Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹የኮንትሮባንድ ዕቃዎች››

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

በናታን ዳዊት

ከሥራዬ ጋር በተገናኘ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ወደ ሐረርና ጅጅጋ ተጉዤ ነበር፡፡ እግረ መንገዴንም በሁለቱም ከተሞች የሚገኙ አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችን ተዘዋውሬ ተመለከትኩ፡፡ ለመመልከት የገፋፋኝ ጅጅጋ ውስጥ ያስተዋልኩት አንድ አጋጣሚ ስለነበር ነው፡፡ በወቅቱ ካረፍኩበት ሆቴል አጠገብ ወዳለ አንድ አነስተኛ መደብር እሄዳለሁ፡፡ ወደ መደብሩ የሄድኩት እንደኔው ለሥራ ጅጅጋ የመጣና ከተማዋን በደንብ ከሚያውቅ ወዳጄ ጋር ነበር፡፡

ወደ መደብሩም ሄጄ የምፈልገውን ዓይነት የገላ ሳሙና ስጠይቅ እንደሌለ ተነገረኝ፡፡ አብሮኝ የነበረው ወዳጄን ሌላ መደብር እንጠይቅ አልኩት፡፡

‹‹አንተ የምትፈልገውን ዓይነት ሳሙና ላታገኝ ትችላለህ፡፡ እዚህ እኮ የሚሸጠው የገላ ሳሙና በሙሉ በኮንትሮባንድ የሚገባ ስለሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ከምታውቃቸው ዕቃዎች የተለየ ይሆንብሃል፤›› አለኝ፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረት ወይም በአገር ውስጥ አስመጪዎች የሚከፋፈል ምርት የለም እያልከኝ ነው? ብዬ ጠየኩት፡፡ ጅጅጋ ውስጥ ከመሃል አገር የሚመጣ የምርት ዓይነት እጅግ ጥቂት መሆኑን የተለያዩ ምሳሌዎችን አጣቅሶ አስረዳኝ፡፡

ይህ የወዳጄ መልስ አስገርሞኝ ነው እንግዲህ ካረፍኩበት ሆቴል ብዙ የማይርቁ መደብሮቹን እየዞርኩ ለመመልከት የተነሳሳሁት፡፡ የቻልኩትንም ያህል ዞርኩ፡፡ በእርግጥም በየመደብሮቹ ያሉት ዕቃዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ናቸው በተባሉ ዕቃዎች የተሞሉ ናቸው፡፡

ዘይት፣ ሳሙና፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ የታሸጉ ብስኩቶች . . . በሙሉ በኮንትሮባንድ የገቡ ናቸው፡፡ ያነጋገርኳቸው አንዳንድ ባለመደብሮችም ይህንኑ አረጋገጡልኝ፡፡

በሐረር የጅጅጋውን ያህል አይሁን እንጂ የተመለከትኳቸው አንዳንድ ባለመደብሮች በኮንትሮባንድ የገባነው የተባሉ ምርቶችን ይዘዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንትም በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹የሉም የሚባሉ ምርቶች . . . ›› በሚል ርእስ በቀረበው ዘገባ ውስጥ አስተያየት የሰጡ አንድ የሐረር ነዋሪ እንደገለጹትም፣ በከተማው ውስጥ እየተሸጠ ያለው በኮንትሮባንድ የሚገባ ዘይት በመሆኑ መንግሥት ያወጣውን የዋጋ ተመን መተግበር አለመቻሉን የሚያመለክት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በነገራችን ላይ በተለይ ለጠረፍ ቅርብ የሆኑ የአገራችን ከተሞች ውስጥ በኮንትሮባንድ ገቡ የሚባሉ ዕቃዎች በገፍ የመሸጣቸው ጉዳይ የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከገበያ ሥርዓት አንጻር ግን በግልጽ በኮንትሮባንድ የገባ ዕቃ ነው ተብሎ መሸጡ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

የሐረርዋ ወይዘሮ እንደጠቆሙት፣ በኮንትሮባንድ የሚባው ዘይት መንግሥት ዋጋ ከተመነላቸው የዘይት ዓይነቶች የሚለይ በመሆኑ ለሐረር ከተማ በተተመነው ዋጋ ልናገኝ አንችልም ማለታቸውም፣ በኮንትሮባንድ ገቡ የሚባሉ ምርቶች በግብይት ውስጥ ምን ያህል ተጽእኖ እንደሚያሳርፉ ያመለክተናል፡፡

በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶች የገበያ ሥርዓቱን ከማዛባትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባሻገር ደግሞ ሸማቾች ላይ ሊፈጥር የሚችለው አደጋም ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ በኮንትሮባንድ መልክ ገቡ የሚባሉ የመጠጥና የምግብ ዓይነቶችን ብቻ ብንወስድ አደጋቸው የከፋ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡

ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ የማይሰጥላቸው በመሆናቸውም ሊያስከትሉ የሚችሉት አደጋ ሕይወት እስከማሳጣት ሊደርስ ይችላል፡፡ ለዚህ አባባሌ በአንድ ወቅት ወደ ነቀምት ሄጄ ያጋጠመኝን አንድ ድርጊት ላስታውስ፡፡

ባረፍኩበት ሆቴል ለስላሳ አዘዝን፡፡ ያዘዝነው ኮካ ኮላ ነበር፡፡ ነገር ግን የተሰጠን ከተማ ውስጥ እንደምናውቀው በጠርሙስ የታሸገ አልነበም፡፡ ማሸጊያው ፕላስቲክ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምን ዓይነት ኮካ ኮላ  ነው ብለን ጠየቅን፣ አስተናጋጁ ሳያመነታ የመለሰልን ‹‹በኮንትሮባንድ የሚገባ ነው›› አለን፡፡ ነገሩ በጣም ገርሞን ከመጠጣታችን በፊት ከእሽጉ ላይ ያለውን ጽሑፍ አነበብን፡፡

ይኼኔ ደነገጥን፡፡ የለስላሳ መጠጡ የመጠቀሚያ ጊዜ ካለፈ ከስድስት ወራት በላይ ሆኖታል፡፡ የሚገርመው ግን ሌሎች ሰዎች ይህንኑ የለስላሳ መጠጥ ጠጥተው ሲወጡ ማየታችን ነበር፡፡

ጊዜ ያለፈበት መሆኑን እያወቅን  መጠጣት እንደሌለብን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ለሆቴሉ ባለቤት ማስረዳት እንዳለብን በማመን ሁኔታውን አስረዳነው፡፡ ደግነቱ የሆቴሉ ባለቤት በተፈጠረው አጋጣሚ ይቅርታ ጠይቆ ማቀዝቀዣ ውስጥ ያለውን ለስላሳ ሁሉ እየተመለከትነው አስወገደ፡፡ ወይም ዞር አደረገውም ሊባል ይችላል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ አጋጣሚዎች በቶሎ ሊመረዙ በሚችሉ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ቢሆን ሊደርስ የሚችለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ 

ስለዚህ የኮንትሮባንድ ምርቶች የጥራት ደረጃ ሁሌም አሳሳቢ መሆኑ የማይቀር በመሆኑ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አሁን መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማቀዝቀዝ እየወሰደ ካለው ዕርምጃ ጋር ሊጋጭ የሚችሉ ክስቶችን ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሕጋዊነትን የሚጻረር በመሆኑም በግልጽ በኮንትሮባንድ የገቡ ናቸው እየተባሉ የሚሸጡ ምርቶችን ለመቆጣጠር መትጋት ያስፈልጋል፡፡