በምዕራፍ ብርሃኔ
የሕፃን ቅድመ ዓለም ሙሉ እናት ወ/ሮ ዘርፌ አበበ በ1998 ዓ.ም. በኤድስ ምክንያት ለኅልፈት ከመብቃታቸው በፊት ሕፃን ቅድመ ዓለምንና ሌላ አንድ ሴት ልጃቸውን ለእናታቸው ለወ/ሮ ታደለች ዳምጠው አደራ ይሰጣሉ፡፡
በዚያም መሠረት እኚህ አያት ለልጅ ልጆቻቸው ለቅድመ ዓለምና ለሰላማዊት ሞግዚትና አስተዳዳሪ እንዲሆኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 225/01 መሠረት በ24/11/1999 ዓ.ም. የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት አጽድቆላቸዋል፡፡
ይሁንና የታዳጊዎቹ አባት አቶ ሙሉ አበራ ጤናቸው እጅግ እየታወከ የመጣው ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ነበርና ትንሿን ልጃቸውን (ቅድመ ዓለምን) ይዘው ወደ ጎጃም ይዘልቃሉ፡፡ እዚያም በነበራቸው ቆይታ በጠና ታመው በ1999 ዓ.ም. ለኅልፈት ይዳረጋሉ፡፡ አባት አቶ ሙሉ ከማለፋቸው በፊት ሕፃኗን ልጃቸውን (ቅድመ ዓለምን) ለወንድማቸው ለአቶ ገበየሁ አበራ አደራ ብለው ነበር፡፡
በተሰጣቸው አደራ መሠረት አቶ ገበየሁ ቅድመ ዓለምን እኩዮቿ ከሆኑ ስድስት ልጆቻቸው ጋር ለማሳደግ በገቡት ቃል መሠረት ለታዳጊዋ ሞግዚት ለመሆን ባቀረቡት ጥያቄ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደብረ ኤልያስ ወረዳ ፍርድ ቤት በ8/10/2001 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ጥያቄያቸው ሰምሮላቸዋል፡፡
ይሁንና ሕፃናቱን ለማሳደግና ሞግዚት ለመሆን መጀመርያ ፍርድ የተሰጠኝ እኔ ነኝ የሚሉት ወ/ሮ ታደለች ከታዳጊዎቹ አጎት ጋር የክስ ምልልሶችን ቢያደርጉም በመጨረሻ ላይ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ውሳኔውም እንደሚያትተው ከሆነ በአያትና በአጎት መካከል ተነሥቶ የነበረውን ክርክር በሽምግልና ተፈትቷል፡፡ በመሆኑም ሕፃኗ ቅድመ ዓለም አሁን ባለችበት ሁኔታ ከአጐቷ ጋር እንድትኖርና በየዓመቱ መጨረሻ ክረምቱን ከአያቷ ጋር እንድታሳልፍ እንደተስማሙ አትቶ፣ ክርክሩ እንዲቋረጥና መዝገቡም እንዲዘጋ ይወስናል፡፡
ይሁንና አያት ስምምነቱ ላይ ተታልያለሁ በማለት ቅሬታ እንዳላቸው በመግለጽ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤት ይላሉ፡፡ ቢሆንም ግን መዝገቡ እንደገና የተንቀሳቀሰበት ችሎት ላይ ተከሳሹ አቶ ገበየሁ ባለመገኘታቸው ምክንያት፣ በስምምነት ሐሳብ ስለመለያየታቸው ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ ስለማይችል በሚል፣ ከሳሽ በስምምነቱ መሠረት አፈጻጸሙ ከሚጠይቀው ውጭ በተንቀሳቀሰው መዝገብ ላይ እንደማይታይ አትቶ የአዛውንቷን አቤቱታ ውድቅ አድርጎ መዝገቡን ይዘጋዋል፡፡
ሁኔታዎች በእንዲህ መልኩ የተቋጩ ቢመስሉም፣ የስምንት ዓመቷ ሕፃን ቅድመ ዓለም ከ20 ቀናት በፊት፣ ለ66 ዓመቷ አያቷ እና ለ15 ዓመቷ እህቷ ‹‹ጅቡ ሳይበላኝ ወንዙ ሳይወስደኝ ድረሱልኝ›› በማለት በአንዲት እናት በኩል ደብዳቤ ልካለች፡፡ የደብዳቤው ይዘትም በከፊል የሚከተለውን ይመስላል፡፡ “ውድ አያቴ፣ ምንም እንኳ ባንገናኝም ለአባቴ ልቅሶ ጎጃም ድረስ መጥተሽ እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ ለአጎቴ የፍርድ ቤት መጥርያ ሁለት ጊዜ ይዘሽ መጥተሽ ይገሉኛል ብለሽ ሳታይኝ ተመልሰሽ ሔድሽ፡፡ ለነገሩ አያቴ፣ እንኳን ተመለስሽ፡፡ ቢያገኙሽ ኖሮ ወይ አንድ ነገር ያደርጉሽ፤፡፡ ወይም ደግሞ ይገድሉሽ ነበር፡፡ ይህቺ ባልቴት አያትሽ በእዚህ አቅሟ እኔን አሸንፋ አትወስድሽም፡፡ አሁንም አሁንም እየመላለስሽ አንዴ አያቴ አንዴ እህቴ የምትይው የት ታውቂያቸዋለሽ? እያለ አጎቴ ይሰድበኛል፡፡ እኔ የምፈልገው አያቴ፣ ይኼን ደብዳቤ ለፍርድ ቤት ሰጥተሽልኝ አያቴንና እህቴን እንደምፈልግ እንዲታወቅልኝ ነው፡፡ አንገቴን አሞኝ ጆሮ ደግፍ ነው እያሉ ባቄላና ስንደዶ ያስሩልኛል፡፡ አባቴና እናቴ ወይም አንቺ ራስሽ ብትሆኚ ኖሮ ሲያመኝ ሐኪም ቤት እወሰድ ነበር፡፡ አያቴንና እህቴን እንደክፉ እየጠላ ይናገረኛል፡፡ እኔንና እህቴን በደህና የምታገናኙን እግዚአብሔርና ፍርድ ቤት ናችሁ፡፡ ለኔማ ቀን ጎድሎብኛል፡፡ እኔ ራሴን በኩርኩም ስለምመታ በሽተኛ ሆኛለሁ፡፡ እንደምንም ተብሎ ፍርድ ቤት እንድወሰድ እፈልጋለሁ፡፡ እህቴ ጅቡ ሳይበላኝና ወንዙ ሳይወስደኝ ቶሎ ድረሽልኝ፡፡ አያቴ ያንቺ ናፍቆት ቀንና ሌሊቱን አላስቀምጥ ብሎኛል፡፡ አባቴ እዚህ አምጥቶ ጥሎኝ የሔደው አያቷን ጥሩልኝ ሲላቸው እንቢ ብለውት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን አባቴ እኔን አደራ የሰጠው ለአክስቴ ቢሆንም፣ አጎቴ ግን በጉልበት እኔን እየጎዳኝ ነው፡፡ እናትና አባቷ ሞተዋል እያለ በእኔ ስም ዕርዳታ እየተቀበለ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡ እናትና አባቷን ገፍታ ደግሞ እኛንም ትገፋለች ይለኛል፡፡”
አያቷ ይህን ደብዳቤ እያሳዩን፣ “እንግዲህ ምን ላድርግ፣ ወለል ብዬ ሔጄ ልጄን እንቅ አድርጌ አልወስድ የሰው አገር ነው፣ ለሕይወቴም እሠጋለሁ፤›› ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ይገልጻሉ፡፡
እኚህ አያትም ልጃቸውን ወ/ሮ ዘርፌን ሲያስታምሙ በቫይረሱ ቢያዙም፣ የቅድመ ዓለምን ታላቅ እህት ሰላማዊትን የሚንከባከብ በጎ አድራጊ ድርጅት ስለማይጠፋ፣ እርሷንም አምጥተው እንድትረዳ ማድረግ ቢፈልጉም፣ ሁኔታዎች እንደተወሳሰቡባቸው ይገልጻሉ፡፡
‹‹ለአኗኗርም ሆነ ለምግብ ያለችበት እንደማይመቻት፣ የምትሔደው በባዶ እግሯ መሆኑን፣ ፀጉሯም መላጨቱን፣ እያመማትም መሆኑን፤›› ደብዳቤውን ያመጣችላቸው እንዳስረዳቻቸው ገልጸዋል፡፡
ሕፃኗ ወደ ጎጃም ከሔደች ሁለት ዓመት ከአሥር ወሯ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ አያት፣ “የአደራ ልጄን እንዴት ላግኝ?” እያሉም ይጠይቃሉ፡፡


