Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በዚህ መልኩ ይስተካከል

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ዘሪሁን ከበደ የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን በማስመልከት ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ማብራርያ በእሁድ የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ጋዜጣችሁ ታትሞ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ግን ሚኒስትር ዴኤታው ከሰጡት መረጃ አንጻር አንዳንድ ሊታረሙ የሚገባቸውን ነጥቦች ለአንባቢው ኅብረተሰብ ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት በማሰብ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

1/ ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሕጋዊ መንገድ የሚሄዱ ዜጎችን እንደሚመዘግብና ማንኛውንም ዓይነት ክትትል (በኤጀንሲዎቹ ላይ) እንደሚያደርግ የገለጹት ዶ/ር ዘሪሁን፣ ከዕውቀት ማነስ፣ ሕጉን ካለመገንዘብና ከሌላ ነገርም የተነሳ በሙሉ አገልግሎት ተሰጥቶቸዋል ማለት እንደማይቻል ጠቁመዋል፤›› በማለት የተነሳው ሐሳብ የሕግ ዕውቀት ማነስና ሕጉን ያለመገንዘብ ችግር ብሎም አስፈላጊውን አገልግሎት ያለመስጠት ጉድለት የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን በሚመለከት የተሰጠ ማብራርያና ለዚህም የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለኤጀንሲዎች እንደሚሰጥ መታሰቡን እንጂ የመሥሪያ ቤታችን አገልግሎት አሰጣጥ ችግር በተመለከተ ያለመሆኑ ግንዛቤ ተይዞ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡

2/ ‹‹የሠራተኛን ጉዳይ የሚከታተል (ሌበር አታሼ) ለማቋቋም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ሲጠይቁ ‹‹ኤምባሲዎች ይበቃሉ›› በመባሉ ወደፊት በኤምባሲዎቹ በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል፤›› በሚል የተነሳው፣ በዋናነት ይህንን ተግባር ሊያከናውን የሚችል አደረጃጀት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በኤምባሲዎችና ሚስዮኖች ውስጥ በመደራጀቱና ይኼንን የሚፈጽም ባለሙያ ስለመመደቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያገኘን ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለሥራው መሳካት እንቅፋት የሚሆንብን ችግር ያለመኖሩ የተገለጸ እንጂ ሌበር አታሼ አያስፈልግም የሚል መረጃ አልሰጡም፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ዙርያ የሚስተዋሉ ችግሮች እልባት እንዲያገኙ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ጋር የባለቤትነት ድርሻ አንስቶ እየሠራ መገኘቱ ታውቆ መረጃው በዚህ መልኩ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡

3/ ‹‹ከውጭ ጉዳይና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመሥራት ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁመንና ረቂቂ ደንብ አዘጋጅተን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ልከናል፤›› ተብሎ የተገለጸው፣ አንደኛ የብሔራዊ ኮሚቴው አካላት ሁለቱ የተገለጹት ብቻ ያለመሆናቸው፤ ሁለተኛ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶና በባለድርሻ አካላት ተመክሮበት አስፈላጊውን ግብአት በማካተት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመላክ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ኮሚቴው ያልተቋቋመና የኮሚቴው አካላትም ሁለት ብቻ ያለመሆናቸው ታውቆ በዚህ መልኩ ተስተካክሎ በጋዜጣችሁ እንዲወጣልን እየጠየቅን ሪፖርተር ጋዜጣም በዚሁ የመረጃ ቅብብል ውስጥ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡
(የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር)

*       *       *     *

መዲናችን በትክክል ትጠራ
ብዙ ጊዜ እያስገረመኝ፣ ከአሁን አሁን ይታረማል እያልኩ ሳስብ የቆየሁበት፣ ከብዙሃን አገር ውስጥና ውጭ አገር ካሉ ምሁራን ጋርም ሲያነጋግረን የቆየ ነገር ስላለ ነው ወደ ሪፖርተር ላመለክት ያስገደደኝ፡፡ ይኸውም በውጭው ዓለም የአገራችን መዲና አዲስ አበባ (Addis Abeba) በትክክል መጠራቷ ቀርቶ አዲስ አባባ (Addis Ababa) ተብላ ነው የምትታወቀው፡፡ ጥቂቱን ለመጥራት በዓለም ታላላቅ የዜና ምንጮች በቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጄዚራና በልዩ ልዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች የመዲናዋ ስም በስህተት መጻፉን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ አጠራር በፍጹም ትክክል አለመሆኑን ለማንም ግልጽ ነው፡፡

የዋና ከተማችን ትክክለኛው ትርጉም አዲስ አበባ - ያበበች ከተማ ማለት ሲሆን፣ በባዕድ ቋንቋ አጠራር ግን አዲስ አበባ ማለት አዲስ አባት (የእንጀራ አባት) እንደማለት ነው፡፡ አንድ የውጭ ተወላጅ አሜሪካዊም ይሁን አውሮፓዊ ተሳስቶ የጻፈ እንደሆነ እኛም የሱን ፈር ተከትለን፣ አተረጓጎሙ ትክክል አለመሆኑን እያወቅን ፈረንጅ የተናገረውን እንደትክክል እየወሰድን መከተል የለብንም፡፡ የቃላት አባባልና አጣጣል ዘዴው ትክክል አለመሆኑን አዲስ አበባ (Addis Abeba) እንጂ አዲስ አባባ (Addis Ababa) አለመሆኑን ማረምና ማስተካከል የአገሪቱ ግዴታ ይመስለኛል፡፡ ካልተሳሳትኩ ይህን ማስተካከል የሚገባው የከንቲባው መሥሪያ ቤት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለማስተካከል ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሌሎች አገሮችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ከአፍሪቃ በ1975 ዳሆሜን - ቤኒን በማለት፣ በ1990 ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃን - ናሚብያ በማለት፣ በ1997 ዛዬርን - ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ በማለት፣ ከእስያ 1989 በርማን - ማይንማር በማለት፣ ከተሞችን ስም በመለወጥ ደግሞ በ1995 የህንዱን ቦምቤይን - ሙምባይ በማለት፣ ከሩቅ ምሥራቅ በ1975 ሳይጎንን - ሆቺሚኒ ሲቲ በማለት፣ ወዘተ ሊጠቀስ ይቻላል፡፡ የእኛ አገር መዲና ግን ለውጡ ስሙ ሳይሆን አንድ ፊደል ብቻ ማስተካከል ነው፣ ይኸውም የመሐለኛውን ፊደል ‘ባ’ን (አባባ)  ወደ ‘በ’  መለወጥ ብቻ ነው፡፡ ያ አንድ ፊደል ግን ከስሙ ጋር ምንም የማያገናኝ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ለዓለም ሕዝብ ትክክለኛውን ስም (ፊደል) ለማስተካከል ኮምፒተሩ ከአንድ ሴኮንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይለውጠዋል፡፡

ስለዚህ በእናንተ በተወዳጁ ጋዜጣችሁ በኩል የሚመለከተው መሥሪያ ቤት እንዲያስተካክለው እንድታሳልፉልኝና እንድትከታተሉልኝ በትህትና እጠቁማለሁ፡፡
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር፣
(ጌታቸው ተድላ (ፒ.ኤች.ዲ))


*       *       *     *
ለአገር ልማት ነው የቆምነው
እኛ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማስተዋወቅና ግንኙነት የሥራ ሒደት ባልደረቦች የባንኩ ኮሚኒኬተርም ገጽታ ገንቢም እንደመሆናችን በጋዜጣችሁ ላይ ለምታነሷቸው ጉዳዮችና ዜና ዘገባዎች አድናቆታችን ከፍ ያለ ነው፡፡

በዚህ እምነትም በ16/06/03 የወጣውን ቅፅ 16 ቁጥር 24/1129 ሳምንታዊ ጋዜጣችሁን ስናነብ ስለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአንድ ግለሰብ፤ ይድረስ ለሪፖርተር በሚለው የአንባቢዎች አስተያየት መስጫ አምድ፤

‹‹ይሁንና የመንግሥት ባንኮች በተለይም ልማት ባንክ በመንገዳገድ ላይ የነበሩና ብዙ ሠራተኛ የሚይዙ ፋብሪካዎችን ሠራተኛ አስወጥተው እያሸጉ ለመሸጥ በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ፤›› የሚል የተዛባ አስተያየት መስጠታቸውን ተመልክተናል፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአገር ልማት ፋና ወጊ የሆኑና በልማቱ ዘርፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፕሮጀክቶች ፋይናንስ በማድረግ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው፡፡ በመሆኑም አገሪቱ የነደፈችውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቅድሚያ ረድፍ  ተሰላፊ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ባንኩ ቅድሚያ ትኩረት በሚሰጣቸው በእርሻ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በመፈብረኪያ ኢንዱስትሪና በማዕድን ልማት ዘርፍ የሚቋቋሙ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድግ ለውጤት የሚያበቃና በመቶ ሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠርና ለአገር ልማት የውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚሠራ ባንክ ነው፡፡

ባንኩ አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ ያልሆኑ ፕሮጀክቶችን ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ ለሦስተኛ ወገን እንዲዛወሩ የሚያደርገው፣ አስተያየት ሰጪው በገለጹበት ግንዛቤ ሠራተኛን ለመበተን ሳይሆን፣ ፕሮጀክቶቹን ሊያንቀሳቅስና የተሻለ የሥራ ዕድል ፈጠሮ የተቋቋመለትን የልማት ዓላማ ለማስቀጠልና ከግብ ለማድረስ ሲባል እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
(የኢትዮጵያ ልማት ባንክ)