Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ምርጫ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በምሕረት አስቻለው

አማረ ወርቁ ፣በትምህርት ደረጃ፣ በገንዘብና በሕይወት ልምድ ከሱ ከፍ የምትል ሴት ልጅ ምርጫው አይደለችም፡፡

የምትመጣጠነው ከምትሆንም በሁሉም ረገድ የሚበልጣት ሴትን ካልተጓደነ በቀር ደስታን የሚፈጥር የፍቅር ግንኙነት ወይም ትዳር መመሥረት እንደሚችል አያምንም፡፡ በአካውንቲንግ ቢኤ ዲግሪ ያው ሲሆን፣ ለሰባት ዓመታት በሥራ ዓለም ቆይቷል፡፡ የፍቅር ጓደኛም በመፈለግ ላይ እንደሚገኝ አጫውቶናል፡፡

‹‹በማኅበረሰባችን የወንዶች ሚና ሰጪነት ነው፡፡ ወደ እኔም ስንመጣ ያለው ነገር ይኸው ነው፡፡ በመንከባከብ፣ ስጦታዎች በመስጠት፣ ዕውቀትና የሕይወት ተሞክሮዬን በማካፈል የሰጭነት ሚናዬን መጫወት አለብኝ፡፡ ሴቷ በገንዘብ፣ በትምህርት ደረጃ እንዲሁም በሕይወት ተሞክሮ የምትበልጠኝ ከሆነ ይህን አለኝታ፣ ደጀንነቴን፣ የሰጭነት ሚናዬን አጣለሁኝ፡፡ በተለይም በገንዘብ መብለጥ የግድ ነው፡፡ በእውቀትም ቢሆን የማላካፍላት፣ የማላስቃትና የማላጫውታት ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ረገድ የምበልጣትን ሴት ነው የምመርጠው፡፡››

ወንዶች ከሴቶች የተሻለ ገንዘብ ቢኖራቸው እንኳ በአስተሳሰብ ደረጃ (በዕውቀት) ዝቅ የሚሉ ከሆነ ገንዘብ ሊገዛው በሚችል ቁሳቁስ ብቻ ሴቶችን ማርካት ስለማይችል በእውቀት ወይም በአስተሳሰብ ደረጃ መበለጥም ለወንዶች አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚሆን ያምናል፡፡ በተቃራኒው ገንዘብ ያለው ወንድና የተሻለ አስተሳሰብ ያላት ሴት በአንድ ላይ ቢሆኑ ገንዘቡን ውጤት ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንዲጠቀም አቅጣጫ ልታሳየው፤ አብሮነታቸውም የሰመረ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ቢታይም፣ ይህ የጥቂቶች አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡

‹‹የገንዘብ አቅሜ ከእሷ የተሻለ ሆኖ በተለያየ መልኩ በመንከባከብ ፍቅሬን መግለጽ ካልቻልኩ፣ የተሻለ እውቀትና አመለካከት እንዲያውም የሕይወት ተሞክሮ ኖሮኝ የማጋራት ነገር ከሌለ፣ በውሳኔ ላይም ምንም እንኳ መመካከር ቢኖር የማሳመንና የበላይ ድምፅ ያለኝ መሆን ካልቻልኩ የእኔ ናቸው የምላቸው የወንድ ሚናዎቼን አጣቸዋለሁ፡፡ ሥነ ልቦናዬም ይሰረቃል፤›› ብሎናል፡፡

እንደ አማረ አባባል፣ በሌላ በኩል በሁሉ ረገድ ከምትበልጠው ሴት ጋር ግንኙነት መመሥረት ከሥነ ልቦናዊ ጫና በተጨማሪ ወንዱን ለማኅበራዊ ጫናም ያጋልጠዋል፡፡ ‹ገንዘቧን አይቶ ገባ፤› የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ አስተያየቶች ማኅበረሰቡ ሊሰነዝር ይችላል፡፡ እንዲሁ የምትጎተች አይነት አድርጎም ሊያስብሽ ይችላል፡፡››

ቀደም ሲል የነበረ የፍቅር ግንኙነቱ ምን ይመስል እንደነበር አማረን ጠይቀነዋል፡፡ ፍቅረኛውን በሁሉም ረገድ ይበልጣት የነበረ ቢሆንም ይህ ነው በሚባል መልኩ በገንዘብ እንዳልተንከባከባት፤ ተለያይተው ዛሬ ላይ እሷ ትዳር መሥርታ እንደምትኖር ነግሮናል፡፡  የወንዶች በሁሉም ረገድ የሚበልጧትን ሴት የመፈለግ ስሜት ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ እንደሆነ፤ ሊገድቡት ወይም ሊተዉት የሚከብድ ኃይለኛ ስሜት እንደሆነም ያምናል፡፡

ወ/ሮ ሕይወት በየነ ከሠላሳ አምስት ዓመታት በላይ አስተምረዋል፡፡ አሁንም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የሁለት ልጆች እናት እና የሁለት ሕፃናት አያት ናቸው፡፡ ‹‹እዚህ የደረስኩት እየወለድኩ፣ እየተማርኩ፣ እያስተማርኩ ነው፡፡ ኑሮንም በደንብ አጣጥሜ መጥቻለሁ፡፡ የምደርስበትን ባላውቅም የማይደክመኝ ልቤ ዝም ብሎ የሚገሰግስ  ዓይነት ሰው ነኝ፡፡ ከተራ የአንደኛ ደረጃ መምህርነት የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እስከመሆን ደርሻለሁ፡፡

ማኅበረሰቡ በሁሉም ረገድ ወንድ የበላይ እንደሆነ የሚያስቀምጠው ‹‹ምንም ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ›› የሚለው ብሂል በተለያየ መልኩ እንደሚንፀባረቅ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉትም፣ ትናንትም ዛሬም ለትዳርም ይሁን ለግንኙነት መራጭ ወንድ ሲሆን፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘር ሐረጓ፣ በቤተሰቧ ሀብትና ዝና ሴቷ ትመረጥ ነበር፡፡ የዚህች አይነቷ ሴት ሳትወለድ በማህፀን ውስጥም ‹‹ልጅህን ለልጄ›› ተብሎ ትመረጣለች፡፡ ሀብት፣ ታዋቂነት ዘርና አጥንት የሚተኮርባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ትምህርት ሲስፋፋና ሴቶች ወደ ትምህርት መሔድ ሲጀምሩ ደግሞ ትምህርት ቤት መሔድ ለሴቶች እንደ መባለግ መቆጠር ጀመረ፡፡ የተማረች ጥሩ የቤት አያያዝ አላት ብሎ ማሰብ ሲጀመር ደግሞ፣ የተማረች ሴት መፈለግ ጀመረች፡፡ ግን ደረጃው ዝቅ ያለ ትምህርት መሆን ነበረበት፡፡ ከዚያ ከፍ ያሉና ወንድን የተስተካከሉ ሳያገቡና ሳይወልዱ ቀርተዋል፡፡

ከሥነ ልቦና አንፃር በማኅበረሰባችን ሴትም፣ ወንድ ልጅም እናትና አባታቸውን እያዩ እንደሚያድጉ፤ ሲያድጉና ለትዳር ሲበቁም ወንዱ አባቱ ያደርግ የነበረውን ማድረግ ሲፈልግ፣ ሴቷም እናቷ የሆነችውን ለመሆን ሲጥሩ ይታያል፡፡ ወ/ሮ ሕይወት ‹‹የተማረች ሴት ግን እናቷ ተጎሳቁላ ተጨቁና ከነበረ ያን በራሷ ላይ ልትፈቅድ አትችልም፡፡ ወንዱ ደግሞ እንደ አባቱ ተመቻችቶና ተደላድሎ የበላይ ሆኖ መኖርን ይፈልጋል፡፡ እዚህ ጋ ግጭት ይመጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወንዱ የበላይነትን ሲፈልግ ሴቷ መብለጥን እንኳ ባትፈልግ እኩልነትን ትፈልጋለች፤›› ብለዋል፡፡

እሳቸው ትዳር መሥርተው ያለፉበት ዘመን ከኋላ የቀረ ቢሆንም ዛሬ በወንዶች የሴቶች ምርጫ ላይ ብዙ የተለወጠ ነገር አለ ብለው አያስቡም፡፡ ስለዚህ የትምህርት ደረጃቸው ከፍተኛና የሥራ ሁኔታቸውም ደህና የሆነ፤ ነገር ግን ያላገቡ ሴቶች ሲያጋጥሟቸው ቶሎ እንዲያገቡ፣ ካልሆነም እንዲወልዱ ይመክራሉ፡፡ የወንዶች በሁሉም ረገድ የበላይ መሆን መፈለግና ከነሱ ዝቅ የምትል ሴትን መምረጥ አንዳንዶች ተፈጥሯዊ ሌሎች ማኅበራዊ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል በተለየ መልኩ መበለጥ ብዙም ጥያቄ እንደማይሆንባቸው የሚናገሩ ወንዶች መኖራቸውን ለወ/ሮ ሕይወት ስንገለጽላቸው፣ ‹‹ነገሩ ከአንጀት ወይስ ከአንገት?›› በማለት እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ወንዶች በተጨባጭ የሚሉትን አያደርጉም የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ከዓመታት በፊት ትዳራቸውን እንዳፈረሱ ነገሩን፡፡ ለምን? ብለናቸዋል፡፡ ባለቤታቸው በነገሮች የሚደሰቱና የሚረኩ አይነት ሰው በመሆናቸው፣ እሳቸው ደግሞ በማንኛውም ዓይነት ስኬት የሚደሰቱ እንጂ የሚረኩና በቃኝ የማይሉ አይነት በመሆናቸው ለመለያየት መወሰናቸውን፤ ከዚያ በኋላ ትዳር ሞክረው እንደማያውቁ አጫውተውናል፡፡

አሜሪካዊቷ ዶ/ር ካትሪን ሲምኪንስ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለበጎ አድራጎት አገልግሎት ነው፡፡ ዕድሜያቸው በስድሳዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ትዳር አልመሠረቱም፡፡ ልጆችም አላፈሩም፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚያቀርቡት በወቅቱ እንደሳቸው የትምህርት ደረጃ ያለው ወንድ ባለማግኘታቸው፣ የተለያዩ የሥራና የትምህርት ዕድሎች ስለነበሯቸው ለዚያ ቅድሚያ በመስጠታቸውና የትምህርት ደረጃቸው የወንዶች ምርጫ እንዳይሆኑ ስላደረጓቸው መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ሁለተኛ ዲግሪዬን ከዚያም ፒኤች ዲ ስል ሳላገባ ቀረሁ፡፡ የቀረብኳቸውም በትምህርት ደረጃዬና ይከፈለኝ በነበረው ገንዘብ ደስተኛ አልነበሩም፡፡››

ዛሬ ላይ ከወጣት ሴቶች እንዳደመጡት በተወሰነ መልኩም ቢሆን በማኅበረሰቡ የወንዶች የበላይነት (አባታዊነት) በመኖሩ የትምህርት ደረጃቸው ከፍ ያለ፣ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚያገኙ ሴቶች የወንዶች ምርጫ የማይሆኑበት ሁኔታ በአሜሪካም ይስተዋላል ‹‹ዋናው የጥንዶች ፍላጎትና በስሜት መግባባት ነው›› በማለት ያሰምሩበታል፡፡

ዮሴፍ አባይ፣ በአንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ የጥራት ተቆጣጣሪ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምንም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ አይደለም፡፡ የመጀመርያ ጓደኛው በትምህርትና በሥራ፣ በሕይወት ተሞክሮና በገንዘብ፣ በሌሎች ነገሮችም ከሱ የተሻለች ብትሆንም አንድም ቀን በመካከላቸው ችግር ፈጥሮ አያውቅም፡፡ የተለያት እሱ በወቅቱ ለሥራ ከሔደበት አገር ለመቆየት በመወሰኑ ነበር፡፡ ሳይሳኩ ቢቀሩም ሌሎች በሁለት የፍቅር ግንኙነቶች ውስጥም ነበር፡፡ ከሦስቱ ግንኙነቶች ሁለቱ ሴቶች ዲግሪ ያላቸውና ጥሩ ክፍያ የነበራቸው ናቸው፡፡

‹‹እኔ ዲፕሎማ እንኳ የለኝም፡፡ ነገር ግን ራሴን እንዳስተማረ ሰው እቆጥረዋለሁ፡፡ አነባለሁ፤ ራሴንም በመረጃ አዳብራለሁ፡፡ በዚህም ዛሬ ላለሁበት ደረጃ በቅቻለሁ፤›› የሚለው ዮሴፍ፣ ምንም እንኳ የቀድሞ ሴት ጓደኞቹ በገንዘብና በትምህርት ደረጃ ከሱ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም አንድም ቀን ያልተገባ ግንኙነት ውስጥ እንዳለ ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ሴት ልጅን ለመምረጥ እንደመስፈርት የሚያስቀምጠው ወይም የሚያተኩረው የሴቷ የመረዳት፣ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ከመመልከት ችሎታ ላይ ነው፡፡