የዓለም 12ኛዋ ነዳጅ ላኪ አገር ሊቢያ በፕሬዚዳት ሙአመር ጋዳፊ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ትንቅንቅ እየተደረገባት ነው፡፡ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ደግሞ የአገሪቱን ነዳጅ ማውጫዎችና ማጣሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገው ትንቅንቅ የዓለምን ቀልብ ስቧል፡፡
የሊቢያ ነዳጅ የአገሬውን ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችንም ትኩረት ከመሳቡም በላይ፣ አሜሪካ በሊቢያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የምትፈልገው የሊቢያን ነዳጅ ለመቆጣጠር ስለምትፈልግ ነው የሚል ትችት እየተሰነዘረባት ነው፡፡ በሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ በየቀኑ እያሻቀበ ሲሆን፣ ባለፈው ዓርብ የአንድ በርሜል የነዳጅ ዋጋ 115 የአሜሪካ ዶላር ተሸጧል፡፡
የነዳጅ ፖለቲካው የፈጠረው ግለት የቬኑዚላውን ፕሬዚዳንት ሑጎ ሻቬዝን በድንገት ለሽምግልና ቢያመጣቸውም፣ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች አወዛጋቢው ሻቬዝ ከጋዳፊ የልብ ወዳጅነት በመነጨ ስሜት የሚያደርጉት ሽር ጉድ ፋይዳ ቢስ ነው እያሉ ነው፡፡ ሻቬዝ አሜሪካና ሸሪኮቿ ሊቢያ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ የበለጠ እያባባሱት ነው ብለው፣ በተለይ አሜሪካ ዓለምን ለመቆጣጠር ካላት ፍላጎት የተነሳ በንፁኃን ደምና ስቃይ ላይ ተረማምዳ የሊቢያን ነዳጅ ለመቆጣጠር ተነስታለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሑጎ ሻቬዝ የጋዳፊ ዋነኛ ወዳጅ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ጋዳፊ 40ኛውን በዓለ ሲመታቸውን ሲያከብሩ ትልቁ እንግዳቸው ነበሩ፡፡
ሊቢያ በሰላሙ ጊዜ በቀን 1.6 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለዓለም ገበያ ስታቀርብ ነበር፡፡ ከየካቲት 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በፈነዳው ሕዝባዊ አብዮት ምክንያት ይህ መጠን ቀንሶ በአሁኑ ጊዜ በቀን ከ700 ሺሕ እስከ 750 ሺሕ በርሜል ነዳጅ እያመረተች ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይኼን ያህል ነዳጅ እየተመረተ ያለውም በውጭ ኩባንያዎች አማካይነት ነው፡፡
በሊቢያ እየተጋጋመ በቀጠለው አብዮት ጋዳፊ ከሥልጣን ካልወረዱ ወይም ሰላም ካልሰፈነ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ሄዶ እስከ 150 የአሜሪካ ዶላር ሊገባ ስለሚችል፣ አሜሪካና ምዕራባውያን በዚህ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው እንዲናጋ አይፈልጉም እየተባለ ነው፡፡
ምንም እንኳን አሜሪካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሊቢያን ነዳጅ ለመቆጣጠር እንደምትፈልግ ባትገልጽም፣ የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ በእነማን እንደሚመራ ለማወቅ እንቅልፍ አጥታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ላለፉት 42 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት ጋዳፊ ካሁን በኋላ ሊቢያን መምራት እንደማይችሉ በመገንዘቧ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው እያለች ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋዳፊን በቀጥታ ከሥልጣን ይውረዱ ካሉ በኋላ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከሊቢያ እየሸሹ ያሉ የውጭ ስደተኞን እንዲረዱ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሜድትራንያን ባሕር ላይ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን መታዘዙ፣ አሜሪካ ጋዳፊ በተቃዋሚዎች ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰድ ከጀመሩ ጣልቃ ልትገባ ትችላለች የሚለውን ስጋት አግዝፎታ፡፡ ይህ ዓይነቱ የአሜሪካ እንቅስቃሴ በማየት ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሊቢያን ነዳጅ ለመቆጣጠር የሚደረገው ትንቅንቅ በሊቢያውያን መካከል ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይሎችም ጭምር ነው የሚሉት፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ከ200 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የውጭ ተቀጣሪ ሠራተኞች ከሊቢያ ወደ ቱኒዚያ፣ ግብፅና ኒጀር መሰደዳቸውን የዓለም አቀፉን የስደተኞች ድርጅት ዋቢ አድርገው የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ የኔዘርላንድ መንግሥት ሁለት ሲቪሎችን ከሊቢያ ለማስወጣት ዕርዳታ ያደረጉ ሦስት የባሕር ኃይል ባልደረቦቹ በሊቢያ ወታደሮች መያዛቸውን ገልጻEል፡፡
የሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ በሊቢያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እያባባሱ ያሉት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መሆኑን ለአልጄዚራ አስታውቆ፣ የምዕራቡ ዓለም የሊቢያን ነዳጅ ለመቆጣጠር እየሞከረ ነው ሲል ወቅሷል፡፡ ጋዳፊና በሳቸው ዙሪያ የተኮለከሉ የቅርብ ሰዎቻቸው አሜሪካና አጋሮቿ ነዳጁን ሊቆጣጠሩት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ መክረማቸው አይዘነጋም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋዳፊና ግብረ አበሮቻቸው በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ላደረሱት ወንጀል እመረምራቸዋለሁ እያለ ነው፡፡ መቀመጫውን ዘ ሔግ ያደረገው የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ጋዳፊ፣ ልጆቻቸውና የቅርብ ሰዎቻቸው ባደረሱት ሰብዓዊ ቀውስ ይጠየቃሉ ብሏል፡፡ መብቶቻቸውን በጠየቁ ሰላማዊ ሠልፈኞ ላይ ለተፈጸመው ጭፍጨፋና በአውሮፕላን ድብደባ ሕይወታቸውን ያጡ የበርካታ ሊቢያውያንን ደም እንፋረዳለን እየተባለ ነው፡፡ በሊቢያው አመፅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል እየተባለ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ሺሕ ሰዎች መሞታቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ምዕራባዊውንና ምሥራቃዊውን የአገሪቱን ክፍሎች የተቆጣጠሩት የጋዳፊ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ለመከላከል የታጠቁ ሲሆን፣ በቤንጋዚ ወታደራዊ ምክር ቤት አቋቁመዋል፡፡ ራሳቸውን ያደራጁት እነዚህ ተቃዋሚዎች ጋዳፊን ከትሪፖሊ ቤተ መንግሥት እናባርራለን በማለት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ በጋዳፊና በእነዚህ ተቃዋሚዎች መካከል ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል ስጋት አለ፡፡
ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ማንም ከሥልጣኔ አይነቀንቀኝም እያሉ ናቸው፡፡ የመጨረሻው ሰውና ጥይት እስከሚቀር ድረስ እፋለማለሁ ያሉት ጋዳፊ፣ ሕዝባዊ አመፁን የሚመራው አልቃይዳ ነው ብለዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳት ኦባማ ግን ጋዳፊ በሲቪሎች ላይ የሚፈጽሙትን ግድያ እንዲያቆሙና ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል፡፡ በሊቢያውያን ላይ አመፅ የሚፈጽሙ ለድርጊታቸው ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ የሊቢያውያን የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የክብር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል በማለትም አስጠንቅቀዋል፡፡
የሊቢያ ዕጣ ፈንታ ባለየበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የዓለምን ትኩረት ስባለች፡፡ በየጊዜው እያሻቀበ ያለው የነዳጅ ዋጋም በሊቢያ ሰላም እስካልወረደ ድረስ የበለጠ እየናረ እንደሚሄድ ተሰግቷል፡፡ በሊቢያ አሸናፊ የሚሆነው የነዳጅ አቅርቦቱን የሚቆጣጠረው ኃይል ነው ቢባልም፣ ይህ ትንቅንቅ ከፍተኛ የሆነ እልቂት እንዳይፈጠር ግን ተሰግቷል፡፡


