Friday, May 24th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ለግብይት ሥርዓቱ ጤናማነት

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በናታን ዳዊት

በግብይት ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን ተደርገው የሚወሰዱት ሸማቹና ነጋዴው ወይም አገልግሎት ሰጪውና ተገልጋዩ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት ሁሌም የሚኖርና ተነጣጥለው ሊጓዙ የማይችሉ ናቸው፡፡ ሆኖም በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት ሁሌም ጤናማ ሆኖ የዘለቀ ነው ማለት አይቻልም፡፡

እንደውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንኙነታቸው መተማመንን ወደኋላ በመተው በጥርጣሬ የተሞላ እየሆነ መምጣቱ ይታመናል፡፡ ግንኙነታቸው በእጅጉ መተማመንንና መተሳሰብን መርህ ማድረግ የሚገባ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ይህ ስሜት ተቀዛቅዟል፡፡ ለግንኙነቱ መሻከር እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ በርካታ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ 

አንዱና ዋነኛው ምክንያት ተደርጐ የሚወሰደው ሸማቹ እንደሸማች ነጋዴውም እንደነጋዴ የሚጠበቁባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ አለመቻላቸው ነው፡፡ በተለይ በንግዱ ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ያልተገባ ትርፍ ለማካበት የሚፈጥሯቸው ትርምሶች በሸማችና ሻጭ መካከል ያለውን ግንኙነት ከመቀዝቀዝ አልፎ ለጤናማ የገበያ ሥርዓት ማነቆ እስከመሆን መድረሱ አይካድም፡፡ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር ያለው ተነሳሽነት አነስተኛ መሆንም ሌላ ምክንያት ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሸማቹም በኩል ቢሆን ነጋዴ ሲባል ሁሌም አጭበርባሪ እንደሆነ አድርጐ የመውሰድ አመለካከት የሚፈጥረው ጥርጣሬ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ እንዳይሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ አይካድም፡፡

በእርግጥ ሸማቹ ተጠራጣሪ እንዲሆን ያደረጉት በሸመታ ወቅት የሚያጋጥመው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ለምሳሌ ለሸማቹ ደንታ የሌላቸው አንዳንድ ነጋዴዎች በጤፍ ውስጥ አሸዋ ጨምረው መሸጣቸው፣ ሙዝን ከቅቤ ጋር ዳምጠው ንፁህ ቅቤ ነው ብለው ለገበያ ማቅረባቸው፣ በርበሬ ከተፈጨ ሸክላ ጋር ደባልቀው ንፁህ በርበሬ አስመስለው ለገበያ ማቅረባቸው፣ ዘይትንም እንዲሁ ከባዕድ ነገሮች ጋር አቀላቅለው ለሸማቹ በድፍረት ማቅረባቸው፣ ሸማቹ ነጋዴው ላይ ያለው አመለካከት ቢለውጥ  አይገርምም፡፡

ምናልባት በሸማቹና በነጋዴው መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር ያደረጉት ጥቂት ነጋዴዎች ሊሆኑ ቢችሉም፣ ጥቂቶች በፈጠሩት ሰበብ የግብይት ሥርዓቱ እስከመቼ ተበለሻሽቶ እንደሚቀጥል ሊያሳስበን ይገባል፡፡

የሁለቱ ወገኖች በቁራኛ የመተያየት አባዜ አንድ ቦታ መቆረጥ ካልተቻለ ደግሞ ጉዳቱ በሁለቱ ወገኖች ላይ ብቻ የማያቆም አገራዊ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችልም መገመት ይቻላል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥት እየተደጋጋመ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በገበያ ውስጥ እገባለሁ የማለቱ ዋነኛ ምክንያትም በሁለቱ ወገኖች መካከል የቆየ ያለመግባባት የፈጠረው ዕርምጃ መሆኑን ስናስብ ደግሞ ሸማቹና ነጋዴው ያላቸው ልዩነት ተቀርፎ ተማምነው የሚጓዙበትን ጊዜ እንድንናፍቅ ያደርገናል፡፡

መንግሥት ዋጋን ለማረጋጋት በተወሰኑ ምርቶች ላይ የጣለው የዋጋ ገደብ ውጤት አስገኝቷል፤ አላስገኘም የሚለውን ጥያቄ እንተወውና በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ አለመሆኑን የሚያውቀው ዘንድሮ ነው? የሚለውን ጥያቄ አጉልተን ስናይ፣ በእስካሁኑ የተመሰቃቀለ የግብይት ሥርዓት የመንግሥት አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልነበር ያሳየናል፡፡

ምክንያቱም የግብይት ሥርዓቱ በምን መልኩ እየተጓዘ እንዳለ መረጃ ነበረው፡፡ ቢያንስ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች በምን ያህል ዋጋ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡም ያውቃል፡፡ ዋጋ ለማረጋጋት ተብሎ የሕዝብ ማስታወቂያ በወጣበት ሰሞን እንደተነገረውም የተወሰኑ የምርት ዓይነቶችን እንደፈለገ ዋጋ የሚያወጡና የሚያወርዱ 30 የሚሆኑ ነጋዴዎች ናቸው እስከማለትም ተደርሷል፡፡

እነዚህ ነጋዴዎች ጡንቻቸውን የዚህን ያህል ሲያፈረጥሙና ሸማቹ ላይ ዋጋ ሲቆልሉ መንግሥት አያውቅም ማለት ስለማይቻል ደረጃው ይለያይ እንጂ መንግሥትም ለምንመለከተው ጤናማ ያልሆነ የገበያ ሥርዓት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል ሊባል ይችላል፡፡

ስለዚህ አሁን ባለው የገበያ ሥርዓት ውስጥ ያለውን አለመተማመን ለማስቀረት ከዚህ በኋላ ምን መደረግ አለበት ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ተገቢ መልስ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ ለግብይት ሥርዓቱ መበላሸት ዋነኛ ምክንያት ተደርጐ የሚወሰደውን አለመተማመን ለመስበር በሁሉም ወገኖች በኩል በቅን ልቦና መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡

ነጋዴው እንደ ነጋዴነቱ ለሚሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሸማቹም ለሚፈልገው አገልግሎት የተጠየቀው ክፍያ አግባብ መሆኑን በማረጋገጥ መክፈል ግዴታው መሆኑን ማመን አለበት፡፡ በመንግሥት በኩልም ለጤናማ ግብይት እንቅፋት የሆኑ ምክንያቶችን በመንቀስ አግባብ ያለው ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

በየአጋጣሚው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማርገብ ደግሞ ተደራራቢ ቅጣቶች መፍትሔ ላያመጡ እንደሚችሉ በማመን ምክርንና ማስተማርን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡