በታደሰ ገብረ ማርያም
ብዛታቸው ከሰባት አይበልጥም፡፡ ሁሉም በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሠማርተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በእያንዳንዳቸው ልብ ውስጥ ግን የሕዋ (ስፔስ) ሳይንስ ፍቅር ካደረ ሰነባብቷል፡፡ የሥነ ፈለክና ሕዋ ምርምር ማዕከል (አስትሮኖሚካል ኤንድ ስፔስ ሪሰርች ሴንተር) የማቋቋም፣ በተለይም ወጣቱ በዚህ ሙያ ሥር ተሰባስቦ ለዕድገትና ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክትበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያልማሉ፡፡ ነገር ግን ለሕልሙ እውን መሆን ተገናኝተው የተወያዩበት ወይም ሐሳብ ለሐሳብ የተለዋወጡበት ጊዜ የለም፡፡
ከመካከላቸውም ሦስቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ፣ በፊዚክስ መርሐ ግብር የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ አንደኛው ደግሞ መምህራቸው ናቸው፡፡ የቀሩት ግን በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት የሚያገለግሉና በግላቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከተማሪዎቹና ከመምህሩ በስተቀር እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም፡፡
መምህሩ በኤፍ ኤም ሬዲዮ የአስትሮኖሚና ስፔስ ሳይንስ ፕሮግራም ማሠራጨት ጀመሩ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን በአየር ላይ የሚውለው ይኸው ፕሮግራም ደግሞ የሰዎቹን ቀልብ በይበልጥ ሳበው፡፡ በውስጣቸው የታመቀው የስፔስ ሳይንስ ፍቅር በይበልጥ እየተጋጋለ መጣ፡፡ ሐሳባቸውና ርዕያቸው ሕልም ሆኖ እንዳይቀር ያልፈነቀሉት ድንጋይና ያልወጡት ዳገት የለም፡፡
በአንድ አጋጣሚ እነዚህ ሰዎች የመገናኘት ዕድል አገኙ፡፡ በጉዳዩም ላይ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ ለምን ‹‹የስፔስ ሳይንስ ክለብ›› አናቋቁምም የሚል ጥያቄ አዘል ሐሳብ ሰነዘሩ፡፡ ምንም ሳያቅማሙ በሐሳቡ ተስማሙ፡፡ ከእዚህ ስምምነት ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከመካከላቸው አንደኛው የግላቸው የሆነ ቴሌስኮፕ እንዳላቸው በመታወቁና ራሳቸውን ችለው እስከሚጠናከሩ ድረስ በዚሁ ቴሌስኮፕ እንፍጨረጨራለን ከሚል እምነት ነው፡፡ ከስምምነቱም በኋላ አድራሻቸውን ተለዋውጠውና በቀጣዩ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያዩ፡፡
ቁጥራቸውም ቀደም ሲል ከነበረው ወደ 27፣ ከመንፈቅ በኋላም ወደ 49 በማደጉ በ1996 ዓ.ም. ሚያዝያ ላይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲን በመመሥረት ክለቡን ወደ ማኅበር (ሶሳይቲ) አሳደጉት፡፡ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካልም ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ አደረጉ፡፡ በዚህም መሠረት የኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከልን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ዕቅድ አውጥተው ለተግባራዊነቱ ደፋ ቀና በማለታቸው እንቅስቃሴያቸው በርካታ አባላትን ማፍራት ቻለ፡፡ ለሥራ ማስኬጃም ከአባላትና ከበጎ አድራጊዎች ገንዘብ ማሰባሰብ በመቻሉም በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የስፔስ ሳይንስ ክበባትን አቋቋሙ፡፡ የፓናል ውይይቶችን በማካሔድ የስፔስ ሳይንስ ምንነትን የማስተዋወቁና ግንዛቤ የማስጨበጡን ሥራ በሰፊው ተያያዙት፡፡
ሶሳይቲው በአፍሪካና በአውሮፓ አገሮች ካሉት ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከላት፣ ከሚያካሒዳቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች፣ ሳይንስ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃና አገሪቱ ለሳይንስ ከሰጠችው ትኩረት በመነሣት፣ የማዕከሉን ዲዛይን ሠርቶ በእንጦጦ ላይ ሕንፃውን ለማስገንባት ችሏል፡፡ ከውጭ የመጡ ባለሙያዎችም የሕንፃውን ግንባታ በማየት ‹‹ለሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በምሳሌነት የሚታይ ነው፤›› በማለት አድናቆታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
በዶ/ር ሰሎሞን በላይ የሶሳይቲው የቦርድ አባልና የትምህርትና ምርምር ሊቀመንበር አነጋገር፣ የእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኤንድ ስፔስ ሪሰርች ሴንተር ወይም ኦብዘርቫቶሪ የምርምር ማዕከል፣ ለአስትሮኖሚ ኦብዘርቫቶሪ ብቻ የሚያገለግል አይደለም፡፡ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሲቪል ኢንጂነሪንግን ያካተቱ የተለያዩ የምርምር ክፍሎች፣ እንዲሁም ተማሪውና ተመራማሪዎች የሚጠቀሙባቸው ላብራቶሪዎች ይኖሩታል፡፡ ቀስ በቀስ እያደገ ሌሎችንም ያጠናክራል፡፡
በአገሪቱ ምርምሮች የሚከናወኑት በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ብቻ መሆኑንና ምናልባት አልፎ አልፎ ከሚታወቁት የእርሻ ምርምር ማዕከላት በስተቀር በሳይንስ ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ማዕከላት ባለመኖራቸው የኦብዘርቫቶሪ ማዕከሉ እንደሞዴል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል፣ የምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች ሲቀናጁ ደግሞ ትልቅ የሆነ ጠቀሜታ ያስገኛል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካልሆነ ስተቀር በማኅበር ደረጃ የተደራጁ የኦብዘርቫቶሪ ማዕከላት እንደሌሉ፣ በምዕራብ አፍሪካም ከናይጄርያ በስተቀር በሌሎቹ አለመለመዱን ያወሱት ሊቀመንበሩ፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የኦብዘርቫቶሪ ማዕከል ሕንፃ ግንባታ መጠናቀቁና ለቴሌስኮፕም ግዢ የሚውል ዓለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱን አመልክተዋል፡፡
አሸናፊው እንደታወጀ፣ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ቴሌስኮፕን እንደሚተክልና የተወሰነ የሰው ኃይል በዚህ ሙያ እንደሚያሰለጥን ቴሌስኮፑም የምሥራቅ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ኔትወርክ በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የክፍለ አኅጉሩ ዩኒቨርሲቲዎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለው እንደሚያምኑ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
ቴሌስኮፑን ገዝቶ ለማስተከል ብቻ ቢያንስ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቱ በአጠቃላይ የስፔስ ሳይንስና የአስትሮኖሚ ቴክኖሎጂን በአገሪቱ ለማስፋፋትና ምርምሩንም ለማጠናከር የሚያስችል የፍሬምወርክ ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንጦጦን ኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከልን ለመጠቀም ከሶሳይቲው ጋር በተናጠል መፈራረሙን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስፔስ ሳይንስ ዙርያ የድኅረ ምረቃና የፒኤችዲ መርሐ ግብሮችን ትኩረት ያደረገ ሰፊ የማስፋፋት ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ የእንጦጦ ምርምር ማዕከልን ለመጠቀም የወሰደው ዕርምጃ የማስፋፋት ሥራውን በማፋጠን ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስታውቀዋል፡፡
ለኦብዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከሉ ግንባታ እንጦጦ የተመረጠው በምን ምክንያት ነው? ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹በወቅቱ ከአዲስ አበባ በጣም ርቆ ሌላ ቦታ ላይ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር በጣም የተሻለውና ለአዲስ አበባ በጣም ቅርብ ቦታ የትኛው ነው ሲባል ከከፍታና ከአየር ፀባይ አንጻር ተጠንቶ እንጦጦ አመቺ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከፍታውም 3170 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ቦታዎች ደግሞ ለምርምር በጣም ጠቃሚ ናቸው›› ሲሉ ዶክተር ሰሎሞን መልሰዋል፡፡


