‹‹ወደፊት እግዜር ፈቅዶልኝ ልጆች ከወለድኩኝ›› አለ ወያላው የረጅም ጊዜ ዕቅድህን አሳውቅ የተባለ ይመስል፡፡ ‹‹ለሁሉም ልጆቼ የሴት ስም ነው የማወጣላቸው፤›› እያለ መቀባጠር ጀመረ፡፡
እናቱ የወንድ ስም ስላወጡለት የተፀፀተ ይመስላል፤ ‹‹አበበ ከምትለኝ ይልቅ አበበች ብላኝ ቢሆን ኖሮ ያለጥርጥር የኮንዶሚኒየም ቤት በደረሰኝ ነበር፤ የእናቴን ስህተት እኔ መድገም አልፈልግም፤›› በማለት ብሶቱን ተነፈሰ፡፡ ሾፌሩ ተቀበለውና፣ ‹‹ምነው ሴት ሆኜ በተፈጠርኩ የሚባልበት ዘመን መጣ ማለት ነው?›› አለ፡፡ አንድ ተሳፋሪ እንዲህ በማለት የሾፌሩን ሐሳብ አጠናከረለት፤ ‹‹ድሮ ድሮ ወንድ ልጅ ሲወለድ እልል ይባልና፣ ሴት የሆነች እንደሆነ ግን ትሁን ግድ የለም ነበር የሚባለው፡፡ አሁን ግን ነገሩ ሳይገለበጥ አልቀረም፤›› አለ፡፡ ሌላ ተሳፋሪ ሌላ ርዕስ ይዞ ብቅ አለ፤ ‹‹አሁንማ ያልተገለበጠ ምን አለ? አብዛኛው የአገር መሪ በግድ ነው እንጂ ሥልጣን ላይ የቆየው ከተገለበጠ ቆይቷል፤›› በማለት ከመቅጽበት ወሬውን ወደ ፖለቲካ ገለበጠው፡፡
ታክሲዋ ወዲያው በወሬ ጦፈች፤ ወሬውን ወደ ፖለቲካ የቀየረው ሰውዬ ማውራቱን ቀጥሏል፡፡ ሲያወራ ላዳመጠው እንትን ከሚባለው ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ ቢያንስ ሁለት ዲግሪ ያለው ይመስላል፡፡ ‹‹የሥልጣን ማራዘሚያ መድኃኒት ቢኖር ኖሮ...›› ብሎ ሐሳቡን ሳይጨርስ አንድ ሌላ ተሳፋሪ፣ ‹‹በኪኒንም፣ በመርፌም፣ በሽሮፕም የተዘጋጀውን ሁሉ የአፍሪካ መሪዎች ተቀራምተው ይጨርሱት ነበር፤›› ብሎ ራሱ በተናገረው ነገር ክትክት ብሎ መሳቅ ጀመረ፡፡ ወሬውን የጀመረው ሰውዬ፣ ‹‹ትክክል ነህ፤ እኔም ብሆን ከዚያ ብዙ የተለየ ሐሳብ የለኝም፡፡ እንዲያውም ሞተው አፍሪካ እኛ እንምራሽ፣ ከእኛ ሌላ ላንቺ የሚበጅና የሚጠቅም የለም የሚሉ አይጠፉም፤›› ሲል ጆሮዬን ‹‹ስዊችድ ኦፍ›› ባደርገው ደስ ባለኝ ነበር፡፡
ከስቴዲዮም የተነሳው ታክሲ አብዮት አደባባይን ተሻግሮ ወደታች ትንሽ እንደተንደረደረ ባምቢስ መብራት ጋር ከመድረሱ በፊት ካለው ነዳጅ ማደያ ከሌሎች ታክሲዎችና የቤት መኪናዎች ጋር አብሮ ተሰለፈ፡፡ እንደዚያ እንደ ጥንቸል ሲከንፍ የነበረው ታክሲ ወረፋ ለመጠበቅ እንደ ኤሊ መሳብ ጀመረ፡፡ ተሳፋሪዎች እንሂድ በሚል ስሜት የተለመደ ሰሚ አጥ ጬኸታቸውን አሰሙ፡፡ ወያላው መልስ መስጠት ጀመረ፣ ‹‹መውረድ የሚፈልግ መውረድ ይችላል፤ ነገ ነዳጅ ይወደዳል የሚል ወሬ ሰምተናል ስለዚህ ነዳጅ ሳንቀዳ ከዚህች ንቅንቅ አንልም፡፡ የፈለገ ሰው በሌላ ታክሲ መሄድ ይችላል፤›› በማለት ፍንክች የማይል አቋሙን አቀረበ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ነገ ነዳጅ የለም ቢባል በቢራ አላስነሳው፤›› እያለ መከላከያውን አጠናከረ፡፡ በሌላ ታክሲ እንዳንሄድ ታክሲ የሚበላ ጅብ የመጣ እስኪመስል ድረስ ለዓይናችን ጠፋ፡፡ አንዳንድ ታክሲዎች ቢመጡም እንኳን ሽው ብለው ከማለፍ ውጪ ምንም ሊፈይዱልን አልቻሉም፡፡
‹‹ሰው ከመጠን በላይ ፈሪ ሆኗል፤›› ይላሉ አንዳንዶች አንድ ሰው እንደቀልድ ‹‹ነገ ፀሐይ አትወጣም›› ብሎ ቢያወራ ዛሬ ሕዝቡ ሻማ በመግዛት መደብሮችን ያጨናንቃል እያሉ በሕዝቡ ጭንቀት ላይ ይሳለቃሉ፡፡ ‹‹ነገ ጥሩ ይሆንልኛል›› ብሎ በተስፋ የሚጠባበቃት ቀን ዛሬ ክፉ ትንቢት ሲተነበይባት ሲሰማ በእርግጥ ይደነግጣል፡፡ ከነገ ይልቅ ትናንትን ይመርጣል፤ ቢችል ወደ ትናንት ይሮጣል፡፡ ወደኋላ ያመልጣል፡፡ ችግሩ ሕይወት የኋላ ማርሽ የላትም፡፡ ‹‹የሕይወት የኋላ ማርሿ ትዝታ ነው፤›› ያለው ሰው ማን ነበር? እሱ እስከሚገኝ እኔው የአባባሉ ባለቤት ሆኜ ልዝለቅና ነገ እንደዚህ ይሆናል ብለው ፈርተው የሚያስፈራሩንን ሀይ ማለት ቢቻል ኖሮ እንዴት አሪፍ ነበር? ሕይወት ወደፊት እየተጓዘች መጪውን ጊዜ እንደምታበራው የሚነግረን ሰው ብናገኝ ኖሮ የማሟያ የምርጫ ካርዳችንን ሳናቅማማና ሳንሰስት በሰጠነው ነበር፡፡
ለታክሲና ለሾፌር ማሟያ ማለት አንዳንድ ጊዜ የሚጫን ሰው ጠፍቶ ታክሲው ባዶ ሆኖ ሰው አልገባ ሲላቸው፣ ሾፌሩም ወያላውም እንደተሳፋሪ ሆነው ይቀመጡና ተራ አስከባሪ እንዲጠራ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ማሟያ ምናምን አይገባቸውም፡፡ ሾፌርና ወያላ የሟሟያ የምርጫ ካርድ ውሰዱ እየተባለ በድምፅ ማጉያ ሲለፈፍ መስማታቸውን ተናግረው የተረዱበትን መንገድ ሲገልጹ፣ ሕዝቡ በመንግሥት አሠራር ውስጥ እንዲሳፈር ጥሪ እየተደረገለት ነው ብለው ነው የሚተረጉሙት፡፡
አንድ እናት በትዝታ የኋላ ማርሻቸውን እየነቀነቁ፣ ‹‹የሚያኖር እግዚአብሔር ነው፤›› በማለት፣ ሰው በምግብ አቅርቦት እጥረት አይሞትም፣ በአቅርቦት ብዛትም አይኖርም የሚል ዓይነት አስተያየት ሰነዘሩ፡፡ ቀጥለውም፣ ‹‹ዋናው›› አሉ፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ነው፡፡ እርሱ እንኳን በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ይቅርና ወፍ ጦሟን እንድታድር አይፈቅድም፤›› ሲሉ ሁሉም ሰው በተመስጦ ያዳምጣቸው ነበር፡፡ የኑሮን ጉዳይ በተመለከተ ግማሹ ‹‹ዋናው ነጋዴው ነው›› ይላል፡፡ ግማሹ ደግሞ፣ ‹‹ዋናው መንግሥት ነው›› ይላል፡፡ ሌላው በበኩሉ፣ ‹‹ዋናው ሕዝቡ ነው›› ይላል፡፡ ዋናው ምንድነው? ይህ ጥያቄ ከተመለሰ ዋናችንን ተሟሙተንም ቢሆን እንድንይዝ ይረዳናል፡፡ እማማ ግን፣ ‹‹ዋናው እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ያስባል እግዜር ይፈጽማል፤›› ሲሉ ሁላችንም ጭጭ አልን፡፡ ከፈጣሪ በላይ ማን አለ?
በእንፉቅቅ ተጉዘን ተጉዘን ደረስን፡፡ ነዳጁን ቀድተን ታክሲው መንቀሳቀስ ሲጀምር ወያላው እየተማረረ፣ ‹‹ምነው ዓባይ ነዳጅ በሆነ! ምነው ጣና ነዳጅ በሆነ?›› እያለ የሚያውቃቸውን ሌሎች ወንዞችና ሐይቆችን ጠራ፡፡ አንዳንዶቹ ጠላ እንዲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ጠጅ፣ እንዲሁም ሌሎች የዋጋ ቅናሽ ያልታየባቸውን መጠጦች እየጠራ እንዲሆኑለት ተመኘ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ዶላር የሚያበቅሉ ዛፎችም ቢኖሩ ብሎ ተመኘ፡፡ የወርቅ እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎች ቢኖሩም ብሎ ተመኘ፡፡ ቤንዚን የሚታለቡ ተራራዎችና ሜዳዎች ቢኖሩ ብሎም ተመኘ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምኞት የድህነት ምሬት የወለደው መሆኑን ለሾፌሩ ነገረው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ድህነት በሥራ እንጂ በምኞት አይጠፋም፤›› አለው፡፡
‹‹በጣም የሚያናድደው ነገር›› አለ ሾፌሩ በድንገት፡፡ ‹‹ትናንት ቤት አጥተው በእምባና በሐዘን ስለቤት ውድነት ሲያማርሩ የነበሩ ሰዎች፣ የኮንዶሚኒየም የቤት ዕጣ ሲወጣላቸው የትናንቱን ሕይወታቸውን ከናካቴው ረስተው፣ የቤቱን ኪራይ ጣሪያ ሲያደርሱት ማየት በጣም ያሳዝናል፤›› አለ፡፡ የሾፌሩን ምሬት ተከትሎ ታክሲዋ በዚህ ርዕስ ተሞላች፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤቶች አብዛኛዎቹ በቤት ማጣት ሲንገላቱ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ የኪራዩን ዋጋ ሰማይ ሰቅለው ሰውን ማስመረራቸው ከምን የመነጨ ነው? የቤት እጦት እንዴት እንደሚያደርግ ነጋሪ ያስፈልጋቸዋል ብለን አናስብም፡፡ ከማንም በላይ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ታዲያ ጭካኔው ከየት የመነጨ ነው? ይህ የአብዛኛው ተከራይ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ቤት የደረሳቸው ሰዎች ከድሮ ቤታቸው ፍንክች ብለው አይወጡም፡፡ በዚያው ቤት በቅናሽ ዋጋ እየኖሩ በዕጣ ያገኙትን ቤት በውድ ዋጋ ያከራዩታል፡፡ በወር ለመንግሥት ከሚከፍሉት ዋጋ ሦስት እጥፍ በላይ ማስከፈላቸውን የተማረሩ ተከራዮች ምናልባት ሰሚ ካገኘን ብለው መናገራቸውን አላቆሙም፡፡ ይኼ ሁሉ የምሬት ንግግር የተሰማው እዚህችው ታክሲ ውስጥ ነው፡፡
‹‹ለማንኛውም በሰላም አብሮ ለመኖር ቤተሰብና ኅብረተሰብ ከማንም በላይ እርስ በእርሳችን ልንተሳሰብ ይገባናል፡፡ እኔ ብቻ ልብላ፣ እኔ ብቻ ልጠቀም፣ እኔ ብቻ ልኑር የሚል አመለካከት ከመካከላችን ቢጠፋልን ባንበላም አይርበንም፣ ባንጠጣም አይጠማንም፣ ባንለብስም አይበርደንም፤ በማለት የቅድሟ እናት ምክራቸውን ለገሱ፡፡ አንድ ትልቅ ሰው በሰጡት አስተያየት እናሳርግ፡፡ ‹‹አሥር ሺሕ ሰዎች የኮንዳሚኒየም ዕጣ ከወጣላቸው አሥር ሺሕ ችግር ይቀንስ ነበር፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ ልብ ላጣው ልብ ይስጥልን፤›› ሲሉ፣ ሌላው መልዕክት እንተሳሰብ! እንዋደድ! እንከባበር! በሚል ተጠቃለለ፡፡ የዛሬ ተከራዮች የነገ አከራዮች ምን ትላላችሁ? ሰላም!


