በምሕረት አስቻለው
‹‹ጠዋት ንጋት ላይ ነበር፡፡ እኔና እህቴ እንዲሁም ሌሎች ሴት የሠፈር ጓደኞቻችን ሆነን ከቤታችን ብዙም ወደማይርቅ ጫካ ተወሰድን፡፡
የአራት ዓመት ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ሁላችንም በአንድ ቢላ ተገርዘን ተሰፋን፡፡ ባህላዊ መድኃኒትም ከቁስላችን ላይ ተደረገልን፡፡ እስክናገግምም እግሮቻችን ለቀናት ታሥረው ነበር፤›› በማለት በተገረዘችበት ወቅት ያለፈችበትን ስቃይ ያስታወሰችው የአሥራ ስድስት ዓመቷ ሞሚና ያሲን ነች፡፡
የግርዛት ሥነ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ፤ በግርዛቱ ምክንያት የተፈጠረው አካላዊ ቁስልም ከደረቀ በኋላ ስቃይዋ አላበቃም፡፡ እሷም ጓደኞቿም በመገረዛቸው ምክንያት በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ ሕመምና ስቃይ አለባቸውና፡፡
የሃያ አንድ ዓመቷ ጫልቱ ሲራጅ ተወልዳ ያደገችው በኢሉባቡር ጌቺ ወረዳ ውስጥ ሲሆን፣ የተገረዘችው የአሥራ አምስት ዓመት ታዳጊ ሳለች ነው፡፡ ሃይማኖቷ እንድትገረዝ ስለሚያዝዝ የግድ በዚያ ስቃይ ውስጥ ማለፍ እንዳለባት በቤተሰቦቿ ተነገራት፡፡ እሷም ምንም አልተቃወመችም፡፡
ጋብቻዋን የፈጸመችው ደግሞ በሃያ ዓመቷ ነው፡፡ ተጓዳኟን የመረጡላት ቤተሰቦቿ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድም ቤተሰቦቿ የሚመርጡትን ከመቀበል ባሻገር የመወሰን ሥልጣን አልነበራትም፡፡ ‹‹አረገዝኩ፤ በአንድ ምሽትም በምጥ ተያዝኩ፡፡ ምጡ ከባድ በመሆኑ ሕመሙ ልቋቋመው የምችለው አልነበረም፡፡ በአቅራቢያ ሆስፒታል አልነበረም፡፡ ትራንስፖርት ማግኘትም እንደዚያው ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህ ለሁለት ቀን ተኩል ስቃዬን ችዬ እቤት ውስጥ መቀመጥ ነበረብኝ፡፡ በመጨረሻ ቤተሰቦቼ በሸክም ወደ ሆስፒታል ቢወስዱኝም ከመዘግየቴ የተነሳ ጽንሱ በሕይወት አልተገኘም፡፡ ምጡም ብዙ ነገሬን አቃውሶት ነበር፡፡ ፊስቱላ ያዘኝ፤ ሽንቴን መቆጣጠርም አቃተኝ፡፡ ከማሕፀኔ የሚወጣው ፈሳሽ ሽታም ይረብሽ ነበር፡፡›› የምትለዋ ጫልቱ በመጨረሻም ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅቶች አማካይነት የሕክምና እርዳታ ማግኘት መቻሏን አውስታች፡፡
ከግርዛት ጋር በተያያዘ ወሲብ መፈጸም፣ የወር አበባ፣ ምጥና ሌሎችም ተመሳሳይ ነገሮች ስቃይ የሆኑባቸው፣ ይህ ስቃይም የሕይወታቸው አንድ ክፍል የሆነባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ሥነ ልቦናዊውም ሆነ አካላዊው ሕመም አንድ ጊዜ መጥቶ የሚሔድ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዓመት ዓመት እየተከተለ ያሰቃያቸዋል፡፡ ዘወትር የተገረዙበትን ሁኔታ አንዳች ነገር ሲያስታውሳቸው ጥልቅ ሐዘን ውስጥ የሚገቡ፣ በምሽት በመገረዛቸው ጨለማ በተለየ መልኩ የሚያስፈራና የሚያስጨንቃቸው ሴቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ ‹‹የወር አበባ አንድም ቀን ለኔ ቀላል ሆኖ አያውቅም፡፡ ሁሌም መከራ ነው፡፡ አምስት ልጆች ብወልድም ሁሉንም የተገላገልኩት በከባድና ስቃይ በተሞላ ምጥ ነው›› ያለችው ደግሞ በአዋሽ አንዱ ቀበሌ በሆነው ዶሆ ኗሪ የሆነችው መሪማ አደን ነች፡፡
2010 ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መጽሔት ላይ ግርዛት ከባድ የጤና ቀውስ እንደሚያስከትል ተቀምጧል፡፡ ብዙዎች ላይ የሚታየውም ከባድ ሕመም፣ መድማትና ኢንፌክሽን ነው፡፡ የሥነ ልቦና ጉዳት፣ ከወሲብ ጋር የተያያዘ ችግር፣ መካንነትና ሌሎችም ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡
የሴቶች ግርዛትን ለማስቀረት መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም ብዙዎች ዛሬም የድርጊቱ ሰለባ ከመሆን አልዳኑም፡፡ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ድርጊቱ በአንድ በኩል ከባህል፣ በሌላ በኩል ከሃይማኖት ጋር መያያዙ የሴቶች ግርዛትን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡ ይህንኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ቢወጡም በኅብረተሰቡ አመለካከትና በድርጊቱ ከባህልና ከሃይማኖት ጋር መያያዝ ተፈጻሚነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡
ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ፣ ሕገ መንግሥቱም፣ የቤተሰብ ሕግና ሌሎችም ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በተወሰነ መልኩ ድርጊቱ የመቀነስ አዝማሚያ ያሳየባቸው ክልሎች ቢኖሩም ዛሬም በርካቶች በግርዛት ይሰቃያሉ፡፡
የሴቶች ግርዛትን ለማስቆም ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር ያየህይራድ ቅጣውም ለዚህ ድርጅት አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ 1997 እና በ2007 ማኅበሩ ካደረገው ጥናት፣ እንዲሁም በ2000 እና በ2005 በአጠቃላይ በአገሪቱ ከተደረገው ሥነ ጤና ጥናት በመነሣት የሴቶች ግርዛት የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ነግረውናል፡፡ ማኅበሩ ባደረጋቸው ጥናቶች መሠረትም በአሥር ዓመት ውስጥ ሃያ አራት በመቶ መቀነሱን ማየት ተችሏል፡፡
‹‹ለምሳሌ፣ ትግራይ የሴቶች ግርዛት በስፋት ይካሔድበት የነበረ ቦታ ነው፡፡ አሁን ግን ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ታይቷል፡፡ እንደ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ደግሞ ድርጊቱ አሁንም ያለባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ የመስፋቱ ነገር ግን የቀነሰበት ሁኔታ አለ፡፡››
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከሴቶች ግርዛት ጋር በተያያዘ ያለው የሕግ ማዕቀፍ ምንም ዓይነት ችግር ባይኖረውም ከተፈጻሚነቱ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ሊነሡ ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳ የሴት ልጅ ግርዛት ሕገወጥ መሆኑን የሚያትቱ፤ በዚህ ተጠያቂ የሚሆኑ ላይም የሚጣለው ቅጣት ቢቀመጥ ሕጉ ስለመኖሩ የሚያውቁ ጥቂት ናቸው፡፡ በተለይም ድርጊቱ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ስለ ሕግ ማዕቀፎቹ ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
በዶ/ር ያየህራድ አነጋገር፣ ‹‹ሕጉ በሕዝቡ ስላልታወቀ፣ ብሎም ስላልሰረፀ የሕዝብ ሳይሆን የመንግሥት ብቻ ሆኖ እየታየ ነው፡፡ ግርዛት በድብቅ ይፈጸማል፤ ለሚመለከተው አካል ሕገወጥ ድርጊቱን ለመጠቆም ያለው የሕግ ከለላም፣ የሕግ አስፈጻሚዎቹም ምላሽ ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ በመሆኑ ሴት ልጁን በድብቅ ያስገረዘ ሕግ አስፈጻሚ ለሚደርሱት ጥቆማዎች ምን ዓይነት ምላሽ ሊኖረው ይችላል? ድርጊቱ እውነት ጐጂ፣ ወንጀልም እንደሆነ ሳያምንበት እንዴት ለሕጉ ተፈጻሚነት ሊሠራ ይችላል? ዓይነት ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡
ድርጊቱ በአንድ በኩል ከሃይማኖት፣ በሌላ በኩል ከባህል ጋር ተያይዞ ስለሚታይ የቱ ባህል ወይም ጐጂ ልማድ እንደሆነ፤ ከግርዛት ጋር በተያያዘ በተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የኅብረተሰቡ አመለካከት እስካልተለወጠ ድረስ ግን ሕግ በማውጣት ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡
ድርጊቱ ጐጂ፣ ሕገወጥም እንደሆነ ቢነገር የተለያዩ አስተምህሮቶችም ቢሰጡ የኅብረተሰቡ አካል እንደመሆናቸው የድርጊቱ ሰለባ የሚሆኑት ሴቶች እንኳ ‹‹ባህላችን ነው፡፡ እንዴት ይቀራል፣ ተገርዘን ስንት ልጆችን ወልደን የለ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
‹‹ያልተገረዘች ሴት ለትዳር የማትፈለግ፣ እንደ ባለጌ የምትታይ፣ ያልተገረዘች ተብላ የምትሰደብ፣ የአካባቢውን ወግና ሥርዓት የጣሰች ተደርጋ የምትታይና ከማኅበረሰቡ የምትገለል ከሆነ እስካለች በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ለመኖር ወግና ሥርዓት የተባለውን ጐጂ ልማዳዊ ድርጊት ከመቀበል ውጭ ሌላ ምን ምርጫ ይኖራታል?››
ከዚህም ባሻገር በማኅበረሰብ ውስጥ ህልውናን ጠብቆ ለመቆየትም ብቻ ሳይሆን ባህላችን ወጋችን እንዴት ይቀራል? ተግባሩም ትክክል ነው፤ ብለው የሚያምኑ ሴቶችም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህም ባህልን፣ ከጐጂ ልማድ ለመለየት፣ ግርዛት ከሃይማኖትና ከባህል ጋር አለው በሚባለው ቁርኝት ላይ በሚሠሩ ሥራዎች የሃይማኖት መሪዎችን፣ የአካባቢ ሽማግሌዎችና አባቶችን ማሳተፍ የግድ ይሆናል፡፡
ከዶ/ር ያየህይራድ ንግግር እንደተረዳነው፣ በጥቅሉ ሲታይ የሴት ልጅ ግርዛት በአገሪቱ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ ይህም እንደ ትግራይና አማራ ባሉ ክልሎች ታይቷል፡፡ በሌላ በኩል በአጐራባች አካባቢዎች ተቃራኒ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ በከንባታ ውስጥ የሴቶች ግርዛት ሲቀንስ በአጎራባቹ አላባ ግን ምንም የመቀነስ አዝማሚያ አይታይም፡፡ በደቡብ ኦሞ የሴት ልጅ ግርዛት ጨርሶ የማይታወቅበት ቦታ ሲሆን በተቃራኒው ሴት ልጅ እንዴት ሳትገረዝ? የሴት ልጅ ግርዛት ምንም ጥያቄ የማይነሣበት ድርጊት ተደርጐ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ በትግራይ ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ ግርዛት የቀረበት አካባቢ አለ፡፡
(የግለሰቦቹን ታሪክ የወሰድነው ከኤፍጂኤም ኔትወርክ ሕትመት ነው፡፡)


