /እስከአሁን ድረስ ማለት ይቻላል/ በጥቂት ባለሀብቶች ይዞታ ሥር ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ይህ የራሱ ታሪካዊ ምክንያት አለው፡፡ መንግሥት በአገሪቷ ለበርካታ ዓመታት ተዳክሞ የነበረውን የባንክ ሥራ እንዲያንሠራራ ለማስቻል ከወሰደው ተቀዳሚ ዕርምጃ አንዱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሠማሩ መፍቀዱ ነበር፡፡ በወቅቱ በዘርፉ የሚሠማሩ ባለሀብቶችን ከማበረታታት አኳያ፤ መንግሥት ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን ዝቅተኛ ከማድረጉም ባሻገር የግል ባለሀብቶች በአንድ ባንክ እስከ 2ዐ በመቶ የሚደርስ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ይህ አሠራር ለዓመታት ቀጥሎ ከሦስት ዓመታት በፊት በተሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ የአክሲዮን ይዞታ መጠን ከአምስት በመቶ እንዳይበልጥ የሚደነግግ አዋጅ ወጥቷል፡፡ /ተግባራዊነቱ ገና በሒደት ላይ የሚገኝ ቢሆንም/
ከዚህ ታሪካዊ ሒደት ጋር በተያያዘ ከአሥርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ አብዛኛዎቹ የግል ባንኮች በጥቂት ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት ሥር ወድቀው እናገኛቸዋልን፡፡ አንድ ባንክ በ2ዐ ሰዎች ተቋቋሞ በ2ዐዐ ሰዎች የባንክ አሠራር ደንብና መመሪያ ጠንካራ ሆኖ ተግባራዊነቱ እስከተረጋገጠ ጊዜ ድረስ የባለቤቶቹ ቁጥር ማነስና መብዛት በራሱ የችግር ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው በጥቂት ባለሀብቶች የተቋቋሙ ባንኮች የባለቤትነት መሠረታቸውን እያሰፉ ወደሕዝብ ባንክነት ራሳቸውን እየቀየሩ፤ በዛው መጠን ከጥቂት ግለሰቦች ተጽእኖ እየወጡና ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር እየተከተሉ እንደሚጓዙ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው አማዴዎ ጂናን በተባለ ኢጣሊያ በ1904 የተቋቋመውና ዛሬ በምድረ አሜሪካ የባንክ ሥራን በከፍተኛ ደረጃ ተቆጣጠሮ የሚገኘው ባንክ ኦፍ አሜሪካ ነው፡፡
በእኛ የግል ባንኮች እየተስተዋለ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከአሥርት የሥራ ዓመታት በኋላ የግል ባንኮች የባለቤትነት ድርሻን ለመረመረ የ‹‹3ዐዎቹ›› የአንበሳ ድርሻ እምብዛም ሳይቀየር ለመቆየት በቅቷል፡፡ ይህ ደግሞ ባንኮቹ እንደባንክ ከ‹‹3ዐዎቹ›› አሉታዊ ተጽእኖ ተላቀው በነፃነት መሥራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡
የግል ባንኮች በ‹‹3ዐዎቹ›› ተጽእኖ ሥር ወድቀው እንዲቀጥሉ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ መንግሥት የራሱን ሚና ተጫውቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግሥት የባንክ የንግድ ዘርፍ በአገር በቀል ባለሀብቶች ይዞታ ሥር እንዲሆን የቀየሰው ፖሊሲ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፤ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከባለቤትነት ይዞታ ጋር በተያያዘ የሚመነጩ አደጋዎችን ለመታደግ የሚያስችል ተመጣጣኝ የማስተካከያ እርምጃ ያለመውሰዱ ለችግሩ መፈጠር አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋልን፡፡ ይህ ደግሞ የባንኮችን ሥራ የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር አቅም በተመጣጣኝ መልኩ ካለመጎልበቱ ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት በኩል በግልጽ የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡
በአንድ ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈረንሳይ አገር ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ላይ የባንክ ሴክተሩ ለውጭ ባለሀብቶች ለምን ክፍት እንዳልተደረገ በፈረንሳይ ባለሀብቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ የመለሱት፣ ‹‹የባንኮች ሥራን የሚቆጣጠረው ማዕከላዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅሙ ገና ያልዳበረ፤›› መሆኑን በመግለጽ ነበር፡፡ እውነታቸውን ነበር፡፡ በወቅቱ ማዕከላዊ ባንኩ እንኳን በአሠራር የዳበሩትን ዓለም አቀፍ ባንኮችን ለመቆጣጠር ቀርቶ፤ በመዳህ ላይ የሚገኙትን አገር በቀል ባንኮችንም በተሟላ መልኩ ለመቆጣጠር የሚያስችለው የሠለጠነ የሰው ኃይልም ሆነ የአሠራር ሥርዓት ብሎም ቴክኖሎጂ አልነበረውም ማለት ይቻላል፡፡
እንግዲህ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ነበር ‹‹3ዐዎቹ›› በግል ባንኮች በኩል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የበቁት፡፡ ጉዳዩን ለአንባቢ ግልጽ ለማድረግ ‹‹3ዐዎቹ›› ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ባለፉት በርካታ ዓመታት የተጓዙበትን መንገድ አለፍ አለፍ እያልኩኝ ላስቀምጥ፡፡ አክዬም በዚህ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ‹‹3ዐዎቹ›› የፋይናንስ አቅማቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ከመጣል አልፈው ባንኮቹን ተከልለው በንግድ ተፎካካሪዎቻቸው ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ በገበያ ውስጥ ሊፈጠር የሚገባውን ተወዳዳሪነት በማቀጨጭ የግብይት ሥርዓቱን ለመቆጣጠር የተከተሉትን ስልት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ዓላማዎችን ከማሳካት አኳያ ‹‹3ዐዎቹ›› በባንኮች ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ ተጠቅመውና ራሳቸውን አደራጅተው በመጀመሪያ የሚቆጣጠሩት የባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድን ነው፡፡ የባንኮች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በተጠራ ቁጥር የእሁድ ጋዜጦችን አምድ ሞልቶ የሚታየው ‹‹የእነእገሌ ቡድን የራሱን የዳይሬክተሮች ቦርድ አስቀመጠ›› ‹‹እገሌ ከቦርድ ተነሳ፤ በእገሌ ተተካ›› ወዘተ የውዝግብ ዜና የሚመነጨው ‹‹3ዐዎቹ›› ባንኮቹን ከመቆጣጠር አኳያ ከሚያደርጉት ፍልሚያ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከ‹‹3ዐዎቹ›› ዘንድ በቦርድ የሚቀመጡ ዳይሬክተሮች ታማኝነትና ታዛዥነት ለድርድር የሚቀርብ አጀንዳ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለዓመታት ጓደኛሞችና የንግድ ሸሪኮች የሆኑ የባንክ ባለቤቶች በቦርድ አባላት ምርጫ ሐሳብ ልዩነት ፈጥረው እስከመጨረሻው የሚቆራረጡበት ዋናው ምክንያት በቦርድ በኩል የሚያስጠብቁት የግል ጥቅማቸውን ለድርድር ለማቅረብ ልባቸው ስለማይቀበለው ነው፡፡
እናም የ‹‹3ዐዎቹ›› የቅድሚያ ትኩረት የግልና የቡድን ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ አኳያ ያለማወላወል ዘብ የሚቆም ኃይልን በቦርድ አባልነት ማሰባሰብ ላይ ይሆናል፡፡ ለዚህም ዳጎስ ያለ የቦርድ አባል ክፍያ በመደለያነት ይቀርባል፡፡ /ይህን አገር ያባላ የአበል ጉዳይ ዘግይቶም ቢሆን በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ገደብ የተጣለበት መሆኑን ከጋዜጦች ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ያስቀመጠው ዝቅተኛ የአበል መጠን ግን ነገ እንደፓልም ዘይት ዋጋ እንይከለስ ፍርሀት አለኝ፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ሌሎች ጥቅሞችም በማበረታቻነት በማቅረብ የጥቅማቸው አስጠባቂ ኃይል ተግቶ እንዲሠራ ተደርጎ ይዋቀራል፡፡ በዛው መጠን የ‹‹3ዐዎቹ››ን ጥቅም አላስጠበቁም ወይም አያስጠብቁም ተብሎ የታመነባቸው የቦርድ አባላት አቋማቸው በየጊዜው እየተፈተሸ እንደአሮጌ ቁና እየተጣሉ፤ በሌሎች ታማኝ ተብዬዎች እንዲተኩ ይደረጋል፡፡ እነርሱ እንቅፋት ይሆናሉ ብለው የጠረጠሯቸውን የቦርድ አባላትን አንዳንድ ጊዜም ባንኩን ተጠልለው ወንጀል እንደሠሩ በማስመሰል ሲከስሷቸውና ሲያስከስሷቸው ይታያል፡፡
‹‹3ዐዎቹ›› የቦርድ አባላት ምርጫን በከፍተኛ ጥንቃቄ የብሔራዊ ባንክ መመሪያን በማይጥስ መልኩ ሲያከናውኑ ይታያል፡፡ ተቆጣጣሪው ባንክ ‹‹3ዐዎቹ›› የሚያቋቁሙት ቦርድ ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም የቆመ መሆኑን እንኳን በሆዱ ቢያውቅም፣ መመሪያ ያለመጣሱን ብቻ እየተመለከተ ሁኔታውን በዝምታ ያስቀጠለበት ጊዜያት ተስተውሏል፡፡
በአንድ የግል ባንክ ተፈጸመ የተባለውን ላጫውታችሁ፡፡ ‹‹3ዐዎቹ›› ዓይን ባወጣ መንገድ በግል ድርጅቶቻቸው ደመወዝ እየቆረጡ የሚያሠሯቸውን ሠራተኞች በቦርድ አባልነት አስመርጠው ማሠራት ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ የቦርድ አባላት ብዙም ሳይቆዩ ለውሳኔ በቀረበ በአንድ ከፍተኛ የባንኩ አጀንዳ ላይ አሠሪዎቻቸው የያዙትን የተንሸዋረረ አቋም ባይጥማቸውም ተቀብለው ለማስፈጸም ሲሯሯጡ፣ ከሌሎች የቦርድ አባላት ጋር በፈጠሩት የሐሳብ ልዩነት ምክንያት ቦርዱ ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ በዚህም የተነሳ ቦርዱ የዕለት ሥራው ጭቅጭቅ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ጉዳዩ ብሔራዊ ባንክ ጆሮ ደርሶ ባንኩ ጣልቃ ይገባል፡፡ በቦርዱ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መንስዔው የከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ጣልቃ ገብነት መሆኑን የቦርዱ አባላት በብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣኖች ፊት አምነው ችግሩን ለማስተካከል ቃል ገብተው ይለያያሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ብሔራዊ ባንኩ እነዚህ ችግር ፈጥረዋል ያላቸውን ግለሰቦች አስጠርቶ እጃቸውን በባንኩ ሥራ እንዳያስገቡ ማስፈረሪያ አዘል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ ከዛስ በኋላ ምን ተፈጠረ? ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ብሔራዊ ባንኩ እጃችሁን አውጡ ብሎ እንዳልመከረ፤ እንዳላስፈራራ ባልታወቀ ምክንያት ቀስ ብሎ የራሱን እጅ ሰበሰበ፡፡ እናም ሁኔታዎች በዛው እንዲቀጥሉ የዝምታ ፈቃዱን ሰጥቶ ጉዳዩ ተዳፍኖ ቀረ፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ አንድ ነገር ልጨምር፡፡ አንድ ሰሞን ከፍተኛ የባንክ ባለአክሲዮኖች በባንኮች የውስጥ አሠራር ጣልቅ እየገቡ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖ ለማስወገድ በማሰብ ብሔራዊ ባንኩ አዲስ የባንኮች መተዳደሪያ አዋጅ አዘጋጅቶ በተቻኮለ መልኩ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አጸድቆ ነበር፡፡ ይህ አዋጅ በጊዜው ከፍተኛ የሚባል ተቃውሞ ከየአቅጣጫው ገጥሞት ነበር፡፡ በተለይም ከባንክ ባለአክሲዮኖችና ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት አካባቢ፡፡ የተቃውሞው ምክንያቶች ሁለት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛውና ዋነኛው አንድ በባንክ ሥራ መዋዕለ ንዋዩን ያፈሰሰ ባለሀብት በራሱና በቤተሰቡ ወይንም ተዛማጅ ድርጅቶቹ በኩል በባንክ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው አጠቃላይ የአክሲዮን ድርሻ መጠን ላይ ገደብ መጣሉ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ አዋጁ ከአሠራር ጥሰት ጋር በተያያዘ በባንክ ቦርድና ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ላይ ያስቀመጠው የወንጀል ቅጣት ከፍተኛ መሆኑ ነበር፡፡
የሚገርመው ግን ይህ አዋጅ በምክር ቤቱ ቀርቦ እ.ኤ.አ በነሐሴ 2ዐዐ8 የፀደቀ ቢሆንም፤ ወደተግባር ለመሸጋገር ዓመታትን ማስቆጠሩ ሳያንሰው፤ አዋጁን ለማስፈጸም ዘግይተው የወጡት መመሪያዎች /በተለይም የአክሲዮን ይዞታን ማስተካከያ አፈጻጸም መመሪያ/ ዘገምተኛ በሆነ መልኩ እንዲሄድ ተፈርዶበት ሲድህ ይታያል፡፡ ለዚህ ባንኩ የሚሰጠውን ምክንያት ባላውቅም፤ እኔ በግሌ የ‹‹3ዐዎቹ›› ረጅም እጅ ጣልቃ ገብነትን መጠርጠሬ አይቀርም፡፡
ወደተነሳሁበት ነጥብ ልመልሳችሁና ከላይ ባስቀመጥኩት አካሄድ የተፈጠረው ቦርድ የ‹‹3ዐዎቹ››ን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ይህንን ተልዕኮ በብቃት ከመወጣት አኳያ በቅድሚያ ቦርዱ /የባለአደራ ቦርድ ማለቱ ሳይሻለኝ አይቀርም/ የሚወስደው ዕርምጃ ቃል ኪዳኑን ያለማወላወል የሚያስጠብቅለት የባንክ መሪ በሥሩ ማስቀመጥ ይሆናል፡፡ ይህ በሁለት መልኩ ይኬድበታል፡፡ በወቅቱ የሚገኘው የሥራ መሪ ይህንን ዓላማ ለማስፈጸም እንቅፋት ነው ተብሎ ከታሰበ፤ ሰውየውን በፍጥነት ከቦታው በማንሳት ወይም በማባረር ቦርዱ ሥራውን አሀዱ ብሎ ይጀምራል፡፡ አዲስና ታማኝ ትዕዛዝ ፈጻሚ መሪም በምትኩ ያስቀምጣል፡፡ ቦታውን ይዞ የተቀመጠው ከ‹‹3ዐዎቹ›› ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሥራውን የሚያቀላጥፍ ከሆነም፤ ቦርዱ ‹‹የቡድን ሥራ›› የሚያሰፍን የሥራ ክፍፍል አበጅቶ Status quo አስከብሮ ያስቀጥላል፡፡
በ‹‹3ዐዎቹ›› ተጽእኖ የተፈጠረው ሥርዓት እንደትናንሽ ባለአክሲዮኖች የባንካቸው ጠንካራና ትርፋማ መሆን ብዙም ሲያስጨንቃቸው አይታይም፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ አክሲዮኖቻቸውን ለብድር ዋስትና በማስያዝ ገንዘባቸውን ወጪ ያደረጉ በመሆኑ ባንኮቹ ቢከስሩ እንኳን ከአደጋው ቀድመው ያመለጡ መሆናቸውን ስለሚረዱ ነው፡፡ ሌላው እንደማንኛውም የአክሲዮኖች ባለቤቶች የባንኩን ትርፍ ተጋሪ ከመሆን የሚገድባቸው የሕግም ሆነ የፖሊሲ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የትርፍ ክፍያውን እንደመብት አድርገው (For Granted) ይወስዱታል፡፡
ይህንን መንደርደሪያ ነጥብ ካስቀመጥኩኝ ‹‹3ዐዎቹ›› ባንኮችን የሚቆጣጠሩት ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ልሞክር፡፡ በእኔ አስተያየት ‹‹3ዐዎቹ›› ባንኮቹን ለመቆናጠጥ ሌት ተቀን የሚማስኑት ለራሳቸውና ለሸሪኮቻቸው የማያቋርጥ የገንዘብ /የብድር/ ድጋፍ በማግኘት ንግዳቸውን ለማስፋፋት ሲሆን፤ በተመሳሳይ መልኩ ለንግድ ሥራቸው ወሳኝ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ በተፈለገው መጠንና ጊዜ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ባንኮቹን ከለላ በማድረግ በንግድ ተፎካካሪዎቻቸውና ታዳጊ ነጋዴዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር ገበያውን ለብቻቸው የሚጋልቡበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በዚህም ሒደት ባንኮቹ ለ‹‹3ዐዎቹ›› ‹‹እናት›› ለሌሎች ደግሞ ‹‹የእንጀራ እናት›› እንዲሆኑ ይዳርጓቸዋል፡፡
ከላይ የተፈጠሩትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ‹‹3ዐዎቹ›› ሕግ የፈቀደላቸውን ያህል ብድርና የውጭ ምንዛሬ በራሳቸውና በተዛማጅ ድርጅቶቻቸው ያለውጣ ውረድ እየወሰዱ፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በወዳጆቻቸው በኩል አመቻችተው የፋይናንስ ፍላጎታቸውን ያሟላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪም እንዲሁ፡፡ /ጎበዝ!! ይህ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ጉዳይ በእያንዳንዱ ባንክ ከተፈተሸ ‹‹3ዐዎቹ›› የተጫወቷት ጨዋታ አንድ ሰሞን Wall Street የሞሉት ደላሎችና የግዙፍ ኩባንያ ሥራ አስኪያጆች አሳይተዋል የተባለውን የስግብግብነት (Greed) ሪኮርድ የሚበጥስ እንደሆነ አንድ ሰሞን የከተማው መነጋገሪያ ወሬ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡/
የ‹‹3ዐዎቹ›› ሚና ከላይ እንደጠቆምኩት የራሳቸውን ጥቅም በማስጠበቅ ብቻ አይቆምም፡፡ ይልቁንም ለእኔ ይበልጥ አስከፊ ሆኖ የሚሰማኝ፤ የንግድ ተፎካካሪዎቻቸው የፋይናንስ አቅም እንዳያድግ እንቅፋት መፍጠራቸው ላይ ነው፡፡ እነርሱ ‹‹ጠጠር›› የምታክል ዋስትና ይዘው ‹‹ቋጥኝ›› የሚያክል ብድር የሚወስዱበትን ሁኔታ እያመቻቹ፤ በተቃራኒው ሌላው ወገን-የለሹ ነጋዴ በተቃራኒው እንዲስተናገድ ያደረጉታል፡፡ ይህ አካሄድ የማያመች ሆኖ ሲያገኙት መሠረት የሌለው ወሬ እየነዙ /ስም እያጠፉ/ የብድር ሒደትን በማጓተት የተጠየቀው ብድር ከሚፈለግበት ጊዜ በላይ ዘግይቶ እንዲሰጥ፤ ወይም የብድሩ መጠን ከሚፈለገው በታች እንዲሆን በማድረግ የተፎካካሪ ነጋዴዎችን የመወዳደር አቅም ይሸረሽራሉ፡፡ በተለይም ወደአገር ውስጥ ሸቀጥ በማስገባት የተሰማሩ መለስተኛና ትናንሽ ነጋዴዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ወይም ድርቅ እንዲሰቃዩ በማድረግ እነርሱ ያስገቡአቸውን ሸቀጦች ያለተቀናቃኝ በፈለጉት ዋጋ ይቸበችባሉ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከላይ በጠቃቀስኳቸው ወይንም በሌላ ውጫዊ ምክንያቶች የንግድ ተፎካካሪዎቻቸው የወሰዱትን ብድር በጊዜ ለመክፈል ጊዜያዊ ችግር ሲያጋጥማቸው፤ ከባንኩ ተገቢውን እርዳታ ሳያገኙ ወደሞት /ኪሳራ/ ወረዳ እንዲወረወሩና ዋስትና ያስያዙት ንብረቶቻቸው በፎርክሎዠር አዋጅ ተሸጦ ከገበያ እንዲወጡ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡ ይህም ካልተሳካ ወደፊት ከባንኮች ብድር የማግኘት እድል እንዳይኖራቸው ስማቸውን በማጥፋት ሒደት ይሰማራሉ፡፡ በተቃራኒው ችግር የደረሰበት የ‹‹3ዐዎቹ›› ወገን ሲያጋጥም ‹‹ባንካቸው›› ከመስመር ወጣ ብሎ ልዩ ድጋፍ እንዲያደርግለት በየአቅጣጫው ይጥራሉ፡፡ ለዚህም መሳካት በቦርድና በሥራ አመራሩ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ይፈጥራሉ፡፡
የ‹‹3ዐዎቹ›› የተጽአኖ አድማስ እስከአሁን ካልኳቸው በላይ የሚሄድበት ሁኔታም አለ፡፡ ለዚህም እንዲያመቻቸው እስከሥር ሠራተኛ ድረስ በመውረድ በባንኩ ውስጥ የሚከናወኑ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ይቆጣጠራሉ፡፡ በተለይም የብድርና የውጭ አገር ባንኮች ግንኙነት መምሪያዎችን በተቻለ መጠን በራሳቸው ሰዎች እንዲያዙ ያደርጋሉ፡፡ በተወሰነ ደረጃም የበታች ሠራተኞችን በጥቅም እየደለሉ ‹‹ማን መቼ ብድር እንደጠየቀ››፤ ‹‹ምን ያህል ብድር እንደጠየቀ››፤ ‹‹የትኛው ነጋዴ ምን ዓይነት እቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ኤል ሲ እንደከፈተ››፤ ‹‹ከየትኛው የውጭ ኩባንያ ጋር የንግድ ግንኙነት እንደመሰረተ››፤ ‹‹በምን ያህል ዋጋ እቃዎቹን እንደገዛ›› ወዘተ በአጠቃላይ የተወዳዳሪ ድርጅቶችን /አንዳንዴ የወዳጆቻቸውንም የንግድ ሚስጥር ካላወቁ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ሰዎች አሉ/ መረጃ እያሰባሰቡ ለራሳቸው ፍጆታ ያውሏቸዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ዋጋ ይሰብራሉ፣ ዋጋ ይሰቅላሉ፤ አዋጭ መስሎ ከታያቸውም የገንዘብ አቅማቸውን ተጠቅመው ‹‹ብቸኛ የንግድ ወኪል›› የሚለውን ታፔላ ካዳከሟቸው ነጋዴዎች ነጥቀው እነርሱ ይከብሩበታል፡፡
ከእዚህ ጋር በተያያዘ በማላውቀው ጉዳይ ገብቼ መፈትፈት እንዳይሆንብኝ እንጂ ‹‹3ዐዎቹ›› የጉምሩክን ጓዳ እንደራሳቸው ቤት እየተሽሎከለኩ የነጋዴውን የንግድ ሚስጥር በመቆጣጠር የግብይቱን ሚዛን ለማዛባት የሚጫወቱት ሚና ቀላል እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ውስጥ አዋቂ ነኝ የሚል ካለ ይጻፍበት፡፡
ከፋይናንስ ሴክተሩ ትንሽ ወጣ ልበል፤ እንዳላሰለቻችሁ፡፡ በእኔ እምነት ‹‹3ዐዎቹ›› የአገሪቱን የግብይት ሠንሠለት ለመቆጣጠር የቻሉት የፋይናንስ አቅማቸውን ከላይ በዝርዝር በጠቀስኩት ሁኔታ ማጎልበት በመቻላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ የገነቡት የፋይናንስ አቅም ሌላም ግዳጅ እንዲጥሉ አስችሏቸዋል፡፡ የገንዘብ አቅማቸውንም ተጠቅመው ‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› የሚለውን አባባል ቀስ በቀስ ‹‹ጠንካራ ኔትወርክ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› ወደሚለው እየቀየሩ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ሰፊ የሆነ፤ ምናልባትም ለራሱ ለመንግሥትም አሳሳቢ የሆነ ኔትወርክ ለመዘርጋት ችለዋል፡፡ በጣም አጋነንከው አትበሉኝና በዚህ ሒደት ‹‹ትንሽ ትንሽ መንግሥት፤ መንግሥት›› ለመሽተትም ዳድቷቸዋል፡፡
‹‹3ዐዎቹ›› የፈጠሩትን ጠንካራ ኔትወርክ በመጠቀም ከባንክ አመራር ጀምሮ የፍትሕ አካላቱን ነካክቶ፤ የጉምሩክ አሠራርን አሻሽቶ፤ በፀጥታ አስጠባቂ አካላት ክፍተት ገብቶ፤ የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸውን ባለሥልጣናትን በጋሻ ጃግሬነት አነካክቶና ማጣፈጫ አድርጎ የንግድ ሥራቸውን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ለማስኬድ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ጠንካራ ኔትወርክ በጊዜ ካልተቋጨ ቀስ በቀስ ሜክሲኮን ሰንገው የያዟት የአደንዛዥ እጽ ቱጃሮች ወደፈጠሩት የሕግ አልባነት ሥርዓት አደጋ የማንገባበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
ቀደም ሲል ‹‹3ዐዎቹ›› በግል ባንኮች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ማሳረፍ የማይችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አለመቻሉ አንድ የመንግሥት ድክመት አድርጌ አንደቆጠርኩት ሁሉ፤ የግብይት ሥርዓቱን ጨምሮ በሌሎችም መስኮች የ‹‹3ዐዎቹ›› ተጽእኖ ያለገደብ ሲናኝ በመንግሥት በኩል ጠንከር ያለ ዕርምጃ ያለመውሰዱ መንግሥትን የሚያሳማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሰሞኑን ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ የከተማችን መነጋገሪያ ወሬ ሆኖ የሰነበተው ዜና የሚያስተላልፈው መልዕክት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የቦሌ ምድብ ችሎት ዳኛ በነበሩ አንድ ግለሰብ ተፈጽሟል ባለው የሥነ ምግባር ግድፈት መነሻነት ዳኛው ከሥራ እንዲባረሩ መደረጉን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቦናል፡፡ እርምጃው በራሱ በጎ ጅምር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
እኔን በጣም ያስገረመኝ ከኃላፊነታቸው በተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ የተነሱት ዳኛ ለፈጸሙት የሕግ ጥሰት በምክንያትነት አቀረቡ ተብሎ ይፋ የተደረገው ጉዳይ ነው፡፡ ጋዜጣው እንዳስነበበን ‹‹ዳኛው›› የአቃቤ ሕጉ የብዕር ቀለም ሳይደርቅ የክስ ፋይሉን ለመዝጋት ያበቃቸው አንዱ ምክንያት ‹‹የተከሳሹ ጠበቃ የታወቁ›› በመሆናቸው እንደሆነ ነው፡፡ ይህ መልዕክት የሚሰጠኝ ትርጉም፤ ‹‹የፈለገ ወንጀል›› ቢፈጸም ጉዳዩን ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ ሰዎች ካጀቡት /የተከሳሹ ጠበቃ በቅርቡ የተቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት አባል እንደሆኑ በሚዲያ በተደጋጋሚ ተገልጿል/ ጉዳዩ ከሕግ ማዕቀፍ ውጭ ተኪዶም ቢሆን የሚታይበት አግባብ እንዳለ ነው፡፡
እስቲ ይታያችሁ፤ አንድ በአገሪቷ ከፍተኛ የሕግ መወሰኛ አካል ውሳኔ ብቻ የሚሾምና የሚሻር ዳኛ፤ ከዛም አልፎ ሙያዊ ሥነ ምግባሩ ከማንም ተጽእኖ ነፃ ሆኖ እንዲሠራ የሚያስገድደው ዳኛ፤ ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ የሚያሳልፍ ከሆነ የእኔ ቢጤው የቢ.ፒ.አር አሞራ ከዛሬ ነገ ወደየሎስ ይጥለኛል እያለ የሚሰጋ ሠራተኛ ወይንም በባንኮች ውስጥ የቦርድንና የማኔጅመንቱን ስሜት እየጠበቀ የዕለት ጉርሱን ላለመነጠቅ አንገቱን የደፋ የባንክ ባለሙያ፣ በምን አቅምና ድፍረቱ ነው የ‹‹3ዐዎቹ››ን ተጽእኖ መቋቋም የሚችለው? ይልቁንም አንደ ‹‹ዳኛው›› የ‹‹3ዐዎቹ›› ፍላጎት የመንግሥት ፍላጎት ነው እያለና በራሱ አእምሮ እየፈጠረ የጠየቁትን በስጋት ከማስፈጸም ወደኋላ የሚልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
ከላይ ያነሳሁትን የሥነ ልቦና ተጽእኖ በየደረጃው ባሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት ሠራተኞች እንዲፈጠር ዋናው ምክንያት ‹‹3ዐዎቹ›› ያሻቸውን ጉዳይ /ሕጋዊ ባይሆንም እንኳን/ በቀላሉ ማስፈጸም የሚችሉ መሆኑን ለወዳጅም ሆነ ለጠላት በተግባርና በይፋ ማረጋገጥ በመቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹3ዐዎቹ›› የመንግሥት ወይም የገዢው ፓርቲ ወዳጅ መሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሕዝቡ እንዲደርስ ሚዲያውንም ሆነ ሌሎች አጋጣሚዎችን በጥንቃቄ ይጠቀሙበታል፡፡
ከዚህ ዓላማቸው በመነሳት መንግሥት ወይም ለመንግሥት በሚቀርቡ ተቋማት ወይም ድርጅቶች የቴሌቶን ዝግጅት ላይ ተቆርቋሪና አጋር መስለው ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊነት እንዲጎናጸፍላቸው መንግሥትን ‹‹ማኖ›› ያስነካሉ፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ ጽ/ቤት ማሠሪያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሲንቀሳቀስ ያላማው ደጋፊ መስለው በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ፡፡ ከዛም ባለፈ ዳጎስ ያለ ገንዘብ በማዋጣት በመንግስትና በሕዝብ አእምሮ ለመቀረጽ ይጥራሉ፡፡ የአገራዊ ምርጫ ዋዜማማ ‹‹ከጳጳሱ ቄሱ›› እንዲሉ ራሳቸውን የገዢው ፓርቲ ጠበቃ አድርገው ለማሳየት ድራማ ይሠራሉ፡፡ ከዋና ዋና የመንግሥት ባለሥልጣኖች /የፓርቲ ኃላፊዎች/ ጋር ትከሻ ለትከሻ ይተሻሻሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ የቁርጥ ቀን ልጆች ነን ብለው ያስወራሉ፤ ይህም ከባለሥልጣኖች ጆሮ የሚደርስበትን ሁኔታ ይቀይሳሉ፡፡ አስተዋጽዎአቸው በሚዲያ ከሚፈለገው በላይ ጎልቶ እንዲስተጋባ ገንዘባቸውን ያፈሳሉ፡፡ በሚዲያ የተነገረ ሁሉ እውነት የሚመስለው የእኔ ቢጤ ታዲያ ‹‹3ዐዎቹ›› ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሙሽራ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲመለከት እንዴት እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ድጋፍ የላቸውም ብሎ ይጠርጥር? አሰላለፉን በዛው ልክ ያሳምራል እንጂ!
ነገሬ ብዙ ስለተንዛዛ ላጠቃል፡፡ የ‹‹3ዐዎቹ›› ጉዳይ በጋዜጣ ብቻ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ከላይ ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ ‹‹3ዐዎቹ›› አይደለም የሸቀጥ ዋጋን የፈልጉትን ለማስፈጸም ስልክ ብቻ ማቃጨል በቂ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እድሜ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለገነቡት የፋይናንስ አቅምና ለዘረጉት ጠንካራ ኔትወርክ!
እናም ለዋና ዳይሬክተሩም ሆነ ለመንግሥት መልእክቴ በአጭሩ፤ ‹‹መንግሥት ሆይ! ኢሕአዴግ ሆይ! ጨዋታው ከዛ በላይ ነው፡፡ ዓይናችሁን ክፈቱ፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ በኢሕአዴግ ቸልተኝነት ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን ‹‹ኔትወርክ›› በመበጣጠስ ዙሪያ ስሩ፡፡ የባንክ አገልግሎት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለሁሉም ዜጋ የሚዳረስበትን ሁኔታ አመቻቹ፡፡ የሕግ የበላይነት ወገን ሳይለይ የሚሰፍንበትን ሁኔታ ፍጠሩ፡፡ አሁን የተጀመረውን ‹‹ዘመቻ›› ወደ ዘላቂ ‹‹ሥርዓት›› በመቀየር በሁሉም ዘንድ እምነት የሚጣልበትን አሠራር ዘርጉ፡፡ እናም ግልጽ በሆነ አካሄድ መንግሥት ከ‹‹3ዐዎቹ›› ጋር ‹‹31ኛ›› ሆኖ እንዳልተሰለፈ በማሳየት ሕዝቡ ከ‹‹3ዐዎቹ›› ጋር በተያያዘ የተፈጠረበትን ውዥንብር እንዲያጠራ እርዱት፡፡ መንግስት የሁላችንም መንግሥት መሆኑን በተግባር አረጋግጡ፡፡ ‹‹3ዐዎቹ›› አግባብ ላልሆነ ጥቅም ወደመንግሥት ስልክ ሲመቱ ‹‹መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል››፣ የሚል መልዕክት በመንግሥት በኩል ያለማቋረጥ እንዲተላለፍ አድርጉ፡፡ የዚያን ጊዜ እኔን ጨምሮ ኅብረተሰቡ ‹‹3ዐዎቹ››ን በድፍረት ተጋፍጦ መብቱን ለማስጠበቅ ግራና ቀኝ ማማተር ሳያስፈልገው ለፍትሐዊ አሠራር በጽናት ይቆማል፡፡
በመጨረሻም አንተን ብሎ መካሪ ካልተባልኩኝ በስተቀር መንግሥት ከመስመር የወጣውን የግብይት ሥርዓት በጥንቃቄ በመፈተሽ ጤነኛውን ከበሽተኛው በመለየት ሕግ አክባሪ የሆኑትን የንግድ ማኅበረሰቡ አባላትን ጥቅም በዘለቄታው ከማስጠበቅ አኳያ ተገቢውን ጥረት እንዲያደርግ አስተያየቴን እሰጣለሁ፡፡ የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዶሮን አያርዷትምና!!
ቸር እንሰንብት፡፡


