በምሕረት አስቻለው
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእናቶችና የሕጻናት ክሊኒክና ሆስፒታሎች በብዛት እየተከፈቱ ነው፡፡ ይህም አቅም ላላቸው ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የተለያዩ የሕክምና አማራጮችን ሰጥቷል፡፡
አማራጭ መብዛቱ፣ በእነዚህ የጤና ተቋማት አማካይነት የማዋለድ አገልግሎት በስፋት መሰጠቱ በመልካም ጐኑ ሲነሣ የማዋለጃ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየናረ መምጣቱ ደግሞ የብዙዎች የዘወትር ቅሬታ ሆኗል፡፡ በግሉ ዘርፍ ለሚሰጠው የማዋለድ አገልግሎት ክፍያ በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ለሚሰጠው አገልግሎት ከሚጠየቀው ክፍያ እኩል ይሁን ባይባልም፣ በሁለቱ ተቋማት የማዋለድ አገልግሎት ክፍያ ላይ የሚታየው የተጋነነ የዋጋ ልዩነት ግን ለሚሰነዘሩ ቅሬታዎች መሠረታዊ መነሻ ነው፡፡
የመንግሥት ከሆኑት መካከል በየካቲት 12 ሆስፒታል ለመደበኛ የማዋለድ አገልግሎት ሃምሳ ብር፣ የማሕፀን አፍ ሲጠብ ትንሽ ማደንዘዣ ተሰጥቶ ለሚደረገው አነስተኛ ቀዶ ሕክምና (መቆረጥ) ሰባ ብር፣ በተለያዩ የማዋለጃ መሣርያዎች እገዛ ለሚደረግ ማዋለድ ዘጠና ብር፣ ለሙሉ ቀዶ ሕክምና ማዋለድ ደግሞ መቶ አርባ ብር ይጠየቃል፡፡
ነገር ግን ወላዶች የሚገላገሉበት አልጋ (Delivery Couch) ቀደም ሲል ሦስት የነበረ ሲሆን፣ ብዙ ወላዶች የሚገለገሉበት እንደመሆኑ በተደጋጋሚ ስለሚታጠብ አንደኛው በመሰበሩ ሁለት ብቻ መቅረቱን በሆስፒታሉ አጠቃላይ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትና የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ የሥራ ሒደት መሪ የሆኑት ዶ/ር አዳነ ኃይሌ ነግረውናል፡፡ ከተገላገሉ በኋላ ወላዶች ከሆስፒታሉ እስኪወጡ ድረስ የሚያርፉበት አልጋ ብዛት ደግሞ አራት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት እጥረት ጥቂት በማይባሉ የመንግሥት ሆስፒታሎች የሚታይ በመሆኑ የማዋለጃ ክፍያ አነስተኛ መሆን በራሱ ብቻውን ሁኔታዎችን ለተገልጋዩ ምቹ አያደርግም፡፡
በሌላ በኩል በተወሰነ መልኩ የተጋነነ ዓይነት ክፍያ ይጠየቃል በማይባልበት በአንድ የግል የእናቶችና የሕጻናት ሆስፒታል ለመውለድ አልጋ የምትይዝ እናት ቢያንስ 4 ሺሕ ብር እንድታስይዝ ይጠየቃል፡፡ በምጥ ከተገላገለች 2 ሺሕ 8 መቶ፣ በሙሉ ቀዶ ሕክምና ደግሞ 6 ሺሕ 5 መቶ ይከፈላል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን ወላዶች በወሊድ ወቅት እንዲጠቀሙ እንደሚደረጉት መድኃኒት ሊጨምር እንደሚችል ተመልክተናል፡፡
ባለቤቱ በአንድ የግል የእናቶችና የሕፃናት ሆስፒታል የተገላገለችው ከስድስት ወራት በፊት ነው፡፡ የተገላገለችው በሙሉ ቀዶ ሕክምና በመሆኑ ለሁለት ቀናት በሆስፒታሉ አልጋ ይዛ እንድትቆይ ተደርጓል፡፡ መጀመርያ ላይ እንዲያስይዙ የተጠየቁት ሰባት ሺሕ ብር ቢሆንም በመጨረሻ የፈጸሙት ክፍያ በጥቅሉ አሥር ሺሕ ብር መድረሱን ነግሮናል፡፡
‹‹በወቅቱ በጣም ደንግጬ ነበር፡፡ ማንም ቢሆን ምጥን እንደ ቀላል ሊመለከተው አይችልም፡፡ የሁለት ነፍስ ጥያቄ በመሆኑ፣ እኔም በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ይደረግ፣ እንደዚህ መሆን አለበት ስባል መልሴ እሺ ብቻ ነበር፡፡ በመጨረሻ ያ ሁሉ ጭንቀት አልፎ ልጃችንን ይዘን ወደ ቤት ስንገባና ወደ ራሴ ተመልሼ ኪሴን፣ ኑሮዬንና ነገን ስመለከተው ሚስቴ በሰላም በመገላገሏ፣ ልጅ በማግኘቴ ተሰምቶኝ የነበረው የተለየ ደስታ ጠፍቶ ደስ በማይል ሌላ ስሜት ተተክቷል፡፡ ልጅ ገዛሁ ወይስ ልጅ ወለድኩ ነው የሚባለው?››
ካስያዘው ሰባት ሺሕ ብር በተጨማሪ ሌላ ሦስት ሺሕ ብር ገደማ እንዲጨምር ሲጠየቅ ደንግጧል፡፡ ሊጨምር ይችላል የሚል ምንም ዓይነት ግምት ያልነበረው ቢሆንም፣ ለምን? እንዴት? ብሎ አልጠየቀም፡፡ አዝኖ የተባለውን ክፍያ መፈጸምን መርጧል፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን ለሰዎች በተለይም ለተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች በመንገርና ጉዳዩን የመወያያ አጀንዳ በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶችን ማግኘት ችሏል፡፡ በዚህም በሕክምናው መሠረታዊ ልዩነት አለመኖሩን፣ ይልቁንም የተቋማቱ የቤት ኪራይና የሠራተኛ ክፍያ፣ ሌላም ሌላም ወጪ በተገልጋዩ ላይ ጫና መፍጠሩ በአንድ በኩል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ማጠቃለል ባይቻልም በማዋለዱ የሕክምና ዘርፍ ከሥነ ምግባር ውጭ የቢዝነስ ዓይነት አካሔድ እየተስተዋለ መሆኑን የሚያሳዩ አስተያየቶችን በብዛት እንዳገኘ አጫውቶኛል፡፡
ጥቂት የማይባሉ ወላጆች አምጠው ከመውለድ ይልቅ በሕክምና ባለሙያዎች በኦፕሬሽን ወይም በስቲች እንዲወልዱ ግፊት ይደረጋል የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ ሲሰነዘር ቢደመጥም፣ ያነጋገርነው ግለሰብ ሚስት ግን አምጣ ለመውለድ እንድትሞክር ተደርጎ ነበር፡፡
‹‹በግሉ የእናቶችና የሕጻናት ሕክምና ተቋማት የሚሰጠው የማዋለድ አገልግሎት በመንግሥት ከሚሰጠው የተሻለ እንደሆነ ጥያቄ የለውም፤ ነገር ግን አማካይ ክፍያ ከ3ሺሕ 500፣ ከፍተኛው 5 ሺሕ ከበለጠ አገልግሎቱን ከሌላ ቢዝነስ ለይቼ አላየውም፡፡ በሚዲያ ‹እናት በወሊድ መሞት የለባትም› ይባላል፤ እዚህ ጋ ደግሞ የማዋለድ ዋጋ አሥራ አምስት ሺሕ ደርሷል፤›› ብሏል፡፡
ሌላው አባት ደግሞ፣ ባለቤቱ የተገላገለችው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢሆንም፣ በእርግዝናዋ ወቅት ብዙም ትመገብ ስላልነበር ለሕክምና እርዳታ ለሦስት ቀናት በአንድ የእናቶችና የሕፃናት ክሊኒክ ተኝታ እንደነበር፤ ለሦስት ቀናት ከግሉኮስ በስተቀር ሌላ ምንም ዓይነት መድኃኒት ሳይሰጣት በመጨረሻ 5 ሺሕ ብር መክፈላቸውን ይናገራል፡፡ በመጨረሻ ሰዓታት አምጣ በሰላም የተገላገለችው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሆኑን ካስያዘው 200 ብርም በመጨረሻ የተወሰነ እንደተመለሰለት አጫውቶናል፡፡
ዶ/ር ሰለሞን ደሳለኝ የማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሕክምና አሥራ አምስት ዓመታትን፣ ስፔሻላይዝ አድርገው ደግሞ ለሰባት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሴማህ ከፍተኛ ክሊኒክ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
በየትኛውም የሕክምና ደረጃ የሚፈለገው አንድ እናት በተፈጥሯዊ መንገድ እንድትወልድ እንደሆነ፤ ነገር ግን የቅድመ ወሊድ ክትትልም ሆነ በምጥ ላይ የሚደረጉ ምርመራዎች ጠንከር እያሉ በሔዱ ቁጥር ችግሮች ይበልጥ እየታዩ የመሔዳቸው ዕድል እንደሚጨምር ይናገራሉ፡፡ ችግሮች ከተገኙ ደግሞ በቀዶ ሕክምና ወደማገላገል ሊኬድ ይችላል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ የሚነገረው የእናትም ሆነ የልጅ ሕይወት ከአደጋ ላይ እንዳይወድቅ ነው፡፡ ማዋለዱ ላይ የሚተኮረው ሕይወታቸውን ለማቆየት ብቻ ሳይሆን፣ የሁለቱም የወደፊት አካላዊና አእምሯዊ ጤናም ከግንዛቤ ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡
‹‹በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ላይ ያሉ ችግሮች በተለያዩ ክትትሎች በተገኙ ቁጥር በቀዶ ሕክምና የሚወልዱ እናቶች ይጨምራሉ፡፡ በርግጥ በየትኛውም አገር በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ሕክምና ምን ያህል መሆን እንደሚገባው የሚያሳዩ መለኪያዎች አሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የቀዶ ሕክምና በአንድ የጤና ተቋም ውስጥ ከ20 እስከ 25 በመቶ ብቻ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ግን አንዳንዴ ከዚያም ሊያልፍ ይችላል፡፡ በርግጥ የተቋሙ ሁኔታና ዓይነት ወሳኝ ነው መጠኑን ለመወሰን›› በማለት፣ የተለያዩ ሰዎች እንደሚሉት በቀዶ ጥገና የሚወልዱ እናቶች የበዙት የጤና ተቋማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት በሚከተሉት አካሔድ ሳይሆን የችግሮች በበለጠ ደረጃ መታየት መጀመር ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
እንደ እሳቸው አገላለጽ፣ የቤት ኪራይና የሠራተኞች ክፍያ፣ የመድኃኒትና የሕክምና መሣርያ፣ ሌሎች ወጪዎችም በማዋለድ አገልግሎት ክፍያ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አላቸው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ‹‹በቀዶ ሕክምና እንድንወልድ ጫና ተደረገብን፤›› የሚሉ ወላዶች አጋጥመዋቸው ስለሚያውቁ፣ የዚህ ዓይነቱን ጫና የሚፈጥሩ ሐኪሞች በፍጹም አይኖሩም ብለው አልደመደሙም፡፡
የሕክምና ባለሙያዎች በተለይም የነርሶች ከግሉ ዘርፍ ወደ መንግሥት የመሔድ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን፤ ይህም በግሉ ዘርፍ ለሚጠየቀው የማዋለጃ ክፍያ መጨመር የራሱ ድርሻ እንዳለው ይሰማቸዋል፡፡
የሕግ ተጠያቂነትም ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው የሚናገሩት ዶ/ር ሰሎሞን፣ ‹‹በግል የሕክምና ዘርፍ ትንሽም ይሁን ትልቅ ስህተት ቢገኝ ተጠያቂነቱ ከባድ ነው፡፡ በተለያዩ የግል ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ላይ የተመሠረቱ ክሶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህም በፍርሀት እንደዚህ ዓይነቱን ክፍተት ለማጥፋት የሚሰጠውን የማዋለድ አገልግሎት ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚጠየቀውን ክፍያ ከፍ እንደሚያደርገው ግልጽ ነው፡፡ እንዲያውም በተለያዩ አገራት በሕግ በኩል ያለውን ተጠያቂነት በመፍራት የጽንስና የማሕፀን ሐኪም መሆን ቀንሶ የታየበት አጋጣሚ አለ፤›› ብለዋል፡፡
ከቤት ኪራይና ከባለሙያ ደመወዝ በተጨማሪ፣ ለምሳሌ በአካልም ባይሆን በፈለጉ ሰዓት በማንኛውም ሁኔታ በስልክ ሐኪምን ማግኘት መቻል፣ እንደ ሕክምና ተቋማቱ ዓይነት የሚሰጡ የተለያዩ ተጨማሪ አገልግሎቶች የራሳቸው ዋጋ ይኖራቸዋል ብለውም ያምናሉ፡፡ እነዚህም ለአጠቃላይ ክፍያው መጨመር አስተዋጽዖ አላቸውና፡፡


