Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ልጅ ያለ ጎጆ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በምሕረት አስቻለው

‹‹በአስተሳሰብና በገቢ በብዙ መልኩ ሴቶች እየተቀየሩ ነው፡፡ በወንዱ በኩል ያለው ለውጥ ግን ብዙም አይደለም፡፡ የተሻለ ኑሮ ለመኖር፣ በነፃነት ተደስቶ ለመኖር ራስን ችሎ ለመቆም በኢኮኖሚ ጠንካራ መሆን እንደሚያስፈልግ ሴቱ ተረድቶ በዚያ መልክ መጓዝ ጀመረ፡፡ በተቃራኒው የተማሩ የሚባሉ ወንዶች እንኳ እንደ ቀድሞ፣ ወሳኝ፣ የቤት ራስና በገንዘብ የበላይ መሆን የመፈለጋቸውን ነገር በቀጥታም ባይሆን በተለየ መልክ ያንፀባርቁታል፤›› ያለችን በሃያዎቹ መጨረሻ የምትገኝ ወጣት ነች፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት የምትሠራ ሲሆን፣ የድኅረ ምረቃ ትምህርቷንም በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በተማሩ፣ በኢኮኖሚ ራሳቸውን በቻሉ ሴቶች ወንድ የሌለበትን ቤተሰብ የመመሥረት ፍላጎትና አዝማሚያ እየታየ እንደሆነ ይሰማታል፡፡ ይህም ወንድን በጾታው በወንድነቱ ያለመፈለግ ሳይሆን፣ በትዳር ውስጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመሸሽ ነው፡፡ በማኅበረሰባችን ‹‹ወንድ አንፈልግም›› በሚል ጽንፈኛ አቋም ሳያገቡ የሚወልዱ፣ ወይም ጨርሶ የማያገቡና የማይወልዱ ጥቂት እንዳልሆኑ፤ ይልቁንም ሳታገባ የምትወልድ ሴት ወይም ሳታገባ ለመውለድ የምትወስን ሴት ይህን የምታደርገው የወንድን ተጽዕኖ በመሸሽ እንደሆነ ታምናለች፡፡

‹‹እንደ ቀድሞ ልጅ መውለድ ሲፈለግ ባል ይምጣ የሚባል ነገር ቀርቷል፡፡ እየተስተዋለ ያለው ትዳር፣ ባል የሚባሉትን ነገሮች ወደ ጎን ብሎ መውለድ ነው፡፡ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሦስት ጊዜ ደጋግሞ በዚህ መልኩ መውለድ፡፡ ሳያገቡ መውለድ የሚያስከትላቸው ተጽዕኖዎችም በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሱ ነው፡፡ ጋብቻም ሆነ መውለድ በሴቶች በኩል ከኢኮኖሚ አቅም አንፃር እየታየ መምጣት የጀመረ ይመስለኛል፡፡ የቤተሰብ ለምን አታገቢም? ጥያቄ ለምን አትወልጂም ጋር እኩል እየሆነ የመጣበት ሁኔታም ይታያል፤›› ስትል አክላለች፡፡ 

‹‹ራሴን ከቻልኩና ወልጄ ብቻዬን የማሳደግ አቅም ካለኝ ማግባት ለምን ያስፈልገኛል? ጋብቻ ውል ነው፡፡ ካለ ውል ወልደሻል ብሎ ፈጣሪ ይኮንነኛል ብዬ አልፈራም፤›› የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ሐሳቦች ሳያገቡ የመውለድ አቋም ካላቸው ሴቶች ያደመጥናቸው ናቸው፡፡

ስለ ትዳር የሚሰማውና የሚታየው ነገር ሴቶችን ወደዚህ መስመር እንዳመጣቸው፣ በሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች እንኳ በምኞት ደረጃ ሳያገቡ መውለድ የመፈለግ አዝማሚያ በብዛት እንደሚስተዋልም ትናገራለች፡፡ በሌላ በኩል ሳያገቡ በሚወልዱ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉና ሳያገቡ የወለዱ ሴቶች ዛሬም ጠንካራ ተጽዕኖ ሲያርፍባቸው ይስተዋላል፡፡

እንደ እሷ አመለካከት ትልቁ ጥያቄ የሴት  ልጅ ራስን የመቻልና ወልዳ የማሳደግ አቅም ነው፡፡ በጣም ወግ አጥባቂ በሆነ ቤተሰብና ማኅበረሰብ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የተማሩ፣ በኢኮኖሚያዊ አቅማቸውም ራሳቸውን የቻሉ ሴቶች ሳያገቡ መውለድ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ እንደ ነውር የሚታይበት ሁኔታ የለም፡፡

‹‹የተማሩ፣ ጥሩ ሥራ ያላቸው፣ በንግድም ይሁን በሌላ ሥራ ተሠማርተው ራሳቸውን የቻሉ፣ ነገር ግን ሳያገቡና ሳይወልዱ የቀሩ ሴቶች ሕይወት፣ ወላጆችን በጥቅሉ ማኅበረሰቡን ጥሩ ትምህርት ያስተማረ ይመስለኛል፡፡ በወላጆች ዘንድ ልጃችን ሳታገባም፣ ሳትወልድም ሁሉንም ከምናጣ ወልዳ ራሷን ትተካ፤ እኛም ዓይናችንን በዓይናችን እንይ የሚል ሐሳብ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ያልሆነውን ነገር ለማስቀረት የሚደረግ ምርጫ ነው፤›› በማለት አንዳንድ አክራሪ ቤተሰቦችን ለማሳመን ‹‹በሽታ ይዛ ብትመጣ ታስታምሟት አልነበር ወይ?›› ዓይነት ሽምግልና፣ ወላጆች የሴት ልጆቻቸውን ሳያገቡ መውለድ እንዲቀበሉት ያደረገበት አጋጣሚ ማየቷን በንጽጽር ነግራናለች፡፡

ወይዘሮዋ ሁለት ልጆቻቸውን ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መምህርት ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን ያሳደጉት ያለ ባል ሲሆን፣ ዛሬም የብቸኝነት ሕይወት በመምራት ላይ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በተማሩና ራሳቸውን በቻሉ ሴቶች በኩል ባል ማግባት ያለመፈለግ፤ ሳያገቡ የመውለድ ሁኔታ በብዛት እየተስተዋለ በመሆኑ ላይ ከወጣቷ ጋር ይስማማሉ፡፡

‹‹ከወንድ ጋር መሔድ ትልቅ ነውር ነበር፡፡ የእገሌ ልጅ ዲቃላ ወለደች መባል ትልቅ መነጋገርያ ጉዳይ ነው፡፡ ሰፈሩና መንደሩ ሁሉ ልጅ አሳዳጊ ነው፡፡ የእገሌ ልጅ ባልጋለች፤ ለወላጆቿ እናገራለሁ የሚባል ነገር ባለመኖሩ ሁሉም አሳዳጊ ሁሉም ተቆጪ ነው፡፡ ስለዚህ ማስወረድ በብዛት ነበር፡፡ አንዳንድ የሀብታም ልጆች ገጠር ወደ አክስት፣ አጎት ሔደው ተደብቀው ይወልዱ ነበር፡፡››

በዚያ ዘመን ብዙ ሴቶች እርግዝናቸውን ደብቀው ኖረው በተመሳሳይ ተደብቀው በመውለድ ልጆቻቸውን ለአሳዳጊና ለማደጎ ድርጅቶች ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ጥቂት የማይባሉ እናቶች ለሥነ ልቦና ቀውስ ሲጋለጡ፣ ልጆቹም በማንነት ጥያቄ ለዓመታት ተሰቃይተዋል፡፡ በአንድ ወቅት የ17 ዓመት ታዳጊ የሆነች የቅርብ ጓደኛቸው ልጅ አርግዛ፤ እርግዝናዋም ተደብቆ ስትወልድ ቂርቆስ አካባቢ ለምትገኝ አንዲት ሴት ሕፃኑ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ ልጅቷ አድጋ ራሷን ስትችል ልጇን ለመውሰድ ስትፈልግ አሳዳጊዋ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቤተሰብ ተረብሿል፡፡ ይህ ደግሞ ቀደም ባሉት ዓመታት የጥቂቶች ሳይሆን የብዙዎች የሕይወት አጋጣሚ ነበር፡፡

እንደ እሳቸው እምነት ላለማግባት፤ ግን ለመውለድ የሚወስኑ ሴቶች መወሰን የሚችሉ፣ በራስ መተማመን ያላቸውና በራሳቸው መቆም የሚችሉ ሲሆኑ መነሻቸውም እናቶቻቸው፣ እህቶቻቸውና ጓደኞቻቸው ያለፉበት የትዳር ውጣ ውረድን መሸሽና ሰላምን መፈለግ ነው፡፡ ትዳርን የመሰለ ክቡር ነገር ባይኖርም መተዛዘን፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳትና መዋደድ በብዙዎች ትዳር በማይታይበት፣ ይልቁንም ትዳር ፉክክር በሆነበት በአሁኑ ወቅት የእነዚህ ዓይነት ሴቶች አቋም ትክክል ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም፡፡

‹‹እግር ከእግር በሚጋጭበት ዓለም በባልና ሚስት መካከል አለመግባባት ለምን ተፈጠረ ሳይሆን፣ ጨርሶ ላለመግባባት ስምምነት ላይ የደረሱ ይመስል፣ ዘወትር መጋጨት፤ በተለይም ልጆችን ምስክር አድርጎ መጨቃጨቅ፣ በትዳሮች መሃል ጎልቶ ይታያል፡፡ ሴቷ ላለማግባት ወስና እንዲሁ ስትወልድ፣ የሴትና የወንድ መተባበርና መተጋገዝ እየቀረ መራራቅ ሲንሰራፋ ይህ አካሔድ ወግና ባህላችንን የት ያደርሰዋል?›› ብለው በመጠየቅ በሰለጠነው ዓለም እንደሚታየው፣ ሁኔታው ትዳር ኮንትራት ወደሚሆንበት አቅጣጫ  እንዳያመራ ሥጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ትዳር እንደ ኪራይ ቤት ሊሆን ነው፡፡ ‹‹አስጨርሽኝ›› ‹‹አስጨርሰኝ›› በሚል የትዳር ክብር ሊቀር ይሆን? ይህ ሥጋታቸው ነው፡፡

‹‹አላገባሁም ግን የአንድ ወይም የሁለት ልጆች እናት ነኝ›› ማለት ክብር እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ እናቶችም ልጆቻቸው ሳያገቡ ዕድሜያቸው እንዳያልፍ፣ ባያገቡም እንዲወልዱ መምከር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ለሴቶች ሳያገቡ መውለድ እንደ ነውር ላለመቆጠር ኤች.አይ.ቪ በተወሰነ መልኩ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይሰማቸዋል፡፡ ወይዘሮዋ ‹‹ጤነኛ ሆና ወልዳ ብትኖር ምን አለበት? የባሰውን አያምጣው እንጂ›› ዓይነት አቋም በኅብረተሰቡ እንደተያዘም ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል እንደ ወጣቷ ሳያገቡ መውለድ በአብዛኛው የሚታየው በተማሩና ራሳቸውን በቻሉ ሴቶች ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸውን ባልቻሉና በዚህ ደረጃ ተማሩ በማይባል ሴቶችም ጭምር እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ይህ ሳያገቡ የመውለድ፣ ማግባት ያለመፈለግ አዝማሚያ በእሳቸው እይታ የነፃነትና የሰላም ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማንኛዋም ሴት የምትጠይቀውና የምትፈልገው ነው፡፡

‹‹ራሳቸውን በኢኮኖሚ ያልቻሉ፤ ነገር ግን ሳያገቡ እየወለዱ በእርዳታ ሕይወታቸውን የሚመሠርቱ ሴቶች ብቅ ብቅ ማለታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰምቻለሁ አይቻለሁ፡፡›› ማግባት ያለመፈለግ፣ ሳያገቡ መውለድ ለጊዜው ለሴቶች ሰላም የሚሰጥ ቢመስልም፤ ለውሳኔው ባለቤቶች፣ ለልጆች ብሎም ለኅብረተሰቡ ከባድ አደጋ እንደሚያመጣ ያምናሉ፡፡

ስለዚህ አዝማሚያው እንደ ችግር ታይቶ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ፤ ጥሩ አካሔድ የሚሆነውም ሴቶችን ማስተማር፣ ሴቶችን ማንቃትና ሌላም ሌላም እያሉ በነጠላ ሥራዎችን ለመሥራት መሞከር ሳይሆን፣ ሁለቱንም ማስተማር ትክክለኛ መፍትሔ መሆኑ በሁሉም ሊታመንበት ይገባል ይላሉ፡፡