አለ እንጂ ሞተ በሉ!
ለቱልቱላ ነፊው ሁሉ፡፡
አለ እንጂ ሞተ በሉ! ደግሞ ለዚህ ውሎ አዳሬ፡፡
ከተረኞች ሌት ቧግቼ ከቀነኞች ቀን ቆንጥሬ
ከተራማጅ ተራምጄ፤ ከሃዳሪው ደግሞ አድሬ
አለ እንጂ ሞተ በሉ፤ ደግሞ ለዚህ ውሎ አዳሬ
ተቅማጧ ባሯሯጠኝ፤ በለመጠጠኝ እባጯ፤
ድሪቶዋን በቀማመልኩ፤ በወረሰኝ እድፍ ቀጯ፤
ቁንጫዋን ባስባሁኝ፤ ደም እዤን ሁሉ ገብሬ፤
አድማሷ እያቅላላ፤ በጠዋት ጠልቃ ጀምበሬ፤
ቁጢት ቀልቡን ስቋጠረው፤ እያፈተለክ ክብሬ፤
ከሰው ተራ በወጣሁኝ፣ ዓይነ-ጥላዬን አስሬ፣
አያቴን ለነፃነቷ፣ አባቴን ለአንድነቷ፣ ደሜን ለክብሯ ገብሬ፣
ለባንዲራዋ ቀኝ እግሬን፣ ግራ እጄን በመድፍ አርፌ፣
ያለኝን ሁሉ ሰጥቻት፣ ለምፅዋት መንገድ ብወድቅም፣
እሷ ያው ናት እስከ ዛሬ፡፡
ውሽማዋ አስረግዟት፣ እንደጠፋ ጋለሞታ፣
መሬት ስትቆፍር በእንባዬ፣
ምነው ቢወርድ ከላዬ፡፡
እሷን ብሎ ደግሞ አስቀማጭ፣ እኔን ብሎ ደግሞ አፍቃሪ፣
እንኳን ለተራው ለእኔ፣ መች ሆነችው ለተፈሪ፡፡
ብቻ እሷ፣ ለኖረላት ኖራ አታውቅም፤ ካልተዳሯት ተብለጥልጦ፣
ቀሚሷ ሁሌ ተገልጦ፡፡
እሷን ብሎ ደግሞ አስቀማጭ፣ እኔን ብሎ ደግሞ አፍቃሪ፣
የቋራው ካሳን የፈታች፣ ከሱም በላይ ለሷ ኗሪ፡፡
አበው ምከሯት፣ በአበው ቃል፣ ትውጣ ከልቤ ጠራርጋ፡፡
ቧግቼ ብኖር ምናለ፣ የእሷ ነገር አንገብግቦኝ፣ በአፌ ከስንቱ ልዋጋ
እሷ እንደሁ፣ ያው ናት እስከዛሬ፣ እድፏ በደም ማይጠራ፣
ተራራዋ በያመቱ፣ አደይ ላዩ ሲጎመራ፣
ሰዋ ያው ነው የካቻምናው፣ አጓጉል ዘመን ቆጠራ፡፡
አደይ አበባዋ አይሞት ቅሉ፣ ሰማይ ሲቸር አቆጥቁጦ፣
ዘሪ ለዘር ሳያኖረው፣ በሐሩሯ ተሸንቁጦ፣
ከር ለዘር በየዓመቱ፣ ሜዳ አምባዋን ተራራዋን፣
በአበባው አንቆጥቁጦ፣
ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠባ፣ ወፍ ባልቀመሰ ውሃዋ፣
ሌሊት ተጠምቆ ከምንጯ፣ ሲመለስ ቆጦት ነዋሪዋ፣
እንቁጣጣሽ አባብሎ፣ ከደመራም ተቀጣጥሎ፣
እርጥበቱን ተቀጣጥሎ፣ ሆያ ሆዬ አባብሎ፣
ደባትር በፅጌ ማህሌት፣ ቀሳውስት ከመንበር ግርጌ፣
ሚያኖሩት ቢጫ አበባው፣
እሱ ይሻል አደይ ብቻ በየዓመቱ እየሞተ በየዓመቱ የሚነሳው፡፡
እሱ ይሻል አደያችን፣ በበጋው ወቅት የሚረግፈው
በዋዕዩ ግስሙን አጥቶ፣ በፀደይ ወቅት የሚፈካው፡፡
አጨዱኝ ቀጠፉኝ፣ ብሎ ቅሬታ የማያሰማው፣
እሱ ይሻል አደይ ብቻ፣ በፀደይዋ የሚፈካው፡፡
ስዋም፣ ከካቻምና አምና ዘንድሮ
ያው ነው እስከ ሰንኮፍ ገላው፣ ሽለፈት ክሩን አክሮ፣
በዛው በአምና ጥበቱ፣ በካቻምናው ውል ቀጠሮ፡፡
ቀይ ገብስማ ዶ ቆርጦ፣ በሬ በልቶ በተጋሳ፣
መለወጥ ለሱ ያ እኮ ነው፣ መሬቱን ይዞ ሲነሳ፡፡
ለወቅት አወቅ በረራማ፣ ወቅቱንማ መች ይስታል፣
ጥንባ ጥንት የለመደ፣ ጭልፊት ቁራ ወጥንብ አንሳ፡፡
ከነሱም አነስና እ፣ አበደ አሉኝ ደግሞ ዛሬ፣
ከተረኞች ሌት ቧግቼ፣ ከቀነኞች ቀን ቆንጥሬ፣
በመስተፋቅር ድግምቷ፣ ክረቱ ጠብቆብኝ ፍቅሬ፣
ምንዳቤዋ እየፀናብኝ፣ በምፅዋቷ ሠርክ አፍሬ፣
አበደማ እንዳትሉኝ፣ ደግሞ ለዚህ ውሎ አዳሬ፡፡
ባይሆን አለ ሞተ በሉ፣ ለጥሩንባ ነፊው ሁሉ!
አለ እንጂ ሞተ በሉ፣ ለቀባሪ ሰዋ ሁሉ፡፡
(ይስማዕክ ወርቁ፤ የቀንድ አውጣ ኑሮ፣ 2002 ዓ.ም. አዲስ አበባ)
***************************
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት
የገንዘብ ሚኒስቴር
ለበጀት ዋና መሥሪያ ቤት
አዲስ አበባ
ወይዘሮ ዘውዲቱ ለገሰ 1500 ብር ዋጋ የነበረው አሮጌ የኢትዮጵያ ባንክ ኖት ያገለግለኛል ብዬ ቆጥቤ አስቀምጬው ነበር፤ አሁን ዋጋ የለውም ስለተባልኩ ድህነት ላይ መውደቄ ነው ብለው ለግርማዊነታቸው ስላመለከቱ ባንክ ኖቱ ዋጋ እንደሌለው ከተነገራቸው በኋላ፣ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት መልካም ፈቃድና ቸርነት 500 የኢትዮጵያ ብር ለዳረጎት ከተመደበው በጀት እንዲሰጣቸው ስለተፈቀደ ይኸው ሒሳብ ለወይዘሮ ዘውዲቱ ለገሰ ተከፍሎ መደበኛውን ማዘዣ ለክብርት ሚኒስቴር እንድትቀበሉ ይሁን፡፡
ግልባጭ
ለኢ.ን.ነ.መንግሥት
የጽሕፈት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ
ቡልቻ ደመቅሣ
የበጀት ጥናት ዋና ዳይሬክተር
************************
የድረ ገጹ ሱሰኛ
‹‹ከጥቂት ዓመታት በፊት ቤተሰባችን መኖሪያ ቤት ቀይሮ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት መቀጠል ፈልጌ ስለነበር ፎቶ የሚቀመጥበት ድረ ገጽ አባል እንደሆኑ ጋበዙኝ፡፡ ግንኙነታችን እንዳይቋረጥ የሚረዳ ጥሩ ዘዴ ይመስል ነበር፡፡ ‹የምገናኘው ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር ሳይሆን ከማውቃቸው ሰዎች ጋር ብቻ ስለሆነ ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል?› ብዬ አሰብኩ፡፡
‹‹መጀመሪያ ላይ ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር፡፡ በሳምንት አንዴ ድረ ገጹ ከፍቼ የጓደኞቼን ፎቶና አይና አስተያየት እጽፋለሁ፤ ከዚያም የራሴን ፎቶ አስገባና የጻፉልኝን አስተያየት አነባለሁ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን ሱስ ሆነብኝ፡፡ ለእኔ ባይታወቀኝም እንኳ ረጅም ሰዓት ድረ ገጹ ላይ አሳልፍ ነበር፡፡ የጓደኞቼ ጓደኞች ከድረ ገጹ እንደማልጠፋ ሲረዱ ጓደኛቸው እንደሆን ግብዣ ያቀርቡልኝ ጀመር፡፡ እንደምታውቁት፣ አንድ ጓደኛችሁ ‹ይህ ሰው አሪፍ ነው› ብሎ ሲነግራችሁ እናንተም ግለሰቡን ጓደኛ ታደርጉታላችሁ፡፡ ምንም ሳይታወቃችሁ 50 የኢንተርኔት ጓደኞች ይኖራችኋል፡፡
‹‹ብዙም ሳይቆይ ሐሳቤ ሁሉ ድረ ገጹን ስለ መጠቀም ብቻ ሆነ፡፡ ድረ ገጹን እየተጠቀምኩም እንኳ ሌላ ጊዜ መጥቼ የገባውን አዲስ ነገር የማየውና አዳዲስ ፎቶዎቼን የማስቀምጠው መቼ እንደሆነ ማሰብ እጀምራለሁ፡፡ አንድ ጊዜ የሚጻፉልኝን ሐሳቦች ሳነብ ከዚያ ደግሞ ቪዲዮ ሳስገባ ምንም ሳይታወቀኝ ሰዓቱ ይበራል፡፡
‹‹በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት ተኩል አለፈ፤ በመጨረሻም ሱስ እንደያዘኝ ተገነዘብኩ፡፡ አሁን ግን በኢንተርኔት አጠቃቀሜ ላይ ጥብቅ ገደብ ያበጀሁ ሲሆን፣ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሥነ ምግባር አቋም ካላቸው ሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቼ ጓደኝነት በመመሥረት ላይ አተኩራለሁ፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃ የወሰድኩት ለምን እንደሆነ አይገባቸውም፤ እኔ ግን ከስህተቴ ተምሬአለሁ፡፡›› ኤለን፣ 18
(ንቁ! ፤ ጥር 2011)
*******************
‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እና የካቲት 12 1929
የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 1929 ነው፡፡
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡
‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፉ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይ[ሽ]ር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡
(ባሕሩ ዘውዴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966፤ 1989)
*******************
ገራገር
አሳዎች ምስክር እንዳይሆኑ በመፍራት ተገደሉ
ቺካጎ አርሊንግተን ሀይት በተባለ ቦታ አንድን ቤት የዘረፈ የአሥራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ዝርፊያውን በመፈጸሙ ምንም ዓይነት ምስክር እንዳይኖር በማሰብ እንደ ጌጥ በቤት ውስጥ የነበሩትን ሦስት ወርቃማ ትንንሽ አሳዎች መግደሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በዝርፊያ የተጠረጠሩት ታዳጊዎች ሦስት ቢሆኑም፣ ከመካከላቸው አንደኛው ዝርፊያውን ፈጽመው ከቤቱ ሊወጡ ሲሉ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ምንም ዓይነት ምስክር መተው እንደሌለባቸው ሌሎቹን ለማሳመን አሳዎቹን እንደገደላቸው ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ታዳጊዎቹ የሰረቁት ቪዲዮ ጌም፣ ባዶ ማጫወቻ፣ ሠላሳ የቪዲዮ ጌሞችና 30 ቪዲዮዎችን እንዲሁም ጌጣጌጦችን መሆኑ ሊታወቅ ችሏል፡፡
ታዳጊው ወርቃማ አሳዎቹን የገደላቸውን በውኃ ገንዳቸው ውስጥ የሚያቃጥል ቅመማ ቅመም በመጨመር ነው፡፡ ከሦስቱ ተከሳሾች መካከል አሳዎቹን የገደለው ታዳጊ በዝርፊያና እንስሳትን በማሰቃየት፣ ሁለቱ ደግሞ በዝርፊያ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡


