Tuesday, Jun 18th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ሆቴሎችም ይቃኙ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

መንግሥት ትኩረት መስጠት ያለበት በመጀመርያ ደረጃ በሆቴሎች ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሆቴሎችን መንግሥት ካልተቆጣጠረ የኑሮ ውድነቱ አሁንም ሊቀረፍ አይችልም፡፡ መኝታ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና ካፍቴሪያዎች የኑሮ ውድነትን በዋናነት ያባብሳሉ፡፡ ከክፍለ አገር ለንግድ ግብይት ለሚመጡ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎችና በሥራ ምክንያት ወደ ከተማ ለሚመጡ ሰዎች የኑሮ ውድነቱ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ የእሳትን ቃጠሎ መጠን የሚያውቀው እሳትን የረገጠ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ትኩረት መስጠት የሚገባው ሥፍራ ነው እላለሁ፡፡
(መሐመድ አብዱልቃድር፣ ከአዳማ)

***************
ከሥራ ጉብኝቱ ምን እንጠብቅ?
መንግሥት በውኃው መስክ ባለው ከፍተኛ ራዕይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አቅዶ ከፍተኛ የግድብና መስኖ ሥራዎች ተግባራዊ አድርጎ የአገራችንን የስኳር ፍላጎት ከመጨመር ባሻገር፣ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከፕሮጀክቶቹ በስተጀርባ የሸንኮራ አገዳ ተክልን ከፋብሪካዎቹ ጋር ፍላጎትን በማጣጣም የአገሪቷ ለም ቦታዎችን ከፍተኛ መዋለ ንዋይ መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን እነኚህ ፕሮጀክቶች በታሰበው ዕቅድ፣ ጥራት እንዲያም ሲል ፍጻሜ መድረሳቸውን ጥርጣሬ ውስጥ ይከተናል፡፡ ለእነዚሁ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት መንግሥት ባለፉት ሳምንታት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ቡድን በባለቤትነት በሚገባው የስኳር ኮርፖሬሽኑ ባለቤቶች፤ የቀድሞውንና የአሁኑ የውኃ  ሚኒስተሮች፣ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና በተጨማሪም ፕሮጀክቶቹን በአማካሪና በኮንስትራክሽን የተሰማሩ ድርጅቶች ኃላፊዎች ለሳምንት ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል፡፡

እንግዲህ ከጉብኝቱ በስተጀርባ እውነታው ምን እንደተገኘ ባናውቅም፣ በተንዳሆ የግድቡ ዋናው ካናል ቀደም ሲል በጎርፍ ተጎድቶ አለመጠገኑ፣ የዋናው ግድብ የውኃ መስረግ በግድቡ የወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ዘለቄታ ውሳኔ ማግኘት ላይ፣ በከሰም እስካሁን ድረስ በአካባቢው ባለው ተፈጥሮአዊ ችግር የዋናው ግድብ አለመጀመርና ለዓመታት ለነበረው ሁኔታ መፍትሔው በፍጥነት ሳይሰጥ መዘግየቱ ፕሮጀክቱን ከመዘግየት በስተጀርባ የሀብት ብክነት ማስከተሉ ይታወቃል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ መጓተት ፕሮጀክቱ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚጠጋና ሥራውን የሚገነባው ድርጅት በኃላፊነት ያስቀመጣቸው ኃላፊ ካላቸው የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ በኮንትራት ሕግ መሠረት በማይፈቅደው ሁኔታ በሥራ ላይ መድቦ የታሰበለትን ሥራ በተያዘለት ዕቅድ አለመጓዙ፣ ባለቤቱም በምን መመዘኛ ኃላፊነቱን መቀበሉ አይታወቅም፡፡ በአማራ ክልል በጣና ዙሪያ የሚገነባው ግድብ ከተጀመረ የሦስት ዓመታት ጊዜ የፈጀ ሲሆን፣ ከፍተኛ የአገር ገንዘብ ፈሶበታል፡፡ ዛሬ የዋናው ግድብ ቁፋሮ ብቻ ተሰርቶ ግድቡ ሳይጀመር መዘግየቱ፣ በተለያዩ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ለረጅም ጊዜ በአካባቢዎች ከፍተኛ የግድብና መስኖ፣ የመንገድ ሥራዎችን በአኩሪ ውጤት የሠራን ልምድ ያካበተ የኮንስትራክሽን ፊት አውራሪ መሃደንዲስ፣ በዚህ ፈታኝ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ከሞያው ውጪ መድቦ ሥራ ለማሠራት መሞከር ለሥራ ታሳቢ ነውን?

በመጨረሻ ይህ ከፍተኛ የአገራችን ባለሥልጣኖች ያደረጉት ለየት ያለ ጉብኝት መላ ጎብኚዎቹን ባይጨምርም የተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ከጅምሩ አሁን እስካለበት እንዲሁም በየድርጅቶቹ ያሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮችን የሚያውቁት ይመስለናል፡፡ ታዲያ ጉዞው ራዕይ የሚሰንቅና ሞያና የድርጅቶቹን አቅምና የግለሰቦችን ክህሎት ከአገር ተቆርቋሪነት ጋር አገናዝቦ ወደ ፊት ለሚፈሰው የአገር ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ተገቢ የትምህርትና የሙያ ችሎታ ኖሮአቸው የተካፈሉትን ወደ ሥራው አቅርበው ፈር ቀዳጅ የሆነውን የአገራችን ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ግብ ለመምታት ጎብኚዎቹን መልካሙን እንዲያደርጉ ከወዲሁ በርቱ እንላለን፡፡
(ከብርሃን ተስፋው፣ ከውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት)