በጌታሁን ወርቁ
ለዚህ ሐሳብ መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ለሁሉም ባንኮች የጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡
በዚህ ደብዳቤ ባለሥልጣኑ በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ቁጥር 79/1995 አንቀጽ 20 ከታክሱ ነፃ ከሚሆኑ ፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ዕዳ የመሰብሰብ ወይም የፋይናንስ ውክልና አገልግሎቶችን የማይጨምር በመሆኑ ይህም በተጨማሪ እሴት ታክስ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 21/1997 አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ/1/ እና /2/ በግልፅ የተመለከተ ስለሆነ ባንኮች ነፃ ያልተደረጉ ግብይቶች መኖራቸውን ተረድተው በተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ተመዝግበው የታክስ ግዴታቸውን እንዲፈፅሙ የሚያሳስብ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ባንኮች እዳ በመሰብሰብ ስራቸው ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ መጠየቁ የሕግ መሠረት አለው ወይ? ታክሱን እንዲከፍሉ ቢደረጉ በባንክ ኢንዱስትሪው የሚኖረው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ምንድነው? የሚሉት ነጥቦች የባንክ ኃላፊዎችን ሲያሳስቡ እንደነበር የባንኮች ማኅበርና ባለሥልጣኑ ሲያደርጉት የነበረው የጽሑፍ ልውውጥ አመላካች ነው፡፡ የባንኮች ማኀበር ጉዳዩ በባንኮች የሕግ አማካሪዎች እንዲታይ በማድረግ “የተጨማሪ እሴት ታክስ” ተመዝጋቢ መሆናቸው እንደገና እንዲታይላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑም ጥያቄያቸውን ከመረመረ በኋላ ባንኮች ለሚሰጡት ብድር በዋስትና የያዙትን ንብረት በሚሸጡበት ጊዜ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊከፈል ስለሚገባ ቀደም ሲል በተላለፈው መመሪያ መሠረት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሊመዘገቡ እንደሚገባ ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም. ለባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡ በዚህ ፅሁፍ የባንኮች ማኅበርና ባለሥልጣኑ ያቀረቧቸውን ምክንያቶች በመመርመር ባንኮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገባቸው ስለተገቢነቱና ስለሚኖረው ውጤት ለማየት እንሞክራለን፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የፋይናንስ አገልግሎቶች በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 8/2/ መሠረት ከታክስ ነፃ መሆናቸውን ይቀበላል፡፡ ሆኖም የሚያንፀባርቀው አቋም ሁሉም የፋይናንስ አገልግሎቶች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ አልተደረጉም የሚል ነው፡፡ ለዚህም ደንብ ቁጥር 79/1995 አንቀጽ 20ን በመጥቀስ ከፋይናንስ አልግሎቶች ውስጥ ከታክሱ ነፃ ያልተደረጉ ስለመኖራቸው ይተነትናል፡፡ የደንቡ አንቀጽ 20/2/ ከታክሱ ነፃ የተደረጉ የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚከተሉትን ይጨምራሉ በማለት በ/ሀ/ እና በ/ለ/ የሚከተሉትን ይዘረዝራል፡፡
/ሀ/ በአበዳሪው ወይም በዋስትና ሰጪው የሚከናወን ብድርን፣ የዱቤ ሽያጭን ወይም የብድር ዋስትናን ማስተዳደርን ጨምሮ ብድር፣ የዱቤ ውል ወይም የብድር ዋስትናን መስጠት፣ መደራደር ወይም
/ለ/ ዕዳን መሰብሰብ ወይም በውክልና መሥራትን ሳይጨምር ከገንዘብ /የገንዘብ ምንዛሬን ጨምሮ/፣ ተቀማጭ ሂሳብ፣ ቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ክፍያ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ ዕዳ፣ ቼክ ወይም ከሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶች ጋር በተያያዘ የሚከናወን እንቅስቃሴ
በዚህ ድንጋጌ መሠረት የገቢዎች ባለሥልጣን ከፋይናንስ አገልግሎቶች ውስጥ ዕዳን መሰብሰብ ወይም በውክልና መሥራትን አይጨምርም ይላል፡፡ አቋሙን ለማጠናከሪያም የደንቡን አንቀጽ 20/8/ ይጠቅሳል፡፡ ይህ ድንጋጌ ግልጽነት ቢጎድለውም፣ “በፋይናንስ ወኪል ተይዞ የሚቆይን እዳ ጨምሮ በማናቸውም ሁኔታ የሌላን ሰው እዳ ይዞ ማቆየት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት አይሆንም፡፡ በፋይናንስ ውክልና ወይም ከፋይናንስ ውክልና ጋር በተገናኘ አልግሎት፣ ከሽያጭ ተግባር ጋር የተዛመደ የሂሳብ አያያዝ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ እዳን ከማስመለስ ተግባር ጋር የተያያዘ አገልግሎት፣ ክስን የመከታተል ከባለዕዳዎች የሚፈለግን ዕዳ የማስተዳደር አገልግሎት ታክሎ ይከፈልባቸዋል፤” ሲል ይደነግጋል፡፡
የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሊከፍሉት ስለሚገባ ተጨማሪ እሴት ታክስ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 21/1997 በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ መሠረት ለፋይናንስ አገልግሎት የተሰጠው ከታክሱ ነፃ የመሆን መብት የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡትን በዋስትና የያዙትን የባለዕዳ ንብረት አይጨምርም ይላል፡፡ ከአዋጁና ከደንቡ በተለየ አኳኋን የአፈፃፀም መመሪያው የፋይናንስ ተቋማት ሊከፍሉ ስለሚገባው ተጨማሪ እሴት ታክስ ግልጽ ድንጋጌ ይዟል፡፡
የገቢዎች ባለሥልጣን አቋም የፋይናንስ አገልግሎት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ናቸው፤ ሆኖም ዕዳ ማስመለስን በተመለከተ በደንቡና በአፈፃፀም መመሪያው መሠረት ከታክስ ነፃ አይደሉም የሚል ነው፡፡
የገቢዎች ባለሥልጣን የያዘውን አቋም ሕጉን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ ለማጥናት የአዋጁን፣ የደንቡንና የመመሪያውን ይዘት መመርመር ይገባል፡፡ አዋጁ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ማን እንደሆነ፣ ስለአከፋፈሉ እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ሊከፍል የማይገባው አካል ማን እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ መሠረት የአዋጁ አንቀጽ 8 ከታክስ ነፃ ከሆኑ ግብይቶች ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎት በንዑስ ቁጥር 2/ለ/ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 8 ከተጠቀሱት ከታክስ ነፃ ግብይቶች ውጪ ያልደነገገ ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ አንቀጽ አሻሽሎ የወጣ አዋጅም የለም፡፡ የዚሁ አዋጁ አንቀጽ 8/4/ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ሌሎች ዕቃዎችና አገልግሎቶች ነፃ እንዲሆኑ ሊፈቅድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ አዋጁ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ነፃ የተደረጉትን አገልግሎቶች ለመቀነስ የሚያስችል የሕግ መሠረት አይሰጥም፡፡ የአዋጁ አንቀጹ 64 ደንብና መመሪያ የሚወጣው አዋጁን ለማብራራት ወይም በግልጽ በተሰጠ ሥልጣን አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ የታክስ ነፃ መብትን በመመሪያ/በደንብ ለመሸርሸር የሚያስችል የሕግ መሠረት በአዋጁ ላይ ባለመኖሩ የፋይናንስ አገልግሎት ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ማድረግ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በአዋጁ ነፃ የተደረጉ አገልግሎቶች በደንብ /Regulation/ ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ የሕግ መሠረቱን አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የተጨማሪ እሴት ታክስን ለማብራራት የወጡት ደንቡና መመሪያው በአዋጅ ከተደነገገው ግልጽ ድንጋጌ ጋር የሚጋጩ በመሆኑ ተፈፃሚነታቸው አጠያያቂ ነው፡፡
የባንኮች ማኅበር ለባለሥልጣኑ ባቀረበው አስተያየት ደንቡና መመሪያው ከአዋጁ ጋር መቃረኑን በግልጽ በምክንያትነት ባይገልፅም፣ አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆነው እቃን በመሸጥ ወይም እዳ የመሰብሰብ አገልግሎት ለ3ኛ ወገን በመስጠት ለተሰማሩ ድርጅቶች እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ባንኮች ዕቃ የመሸጥም ሆነ ለ3ኛ ወገን እዳ የመሰብሰብ አገልግሎት ስለማይሰጡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ሆነን ልንመዘገብ አይገባንም የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ባንኮች ከተጨማሪ እሴት ታክስ የኢኮኖሚ ትርጓሜም በመነሳት በባንኮች ላይ የአዋጁን ተፈፃሚነት ይቃወማሉ፡፡ ይኸውም ባንኮች በመያዣ የያዙትን የባለዕዳ ንብረት ሲሸጡ የሚደረግ ተጨማሪ እሴት ባለመኖሩ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝገቡ መባሉ አግባብነት የለውም ይላሉ፡፡
ባለሥልጣኑ በበኩሉ ባንኮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመዘገቡ ያስፈለገው በሚሸጡት ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ ስለሚኖርባቸው እንጂ ዕዳ የመሰብሰብ አገልግሎት ሰለሚሰጡ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ባለሥልጣኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበስበው ተጨማሪ እሴት /Value Addition/ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በአዋጁ አንቀፅ 6 የተገለፀው ታክስ የሚከፈልበት የንግድ እንቅስቃሴ በተከናወነ ቁጥር ነው ይላል፡፡
በመሠረቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ የኢኮኖሚ ትርጉም ታክሱ ሊከፈል የሚገባው ዕቃ ሲሸጥ ወይም አገልግሎት ሲሰጥ በማምረት ወይም በማከፋፈል የተጨመረ እሴት ሲኖር ቢሆንም፣ የአገራችን የተጨማሪ እሴት ታክስ ወሰን ሰፋ ይላል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 6 በተገለፀው መሠረት ታክስ የሚከፈልበትን የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ በተከናወነ ቁጥር የሚከፈል መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ባለሥልጣኑ ባንኮች ‘እቃ በመሸጣቸው’ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሊከፍሉ ይገባል የሚለው ሐሳብ ከባንኮች ስራ ጋር የማይሄድና በመመሪያው ከተገለፀው መንፈስ የራቀ ነው፡፡ ባንኮች እቃ የመሸጥም ሆነ ዕዳ ለ3ኛ ወገን የማስመለስ አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ለሰጡት ብድር በመያዣ የተሰጠን ንብረት ግን ተበዳሪው እዳውን በወቅቱ መክፈል ሳይችል ባለንብረቱን በመወከል በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 98/90 መሠረት በሐራጅ በመሸጥ ብድራቸውን ይሰበስባሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ‘ዕቃ ለመሸጥ’ም ሆነ ‘የሶስተኛ ወገን ዕዳን ለማስመለስ’ ባልተቋቋመበት ሁኔታ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ይመዝገቡ መባሉ ተገቢነት የለውም፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ እንደሚለው፣ ባንኮች ዕዳ በማስመለስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት መፈፀማቸውን መቀበል ያስቸግራል፡፡
በሌላ በኩል ደንቡ ከአዋጁ ይጣጣማል ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እስከወጣ ድረስ /ካልተሻረ/ ተፈፃሚነት ሊሰጠው ይገባል ካልን ደግሞ በደንቡ ድንጋጌዎች ላይ ያሉ የክርክር ልዩነቶችን እንመልከት፡፡ ባለሥልጣኑ በደንቡ መሠረት ከፋይናንስ አገልግሎቶች ውስጥ ዕዳን መሰብሰብ ከታክስ ነፃ አይደለም ይላል፡፡ የደንቡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ግን ይህን አቋም የሚደግፉ አይመስሉም፡፡
መጀመሪያ ደንቡ በአበዳሪው የሚሰጥ ብድርና ዋስትና አስተዳደሩን ጨምሮ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የብድር ዋስትና አስተዳደር ደግሞ የሕዝብ ገንዘብ ለነጋዴ በመስጠት በአግባቡ ማስመለስን ይጠይቃል፡፡ ብድር ከሚመለስባቸው መንገዶች መካከል በአግባቡ በውል መሠረት መክፈል ካልሆነም በመያዣ የተሰጠውን ንብረት በሀራጅ ሸጦ መመለስን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ዕዳ መሰብሰብ የብድር ውል አስተዳደር አካል ነው፡፡ ማበደርን ከታክስ ነፃ አድርጎ ብድር /ዕዳ/ መሰብሰብን ታክስ እንዲከፈልበት ማድረግ፣ በግራ እጅ ሰጥቶ በቀኝ እጅ እንደመንጠቅ ይቆጠራል፡፡ ባንኮችም ባቀረቡት አስተያየት እዳ ከተበዳሪው በጥሬ ገንዘብ /Cash/ ስንሰበስብ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደማንከፍል ሁሉ መያዣውን በመሸጥ እዳ ስንሰበስብም ልንከፍል አይገባም ሲሉ ያቀረቡት ክርክር ውኃ ይቋጥራል፡፡ ባለሥልጣኑ ለባንኮች በሰጠው መልስ በደንቡ ነፃ የተደረጉ የፋይናንስ አገልግሎቶች ውስጥ በአንቀጽ 20/2//ሀ/ ላይ ‘በአበዳሪው ወይም በዋስትና ሰጪው የሚከናወን ብድርን የዱቤ ሽያጭን ወይም የብድር ዋስትናን ማስተዳደር ጨምሮ ብድር. . .’ የሚለውን ድንጋጌ ትርጓሜ ሳይሰጠው አልፏል፡፡ እንደፀሐፊው እምነት ብድር በውል የሚተዳደር ሲሆን፣ ተዋዋይ ወገኖች ብድሩ ባይመለስ በመያዣ የተሰጠው ንብረት ተሸጦ የሚመለስበትን ሁኔታ ጭምር እንዲያካትት አድርገው የሚስማሙበት መሆኑን ባንኮች ከሚፈራረሙት የብድር ውል መረዳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል በደንቡ አንቀጽ 20/ሀ//ለ/ ወይም 20/8/ ላይ የተገለፀው እዳ የመሰብሰብ አገልግሎት “ባለገንዘብ የሆነ አካል የራሱን እዳ ሲሰበስብ” ወይስ “ባለገንዘቡን ወክሎ በመያዣ የተሰጠ ንብረትን በመሸጥ እዳ የሚያስመልሱ አካላትን” የትኞቹን ነው የሚመለከተው? የሚለው ሊጤን ይገባል፡፡ ደንቡ “እዳ መሰብሰብ ወይም በውክልና መስራት” የሚለው በእንግሊዝኛው ቅጅ “Factoring” የሚለውን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም የሶስተኛ ወገኖችን ጉዳይ በመያዝ በዋስትና የተሰጠን ንብረት በመሸጥ ዕዳ የሚሰበስቡ ተቋማትን የሚመለከት ነው፡፡ ባለገንዘቡ የራሱን እዳ ንብረት ሸጦ ካስመለሰ “Factoring” ነው ለማለት የሚያስችል ምክንያት አይኖርም፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች በፎርክሎዥር ሕግ መሠረት የሰጡትን ብድር ራሳቸው ንብረት ሸጠው ያስመልሳሉ እንጂ ለ3ኛ ወገን ኃላፊነቱን ቢሰጡ /outsource ቢደረግ/ ያ ፈፃሚ ተቋም ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የደንቡ አንቀጽ 20/8/ ይህን አተረጓጎም ይደግፋል፡፡ “በፋይናንስ ውክልና ወይም ከፋይናንስ ውክልና ጋር በተገናኘ አገልግሎት 1/ ከሽያጭ ተግባር ጋር የተዛመደ አገልግሎት መስጠት፣ 2/ ዕዳ ለማስመለስ የሚፈፀሙ አገልግሎቶች (በፍርድ ቤት ወይም ከፍ/ቤት ውጪ) ታክስ ይከፈልባቸዋል፤” የሚለው አነጋገር አንቀጽ 20/8/ “Factoring”ን ብቻ የሚመለከት ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የዘረዘራቸው ከፋይናንስ ውክልና ወይም ከፋይናንስ ውክልና ጋር በተገናኘ የሚሰጡ የሽያጭ፣ የዕዳ ማስመለስ፣ ክስ የመከታተልና ከባለዕዳዎች የሚፈለግ ዕዳን የማስተዳደር አገልግሎቶችን የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብይት ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ ስራዎች በባለቤቱ በራሱ ቢሰሩ ነፃ ስለመሆናቸው የተቃርኖ ንባቡን /acontrario reading/ መረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል ባንኮች በፎርክሎዠር አዋጅ ቁጥር 97/1990 አንቀጽ 5 የመያዣ ንብረት በመሸጥ ዕዳ የሚያስመልሱት ባለእዳውን በመወከል እንደተፈፀመ እንደሚቆጠር በግልጽ ያመለክታል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ነው ባለሥልጣኑ በሰጠው መልስ ‘ባንክ ንብረቱን የሚሸጠው የንብረቱን ባለቤት በመወከል ስለሆነ የንብረቱ ባለቤት ንብረቱን በሚሸጠበት ጊዜ ሊሰበሰብ የሚገባውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ለታክሱ ባለሥልጣን ገቢ የማድረግ ግዴታ አለበት በማለት የገለፀው፡፡ የዚህን አቋም ቅቡልነት /Validity/ ለመቀበል አንድ የንብረት ባለቤት ንብረቱን ሲሸጥ ሊከፍል የሚገባውን የታክስ አይነት መመልከት ግድ ይላል፡፡ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 37(1)(ሀ) ለንግድ፣ ለፋብሪካ፣ ለቢሮ የተያዘ ቤት በማስተላለፍ ከሚገኝ ጥቅም አስራ አምስት በመቶ /15%/ ባለቤቱ ሊከፍል እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ በግል መኖሪያነት የተያዘ ቤት በማስተላለፍ የሚገኝ ግብር ደግሞ ይህ ግብር እንደማይከፈልበት አንቀጽ 37/2/ ደንግጓል፡፡ ይህ ታክስ የካፒታል ዋጋ እድገት በሚገኝ ጥቅም ላይ የሚከፈል /Capital Gain Tax/ ሲሆን፣ የገቢ ግብር አዋጁ ቀደም ሲል ተፈፃሚ የነበረውን ይህንኑ የካፒታል ዋጋ እድገት አዋጅ ቁጥር108/87 በመሻር የደነገገው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኮች የፎርክሎዥር አዋጅን ሲያስፈፅሙ ተበዳሪውን በመወከል ሊከፍሉት የሚገባው ግብር ከካፒታል ዋጋ እድገት በሚገኝ ጥቅም ላይ የሚከፈልን ታክስ ሲሆን፣ መጠኑም አስራ አምስት በመቶ ነው፡፡ የዚህ ግብር አከፋፈልም ቢሆን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባንኮች ለብድር በዋስትና የያዙትን ንብረት ብድሩን ለማስመለስ ሙሉ በሙሉ መጠቀም አለባቸው ሲል መመሪያ አውጥቷል፡፡ /ሰኔ 25 ቀን 1994 ዓ.ም.፣ በቁጥር አመ/1/1628/771 የወጣ መመሪያ/ መመሪያው “. . . ባንኮች በዋስትና የያዙትን ንብረት ሸጠው ያገኙትን ገቢ በቅድሚያ ብድራቸውን ለመሸፈን እንዲያውሉ ሆኖ ቀሪ ገንዘብ ካለ ብቻ ለካፒታል ዋጋ እድገት ወይንም ለሌላ ታክስ ወይም ለሌላ መንግስት ዕዳ ክፍያ እንዲውል እንዲደረግ. . .” በሚል ተደንግጎ አናገኘዋለን፡፡
በዚህ ረገድ ባለሥልጣኑ ባንኮች ተበዳሪውን ወክለው የሚከፍሉት ግብር የተጨማሪ እሴት ታክስ ስለመሆኑ ይከራከር እንጂ ከላይ በቀረበው መሠረት በካፒታል እድገት በተገኘ ጥቅም የሚከፈል ግብርን የሚመለከት ነው፡፡ አከፋፈሉም ቢሆን ከዕዳ መሠብሰብ በኋላ ስለመሆኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ግልጽ አድርጎታል፡፡ የካፒታል እድገት ታክስ የሚመለከተው የንግድ ድርጅቶችን እንጂ በግል መኖሪያነት የተያዘ ቤት በሽያጭ ወይም በስጦታ ሲተላለፍ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለሥልጣኑ ባንኮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመዘገቡ ሲጠይቅ ግን የመኖሪያ ቤት ሽያጭን ስለማካተቱም ግልፅ መመሪያ አልሰጠም፡፡
ከሁሉም በላይ ሊታሰብበት የሚገባው ግን አዋጅ ያወጣው አካል /የሕግ አውጭው/ ሐሳብ /Legislative intent/ ነው፡፡ የፋይናንስ አገልግሎትን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ማድረግ ያስፈለገው በገንዘብ ዝውውር የሚጨመር እሴት ስለሌለ ወይም የፋይናንስ ተቋማትን ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውሩን ሊያናጋ ስለሚችል ነው፡፡ የባንክ ዋና ሥራ ደግሞ ከሕዝብ ገንዘብ በቁጠባ መልክ አሰባስቦ ለልማት እንዲውል ማበደር ነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ አገልግሎት ከሆኑት መካከል ብድርን፣ ተቀማጭ ሂሳብን፣ ቁጠባ/ተንቀሳቃሽ ሂሳብ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ ዕዳና ቼክን መሠል አገልግሎቶችን ነፃ አድርጎ “ዕዳ መሰብሰብን” ታክስ እንዲከፈልበት ማድረግ ትርጉም የለውም፡፡ የሕግ አውጭው መንፈስም አይመስልም፡፡ ስለዚህ ደንቡን አዋጁን ካወጣው አካል መንፈስ ውጪ መተርጎም ተገቢ አይሆንም፡፡
ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት ምክንያቶች በአዋጁ ነፃ የተደረጉ የፋይናንስ አገልግሎቶች በደንብ/በመመሪያ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ በደንቡ የሰፈሩት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት አላቸው ብንልም ድንጋጌዎቹ የሚመለከቱት Factoring በመሆኑ፣ ዕዳ መሰብሰብ የብድር አልግሎት አካል በመሆኑ፣ ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶች ነፃ የሆኑበት ምክንያት ለዕዳ መሰብሰብም የሚሰራ በመሆኑ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ዕዳ ሲሰበሰቡ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ የተወሰኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ባንኮች ያበደሩትን ብድር ለማስመለስ ይቸገራሉ፡፡ ባንኮች ያልተከፈለ እዳ በሐራጅ መያዣውን ሸጠው ሲመልሱ ገዥው ከሚገዛበት ዋጋ 15% እየጨመረ ሊገዛ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ንብረቱን ለመግዛት የሚቀርቡ ተጫራቾች ስለሚቀንሱ የገበያ ፉክክርን የሚያሳጣ ይሆናል፡፡ በብድር መልስ የተሰጠ የሕዝብ ገንዘብን እንደተበተነ ይቀራል፡፡
ሁለተኛው ባንኮች የማይመለሱ ብድሮችን እንዲያስታምሙ ይገደዳሉ፡፡ መያዣው በፎርክሎዠር ቢሸጥ በቂ ዋጋ ስለማያዋጣ /በተጨማሪ እሴት ታክስ ምክንያት/ ባንኮች ለተበዳሪው የመክፈያ ጊዜ በመጨመር ወይም በመለማመጥ ከፎርክሎዥር ውጪ ዕዳን የማስተዳደር አቅጣጫን ይከተላሉ፡፡ ይህም ባንኮች በፎርክሎዥር ሕግ በፍጥነት እዳ ለመሰብሰብ እንዲችሉ የታሰበውን ግብ ያፋልሳል፡፡
ሦስተኛው የውስጥ ለውስጥ የመያዣ ንብረት ሸያጭን ያበረታታል፡፡ አበዳሪ ባንኮች ተበዳሪው ራሱ ንብረቱን በግሉ ሸጦ /Private sale/ እዳውን እንዲመልስ ያበረታታሉ፡፡ ይህም በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የገበያ ንብረት ዝውውር ይገታል፡፡
ስለዚህ ባንኮች ዕዳ ሲሰበስቡ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ ማድረግ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን መቃረን ነው፡፡ ተፈፃሚነቱም የፋይናንስ ተቋማትን የሚጎዳ ይሆናል፡፡ በፎርክሎዥር ሕግ ለባንኮች ልዩ ጥበቃ ያስፈለገው እዳ በፍጥነት ለመሰብሰብ እንዲችሉ ነው፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ደግሞ ባንኮች እዳ ሲሰበስቡ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል የሕዝብ ገንዘብ በአግባቡ እንዳይመለስ እንቅፋት መሆን ነው፡፡ ይህ ተቃርኖ በሕግ አውጭው አካል የታሰበ አይመስልም፡፡ ባንኮችን በሚሰበስቡት ዕዳ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ፀሐፊውን በ
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
ማግኘት ትችላላችሁ፡፡


