Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በቴሌ ጉዳይ መንግሥት ዓይቶ እንዳላየ መሆን የለበትም

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

አፄ ሚኒሊክ ከነበራቸው የቴክኖሎጂ ጉጉት በመነሳት በዘመኑ የሳይንስ ግኝት የተፈበረኩ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ላይ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የቴሌፎን አገልግሎት አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም ይህ በአፄ ሚኒሊክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቴሌፎን ቀስ እያለ በድርጅት መልክ በመጀመሪያ የፖስታ፣ የቴሌግራምና የቴሌፎን /ፖቴቴ/ በሚል ተቋቁሞ ቀጥሎም በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ (BTE)፣ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን (ETA)፣ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ እስከ 2003 መጀመሪያ ወራት ድረስ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን  (ETC)፣ አሁን ደግሞ ለፈረንሳይ ቴሌኮም የማኔጅመንት ኮንትራት በመሰጠቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ስሙም ከፍራንስ ቴሌኮም እንዲመሳሰል በማለት ይመስላል ኢትዮ-ቴሌኮም  (ETHIO TELECOME) ተብሎ አዲስ ኩባንያ ተቋቁሟል እያሉን ይገኛል፡፡

ጆሮ የማይሰማው የለምና በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሀብት ላይ መጥቶ ቁጢጥ ብሎ የተቀመጠን አካል ከላይ እንደጠቀስኳቸው የስም ለውጥ ሆኖ ሳለ ‹‹አዲስ ኩባንያ›› ነው፤ ከኢትዮ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ በማለት ክቡር ሚኒስትሩ አቶ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልና ሌሎችም ሹማምንት ሊነግሩን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አባባል ለምን አስፈለገ? አዲስ ኩባንያ ማለትስ ምን ማለት ነው? ወዘተ. ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

በመሠረቱ አዲስ ኩባንያ ማለት በግዥ ወደራሱ ስም ያዞረ ወይም የራሱ አዲስ የንግድና የሥራ ፈቃድ አውጥቶ፣ የራሱን ገንዘብ አፍስሶና አደራጅቶ፣ የራሱን ኃይልና አስፈላጊውን መሣሪያ በአጠቃላይ አስፈላጊውን ሀብት አመቻችቶ ወዘተ. ለሥራ የሚንቀሳቀስ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አዲስ የተባለው ኩባንያ ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን አፍስሶ የተመሠረተ ሳይሆን በእርግጠኝነት የኮርፖሬሽኑን ሀብት ተጠቅሞ ወይም ወርሶ ስሙ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም የተቀየረ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ‹‹አዲስ ኩባንያ ነው›› እየተባለ መጠራቱ ለምን አስፈለገ? መልሱ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠረውን ሠራተኛ ለመበተን ስለተፈለገ አዲስ ኩባንያ ተብዬው ሠራተኛውን ‹‹አላውቃችሁም›› ለማለት እንዲመቸው ብቻ ነው፡፡

የሠራተኛው ብተና ለምን አስፈለገ?
ሚኒስትሩ አቶ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እስካሁን የነበረው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነና ለውጥ እንደሚያስፈልገው (Transformation) በመግለጽ፣ በተለይ የሞባይል ጥራት ጉድለትን እንደ ምሳሌ እያነሱ በትራንስፎርሜሽኑ ምክንያትም አንድም ሠራተኛ እንደማይቀነስና ከክፍል ኃላፊዎች በላይ ያሉትን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጆች ሰብስበው በተደጋጋሚ አስረድተዋል፡፡ ጭራሽ በእጅ እንደተጨበጠ ዓይነት፣ ‹‹አጥንተን አይተነዋል ሠራተኛ ከውጭ ያስጨምር እንደሆነ እንጂ፣ አሁን ያለውን አያስቀንሰንም፡፡ የፈረንሳዮቹን ጥናትም አይተነው ከእኛ ብዙ የተለየ አይደለም፤›› በማለት ነበር ሠራተኛ እንደማይቀነስ ለማረጋገጥ የሞከሩት፡፡

ይህ አነጋገራቸው አሁን እየተፈጸመ ካለው በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠራተኛና ቤተሰብ ጦም ማሳደር፣ ቤት ማዘጋት፣ ጎዳና ተዳዳሪ ማድረግና ያለጥፋቱ መቅጣት፣ የአገርና የቤተሰብ ሸክም ማድረግ ጋር ፍጹም የማይጣጣምና ተጻራሪ ነው፡፡ በተግባር የሚታየው ከአንድ መንግሥትና አገርን ከሚወክሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የማይጠበቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግባር የመንግሥትን ክብር የሚጠብቅ አይደለም፡፡

ሠራተኛው ለምን ይበተናል?
አንደኛ የመንግሥት ፖሊሲ የቴሌኮም አገልግሎትን በመላ አገሪቱ እስከ ቀበሌ ገበሬ መንደር ድረስ ማዳረስ ስለነበር ይህንኑ ለማስፈጸም አገልግሎቱን የሚያስፋፉና በቅርብ ሆነው የሚያገለግሉ ሠራተኞችና የተለያየ ደረጃ ያላቸው ጽሕፈት ቤቶችን ማደራጀት አስፈላጊ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሠራተኛ እየጨመረ ሥራ አጥነትን በመቅረፍም የራሱ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ከመንግሥት ፖሊሲ በተቃራኒ የሕዝቡን፣ የአገሪቱን አሰፋፈርና ቆዳ ስፋት መሠረት ያላደረገ በሠራተኛ ቅነሳ በማድረግ ለሕዝቡ በቅርብ አገልግሎት የሚሰጡትን የሥራ ዘርፎች እየዘጋ ነው፡፡ ንግዱን ከፍተኛ ትርፍ ወደሚያጋብስባቸው በትላልቅ ከተሞች ብቻ እንዲታጠር በማድረግ ሠራተኛው እንዲበተን ምክንያት ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ሠራተኛን በመቀነስና የሥራ ሁኔታን በማጥበብ የሚገኝ ትርፍ በትክክል ትርፍ ነው ማለት ይቻላልን?

ሁለተኛ ትራንስፎርሜሽንና የሥራ ጥራትን ምክንያት በማድረግ ሠራተኛውን መበተን እንደተፈለገ ይገባናል፡፡ ለዚህ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይኼውም ሚኒስትሩ ደጋግመው ያነሱትን የሞባይል ጥራት ጉዳይ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡ የሞባይልና ሌሎች ቴሌኮም አገልግሎቶችን ማስፋፋት ሥራ በቬንደር ፋይናንሲግ ዜድቲኢ ለተባለ የቻይና ኩባንያ በመሰጠቱ፣ ይህ ኩባንያ ከዕቃ ግዥ እስከ ማጓጓዝና መትከል፣ ሥራ ማስጀመር ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፣ ኩባንያው አዲስ ዕቃ ይግዛ ወይም አሮጌ፣ አስተማማኝ ይሁን አይሁን ብዙ የሚቆጣጠረው አካል አልነበረም፡፡ በርካታ ባለሙያዎችም የቻይናው ኩባንያ የእውቀት ሽግግር እየሰጠ አለመሆኑን፣ የሚመጣው ዕቃውም አስተማማኝና ረዘም ያለ የአገልግሎት ዘመን የሚሰጥ እንደማይመስል በመግለጽ በስብሰባ ቢገልጹም፣ ተቀባይነት አላገኙም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በዚህ የጥራት ጉድለት እጃቸው የለበትም፡፡ ስለሆነም ያለጥፋታቸው ነው እየተቀጡ ያሉት፤ ይህም ለሠራተኛው ብተና ሌላው ምክንያት ነው፡፡

ሦስተኛ በዓመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሰበስብ፣ ለመንግሥት በ2002 በጀት ዓመት እንኳን አራት ቢሊዮን ብር ፈሰስ ያደረገ፣ በርካታ ሠራተኞችን በመያዙ ሥራ አጥነትን በመቀነስ የራሱ አስተዋጽኦ በማድረግ የመንግሥትን ሸክም ይካፈል የነበረው በኢትዮጵያ በሀብቱ ተወዳዳሪ የሌለውን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን መሥሪያ ቤት አሁን ለምናየው ሁኔታ መዳረጉ ግራ ያጋባል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የዕድገት መንገድ የሚያመላክት እንጂ ወደ ውድቀት ስላልተጓዘ ለውጭ ኩባንያ የሚሰጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ስሙን በማዛወር ወይም እንደነሱ አጠራር ወደ አዲስ ኩባንያ በመለወጥ፣ ቀደምት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ሠራተኞች እንደ አሁኑ ቴክኖሎጂው ተሻሽሎ ባልነበረበት ጊዜ ረጅም መስመር በበረሃ ሲዘረጉ በውኃ ጥም፣ በረሃብና በወባ ሳይሸነፉ፣ በዱር በገደሉና በጫካው በአውሬው እየተበሉ ሳይሸነፉ፣ የማንዋል ማዞሪያ ሠራተኞችም ሆኑ ሌሎች በኢሠፓና በደርግ ባለሥልጣናት እየታሰሩና እየተዋከቡ እዚህ ያደረሱት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድም የቀድሞዎቹን ፈለግ በመከተል ላይ ሳለ አሁን ግን ከላይ እንደተገለጸው ትርፋማና ከፍተኛ ሀብት ያለው መሥሪያ ቤት ሆኖ እያለ፣ መስፈርቱ በማይታወቅ የይስሙላ ምደባ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠራተኛን ከነቤተሰቡ ከሥራ ማሰናበቱ ፍጹም አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ሚኒስትሩ በስብሰባና በሚዲያ አማካይነት አንድም ሠራተኛ አይቀነስም ሲሉ ቆይተውና በሌላ በኩል ደግሞ ምደባ ጨርሰናል በማለት፣ እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ አሁን የመጨረሻ ሰዓት በመድረሱ የካቲት 2 ቀን 2003 ዓ.ም. የመጨረሻውን መርዶ ነግረውናል፡፡

አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ግን በአንጻሩ የፋይናንስ ቀውስ ባጋጠማቸው ጊዜ የግል ድርጅቶች ሳይቀር ከስረው ህልውናቸው እንዳያከትም፣ ሠራተኛውን የበለጠ እንዳይበትኑና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ቢሊዮን ብር ድጎማ በመስጠት ከውድቀት በመታደጋቸው፣ በአሁኑ ጊዜ አጥጋቢ ባይሆንም በትንሹም በማንሰራራት ላይ መሆናቸው ከማንኛችንም የተሰወረ ነው የሚል ግምት የለንም፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሠራተኞች ግን መንግሥትን አላስቸገረም፣ ደጉሙኝ አላለም፤ ችግር ቢኖርም ሊታረም የማይችል አልነበረም፡፡ የተፈጠረ ችግር እንኳ ቢኖር ለዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡
ስለሆነም አሁንም መንግሥት አሳማኝና በቂ ባልሆነ ምክንያት ብዙ ሺሕ ሠራተኞችን ከሥራ ማባረሩ ጉዳዩ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ዜጋና የአገር ጉዳይ መሆኑ ታውቆ እንደገና በጥሞናና ከስሜት በፀዳ በሰከነ መንፈስ ማየትና ማስተካከል ይገባዋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርም ባለፈው የፓርላማ ስብሰባ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን የገለጹት ስህተት ነው፡፡ እውነቱን ለማየት ውስጡን ገብተው ማየትና መፈተሽ ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ቴሌኮሙዩኒኬሽን ከ120 ዓመት በላይ ዕድሜው፣ በተለይ ደግሞ በኢሕአዴግ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የነበረውን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ፖሊሲ በተቃራኒ አገልግሎቱን በማጥበብ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ተግባራዊ ማድረጉ ጥሩ አይደለም፡፡ የሠራተኛውንና የመሥሪያ ቤቱን ህልውና የሚፈታተን፣ የተገልጋዩን ሕዝብ አገልግሎት የሚጎዳ አካሄድ እየታየ በመሆኑ አስቸኳይና ወቅታዊ የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ መንግሥትም አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ መሆን የለበትም፡፡ 
እውነቱ ከበደ፣ ከአዲስ አበባ