ነገሮች እንኳን በዓለም፣ በአካባቢያችንም ደረጃ እየተወሳሰቡና እየተቆላለፉ ባሉበት ሁኔታ ይቅርና፤ በዓለምም ሆነ በአካባቢ፣ በአገርም ደረጃ ሰላምና መረጋጋት፣ ዕድገትና ሀብት እውን እየሆነ ቢሔድም፤ ዕድገቱን፣ ሰላምና መረጋጋቱን እንዴት እንጠቀምበት? ብሎ መፍትሔ ለማስቀመጥ የግድ ቲንክ ታንክ ያስፈልጋል፡፡
ማለትም ሙያውና ተቆርቋሪነቱ ያላቸው ዜጐች ሁኔታውን እያጠኑ ለመንግሥት ሐሳብ የሚሰጡበት የምክክር ቡድንና መድረክ ያስፈልጋል፡፡
መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ግን ያለንበት የዓለምም፣ የአካባቢም፣ የአገር ውስጥም ሁኔታ ከባድ የኢኮኖሚና የጸጥታ ፈተና ያለበት እንጂ፣ የሰላምና መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና የሰፈነበት አይደለም፡፡ ቀውሱ ጐልቶ በታየበት ዓለማዊ ሁኔታ ውስጥ በመገኘታችን፣ የቲንክ ታንክ አስፈላጊነትን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ፣ ከዋጋ መናር ጋር በተያያዘ፣ ከዓለም ኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘና ሌሎች ነገሮችም በተጫጫኑበት ሁኔታ ምክንያት፣ የንግድና ኢንዱስትሪያችን ሁኔታ በሚገባ መመርመር፣ መገምገምና መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባናል፡፡
የአንዳንድ ምርቶች የዋጋ ጣርያ በመንግሥት ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ዕቃ ከገበያም ጠፍቷል፡፡ በማኒፋክቸሪንግ ላይ እናተኩር ተብሏል፡፡ ነገር ግን በማኑፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ዙርያ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር አለ፡፡ ቀን ተዘግተው ውለው ማታ ብቻ አምርቱ የተባለበት ሁኔታም አለ፡፡ የባንክ ብድር የቆመበት ሁኔታ አለ፡፡ የሚያበድሩ ካሉም ጣርያው እጅግ አነስተኛ ነው የሚሉ ባንኮችም አሉ፡፡ የኮንስትራክሽን ማቴሪያል ውድ ሆኖ ግንባታዎች የተስተጓጐሉበት ሁኔታም አለ፡፡
እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሠቱ ጉዳዩን የሚከታተሉ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ቢኖሩም፣ ከመንግሥት ጋር እየተመካከረ ሐሳብ የሚሰጥና መፍትሔ የሚጠቁም የንግድና ኢኮኖሚ የቲንክ ታንክ ቡድንም በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ የሚጠቀም እንጂ የሚጐዳ ወገን አይኖርምና፡፡
የዓለማችን የኢኮኖሚ ሁኔታንም ስናይ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮች ያለውን ሁኔታም ስናይ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሁለት አማራጮች የያዘ ሁኔታም እየተከሠተ ነው፡፡
ባንድ በኩል ከዴሞክራሲ ርቆ ለዘመናት የቆየው የዓረብ አገር ሕዝብ ወደ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲገባ ዕድል የሚሰጥ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የሕዝብ ጥያቄም ይኸው ነውና፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ቢጮህና ቢሰለፍም የታሰበው ዓላማ ግብ ሳይመታ ወደ አክራሪነት ተገብቶ እንኳን መሻሻል ወደ ኋላ መጓተትም ሊከሠትበት ይችላል፡፡
ወደ ዴሞክራሲ ከተገባ እሰየው ያሰኛል፡፡ ወደ አክራሪነት ከተገባ ደግሞ መርዶ ይሆናል፡፡
በእንደዚህ ዓይነት አካባቢ የምትገኘዋ ኢትዮጵያ የሚኖራት አጀንዳ፣ የራስዋን ፍትሕና ዴሞክራሲ ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭ ሊመጣባት የሚችል የአክራሪነት ጫና መከላከልም ሊሆን ይችላል፡፡ አካባቢው ዴሞክራሲ ቢሰፍንበት ለኢትዮጵያም ትልቅ ድጋፍ ይሆናል፡፡ አክራሪነት ከሰፈነበት ደግሞ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል፡፡ ወሳኙ የራሳችን የኢትዮጵያ ሥራ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ የአካባቢ ጫናም ችላ የሚባል አይሆንም፡፡
ይህ ሁኔታ ከወዲሁ ለመመርመርና መፍትሔ ለማስቀመጥም፣ እውቀቱና ልምዱ፣ አገራዊ ተቆርቋሪነትም ካላቸው ወገኖች ጋር ሆኖ መንግሥት መመካከር አለበት፡፡
ማለትም፣ በፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ዙርያም ቲንክ ታንክ ቡድንና መድረክ ማዘጋጀት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ቲንክ ታንክ የሚያስፈልግበትን ሁኔታ ከሁለት ዐበይት ምክንያቶች አንፃር መጥቀስ ይቻላል፡፡
አንደኛው ዐቢይ ምክንያት፣ ያለው ሁኔታ ከባድና የሚያስፈልገው እውቀትና ልምድ ጥልቅና ሰፊ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት ካለው አቅም ጋር የወገኖች አቅምና ጉልበት ሲጨመርበት ችግሮችን በሚገባ ለማየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየተከሠተ ያለው አንድ በሽታ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡ በሽታውም መንግሥትን በትክክለኛ መረጃ ከመመገብና ያለውን ችግርና እንቅፋት በግልጽና በተቆርቋሪነት ከማሳወቅ ይልቅ፣ ብሶትንና ችግርን እየደባበቁ ለመንግሥት አበረታች፣ ውጤታማ፣ ስኬታማ እያሉ ብቻ መደለል ተለምዷዊ ሆኖ መምጣቱ ነው፡፡ በውሸትና በተሳሳተ መረጃ መንግሥትን ማሳሳቱና ማደናገሩ በተዛመተበት ሁኔታ ለጥቅም፣ ለሹመትና ለገንዘብም ሳይታለል ሐቁን ለመንግሥት የሚነግር ቲንክ ታንክ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
ሲጠቃለልም፣ ቲንክ ታንክ፣ ተጨማሪ እውቀትና አቅም በማግኘት ሳይፈራና ሳይሰጋ ለመንግሥት እቅጩንና ሐቁን የመናገር አቅሙን ማግኘት በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡
ያስፈልገዋል ስንልም፣ እያጋጠሙ ያሉት ችግሮች ጊዜና ፋታ አይሰጡምና አሁኑኑ ይሁን፡፡ ከእኔ በላይ ሐሳብ የሚያውቅ የለም ብሎ ማዳመጥን ከመግታት፣ አዳምጦ የማይጠቅመውን መጣሉ ይበጃል፡፡
ቲንክ ታንክ
አሁንም
ቲንክ ታንክ!!


