ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ መገናኛ ጫፍ የሚሰበሰበውን ታክሲ ጠባቂ ሕዝብ ብዛት አንዳንዶች አጋነው ሲገልጹት፣ ‹‹የባህር ዳር አሸዋ ይመስላል›› ይላሉ፡፡
በእርግጥ በሁሉም የአዲስ አበባ አቅጣጫዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የታክሲ እጥረት አለ፡፡
ቦሌ ድልድይ ውስጥ ቢገቡ ወደ ማለዳና ምሽት ፒያሳና አራት ኪሎ የሚዘልቁ ታክሲዎች ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ ወይም ሃያ ሁለት ካዛንቺስ የሚጠሩ ወያላዎችን ድምፅ ለመስማት የማይናፍቅ የለም፡፡ ከዚያው ከቦሌ ድልድይ ሳንወጣ ወደ ሳሪስ የሚሄዱ ተሳፋሪዎች የሚደርስባቸው እንግልት የሚለመድ አልሆነም፡፡ ከቦሌ ድልድይ መገናኛም ሆነ ገርጂ ለመሳፈር ቢያንስ ፈርጣማ ጡንቻ ያስፈልጋል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚመጡት ታክሲዎች ውስጥ ለመታደም እንደ ነፃ ትግል ስፖርተኞች መታገል የግድ ነው፡፡ ግን አቅም የሌላቸውስ? አዛውንቶችስ? ነፍሰ ጡሮችስ? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ፡፡ ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን ያለርህራሔ እየገፈታተሩ አደጋ የሚያደርሱ ባለ ፈርጣማ ጡንቻዎች እየበዙ ስለሆነ የመፍትሔ ያለህ ማለት የግድ ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤መሸትሸት ሲል ለትዝብት ያህል ስቴዲዮም ቆም ብለው እንደሆነ እዚያም ትንቅንቁ ከባድ ነው፡፡ ከትግሉ ከባድነት የተነሳ ተገፍትረው የሚወድቁ እየበዙ ነው፡፡ መገናኛ በቀጥታ የሚጭን ታክሲ አይገኝም፡፡ ወደ ቦሌ ለመሳፈርም ቢሆን ጭንቅ ነው፡፡ ስቴዲየም አካባቢ በጣም አደገኛና አደንዛዥ የሚባሉ ኪስ አውላቂዎች አሉ፡፡ እንኳንስ እንደዚያ በተመቻቸ ግርግር ውስጥ ይቅርና እንዲሁም አገር ያሰለቹ ናቸው፡፡ ስንቱ ገንዘቡን፣ ሞባይሉንና በጣም አስፈላጊ ሰነዶቹን ተነጥቋል፡፡ ይህ የታክሲ ግርግር የተመቻቸው እነሱን ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ እጥረት በፈጠረው ችግር ስንቶች በእነዚህ ወረበሎች ተዘርፈዋል፡፡ ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንዲሉ፡፡
አንዳንዶቹ ሆን ብለው መርፌ ይዘው ነው የሚዞሩት፡፡ ብቸኛና ለመሰረቅ የተመቸ ሰው ከተገኘ ምናልባትም በሞባይል ስልክ እያወራ ከሆነ በጣም አመቺ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቀስ ብለው ከኋላው በመድረስ በያዙት መርፌ ጥርቁስ ያደርጉታል፡፡ (በመርፌው ምን ያህል ሰው እንደተወጋበት ከእነሱ በስተቀር ማንም አያውቀውም) ብቻ በመርፌ የተወጋው ሰው ምን መጣብኝ ብሎ በድንጋጤ የያዘውን ነገር ሁሉ ወደ ላይ አሽቀንጥሮ ይጥለዋል፡፡ ይኼኔ ግለሰቡ የጣለውን ሞባይልም ሆነ ሌላ ነገር ይዘው በጠራራ ፀሐይ ይፈተለካሉ፡፡ እነሱን አባሮ ለመያዝ መሞከር ዘበት ነው፡፡ በተለይ አንዳንድ የአዲስ አበባ መንደሮች ጠመዝማዛነት ሌቦቹ ያሰቡትን እንዲከውኑ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አበርክቶላቸዋል፡፡ በሚታወቁበትም የፍጥነት ሩጫ የተነሳ ‹‹በራሪዎቹ›› የሚል ቅፅል ስም ወጥቶላቸዋል የሚል ወሬ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ፈጣን ሩጫቸው ላይ ትንሽ ሥልጠና ቢጤ ቢታከልበት በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ይዘው መምጣታቸው ምንም ጥርጥር የለውም የሚሉም አሉ፡፡ አትሌቲክስ የኢትዮጵያዊያን እጅግ በጣም ተወዳጅ ስፖርት እንደመሆኑ መጠን፣ ጀግኖቹ አትሌቶች በታላላቅ የውድድር ሜዳዎች ኢትዮጵያን ሲያስጠሩበት፣ ኪስ አውላቂዎቹ ደግሞ የሰውን ንብረት በመቀማት ለኅፍረት ተግባር አውለውታል፡፡ አንዱ ለአገሩ ሲተጋ ሌላው በሙስና እንደሚዘፈቀው ማለት ነው፡፡
አንድ ሞባይሉ የተቀማበት ሰው ሌባውን የገባበት ጉራንጉር መንደር ውስጥ ገብቼ አባርሬ እይዘዋለሁ እያለ ሲፎክር የሰሙ ሰዎች ‹‹ውይ እሱን ፈልጐ ከማግኘት ውቅያኖስ ውስጥ የሰጠመች መርፌ መፈለግ ይሻልሃል፤›› ሲሉት፣ ሌሎች ደግሞ ‹‹በበራሪዎቹ የተሰረቀብህን ዕቃ መልሼ አገኘዋለሁ ማለት ዓሳን በዋና አባሮ የመያዝን ያህል ቀላል ነው፤›› እያሉ ቀለዱበት አሉ፡፡ ሌሎችም የጠፋውን ንብረት ከሞቱ ዘመዶቹ እንደ አንዱ እንዲቆጥረው መከሩት፡፡ በጣም የሚያሳዝነው በዚህ መሀል በሚዘረፉት ላይ የሚደርሰው ድንጋጤና መረበሽ እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ እነዚህ መንታፊዎች አሮጌ መንደሮች ፈርሰው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲሠሩ በጣም ማዘናቸው ይነገራል፡፡ ተክዘዋል፡፡ የእንጀራ ገመዳቸው እንደተቆረጠ ቆጥረውታል፡፡ መንግሥትን በሆዳቸው ረግመዋል፡፡ እንጀራችን ላይ መንግሥት ውኃ ቸለሰበት ብለው ሐዘን መቀጣቸው ጭምር ይወራል፡፡ ከየጉራንጉሩ እየመጣ መዝረፍ የለመደ ዘመናዊ መንደር ውስጥ ምን ማድረግ ይቻለዋል?
ምን ይኼ ብቻ ቁጥራቸው አይብዛ እንጂ ሞጭላፋ የታክሲ ሾፌርና ወያላዎችም አሉ፡፡ በተለይ ራቅ ካለ ሥፍራ የሚመጡ ሰዎችን አዋክበው የያዙትን ዕቃ ሁሉ ተረክበው ያስለቀሱ፤ ስንቱን በባዶ እጁ የሸኙ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ እግዜሩ ምህረቱን ያውርድላቸው እንጂ ብዙ ሰዎች አምተዋቸዋል፡፡ የእምባ ጐርፍ በጣም ክፉ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ለተሳፋሪ አገልግሎት መስጠት የሚገባቸው ሰዎች የወረበላ ሥራ ሲሠሩ ማየት ያናድዳል፡፡ የታክሲ ሾፌርና ወያላ በዚህ ስማቸው ባይነሳ ጥሩ ነው፡፡
መጀመሪያ ወደተነሳንበት መገናኛ ጫፍ እናቅና፡፡ የሰው ዓይነት ይርመሰመሳል፡፡ ታክሲዎች ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን ለመጫን ፈቃደኛ የሚሆኑት ከሕዝቡ ቁጥር አንጻር ሲታይ እንደ ጠብታ ነው የሚቆጠሩት፡፡ አንድ ታክሲ ሲመጣ የት መሆኑ ሳይታወቅ ኮተቤ፣ ሲኤምሲና ገርጂ በሚባሉ ሰፈር ሰዎች ይወረራል፡፡ ይኼኔ አቤት የሾፌሮቹ ኩራት፣ አቤት የወያላዎቹ ኩራት፡፡ በእነሱ ትዕቢት የማይበሳጭ የለም፡፡ ‹‹አንጭንም፤ መጨረሻችን ነው፤ አለመጫን መብታችን ነው፤›› ሲሉ ንድድ ያደርጋሉ፡፡ በየቀኑ ተሳፋሪው የማይሰማው ነገር የለም፡፡ ከባለታክሲዎቹ ባህሪ የተነሳ ብዙዎቹ ለፀብ ይጋበዛሉ፡፡ ይኼኔ ባለታክሲዎቹ አንጭንም በማለት በኩራታቸው ይገፉበታል፡፡ ሕዝቡም መንገላታቱን ይቀጥላል፡፡ ቀን ቀን ካልተሳፈራችሁ እያሉ ጉሮሮዋቸው እስከሚሰነጠቅ የሚጮሁት ወያላዎች መሸትሸት ሲል በከተማው ሕዝብ ላይ ይነግሱበታል፤ ያመነጫጭቁታል፤ መንገድ ይቆራርጡበታል፤ ታሪፍ ይጨምሩበታል፤ ሌላም፣ ሌላም፡፡ እንዳሻው እየሆነ ያለው የታክሲ አገልግሎት የተቆጣጣሪ ያለህ ቢል ምን ይፈረድበታል?
መንግሥት ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለውን የታክሲ ቀጣና ስምሪት አንዳንድ ተገልጋዮች ሙባረክ እንደወረዱላቸው ግብፆች ደስታቸውን ሲገልጹ፣ አንዳንድ የአገልግሎቱ ሰጪዎች ደግሞ ጋዳፊ አልወርድም እንዳሉዋቸው ሊቢያዊያን ደስተኞች አልሆኑም፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ የታክሲ ቀጣና ስምሪት መጀመሩ መልካም ዜና ሆኖ ሳለ፣ ችግር ብለው የሚያነሱት የሕዝቡና የተሽከርካሪዎች ቁጥር መጠን አለመመጣጠኑን ነው፡፡ መፍትሔ ነው የሚሉትም በርካታ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እንጂ፣ የተሽከርካሪዎቹ ቁጥር እንዳለ ሆኖ ምንም ዓይነት ዕቅድ ቢወጣ ጥቅም የለውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ከስምሪቱ ጐን ለጐን በርካታ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች መዘጋጀት አለባቸው እያሉም ይጠይቃሉ፡፡ በየቀኑ ቁጥሩ እያደገ ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ችግር አሁን ባሉት ተሽከርካሪዎች አስተነፍሰዋለሁ ማለት ዘበት ነው በማለት ለችግሩ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ይጠይቃሉ፡፡
በሥራ ወይም በትምህርት ምክንያት አምሽተው ከሆነ ወደ ቤትዎ የሚገቡት ኪስዎን እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ዓይነት ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አዲሳበባዊያን ከትራንስፖርት እጦት እንግልት ነፃ ወጥተው በሚፈልጉበት ሰዓት ወጥተው እንዲገቡ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የሁሉም ሰው ፍላጎት ነው፡፡
ከመገናኛ ቦሌ የተሳፈርንበት ሐይገር ባስ እጅግ ከመሙላቱ የተነሳ በጥጥ የተጠቀጠቀ ጆንያ መስሏል፡፡ ሾፌሩና ወያላው ግን ደንታ የሰጣቸውም አይመስሉም፡፡ በየፌርማታው እያቆሙ ይጭናሉ፡፡ ገንዘብ እያስከፈሉ ሳይሆን የነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ይመስላሉ፡፡ ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ ተጭኖ መተንፈሻ የጠፋበት አውቶቡስ ውስጥ ተስቦ ቢገባ ምን ይፈጠር ይሆን? ወያላው ተጠጋጉ እያለ ሰው በሰው ላይ እያደራረበ ነው፡፡ እንኳን የቆሙት የተቀመጡት ሳይቀሩ ተጨናንቀዋል፡፡ መስኮቶቹ በሙሉ ጥርቅም ተደርገው ተዘግተው አየር የሚባል ነገር የለም፡፡ የሞቀ ትንፋሽ ከያቅጣጫው የሰውን ፊት ይለበልባል፡፡ እየተጋፋ የሚገባው ተሳፋሪ መብዛቱ ያስመረራት አንዲት ኮረዳ፣ ‹‹ኧረ በቃህ፣ ከዚህ በላይ የት ልትከታቸው ነው? በሙቀት ማለቃችን እኮ ነው፤›› ስትል ለወያላው የምልጃ ጥሪ አቀረበች፡፡ ወያላው እየተነጫነጨ፣ ‹‹ተጠጋጉ ይበቃል፤›› አለ፡፡ ኮረዳዋ በጣም እየጮኸች፤ ‹‹እንኳን ለመጠጋት መቆም አልቻልኩም፤›› አለችው፡፡ ወያላው እየጮኸ፣ ‹‹ቦሌ ብዙ ወራጅ ስላለ እስከዚያው በአንድ እግርሽ ቁሚ፤ ሌሎቻችሁም እንዲሁ ብታደርጉ ይመረጣል፤›› ሲለን የባሰ አታምጣ ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻል ነበር? ዛሬ በአንድ እግር ቁሙ ያለን ወያላ ነገ ምን ይል ይሆን? እያልን ነው፡፡


