በታደሰ ገብረ ማርያም
የኩላሊት ችግር ያለባቸውን ሕፃናት ደማቸውን በሰው ሠራሽ (አርቲፊሻል) ኩላሊት አማካይነት ለማጣራትና በሌላ ኩላሊት ለመቀየር በድምሩ ከ36ሺሕ ዶላር በላይ እንደሚያስወጣ ዶክተር ዳምጤ ሽመልስ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል አጠቃላይ ሆስፒታል የሕጻናት ሐኪም፣ የሕፃናት ኩላሊት ስፔሻሊስትና የሕፃናት ክፍል ኃላፊ ገለጹ፡፡
ለአምስት ቀናት ያህል የተካሔደውን የክሊኒካል ኢሞሎኖጂ ሥልጠናን አስመልክተው ዶክተር ዳምጤ በተለይ ለሪፖርተር እንዳመለከቱት፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ 600 ዶላር ለደም ማጣርያ ሲውል፣ 36ሺሕ ዶላር ደግሞ ኩላሊትን ለመቀየር የሚያስችል ነው፡፡
የማጣራቱ ሥራ የሚከናወነው በሳምንት ለሦስት ቀናት ሆኖ ለእያንዳንዱ ቀን የማጣራት ሥራ 200 ዶላር እንደሚያስፈልግና የማጣራቱም ተግባር አራት ሰዓት ይፈጃል፡፡ በተለይ ኩላሊትን የመቀየሩ ሕክምና የሚከናወነው በውጭ አገር መሆኑ ለዚህም የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን የትራንስፖርት ወጪን አይሸፍንም፡፡
የኩላሊት ሕክምና ከማድረግ አልፎ ኩላሊትን እስከ መቀየር ድረስ ችግር ያለባቸውን ሕፃናት በአገር ውስጥ ለማከም በጣም እንደሚያስቸግርና አቅምም እንደሌለ፣ አብዛኛው የሕፃናት የኩላሊት ሕክምና ዘላቂ ችግር የሚያመጣ፣ ቶሎ ታውቆ ወዲያው ሕክምና ከተደረገለት ግን ሊድን የሚችል መሆኑን ከዶክተር ዳምጤ ማብራርያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የካቲት 6 ቀን 2003 ዓ.ም. የተጠናቀቀውና ወደ 30 የሚጠጉ የሕፃናት ክፍል የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና የዲፓርትመንቱ አባላት ተሳታፊ የሆኑበት ይህንኑ ሥልጠና በመተባበር ያዘጋጁት በእስራኤል የሚገኘው የቤንጐሪዮም ዩኒቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ስኩል ኦፍ ሜዲሰንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤት መሆናቸው ታውቋል፡፡


