Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ዲያስፖራው ዕውቀቱን የሚያካፍልበት አካሔድ ገና አልተሠራም

E-mail Print PDF
User Rating: / 4
PoorBest 

በታደሰ ገብረ ማርያም

ዶክተር ተዋበች ቢሻው በዲያስፖራ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ‹‹አሊያንስ ፎር ብሬን ጌይን ኤንድ ኢኖቬቲቭ ዴቨሎፕመንት›› (አባይድ) የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በሥራ ዓለም በቦንጋና ድሬዳዋ ጤና ጣቢያዎች፣ በሐረር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት በልዩ ልዩ የጤና ዘርፍ ሲያገለግሉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና አጠባበቅ ትምህርትና የሰው ኃይል ማደራጃ መምርያ ኃላፊም ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዛም በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባልደረባ ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ በሕንድ የጤና ፕሮግራም ኃላፊ፣ በቦትስዋና ምክትል ተጠሪ፣ በናሚብያ የጤናና የሥነ ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ በመሆን ለ15 ዓመታት ሠርተዋል፡፡

የመምርያ ኃላፊ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ መዓለ ንዋይ አፍስሳ ያሰለጠነቻቸው የሕክምና ባለሙያዎች ለከፍተኛ ሥልጠና ወደ ተለያዩ የባዕድ አገሮች ሲላኩ አብዛኞቹ ሳይመለሱ እንደወጡ ይቀራሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ውስጣቸውን ይከነክናቸው ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች የገበዩትን ዕውቀት ላስተማራቸው ኅብረተሰብ እንዴት አድርገው ማዳረስ ይችላሉ የሚለውም ሐሳብ በአእምሮአቸው ይመላለስ ነበር፡፡

በዚህም የተነሣ ከዩኒሴፍ ሥራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ፣ ውለው ሳያድሩ ይህንኑ አባይድ የተሰኘ ድርጅት ለመመሥረት በቅተዋል፡፡ ዶክተር ተዋበች እንደገለጹት፣ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቃቂ ካምፓስ ውስጥ ያደረገው ድርጅታቸው ከቮለንተሪ ሰርቪስ ኦርጋናይዜሽን ጋር በመተባበር ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሦስት ካናዳውያን ባለሙያዎችን በማስመጣት አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት ካሪኩለም ማሻሻያ፣ በኤችአይቪ/አዲስ ሕክምናና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ዙርያ ፍሬያማ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ከእነዚሁ ባለሙያዎች መካከል አንደኛው ለስድስት ወራት፣ የቀሩት ደግሞ እያንዳንዳቸው ለሦስት ወራት ያህል ማገልገላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዶክተር ተዋበች ማብራርያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ዲያስፖራው ባለበት አገር ሆኖ በቴሌ ኮንፈረንስ፣ ሶፍት ዌር በመላክና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ያስችለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለአጭር ጊዜ መጥቶ የአሠልጣኞች ሥልጠና የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸትና በምርምር ዘርፍም እዚህ ካሉት ተመራማሪዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ የምርምር ውጤቱ ለአገር ልማት የሚውልበትን መንገድ መቀየስ ይቻላል፡፡

እነዚህንና ሌሎች አካሔዶችን በመከተል ሕንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ ወዘተ. በሚገባ እንደተጠቀሙ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ገብተው በመካሔድ ላይ ባለው የልማትና የግንባታ እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን መንገድ ማመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

ለእንቅስቃሴውም እውን መሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ ጉዳዮችን የሚከታተል ዳይሬክቶሬት መቋቋሙ፤ በክልሎችም ይህንኑ እንቅስቃሴ የሚያስተባባር ምቹ ሁኔታ መኖሩ መንግሥት ለውጭ ያሉ ምሁራንን የማምጣት ፍላጎት እንዳለው በግልጽ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን በብዛት ትኩረት የተሰጠው ገንዘባቸውን ወደ አገር ቤት በሚልኩበት አካሔድና በኢንቨስትመንት ላይ ሊሳተፉ በሚችሉበት መንገድ ላይ መሆኑ ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም፣ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች መጥተው በጤና ድርጅቶች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በሌሎችም ዕውቀት በሚጠይቁ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው እዚህ ካሉት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት አገልግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት አካሔድ ላይ ገና እንዳልተሠራበት አስረድተዋል፡፡

በዶ/ር ተዋበች አገላለጽ፣ በግለሰብ ደረጃ በቡድን መጥተው በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች አንዳንድ ሥራዎችን አጠናቅቀው ቢመልሱም በሥርዓትና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ስላልተያዘ ለልማት የሚኖረው ግብዓትነት በጣም አናሳ ያደርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት አባይድ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ምሁራን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሥርዓት ባለውና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ወደ አገር ቤት በማስመጣት ዕውቀታቸውን ለአገር ልማት ላይ ሊያውሉ የሚችሉበት አካሔድ በመቀየስ ለተግባራዊነቱም ከአዲስ አበባ፣ ከጅማ፣ ከባሕር ዳርና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዲያስፖራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከሚንቀሳቀሰውና በአሜሪካ ከሚገኘው ፒፕል ቱ ፒፕል ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ዶ/ር ተዋበች እንዳሉት፣ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ካቋቋሙት ‹‹አሶሴሽን ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ኤጂዮኬሽን ፎር ዴቨሎፕመንት›› ከተባለ ድርጅትም ጋር ተመሳሳይ ሰነድ መፈራረሙን፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ እና ፊዚሲስት ማኅበራት፣ እንዲሁም ‹‹ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ኢን ሒውስተን (ቴክሳስ)›› ብለው ራሳቸው ካደራጁ ዲያስፖራዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱም ትኩረት ያደረገው በዲያስፖራ ሊሞላ የሚችለውን የሰው ኃይል ፍላጎትን ለይቶ ማውጣት ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በዲያስፖራ ለመጠቀም የተከናወነው ሥራ ምን እንደሚመስልና ዲያስፖራው ያቀናው ነገር ምንድነው? የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል ስልት አካትቷል፡፡

ዲያስፖራው በአገር ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ ዘለቄታዊ የሆነ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችልበትን አካሔድ ሥርዓት ባለውና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማደራጀት የሚቻልበትን መንገድና ሌሎችንም ተዛማጅ ጉዳዮችን ማቀፉን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ከተቋቋመ አራት ዓመት የሞላው የዚሁ ድርጅት ትልቁ ችግር የፋይናንስ አቅም ማነስ መሆኑንና ገንዘብ ለማግኘት በየጊዜው የፕሮጀክት ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) እያዘጋጀ ለተለያዩ የዕርዳታ ሰጪዎች ቢያቀርብም እስከዛሬ ድረስ የተሳካና ጠቀሜታ ያለው ምላሽ እንዳላገኘ፣ ድርጅቱ የቆመለት ዓላማ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ሁሉም እንደሚያምኑ ነገር ግን አዲስ ሐሳብ ከመሆኑ ይመስላል እጃቸውን ከመዘርጋት ሲቆጠቡ እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡