በቅርቡ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ሌሎች አገሮች ለዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲታቀቡ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን (travel advisories) አሠራጭተው እንደነበር ከድረ ገጾች ዘገባዎች አንብቤ የተለመደው ቅዠት ነው ብዬ ነበር፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በአዲስ አበባችን ሲካሄድ የተለያዩ አገሮች መሪዎች ወደ አዲስ አበባችን ስለሚመጡ፣ ጥንቃቄው እንዲበረታ በማሰብ ያሠራጩት ነው ብዬ ገምቼም እንደነበር ልሸሽግ አልፈልግም፡፡
ብዙም ሳይቆይ በኤርትራ መንግሥት ተገዝተው ሕዝባቸውንና አገራቸውን ለማጥፋት የተላኩ የኦነግ አሸባሪዎች መያዛቸውን፣ ሲ-ፎር የተሰኘ ተቀጣጣይ ፈንጂ በተለያዩ የከተማችን ክፍሎች ለማፈንዳት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ፣ ፈንጂዎቹ ወደ አገራችን የገቡት በጅቡቲ በኩል እንደነበር፣ ኤርትራ በርካታ ፈንጂዎችን ወደ ጅቡቲ በመላክ ላይ መሆንዋንም ጭምር ከጋዜጦችና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ተገነዘብኩ፡፡ በቀጣይነትም ኦነግ በመንግሥታት በአሸባሪነት የተፈረጀች አገር ሥር መግባቱ ለኦሮሞ ሕዝብ ምን ፋይዳ ሊያመጣ ይችላል ብዬም ራሴን ጠየቅኩ፡፡
ለምን ንፁኃንን (የኦሮሞን ሕዝብ ጭምር) በማያውቁት ምክንያት ለመጨረስ አስፈለገው? በማለት ለራሴ ጥያቄ አቀረበኩ፡፡ ሌላው ቢቀር የኢሳያስ አፈወርቂ ተላላኪና ሽብር ፈጣሪ መሆናቸው ለኦሮሞ ሕዝብ በራሱ ውርደት አይደለም ወይ? በማለትም ጠየቅኩ፡፡ ዕድሜ ለፖሊስ፣ ለመረጃና ድኅንነት አባላት እንጂ ፈንጂዎቹ እንደታሰበው ቢፈነዱ ኖሮ የኦነግ ቅጥረኞች የኦሮሞ ተወላጆችን ጭምር ለመፍጀት የመጡ ነበር፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ ፍንዳታውን ለማካሄድ መወሰናቸው ደግሞ፣ አገሪቷ ሰላም የላትም በማለት የአዞ እንባ ለሚያነቡና የአፍሪካ ኅብረትን ጽሕፈት ቤት ከአገራችን ለማስነሳት ለሚታገሉ አንዳንድ ያልተገሩ መሪዎችን የኢሳያስን ጨምሮ ዓላማ ለማሳካት ካልሆነ በስተቀር እስቲ ለማን ሊበጅ ነው በማለት መጠየቁ አሁንም ግድ ሆነብኝ፡፡ ድርጅቱ ከአዲስ አበባችን ቢነሳ ተጎጂዎቹ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ኦነግ ቆሜልሃለሁ የሚለው የኦሮሞ ሕዝብም ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ለዚህም ይሆናል አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ኦነግን አንቅሮ የተፋው፡፡ ለእኔ ግን ኦነግ የኤርትራ ቡችላ ከመሆን ተቆጥቦ በራሱ የጥፋት ጎዳና ቢቀጥል ይሻለው ነበር፡፡
ሻእቢያ ነገም ሆነ ዛሬ በተለይም ኢሳያስ በሥልጣን እስካለ ድረስ ለኢትዮጵያ ፈጽሞ አይተኛም፡፡ የኦነግ ቡችሎች ተመሳሳይ የጥፋት ተግባራት ለማከናወን ከኤርትራ የተላኩት ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ የመረጃ ደኅንነታችንና የፖሊስ ኃይሎቻችን ምስጋና ይግባቸውና ባለመበገራቸው የኤርትራ መንግሥትና የኦነግ ቅጥረኞች የጥፋት ጥረት በተደጋጋሚ ከሽፏል፡፡ ዛሬ ደግሞ የሕዝባችን ተሳትፎም እጅግ በመጠናከሩ ሽብርተኞችን ለመቆጣጠር ብቃታችን እየጨመረ ነው፡፡
ሻአቢያ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚያሴረው ቅጥረኞችን በመላክ ብቻ አይደለም፡፡ በሶማሊያ በኩል ሲያደርግ የነበረው መጠነ ሰፊ ጥረት ብዙ የተባለለት ስለሆነ መደጋገሙ አያስፈልግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ደኅንነት፣ ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት ለማይዋጥላቸው አገሮች ተላላኪነቱ ወደፊትም እንደሚቀጥል ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከአሸባሪዎች ጋር እጅና ጓንት ሆና መቀጠሉም ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ ይኼንንም ሕዝባችን እየተረዳው ስለሆነ እንደተለመደው በንቁ ተሳትፎ የሚከሽፍ ይሆናል፡፡
በጂቡቲ በኩል ያለውስ ብንልና ትንሽ ሰፋ አድርገን ብናይ ይህም ለኢትዮጵያ ጥፋት የታለመ መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም፡፡ ወደድንም ጠላንም ጂቡቲ በአሁኑ ጊዜ የወጪና ገቢ ንግዳችን መተላለፊያ አገር ናት፡፡ በመሆንዋም ጉሮሮአችን ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጂቡቲ ቀውስ ውስጥ ገባች ማለት ኢትዮጵያ ችግር ላይ ወደቀች ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኤርትራ ጅቡቲ ውስጥ ከጎሮቤት አገሮች ጋር በሰላም፣ በመከባበርና በመረዳዳት መርህ የሚያምን መንግሥት እንዲኖር አትሻም፡፡ ከተሳካላት የራስዋን አጀንዳ የሚያራምድላት ቡችላ መንግሥት ጂቡቲ ውስጥ ለማስቀመጥ ትሻለች፡፡ ለዚህም ማንኛውንም መስዕዋትነት ለመክፈል በኢሳያስ አፈወርቂ ሥር ያለችው ኤርትራ ወደ ኋላ አትልም፡፡
ይህም የሚሳካ ባለመሆኑ በጂቡቲ ውስጥ ሽብርን ማበረታታት ሌላው አጀንዳዋ ነው፡፡ ይህንንም መንግሥታችን በዝምታ ያየዋል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግን የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊ ዕውቀቱ ስለሌለኝ ስትራቴጂውን ማመላከት ያስቸግረኛል፡፡ እንደዜጋ ይህን ካልኩና ለውይይት መነሻ ይህችን ከሰነዘርኩ ሌሎቻችሁ ደግሞ ይበልጥ እንደምትነግሩን እምነቴ ነው፡፡ መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝባችንን እንዲያወያይና አቋም እንድንይዝ ሊረዳን ይገባል የሚልም አመለካከት አለኝ፡፡ ሽብርተኞች ስለማያፍሩና ካለፈውም ድርጊታቸው ስለማይማሩ በጠንካራ ዝግጅትና ጥንቃቄ ልንከታተላቸው ይገባል፡፡ ሽብርን ልንታገሰው ፈጽሞ አይገባምና፡፡
(በስጦታው በፀጋ ዓለሙ፣ ከአዲስ አበባ)
* * *
መናፈሻ ቦታዎች ያስፈልጉናል
ጎበዝ ዛሬ በከተማችን ሙቀቱ በዝቶ መድረሻ አሳጥቶናል፡፡ በዚህ ላይ እኛ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች አንድ አረንጓዴ የመናፈሻ ቦታ የሌለን በመሆኑ በሙቀት እየተማረርን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜያት ግርም የሚለኝ ነገር አለ፤ ምን አትሉኝም? ለተወሰኑ ዓመታቶች ያህል አውሮፓ ውስጥ ኖሬያለሁኝ፡፡ አሁን ወደ አገሬ ተመላሽ የሆንኩኝ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ) ነኝ፡፡ በኖርኩባቸው አገሮች ያየሁትኝ ነገር፣ አገሬ እንዲኖራት እመኛለሁኝ፡፡ እነሱ በሚሠሩአቸው የመኖሪያ ሕንፃዎች አካባቢ የልጆች መጫወቻዎችን አካተው የሚገኙ መናፈሻዎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም እናቶች ልጆቻቸውን የሚያጫውቱባቸውና ጓዳ ጐድጓዳቸውን የሚወያዩበት፤ አባቶች የሆዳቸውን የሚጫወቱበትና ጥንዶች ፍቅራቸውን የሚኮመኩሙበት ቦታ ቢኖር ምኞቴ ደረሰ ማለት እችላለሁ፡፡
የአብሮ አደግ ባልንጀራዬ ያወጋኝን ላጫውታችሁ፡፡ ይኸው አብሮ አደጌ ከባለቤቱ ጋር ሆኖ ሁለት ልጆቹን ጨምሮ በአንድ ስቱዲዮ ክፍል ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ክፉውንም ደጉንም በዛችው ክፍል ውስጥ ነው የሚነጋገሩት፡፡ ልጆቹም በቤት ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት የወላጆቻቸውን ጭቅጭቅ መስማት ግዴታቸው ነው፡፡ ልጆቹም ጭቅጭቁን ላለመስማት የሚሄዱበት ቦታ ባለመኖሩ ሁሌም ይረበሻሉ፡፡ ሆኖም ጥሩ ዜጋ ለመፍጠር እነዚህ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡
ቤቶች ላይ ብቻ ኢንቨስት እያደረግን ጥሩ ትውልድ ኢንቨስት ካላደረግን፣ ወደፊት የትውልድ ጥፋት እንዳይኖር እሰጋለሁኝ፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ጭቅጭቅና ንትርኮች በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለትና ሦስት ክፍል ባለበት ቤት ውስጥ አንደኛው ወገን ወደ አንደኛው ክፍል ወይ ከላይ እንደጠቀስኩት ወደ መናፈሻ ቦታዎች በመሄድ ነገሮችን ሊያበርዱባቸው የሚቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙቶች ለመፍጠርና ትልቅ የወንጀል መቀነሻ መሆኑም በጥናት ጭምር የተረጋገጠ በመሆኑ፣ የሚመለከተው አካል ልብ ይበልበት ስል አሳስባለሁ፡፡
(ጀማል ከድር፣ ከአዲስ አበባ)


