Tuesday, May 21st

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹የጥንቱ ትዝ አለኝ››

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በጥበበሥላሴ ጥጋቡ

በሳምንት መገባደጃ ላይ አካባቢ ሐሙስ ቦሌ ወደሚገኘው አሊዜ ክለብ ጎራ ቢሉ የኢትዮጵያን የ1950ዎቹና 60ዎቹ ሙዚቃን ይሰማሉ፡፡ በክብር ዘበኛ የሙዚቃ ጉዟቸውን ሀ ብለው የጀመሩት አየለ ማሞ በሳምንት አንድ ጊዜ የዱሮ ሙዚቃዎችን  ከአሁኑ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅ  ከሚጥሩት ባንዶች አንዱ በሆነው የአዲስ አኩስቲክ ሬናይሰንስ ባንድ አባል ናቸው፡፡

የባንዱ መሪ ግሩም መዝሙር ሙዚቃቸውን ከመጀመራቸው በፊት ይሄ ባንድ የተመሠረተው በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚወደዱትን ሙዚቃዎች ለማስታወስ እንደሆነ ይናገራል፡፡

‹ካሊፕሶ› በሚለው ዘፈናቸውና በማንዶሊን ተጫዋችነት የሚታወቁት አየለ ማሞ የባንዱ አባል ሲሆኑ፣ በሚዘፍኑበት ወቅት ተመልካቹም ‹ካሊፕሶ ወይ ካሊፕሶ›› በማለት ያጅባቸዋል፡፡ ‹‹የዱሮ ሙዚቃዎች ሰዎችን የመሳብ ኃይል እንዳላቸውና ትውልዱም ሙዚቃዎቹን እንዴት እንደሚወዳቸው መረዳት ችያለሁ፡፡ ሁለት ትውልድንም መሻገር ችሏል፤›› የሚሉት አየለ፣በሙዚቃ ሕይወታቸው ትልቅ ቦታ አደረሰኝ የሚሉት ክብር ዘበኛን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩት ገጣሚዎችና ሙዚቀኞች ሙዚቃውን እዚህ እንዳደረሱትም ይናገራሉ፡፡ ለአሁን ዘመን የጥበብ ቤተኞችም የሚሉት አላቸው፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ሙዚቀኞች አሉ፤ ወጣቱም የተቻለውን ያህል እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን እንደዱሮ ሙዚቃዎች ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎችን ለመሥራት ጠንክረው መሥራት አለባቸው፡፡››

ካዛንችስ አካባቢ ወደ ምትገኘው ፈንዲቃ አዝማሪ ቤት ዓርብ ምሽት ጎራ የሚሉ ከሆነ ቤቷ በሰዎች ጢቅ ብላ ትሞላለች፡፡ በአካባቢውም ግርግር አይጠፋም፡፡ ትንሻE ቤት ከአቅሟ በላይ ሰው ሞልቶባት ትጨናነቃለች፡፡ ተመለሱ የተባሉትም በሁኔታው ደስተኛ አይሆኑም፡፡ ሁለት ሰዓት አካባቢ ደርሰው ወንበር ሲያገኙ የሚቀበልዎት የዱሮ ሙዚቃ ነው፡፡ ወንበር ያጡም ወለል ላይ ተቀምጦ ማዳመጡን ችላ አይሉትም፡፡

ከ1950ዎቹ ጀምሮ ያሉትን የተመረጡ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ለሁለት ሰዓታት ያህል የሚያጫውቱት ቅዱስ (‹‹ዲጄ ሚጥሚጣ››) እና ዮናታን ናቸው፡፡ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ይደመጣሉ ተብለው የማይጠበቁ ዘፈኖች ማድመጥም የተለመደ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቀረጸ የሠርግ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡

ነቢዩ የ45 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ የዱሮ ሙዚቃዎችን ከመውደዱ የተነሣ ከሚሰሙበት ቦታ አይጠፋም፡፡ በፈንዲቃ ከሐቻምና ጀምሮ በየሁለት ሳምንቱ ዓርብ ቀጠሮውን ካዛንቺስ ላይ አድርጓል፡፡ እንዲህም አለን፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ 1960ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ማለት የተለመደ ነው፡፡ ይሄ ነገር ምናልባት አባባል ብቻ ቢመስልም፣ የአሁኑ ጊዜ ሙዚቃ ስንሰማ ግን በእውነቱ ያ ጊዜ ወርቃማ ዘመን ነው የሚለው አባባል እውነት ያደርገዋል፡፡››

የሚደመጡት የዱሮ አማርኛ ዘፈኖች ብቻ ሳይሆኑ  የኦሮምኛና ትግርኛ ዘፈኖችም አሉበት፡፡

ለማህሌት ገብረ መስቀል እዚህ ቦታ ላይ በጣም የገረማት ነገር ቢኖር በጊዜ ብዛት የተረሱ እና በየትኛውም ቦታ የማይሰሙ ዘፈኖች፣ ለምሳሌ የዘኒት ሙሃባን እዚህ ቦታ ላይ መስማቷ ነው፡፡

ዘኒት ሙሃባ ‹‹ከምበል ደፋ›› በሚለው ዘፈኗ የምትታወቅ ስትሆን በአጭር የሕይወት ቆይታዋ የራሷን አሻራ ጥላ ማለፍ እንደቻለች ማህሌት ታስረዳለች፡፡

የፈንዲቃ ባለቤት ታዋቂው የባህል ተወዛዋዥ መላኩ በላይ ሲሆን፣ ይሄንን ቦታ ያቋቋመው ለባህል ሙዚቃዎችና የዱሮ ዘፈኖችን ለአሁኑ እና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በሳምንቱ ውስጥ አዝማሪ ቤቶች እንደሚባሉት አይነት ዝግጅት ሲኖረው፣  በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ በሚኖረው ዝግጅት ደግሞ ከዱሮ ሙዚቃ በኋላ የባህል ባንዱ ኢትዮ ከለር ይጫወታል፡፡

መላኩ እንደሚናገረውም፣ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ፈንዲቃ የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ‹‹ብዙ ሰው የዱሮ ሙዚቃዎችን በጣም ይወዳል፡፡ አንደኛው ምክንያት  የአሁኖቹ ዘፈኖች በአንድ ኪቦርድ ላይ ስለሚሠሩ የተሰለቸ ድምፅ ስለሚያወጡ ይመስለኛል፡፡ የዱሮዎቹ  ግን የኦርኬስትራ አይነት ድምፅ ስላላቸው የተለያዩ የሙዚቃ መሣርያዎችንም መስማት ይቻላል፡፡›› መላኩ እንደታዘበው፣ የዱሮ ሙዚቃዎች አሁን በወጣቱ ዘንድ በብዛት ይሰማሉ፡፡

ለየት ያለ አስተያየት ያላቸው ደግሞ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ናቸው፡፡ አርቲስት ጌታቸው፣ የ1960ዎቹ ሙዚቃ ወርቃማ መባሉን እንደማይስማሙበት ይናገራሉ፡፡ ወርቃማነቱ በዛን ጊዜ ለነበረው ትውልድ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

ባሁኑ ጊዜ ያለው አለባበስ እንደተቀየረ ሁሉ  ሙዚቃውም  የራሱ ጉዞ አለው፡፡ ሙዚቃውም በፍጥነት እንደሚሠራና ቶሎ ቶሎ የሚል አካሄድ እንዳለውም ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉትም፣ ዱሮ የዱሮ ነበር፡፡ ዛሬ የዛሬ ነው፤ የዱሮውን ሙዚቀኞችና ሙዚቃውን ከማወደስና በተቃራኒው ደግሞ የአሁን ሙዚቀኞችን ከመንቀፍ፣ ሙዚቃው የራሱን ጉዞ እንዲጓዝ መተው አለብን ይላሉ፡፡

‹‹የያሬድ፣ የሞዛርት ወይም የቤትሆቨን ሥራዎች ለአሁኑ ትውልድ ኮ ለቅሶ ሊመስለው ይችላል፡፡››

በአሁኑ ጊዜ ሙዚቃው ቀድሞ ከነበረው ትልቅ ባንድ ወደ ኪቦርድ መምጣቱንም አርቲስት ጌታቸው አይቃወሙትም፡፡

‹‹እኛ ከዓለም የምንለይበት ነገር የለም፡፡ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘዴ እንደሚቀየረውም ሙዚቃውንም ይቀይራል፡፡ የዱሮውን ወርቃማ የአሁኑን ብራማ ዘመን ማለት የለብንም፡፡››

አርቲስት ጌታቸው፣  የተለያዩ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች መከፈት ለዚህ ትውልድ ጥሩ  እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የዱሮዎቹም ሙዚቃዎች የታሪክ አሻራቸውን እንደማሳረፋቸው በጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል የሚል መልዕክትም ያስተላልፋሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የሁለተኛ ዲግሪውን ማሟያውን ‹‹ሙዚቃ እና ፖለቲካ በ20ኛው ምእት ዓመት ኢትዮጵያ (Music and Politics in 20th century of Ethiopia) በሚል ርእስ የሠራው ስሜነህ በትረ ዮሐንስ፣ የ1960ዎቹን ወይም የዱሮ ጊዜን ወርቃማ ዘመን እያሉ ማሞካሸቱ በተወሰነ መልኩ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ያብራራል፡፡

‹‹የወቅቱን ዘፋኞች ብንመለከት የጥላሁን ገሠሠን ወይም የሙሉቀን መለሰንና የመሳሰሉት ታዋቂ ዘፋኞችን ሥራ ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ይሄም ሁኔታ ወጣቱ የራሱ ፈጠራ እንዳይሠራ ገድቦታል፡፡››

የመጀመርያው ሸክላ የታዋቂው ሙዚቀኛ አዝማሪ ተሰማ እሸቴ ሲሆን፣ ከወጣም 103 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚያም በኋላ ንጋቷ ከልካይና ፈረደ ጎላ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ በሸክላቸው አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡

በዛን ጊዜ የነበሩት የተለያዩ የባንዶች እንቅስቃሴና በቴአትር ቤቶቹ የሚደረገው ውድድር ሙዚቃውን አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንዲሔድ እንዳደረገው ስሜነህ ይናገራል፡፡ ‹‹በዛን ጊዜ የነበሩት ሙዚቀኞች በቴሌቬዥንና በሬዲዮ ይቀርቡ ነበር፡፡ የምሽትም ሕይወት በደርግ ጊዜ ቢቀዘቅዝም ከዛ በፊት በነበረው ጊዜ ሞቅ ያለ  አካሔድ ነበረው፤›› በማለትም ያክላል፡፡

‹አቢሲኒያ ስዊንግ› በሚል ጥናታዊ ፊልምና ተከታታይ 27 ቅጽ ኢትዮጲከስን ያዘጋጀው ፍራንሲስ ፋልሴቶ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ከየት ተጀምሮ የት እንደደረሰ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ‹‹የዘመናዊ ሙዚቃ›› ታሪክ የጀመረው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፣ በተለይም ከዓድዋ ድል በኋላ የውጭ አገር ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሌላውን ዓለም ተጽዕኖ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ማሳረፉ አልቀረም፡፡ በተለይም አፄ ኃይለ ሥላሴ ኢየሩሳሌምን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ በአፄው ግብዣ 50 የሚሆኑ አርመናውያን ሙዚቀኞች መምጣት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃም መጀመሩን አብስሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቃ የአርመናውያን ተፅዕኖ አለው ቢባልም፣ አርመናውያን በስምንት ስኬል ወይም (Octatonic) በሚባለው የሚሠራ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ግን በአምስት ወይንም (Pentatonic) ስኬል ይጠቀማል፡፡ ፋልሴቶ እንደሚናገረውም፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከባህል ሙዚቃው ብዙ ነገሮችን ወስዷል፡፡

በመጀመርያ ላይ የነበሩት ሸክላዎች የሚቀረጹት በሀገር ፍቅር ቴአትር ሲሆን፣ በ1960ዎቹ መጀመርያ ላይ አምሀ እሸቴ ትውልድ የማይረሳቸውን ዓለማየሁ እሸቴ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ግርማ በየነ የመሳሰሉትን ሥራዎች በሸክላ አስቀርጻFል፡፡

ስሜነህ እንደሚያስረዳው፣ ከ1960 ጀምሮ እስከ ደርግ መባቻ ድረስ 100 ያህል ሸክላዎችን አምሀ ቀርፆ አውጥቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የነዚህ ሙዚቃዎች ኮፒ ራይት ባለቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ 18  ባንዶች  ከነሱም መካከል የፈረንሳዩ ባንድ ‹‹አካሌ ውቤ››፣ ‹‹ኢምፔሪያል ታይገር ኦርኬስትራ››፣ ‹‹ደቦ›› እና ‹‹አራት ኪሎ›› የሚባሉት የዱሮዎቹን የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች አንዳንዴም ከጃዝ ጋር በማቀላቀል ይጫወታሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሶማሊያዊው ራፐር ኬናን ‹‹ትሩባዶር›› በሚለው አልበሙ ላይ የጌታቸው መኩሪያን፣ የጥላሁን ገሠሠ እና የዓለማየሁ እሸቴን ሥራዎች ቀላቅሏል፡፡

በቅርብ ጊዜ ወጥቶ በአሜሪካ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት የቻለው የዴሚየን ማርሌ እና የናስ አልበም የሆነው ዲስታንት ሪላቲቭስ (Distant Relatives) የሙላቱ አስታጥቄን ‹‹የእገሌ ትዝታ››ንም አካትቷል፡፡

አማርኛን የሚናገረው ቅዱስ፣ በአምስት ዓመታት ቆይተው የኢትዮጵያ ላይቭ ሙዚቃ እንዴት እንዳደገ መረዳት ችሏል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም የዱሮዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተሰሚነት እንዳላቸውም ይናገራል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት አድርጎ ከሚያቀርባቸው ውስጥ የኢትዮ ጃዝ ፈጣሪ የሆነው ሙላቱ አስታጥቄ፣ እስከ ኦስካር መታጨት ደረጃ ለደረሰው ‹‹ብሮክን ፍላወርስ›› (Broken flowers) የሙዚቃ ማጀቢያ መሥራቱ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጲከስ መውጣት ለብዙዎች በቀላሉ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡

የተለያዩ ሙዚቃዎችን በትርፍ ጊዜው የሚሰበስበው ቅዱስ፣ ለቴፕ ካሴቶች ጥልቅ ፍቅር ያለው እንዳለውና፣ ለዚህ መሠረት የሆነው ደሴ ውስጥ የሚገኘው የትዝታ ሙዚቃ ባለቤት ጸጋዬ ሐጎስ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በነዚህም አምስት ዓመታት የተለያዩ ሙዚቃዎችን ከታዋቂዎቹ አማርኛ ዘፈኖች በተጨማሪ ብዙ ትኩረት አላገኙም የሚላቸውን ኦሮምኛና አፋርኛ ዘፈኖች ሰብስቧል፡፡ አምና ታምራት ሥዩም ከሚባል ጓደኛው ጋር ሙዚቃ ቤት የከፈተውም  ለየት ያለ ሙዚቃ ለማስተዋወቅ እና በገበያውም ላይ በቀላሉ እንዲገኙ በማለት ነው፡፡

‹‹የዛን ጊዜ የነበረው ሙዚቃ ለየት ያለ ነበር፤ ዘፋኞቹም በጣም ጠንካራ ድምፅ ነበራቸው፡፡ የሚቀረጹትም በባንድ ታጅበው ስለነበር እዛው ቦታ ላይ የመገኘት ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ የአሁኖቹ ሙዚቃዎች ግን በአንድ ኪቦርድ ስለሚታጀቡ ጥራት ይጎድላቸዋል፡፡››

አቧሬ አካባቢ የምትገኘው ሙዚቃ ቤቱም የኤርትራ ዘፋኝ የሆነችውን ፀሐይቱ ባራኪን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጲከስ ሲዲዎች፣ የጋሻው አዳል፣ የጥላሁን ገሠሠ፣ የአስቴር አወቀ፣ የሙሉ ቀን መለሰ፣ የብዙነሽ በቀለ እና ሌሎች ባህላዊ ሙዚቃዎችን ይዛለች፡፡ ካሴቶቹንም 15 ብር እንደሚሸጣቸውና ጥሩ ሙዚቃ የሚወዱ ደንበኞችም እንዳሉትም ይናገራል፡፡

‹‹የቀድሞው ሙዚቃ ሲነሣ የዘመኑ አርቲስቶች አይረሱም፡፡ ብዙዎቹ በድህነት ቢያልፉም ትዝታቸውን ግን ጥለው አልፈዋል›› የሚለው የዱሮ ሙዚቃ ወዳጁ ተፈሪ ለማ ነው፡፡ አያይዞም፣ ‹‹በዚያን ጊዜ የነበሩት ዘፋኞች፣ ገጣሚዎች፣ አቀናባሪዎችና በአጠቃላይ አርቲስቶች እንደ ሻማ ራሳቸውን አቅልጠው፣በሥራቸው እንድንደሰት አድርገውናል፤ ባለውለተኝነታቸውን ለአንድ አፍታ መዘንጋት የለብንም፤ በቻልነው ሁሉ መርዳት አለብን፡፡›› ብሏል፡፡