Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የጽዳት ያለህ!

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

ነዋሪነታችን በምዕራብ አዲስ አበባ አስኮ አካባቢ በአሁኑ አጠራር ወረዳ 13 ልዩ መጠርያው መንደር ሁለት፣ በተለምዶ ቀድሞ ወደ አስካለ ጠጅ ቤት አሁን አስኮ ፕሮግሬስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ ነው፡፡ በመንደራችን የቤት ቁጥሩ 227 ከሆነ ቡና ቤት መጸዳጃ ቤት የሚወጣ አካባቢ በካይ ፍሳሽ በመንገዳችን ላይ ያለማቋረጥ እየፈሰሰ በመሆኑ እኛንም ሆነ ልጆቻችንን ለበሽታ እየዳረገን ነው፡፡

ቀደም ሲል ከአካባቢው ኅብረተሰብ የተውጣጣን ሰዎች የድርጅቱ ባለቤት ከአድራጎታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም፣ የቀድሞው የቀበሌ 15/16 ደንብ ማስከበርም ድርጊቱ እንዲታረም ውሳኔ ቢያስተላልፍም ውሳኔውን ከግምት ባለማስገባት፣ ፍሳሹን በኅብረተሰቡ መተላለፊያ መንገድ ላይ ጧትና ማታ በመልቀቅ የአካባቢ ብክለት እያደረሱብን ይገኛሉ፡፡

በአካባቢያችን በሚገኘው የአስኮ ፕሮግሬስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ በርካታ ሕፃናት የሚመላለሱበት፣ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በትምህርትም ሆነ በዕረፍት ሰዓት የሚመጣው የፍሳሹ ሽታ ለጉንፋንና ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በሽታ እየዳረጋቸው በመሆኑ ክፍለ ከተማውም ሆነ ወረዳው፣ የከተማይቱ የጤና ቢሮ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስድልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች 

*   *  *  *  *
መረጃው ይስተካከል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ (www.nbe.gov.et) መረጃ ሳገላብጥ የገረመኝንን ላጋራችሁ፡፡

በFaq ክፍል የቁጠባ አነስተኛ ወለድ መጠን 4 በመቶ ይላል፡፡ በሬዲዮ እንደሰማሁት ከሆነ ወደ 5 በመቶ ከተለወጠ ሰንብቷል፡፡ እንዲህ ያለ ወቅታዊ ያልሆነ መረጃ በማየቴ በዚህ ድረ ገጽ ሌሎችን መረጃዎች ለማመን ተቸግሬያለሁ፡፡
ሼህ ሙሄ፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት

* * *  *  * * *
የደኑ መራቆት ይታሰብበት
በቅርቡ ማለትም ባለፈው የካቲት ወር ውስጥ ለመዝናናት ወደ ወንዶ ገነት የፍል ውኃ መዝናኛ ስፍራ የመሔድ አጋጣሚውን አግኝቼ ነበር፡፡ ወደ ሥፍራው ከዚህ ቀደም በግምት ከአምስት ዓመት በፊት ሔጄ ስለነበር የአካባቢውን ለውጥ ለመረዳት ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ወደ ወንዶ ገነት ለመሔድ ሁለት አቅጣጫዎች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ የቀድሞው መንገድ በሻሸመኔ በኩል ሲሆን፣ ሁለተኛው በሐዋሳ በኩል ወንዶ ማዞርያ በሚባለው በኩል ነው፡፡ እኔ በአጋጣሚ የተጓዝኩት በሁለተኛው መስመር ነበር፡፡ እስከ ግማሽ ድረስ መንገዱ በጥሩ የአስፋልት መንገድ በመሠራቱ ምቾት ነበረው፡፡ በጉዞዬ ላይ አካባቢውን እየቃኘሁ ስጓዝ በገበሬዎች እርሻ ላይ በአብዛኛው የሚታየው የጫት ማሳ እያስገረመኝ መሬቱ ሁሉ በጫት ከተያዘ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እንዳያሰናክል ስጋት አደረብኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ እየተጓዝኩኝ እያለ ድንገት አንድ ነገር እይታዬ ውስጥ ገባ፣ የፈረሱና የተቃጠሉ ቤቶች ቁጥራቸው ጥቂት ባለመሆኑ ግራ ገብቶኝ አጠገቤ ያለውን ጓደኛዬን ጠየቅኩት፡፡ በሁለት ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት መሆኑን አስረዳኝ፡፡ ቤቶቹ ዘመናዊ የከተማ ቤቶችና የሳር ጎጆ ቤቶችም ሲሆኑ፣ በመንገዱ ግራና ቀኝ ሲታዩ በአውሮፕላን የተደበደበ ከተማ መስሏል፡፡ ነዋሪዎቹ ግን የሉም፡፡ ሕግና መንግሥት ባለበት አገር ይህ ሁኔታ መከሰቱ ለምን ይሆን? የሰው ሕይወትም እንደጠፋ ይነገራል፡፡ ነገሩ በጣም አሳዛኝ ነው፤ ጉዳቱ ቀላል አይደለም፡፡ የውጭ ዜጎች ይህንን ቢያዩ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ አንድን አነስተኛ መንደር በድንበር ከፋፍሎ ሕዝብ እንዲጋጭ በማድረግ ንብረትና ሕይወት ከሚጠፋ ሌላ አማራጭ ፈልጎ በሰላም መኖር ይበጃል፡፡ ይህንን እግረ መንገዴን ያየሁትን በአጋጣሚ ገለጽኩኝ እንጂ ዋናው አስተያየቴ ወንዶ ገነት ካደረስኩ በኋላ ስለተመለከትኩት ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ከወንዶ ገነት የፍል ውኃ መዝናኛ አናት ላይ ቀና ሲባል ሰንሰለታማ ተራራዎች ይታያሉ፡፡ እነዚህ ተራሮች ከአምስት ዓመት በፊት ሳያቸው በአብዛኛው በደን የተሸፈኑ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን በእጅጉ ሳስተው ቁጥቋጦ ብቻ ነው፡፡ በአብዛኛው የሚታየው የእግር መንገድም በተራሮች አናት ላይ ከሩቁ ይታያል፡፡ የደኑን መራቆት ምክንያት ማንም ሰው በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡ ይኸውም ከተራሮቹ አካባቢ ቁልቁል ወደ ከተማዋ ከሚጓዘው የአካባቢው ነዋሪ አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ፍልጥ እንጨት እየታዘለ ወደ ገበያ ለሽያጭ ይጋዛል፡፡ ይህንን የተመለከትኩት ለግማሽ ሰዓት በከተማዋ በቆየሁበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ያለ ጥርጥር የአካባቢውን የአየር ንብረት እንደሚለውጠው አያከራክርም፡፡ የአካባቢው አስተዳደር ይህንን ጉዳይ ለምን ሊቆጣጠረው እንዳልቻለ ምክንያቱ ምን ይሆን? የተራሮቹ መራቆት ከተማዋን ጎርፍ ሊያጥለቀልቃት እንደሚቻል መገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ስለ አካባቢ ጥበቃ በአሁኑ ወቅት ለገበሬው ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃን እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ለወንዶ ገነት አካባቢም ነዋሪዎችና ገበሬዎች ለአመራሩም ሥልጠና ቢሰጥ ከዚያም በተግባር መተርጎሙንም ክትትል ማድረጉ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ የደን ኮሌጁም አጠገቡ ደን ሲወድም እንዴት እያየው ነው?
ማቴዎስ ሽመሎ፣ ከሐዋሳ