በምዕራፍ ብርሃኔ
‹‹የመጨረሻ ሴት ልጄን ስቀብር መንትያ ወንድሟ አገር ውስጥ ስላልነበር የቀብር ሥነ ሥርአቱን በቪዲዮ አስቀርጨ ነበር፡፡
ይሁንና ሣልስት ካለፈ በኋላ ቪዲዮውን ወንዱ ልጄ ወዳለበት ጣሊያን ለመላክ ያደረግኩት ጥረት አልተሳካም፤›› ያሉት የ49 ዓመቷ እናት ወይዘሮ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ ለወንዱ ልጃቸው የእህቱን ቀብር የያዘውን የቪዲዮ ካሴት ለመላክ የወሰኑት ልጃቸው የእህቱን ሞት በደንብ እንዲረጋገጥለትና ሐዘኑም እንዲወጣለት በሚል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ካሴቱ ወደ ታቀደለት አገር መሄድ ባለመቻሉ ወይዘሮዋ እጸገነት ከሰው እየተደበቁ ቪዲዮውን በመመልከት ለበርካታ ጊዘያት እያለቀሱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹የሞተችብኝ የመጨረሻዋና አንድ ፍሬዋ ልጄ ናት፡፡ እንዴት አድርጌ ሐዘኔን ልተው? እንዴትስ አድርጌ የሷን ቀብር የሚያሳየውን ቪዲዮ እቤቴ ተቀምጦ አለመመልከት እችላለሁ፤›› ሲሉ ግራ በተጋባው ስሜት ይጠይቃሉ፡፡ አኚህ እናት ሐዘናቸውን አልረሳ ስላሉና በየጊዜው ራሳቸውን እየጎዱ ስለሆነ፣ ቤተሰባቸው የቪዲዮ ካሴቱን ለማበላሸት ተደብቆበታል ተብሎ የጠረጠሩትን ሳጥን ቢሰብሩም፣ ካሴቱ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ‹‹ዘመዶቼ የሰበሩት ሳጥን አንድ ብቻ አይደለም፡፡ ሐዘን ማክበድ ጥሩ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን መርሳቱን እንዴት ልቻል? አኔ ቆሜ እያለሁ ትንሿ ልጄ ስትሞት የማንስ እናት አንጀት…›› ወይዘሮዋ ልጃቸው ያረፈችው ከሦስት ዓመት በፊት ቢሆንም ዛሬም ባስታወሷት ቁጥር ያለቅሳሉ፡፡
ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ቀብሮች በቪዲዮ መቅረጽ እየተለመደ የመጣ ክሥተት ሆኗል፡፡ ቀብር ሥነ ሥርዓቶች በቪዲዮ መቀረጻቸውንም ሆነ አለመቀረጻቸውን የሚደግፉ በርካቶች ናቸው፡፡
የሜካኒካል ኢንጂነሩ የ28 ዓመቱ ዐቢይ ሱራፌል እንደሚለው ከሆነ፣ ‹‹እናቱ ከሞቱ ገና አሥረኛ ቀናቸው ነው፡፡ ‹‹ለትምህርት ስዊድን የሔደው ታናሽ ወንድሜ ለቀብርም ሆነ ለለቅሶው መምጣት ስላልቻለ ቪዲዮ ቀርጻችሁ ላኩልኝ በማለቱ፣ እኔ ተቃውሜ ነበር፤›› ያለው ይህ ወጣት፣ የተቀረው የቤተሰቡ አባላት ግን ይህ ውሳኔ በተማረ ጭንቅላት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ከስሜት ጋር እጅግ የሚቆራኝ በመሆኑ ቪዲዮው ተቀርጾ ከመላክ እንዳላዳነው ተናግሯል፡፡
በርካቶች የቀብር ሥነ ሥርዓት በቪዲዮ እንዲቀረጽ የሚፈልጉበት ምክንያት፣ ውጭ አገር ላሉ የሟች ቤተሰቦችና የቅርብ ዘመዶች በሐዘኑ ወቅት መገኘት ስላልቻሉና ሟች እውነት ስለመሞቱ የሚያሳይ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል የሚለው አንዱ ምክንያት ቢሆንም፣ በትምክህት የእከሌ ለቅሶ ጊዜ ይሄን ያህል ሰው ተገኝቶ ነበር፣ የቀብሩም ሥርዓት እንዲህ ሞቅ ያለ ነበር ብሎ ለማሳየት ደግሞ ሌላው ምክንያት እንደሆነ ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡
‹‹ያባቴን ቀብር የቪዲዮ ቀረጻ ባለሙያዎችን በማስመጣት የነበረውን ትዕይንት አስቀርጨ ነበር፡፡ እኔም ሆንኩ ዘመዶቹ ቪዲዮውን መመልከት በፈለግንበት ጊዜ ተሰብስበን እንመለከተዋለን፤›› ያለው የ40 ዓመቱ ታምራት ባየህ፣ በምድር ላይ መርሳት የማይፈልገው ነገር አባቱን በመሆኑና መሞታቸው ለእርሱ ከባድ ሐዘንም ስለሆነ መርሳትን ፈጽሞ እንደማይሻ ይናገራል፡፡
ስለ ጉዳዩ አስመልክተን ካነጋገርናቸው የተለያዩ የእምነት ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ ሐጂ ራህመቶ ከበደ የቦሌ ክፍለ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ሊቀመንበር በበኩላቸው፣ ‹‹በእኛ ሃይማኖት እንኳን የቀብር ሥርአትን በቪዲዮ ልናስቀርጽ ይቅርና በሕይወት ያለን ሰው እንኳን ፎቶ ማንሣት ቁርአን ይከለክላል፤›› ብለዋል፡፡ እንደ ሐጂ ራህማቶ ከሆነ፣ ሰዎች ለሚኖሯቸው መታወቂያዎች እንኳን ፎቶ እንዲነሡ የተፈቀደው፣ የሃይማኖቱ አባቶች አስፈላጊውን ውይይት ካደረጉበት በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እስከማውቀው ድረስ በሙስሊም እምነት ተከታዮች ዘንድ ቪዲዮን የማስቀረጽ ሁኔታ እስከዛሬ ተደርጎ አያውቅም፡፡ የሌሎች እምነት ተከታይ የሆኑ ግለሰቦች እንኳን ቪዲዮ ቢያስቀርጹም፣ እንደ ሰውኛ ታስቦ እንጂ፣ እንደ እምነት ታስቦ ሊሆን አይችልም፡፡ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ባለሥልጣንም በሞት ቢለዩ፣ ቀብራቸው በቪዲዮ አይቀረጽም፤›› ሲሉ ሐጂ ራህመቶ አክለዋል፡፡
አቶ ንጉሴ ቡልቻ፣ የቃለ እግዚአብሔር አንባብያን ማኅበር ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰው ሲሞት ማልቀስና ሐዘንን መግለጽ ተገቢ ነው፡፡ ሐዘንተኛውም ወዳጅ ዘመዶቹ ከጎኑ ሆነው ቢያስተዛዝኑት መጽናናትን ያገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ሐዘኑ በልክ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አለዚያ ግን ለሐዘንተኛው ስቃይ ነው፡፡›› አቶ ንጉሴ ዋናው ጥያቄ ሊሆን ይገባዋል ያሉትም፣ በለቅሶ ጊዜ የሚቀረጹት ቪዲዮዎች ከበስተጀርባቸው ያለው ዓላማ ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ‹‹ውጭ አገር ላሉ ቤተዘመዶች ተልኮ እነርሱም አልቅሰው ይወጣላቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ አንዳንዴም እንደማስታወሻነት ስለሚቀመጥና አልፎ አልፎ ደግሞ የእናቴ/የአባቴ ለቅሶ ለየት ያለ ነበር፤ ሞቅ ያለና ብዙ ሰው ታድሞ ነበር፤ ለማለትም ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት አቶ ንጉሴ፣ ‹‹በመጨረሻዎቹ ሁለት ምክንያቶች ፍጹም ባልስማማም፣ ውጭ ላለ ሰው ለመላክ ነው ለሚለው ምክንያት ግን ለመቃወም በቂ ምክንያት አላገኘሁለትም፤›› ብለዋል፡፡
ለቅሶን በቪዲዮ መቅረጽን በተመለከተ ልዩ የሆነ አቋም እንደሌለ የተናገሩት አቶ ንጉሴ፣ ሰዎች ፎቶግራፍ እያዩና ወደ መቃብር እየወረዱ እንደሚያለቅሱት ሁሉ፣ በድምፅና በሥዕል እንዲሁም በዘመድ ዋይታ ታጅቦ የተቀረጸውን ቪዲዮ ደግሞ ሲመለከቱ ሐዘንን ላለመርሳት ዋነኛና ትክክል ያልሆነ መሣርያ ይሆናል፤ ሲሉም አቶ ንጉሴ አክለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ የወንጌላውያን የለቅሶ ሥርአት ማልቀስ ብቻ ሳይሆን የጸሎት፣ የቃለ እግዚአብሔር ትምህርትና የመዝሙር ፕሮግራም ስለሚካተትበት፣ በቪዲዮ ተቀርጾ ውጭ አገር ላለ ሰው ቢላክ፣ በዚያ የሚገኘው ሰው ቪዲዮውን ሲያይ ማልቀስን ብቻ ሳይሆን መጽናናትንም ጭምር ያገኛል፡፡
በኦርቶዶክስ፣ በወንጌላውያንና በሙስሊም እምነቶች ዘንድ አንድ ሰው በሞት ሲለይ ሊለቀስለት የሚገባው ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ፣ ለቀብር አስክሬኑ ከመኖርያ ቤቱ ሲወጣና ወደመቃብር ጉድጓድ ውስጥ ሲገባ እንደሆነ ይታመናል፡፡


