Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የሴት ልጅ ውበቷ ምኗ ነው?

E-mail Print PDF
User Rating: / 6
PoorBest 

በምሕረት አስቻለው

‹‹ዓይን፣ ጥርስ፣ ፀጉር እያሉ የሴት ልጅ ውበትን መዘርዘር በአሁኑ ወቅት የቀረ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ነገሮች በዱሮ ዘፈን ላይ ብቻ እንደቀሩ ይሰማኛል፡፡ ስለ ሴት ልጅ ውበት ከተነሣ የሚወራው ስለ ሰውነት ቅርፅ፣ ስለ ዳሌ ነው፤›› ያለን አቶ ወንደሰን በየነ ነው፡፡

አንዳንዶች የሴት ልጅ ውበት አካላዊ ነው በማለት ጎላ ጎላ ያሉ ዓይኖች፣ ስንደዶ አፍንጫ፣ ሌላም ሌላም እያሉ ይቀጥላሉ፡፡ በተቃራኒው ውበት በጥቅሉ ውሳጣዊ እንጂ አካላዊ አለመሆኑን፤ በራስ መተማመን፣ መንፈሰ ጠንካራነት ከሁሉም በላይ ዋጋ የሚሰጣቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ለአንዱ ውብ ሆኖ የታየ ለሌሎችም ተመሳሳይ ስሜት ሳይሰጥ ሲቀር ይታያል፡፡ በተቃራኒው ለአንዱ ምንም ዓይነት መስህብ የሌለውና የማያምር ሆኖ የታየው ለሌላው ውብ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ የእይታ ልዩነት ከግለሰቦች ማንነት፣ ባሕርይ፣ ሥነ ልቦና፣ አስተዳደግ፣ የኑሮ ዘዬና በሌሎችም ተመሳሳይ ነገሮች ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ በእነዚህ ተጽዕኖዎች ቅላት ውበት ነው ብሎ ለሚያምን ጠይም ሴት የሱ ምርጫ ወይም ውብ የሚላት ላትሆን ትችላለች፡፡ ጠይምነት ውበት ነው ብሎ የሚያስብም ደግሞ ስለ ቀይ ሴቶች የሚሰማው በተመሳሳይ መልኩ ይሆናል፡፡

ስለዚህም እንደ ተመልካቹ የሴት ልጅ ውበቷ ፀጉሯ፣ ዓይኗ፣ ጥንካሬዋ፣ ሌላም እየተባለ ሲነገር ይሰማል፡፡ ለወንደሰን በእሱ እይታ የሴት ልጅ ውበት ምን እንደሆነ ጠይቀነዋል፡፡ እሱ ከሁሉም በላይ ዋጋ የሚሰጠው ለሴት ልጅ አካላዊ ሳይሆን ውሳጣዊ ውበት እንደሆነ ነግሮናል፡፡ ይህ ማለት ግን ከሴት ልጅ አካል በተለየ መልኩ የሚሳብበት ወይም የሚያስደንቀው ክፍል የለም ማለት አይደለም፡፡ ዘወትር በሚያምሩ የእግር ጣቶች ይማረካል፡፡ የዲግሪ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በነበረበት ወቅት የገጠመውንም፣ ‹‹አንድ ቀን በእጅ መታጠቢያ ገንዳ ላይ ብዙ ሆነን እጃችንን ስንታጠብ ከጎኔ የነበረች ሴት ልጅ የእግር ጣቶች በጣም የሚያምር ስለነበር ዓይኔን ከእግሯ ላይ መንቀል አቃተኝ፡፡ አስተያየቴ የተለየባት ልጅም ግራ ተጋባች፤ ተደናገጠችም፤ ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ ከጣቶቿ ላይ ዓይኔን መንቀል አቅቶኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን መረበሿ፣ እንደዚያ እግር እግሯን ማየቴም ትክክል እንዳልሆነ ተሰምቶኝ ይቅርታ ጠየቅኳት፡፡ ከዚያም ተግባብተን ለምን እንደዚያ እንዳየኋት ነገርኳት፤›› በማለት አስታውሷል፡፡

ስለ ውጫዊውም ሆነ ውስጣዊ የሴት ልጅ ውበት ሲወራ ሴት ልጅን በቤት ይመስላል፡፡ የቤቱን በር በውጫዊው የሴት ልጅ አካል፣ ቤት ውስጥ የሚኖሩትን ዕቃዎች ደግሞ በውስጣዊ ማንነት ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ እንደ እሱ እምነት በር መግቢያ እንደመሆኑ ውጫዊ የሴት ልጅ ውበትም የግንኙነት መጀመርያ እንጂ ግንኙነቱን ማቆያ ወይም ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ የሚያሸጋግር ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ በመነሣት ‹‹የሴት ልጅ ውበቷ ውስጣዊው ማንነቷ፣ መልካም ሥነ ምግባርና በራስ መተማመኗ ነው፡፡ ብዙዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን ሳይሆን በሩን ሲያደንቁ ይታያል፤›› ብሎናል፡፡  

ውጫዊ አካላቸው አንድ በአንድ ሲታይ ይሄ ነገራቸው ውብ ነው ብሎ ብዙ ሰው ሊስማማ በማይችልባቸው ሴቶች ዙርያ በርካታ ወንዶች የሚገኙ፤ እንደዚህ ያሉ ሴቶችም በተለየ መልኩ ከሚቀርቧቸው ወንዶች ተደጋጋሚ የፍቅር ጥያቄ ሲቀረብላቸው እንደሚስተዋል የሚናገረው ወንደሰን፣ ምንም እንኳ ብዙዎች በውጫዊው የሴት ልጅ አካል መሳባቸው ቢታይ ውስጣዊውን ነገር በአንድ አጋጣሚ ማየት የቻሉት ደግሞ ውበት ውሳጣዊ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል እንደሚረዱ ያስረዳል፡፡

‹‹ለምሳሌ፣ የምናገረውን  ነገር የማትረዳና ሁሌ ምን ለማለት ፈልገህ ነው? የምትል ሴት የሕይወት ተጓዳኜ እንድትሆን አልፈልግም፡፡ ይህ ማለት ግን ውሳጣዊ ማንነቷ መልካም ከሆነ፣ በራስ መተማመን ካላት ሴት ጋር ሁሉ እስማማለሁ ማለት አይደለም፡፡ በራስ መተማመን በምን ያህል ደረጃ፣ መልካምነትስ እስከ ምን? ሌላም ሌላም፡፡ ይህ ደግሞ በመቀራረብ የሚታይ ይሆናል፡፡ ምን ያህል በራስ መተማመን ያላት ሴት ነች ከእኔ ጋር ተጣጥማ መኖር የምትችለው? በምን ያህል ደረጃ ቀና ወይም ጥሩ የሆነች ሴት እያልን ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች የሚመለሱት በመቀራረብና በመተያየት ነው፡፡››

ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የቁንጅና ውድድር በተጀመረበት በ1950ዎቹ አጋማሽ ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱም ሁለተኛ ወጥተዋል፡፡ ዛሬ ላይ ዕድሜያቸው ከስድሳ በላይ ቢሆንም ጠንካራና የሚሠሩ፣ ያሰቡትን ከግብ የሚያደርሱ ዓይነት ሴት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

‹‹ለእኔ ዓይን፣ ጥርስ፣ ዘንካታ ቁመና ብለን የምንጠቅሰው ውጫዊ ውበት ሁሉ እንዳለ የሴት ልጅ ውበት ጥንካሬዋ ነው፡፡ በራሷ የምትተማመን በወንድ ላይ ጥገኛ ሳትሆን ራሷን ችላ የምትቆምና ያሰበችውን ማድረግ የምትችል ሴት በየትኛውም  የዕድሜ ክልል ብትገኝ ለእኔ ውብ ናት፤›› በማለት በተለያዩ ነገሮች ላይ ባላቸው አቋም የሴቶች ጥንካሬና ድክመት እንደሚንፀባረቅ ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው አባባል፣ የሴት ልጅ ጥንካሬ በራስ መተማመን፣ ኃይለኝነት ወይም በትዳር ውስጥ ታዣዥ አለመሆን አይደለም፡፡ ይልቁንም ታዛዥ መሆን መልካም ነገር ነው፡፡ መተኮር ያለበት ሴት ልጅ ምን ዓይነት ትዕዛዞችን መቀበል አለባት የሚለው ላይ ነው፡፡ ማንነቷን ዝቅ የሚያደርግ፣ የሰውነት መብቷን የሚጥስ ትዕዛዝን አለመቀበል ጥንካሬ ሲሆን፣ ይህን ለማድረግም በራስ መተማመን ያስፈልጋል፡፡

‹‹እኔም እንዳንተ ወንድ ነኝ የሚል ግትርነት ብዙም የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ መሥራት፣ ዘወትር ታታሪነትና ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያ መሆንም እንደ ውበት ሊታይ ይገባል፡፡ ሙያ ስንል ደግሞ የግድ ወጥ መሥራት ብቻ አይደለም፡፡ የቤት አያያዝ፣ የበጀት አጠቃቀም ባለሙያ መሆንን ይጠይቃል፡፡››

እሳቸው ውብ ተብለው በቁንጅና ውድድር ላይ በተሳተፉበት ዘመን የውድድሩ መስፈርት በአካል ውብ ሆኖ መታየት ብቻ አልነበረም፡፡ የተወዳዳሪዎቹን አመለካከትና የአስተሳሰብ ደረጃ ለመገምገም የሚያስችሉ ጥያቄዎችም ለተወዳዳሪዎች ቀርበው ነበር፡፡

የሴት ልጅ አካላዊ ውበትን በሚመለከት መቅጠንና ሸንቀጥ ማለት እንደ ውበት የሚቆጠር ነበር፡፡ እሳቸውም እንደ ዛሬው ሳይሆን በጣም ሸንቃጣ ነበሩ፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ዛሬ ላይ በሚያዩት የሴቶች ቅጥነት ግን ውበት ነው ብለው አይስማሙም፡፡ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ጠየቅናቸው፡፡ ‹‹በእኔ ወላጆች ጊዜ ወፈር፣ ሞላ ብሎና ደርበብ ማለት እንደ ውበት ይታይ ነበር፡፡ በእኛ ጊዜ ደግሞ ያ አልነበረም፡፡ ሸንቀጥ ብሎ መታየት ውበት ነበር፡፡ አሁን የማየው ግን ለሞዴሊንግ፣ ለብሶ ለመታየት እንጂ ውብ የሚያስብል አይደለም፤ ምክንያቱም ቅጥነቱ በጣም በዝቷልና፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሴት ልጅ ውበት ጋር በተያያዘ ሙያም ብዙ ትኩረት የሚደረግበት ነገር እየሆነ እንዳልመጣ ይሰማቸዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ግን ቋሚና በሕይወት ዘመን አብሮ ለሚዘልቀው የሴት ልጅ ውሳጣዊ ውበት ዋጋ ቢሰጥ፣ ቢተኮርም መልካም ይሆናል፡፡