Tuesday, May 21st

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የካፋ ቁሳዊ ቅርስ- በቦንጋ ሙዚየም

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

በአዲሱ ዘገየ

እንደጎብኚም እንደአጥኚም ሆነን ወደ ካፋ ( በቀድሞ አጠራሩ ከፋ ያልነው) ዞን ዘለቅን፤ ካፋ ዞን በደቡብ ሕዝቦች ብሔርና ብሔረሰቦች ክልል ያለ ዞን ሲሆን ዋና ከተማዋ ቦንጋ፣ የብሔረሰቡ ቋንቋ ካፊኖኖ ይሰኛል።

ይህ አካባቢ በዓለማችን የመጀመርያው የቡና መገኛ እንደሆነ ተመስክሯል (በጥናት የተረጋገጠ ታሪክ ሳይሆን ይቀራል?) የጫካ ቡና፣ ጥቅጥቅ ደን (ደኑን በግርማቸው የሚሞሉ አራዊትና እንስሳት መኖራቸውን ሳንዘነጋ)፣ ተፈጥሮአዊ ቃናቸውን እንደጠበቁ ያሉ ፏፏቴዎች ወዘተ. ኅብር ፈጥረው (harmony እንበለው) የሚኖሩበት “የታደለ” የሚባልለት አካባቢ ነው።

በቦንጋ ከተማ አፋፍ ላይ እየተገነባ ባለው ዘመናዊ የቡና ሙዚዬም ግቢ ዘለቅን፤ ሙዚዬሙ በአገሬው የቤት አሠራር (ኪነ ሕንጻ) ጥበብ የተከሸነ ባህላዊውን የቤት አሠራር ከዘመናዊ ግብዓቶች ጋር ያዋደደ “ወደፊት ለመሮጥ እንሂድ ወደኋላ” የሚለውን ስንኝና ገጣሚ የሚያስታውስ ነው። በመቃኞ መልክ [ከትልቁና አዲሱ ጋር ስትነጻጸር ማለት ነው] ወደምትገኘው ሙዚየም ገባን፤ ስንገባ አፍ የሚያስከፍቱ ታሪክን አሁንም የኋሊት የሚያስጉዙ ቁሳዊ ባህሎችን በየመልክ በየመልኮቻቸው ተሰድረው አገኘን። እንግዲህ ቁሳዊ ባህል ስንል ምንነቱን ለመግለጥ ትንሽ ማብራሪያ ማከል ያስፈልጋል የሁለት ቃላት ጥምር ውጤት ነው፤ “የቁስ”ና “የባህል” ሁለቱም ቃላት ሰፊ ብያኔን ይዘዋል። ባህል የሰው ልጆች /የእንስሳት፣ የአራዊት፣ የአእዋፋትና የነፍሳት እና የሌሎች ፍጥረታት ሊሆን ይችላል፣ ባህል በሰፊ ብያኔው የዘለለት ልማድ እንደሆነ ስለሚነገር/ ረቂቅ ኅሊናዊ ሀብት ነው። ባህሉ የሚገኝበትንና የሚከወንበትን ማኅበረሰብ የሕይወትም ቢሉ የሞት ፍልስፍና፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አመለካከቶችንና አተገባበሮችን ባንድ ላይ አካትቶ ስለሚይዝም  ርቀቱ በዚህ ይገለጣል። ይህ ረቂቁ ባህል አካልና ቅርጽ ይዞ (ግዘፍ ነስቶ) ከሚገለጥባቸው አያሌ  መከሠቻዎቹ መካከል አንዱ በቁስ ስም መቅረቡ ነው። ረቂቅ ነው የተባለለት ባህል በተጨባጭና በገሃድ፣ በዓይን በሚታዩና በእጅ በሚዳሰሱ ቁሶች አማካይነት ባህልን መግለጫና መገለጫው አድርጎ መቅረቡ ነው። ረቂቁ ባህል በቁሳቁሶች ትእምርትነት ገጸ ብዙ አመለካከቶችን እንዲወክል ሆኖ ይቀርባል።

“ሰው ኑሮውን ይመስላል”፣  “ሰው የአካባቢው ውጤት ነው” እና ሌሎች ተዛማጅ አባባሎች የሰውንና በአካባቢው ያሉ ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን (የአየር ጠባይንም መሰረት ያደረገ) ተጣጥሞ መኖር (harmony በመፍጠር) ምስክሮች የሚሆኑ አባባሎች ናቸው። ጎጀብ ወንዝን መዳረሻው አድርጎ የተመሠረተው የካፋ ዞን የቡና መገኛ ነው ብለናል፤ ለዚህም አሁንም ድረስ ግርማ ሞገሱን ጠብቆ የኖረ የጫካ ቡና፣ በአገር በቀል ዛፎችና እጽዋት የተሞላ ጥቅጥቅ ደን (ይህ ደን በዓለማቀፉ የቅርስ ጥበቃ ድርጅት በ ዩኔስኮ የክብር መዝገብ ለመመዝገብ በቅቷል)፣ አራዊትና እንስሳት (ይህ ማኅበረሰብ በእህትና በወንድምነት ከተጠቀሱ ተፈጥሮአዊ ሀብታት ጋር ተዋድዶ ማደጉ ዕድለኛ ሳያስብለው ይቀራል?) እና ተከባብሮ (ተባብሮም ቢሉ) ከትውልድ ትውልድ የዘለቀ ነው። የማኅበረሰቡ የቤት አሠራር፣ የአለባበስ ልማድ፣ በአካባቢው ያሉ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የጦር፣ የእርሻና የቤት አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሣሪያዎች በቁሳዊ ባህል ስም የሚጠሩ  ናቸው፡፡

የካፋ ማኅበረሰብ ከውጪ ለመጡለት ዘመናዊ ሊባሉ ለሚችሉ የእምነት ሥርዓቶች (ለምሳሌ፡- የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት እምነቶች) ሲያስተናግድና የማኅበሩ አባል ሲሆን ዱሮ የነበረውን የአገር በቀል የእምነት ልማድ ሙሉ በሙሉ በመተውና ለአዳዲሶቹ ሙሉ በሙሉ ራሱን በማስገዛት ሳይሆን፣ ከነበረው የእምነት ልማድ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድን (ማካሔድም ቢሉ) ሲመርጥ ይታያል።

እዚህ ላይ “ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም” ወይም “ለሁለት ጌቶች ሊገዛ የሚችል…” ወዘተ አባባሎችን ዋጋ የሚያሳጣ አተገባበርን እንመለከታለን፤ እኒህ ዘመናዊ እምነቶች ሊያደርሱ የሚችሉትን የእምነት ፍልስፍና ወረራን እንዳለ ሳይቀበሉ (ከፍልስፍናዊ አመለካከት ምስቅልቅሎች ከሚያደርሱትም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ጫናዎች ለማምለጥ) የተመረጠ አካሔድ ነው። ለዚህም አብነት አላሞ የተሰኘውን አገር በቀል የእምነት ሥርዓትና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነቶችን ጎን ለጎን ለማስኬድ የሞከሩበት የቆየ ልማድ ተጠቃሽ ነው። በአንድ ወገን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ ንዋየ ቅድሳትን በመግዛት ቤተ ክርስቲያንን ሲያቋቁሙ በሌላ ወገን ባህላዊውን የአላሞ ስርዓት ሲተገብሩ ይታያል።

ከቤት ውጪ ለመታያ የሚያገለግሉ ባህላዊ ቁሶች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ መልከ ብዙ ትርጓሜዎችን እንዲወክሉ ይደረጋሉ። በፈረስ ወይም በበቅሎ ላይ ለጋላቢው ምቾት  በሚል (በኮርቻ መልክ) የሚውሉ ግላሶች የተጠቃሚውን ግለሰብ ማህበረ ባህላዊ ደረጃዎችን የሚያመላክቱ ናቸው። የክብርና የሀብት መገለጫ ተምሳሌቶች ናቸው፤ የሴቶች ጌጣጌጦች፣ የመኖሪያ ቤቶች አሠራርና የቤተሰቡ አባላትና ከብቶችም በቤት ውስጥ በሚሰጣቸው ቦታ ደረጃዎችን ወሰን ያደረጉ ናቸው። እያንዳንዱ ባህላዊ ቁስ ከአገልግሎቱ ባሻገር አንድና ከአንድ በላይ ትእምርታዊ ይዘትን ያስተላልፋሉ። ከማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ውጣውረዶች ጋር የሚገናኙ ልዩ ልዩ መሣርያዎች ለአንድ ጉዳይ ብቻ በሚል አይፈጠሩም፤ ባንድ ድንጋይ ሁለትና ከዚያ በላይ ወፎችን ማግኘት እንዲቻል ታስበው ይዘጋጃሉ እንጂ።

መከዳ ወይም ትራስ በሚል ስያሜ የምንጠራው ቁስ በካፋ ማኅበረሰብ ጣመንን ከማራገፍና ከጎን ወይም ጭንቅላት መደገፊያነቱ ባለፈ  በዕለታዊው ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ/ውስጥ አንዳች መልዕክትን ያስተላልፋል። ትራሶች በተለያዩ መጠንና ቅርጾች እንዲሁም ዲዛይኖች ይዘጋጃሉ፤ ለስላሳ ሰንበሌጥ በየቀለማቱ ከተዘጋጁ በኋላ በውስጣቸውም ላባዎችንና ወይም የተለያዩ የሳር አይነቶችን ይይዛሉ፡፡ (ዘመናዊውን የላባ ትራስ ያስገኘው ይሄ የአገር በቀል ጥበብ መሆኑን እንገምት)ከመደገፊያነት ባለፈ በግድግዳ ላይ ተንጠልጥለው ቤትን ማስጌጥ እንዲችሉ ሆነው የተሠሩ ናቸው። የትራሱ ጠርዝ/ክፈፍ አልፎ አልፎ በባለቀለማት ጨርቆች አልፎ አልፎም በራሱ በተሠሩበት ሰንበሌጥ ይለጎማሉ።  ትራሶቹ በየመጠኖቻቸው ልዩነት የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶችም በምሽት መኝታ ጊዜ በወንድና ሴቶች መካከል ያሉ ግንኙነቶች ፍላጎትን (በተለይም የሴቷን) መሠረት ያደረጉ ናቸው። ሴቷ ከትዳር አጋሯ ጋር የምታሳልፈው ሌሊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዳለውና እንደሌለው (ዝግጁ መሆን አለመሆኗንም ቢሉ) መልእክት ማስተላለፊያዋ አድርጋ ትጠቀምበታለች። በዚህም የታቀደና የታሰበ ወሲባዊ ግንኙነት እንጂ እንዲሁ በነሲብ በጊዜያዊ ስሜት በመነሣሣት፣ በመጠጥ በመገፋፋትም ቢሆን ወሲብ እንደማይፈጸም በትራሶች አማካይነት መግባባት ላይ ይደረሳል።ሴቷ ለወንዱ “ዛሬ በኔና ባንተ መካከል ፈቃደ ሥጋ የለም” ለማለት በመኝታቸው ላይ በመጠን አነስ ያለውን ትራስ በማስቀመጥ ስትገልጽ፣ በአንጻሩ ፈቃደኛ መሆኗን ደግሞ ሁለቱንም በአንድ ላይ ሊይዝ የሚችለውን ረዥም ትራስ ስሜትን በሚቀሰቅሱ፣ በሚያውዱ መዓዛማ ንጥረ ነገሮች አሻሽታ/ነክራ በማቅረብ ፈቃዷን ትገልጻለች።ይህም ባህሉ ለሴቷ የሰጣትን የውሳኔ ሰጪነት ኃይልና የከበሬታ ቦታ የሚያመለክት ሲሆን   (በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ጠለፋና አስገድዶ መድፈርን የመሳሰሉ ልማዶች ቦታ እንዳልተሰጣቸው ያመላክታል) አንድም ዴሞክራሲያዊው የራስን እድል በራስ የመወሰን ሥልጣን በሴቶች እጅም ያለ መሆኑን ያመለክታል። ዘመናዊነትን አንድ በሉልኝ።

በካፋ ባህል፣ ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ (ልጆችን ማሳደግና፣ ምግብ ማብሰል ወዘተ.) ሲታሰብ ጉልበትንና ጊዜን ሊቆጥቡ የሚችሉ መሣርያዎች ይቀርብላቸዋል፤ ከሸክላ አፈር የሚበጀው ይህ የምግብ ማብሰያ ድስት ባለሁለት ክፍል ነው፤ ለአልጫም ቢሉ ለቀይ ሁለት ድስት አይጣድም። በሦስት ጉልቻ በአንድ ጊዜ ሁለት የማባያ ዓይነቶችን ማብሰል እንዲቻል ልብ ይሏል። በሸክላ ድስቱ ላይ የሚታየው የካፋ አገር በቀል ጥበባት ውጤቶች አንድም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል አንድም ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ለአፋጣኝ አገራዊ ልማት የድርሻችንን እንድንወጣ የሚያተጉ (የሚተነኩሱም) አገር በቀል የፈጠራ ጥበቦች ናቸው። ለነዚህ የማኅበረሰብ አካላት ስለአካባቢያዊ ብክለትም ሆነ ስለምጣኔ ሀብት አጠባበቅ በተለምዶ አነጋገራችን “የግንዛቤ ማስጨበጫ” መድረክ ለመፍጠር ማሰብ ሞኝ ያስብላል። ኑሮአቸው ያስተማራቸው ናቸውና።

ወንዶች ለአደን በሚሰማሩባቸው ወቅቶችም ሆነ ራስን ከጠላት ወረራ ለመከላከል ሰይፍ ወይም ጎራዴን የመሳሰሉ ስለታማ መሣርያዎችን ይጠቀማሉ። ሰይፉን ወይም ጎራዴውን ለመያዝ የሚያገለግለው ከእንስሳትም ሆነ ከአራዊት ቆዳ በአገር በቀል ጥበብ የሚበጀው ማኅደር (ሰገባም ቢሉ) የተጠቃሚውን አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ማህደር በሥሩ በርካታ ንኡሳን ማኅደራትን የሚያካትት ነው። በውጪ ያለ ሰው የሚገጥመው አይታወቅምና በሚል አዳኙ ማቀላጠፊያ እቃ ፍለጋ በሚል ወደቤቱ ጉዳዩን ሳይፈጽም እንዳይመለስ የሚረዱ በርካታ ቁሶችን እንዲያካትቱ የተበጁ ናቸው። አዳኙ ራሱን ከአራዊት ጥቃት የሚከላከልበት የእሳት መፍጠርያ ቁስና ቅመማትን በአንዱ ንኡስ ማኅደር፤ ግዳይ ቢጥልና ቢሳካለት የታዳኝ እንስሳትን ጥሬ ሥጋ ማባያ (ሚጥሚጣ፣ ዳጣ ቢሉ ሰናፍጭ) መያዣ ከረጢት፤ የአራዊቱን ቆዳ በመልክ በመልኩ መግፈፍ የሚያስችል አነስተኛ ሰንጢ/ጩቤ መያዣ ማኅደር፤ እንዲሁም አደን ሲሰማሩ በእሾህና ጋሬጣ መወጋትም ስለሚኖር ስለታማ ነገሮችን ከቁስለኛው አካል መንቀስና ማውጣት የሚያስችል ወረንጦ በአንድ በኩል እንዲይዝ ታልሞ ይበጃል። በጥቅጥቅ ደኑ ውስጥ ሰው ኑሮውን እንዲመስል ጥቅጥቅ ደኑ የብርቅዬ አራዊት መናኸሪያም ነውና እኒህን አራዊት በማደን ለምግብነት፣ ለክብር ማግኛም፣ ቆዳ፣ ቀንድና ጥርሶቻቸውንም ለዓለምና አገር ውስጥ ገበያ በየመልክ በየመልኮቻቸው ማቅረብ እንዲቻል አርቆ አሳቢው የአገሬው ጥበበኛ ማኅዸርን ከነጓዞቹ መያዝና ትጥቅን ማጠባበቅ ሲፈለግ አንድ ባምስት ሊይዝ የሚያስችል ቁስን ለተግባር ሲያውሉ ይታያሉ። እኒህ ለቅምሻ ያህል የቀረቡ ቁሳዊ ባህሎች የአገር በቀል ጥበባት ውጤቶች እንደመሆናቸው በጎ በጎዎቹ እንዲቀጥሉ ከዘመናዊው ጥበብ ጋር ተዋድደው የሚዘልቁ መሆናቸውን በመጠቆም  አድናቆቴንም ለማካፈል ነው። እኒህን ያመረቱ አእምሮዎችና እጆች ግንባር ቀደሞች፣ ፋናወጊዎች እንጂ “ኋላቀሮች” ናቸው የሚል ቢኖር ኋላቀር መሆኑን ልብ በሉልኝ።

ከአዘጋጁ

አቶ አዲሱ ዘገየ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር (ባህል ጥናት) የማስትሬት ዲግሪ ያላቸውና በዲላ ዪኒቨርሲቲ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም ተመራማሪ ናቸው፡፡