Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ሐበሻው ጠላፊ

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

ፈረንጅ አውሮፕላን
ጠልፎ በጥፋቱ
ቢብጠለጠል ስሙ
ዳር ከዳር ተዳርሶ

ስለተወራበት
ብዙ አትገረሙ
ይልቅ ተገረሙ!
ባ’ በሻው ጠላፊ
ባ’ገሬው መናጆ
ህሊናውን ሽጦ
ጨቅላ እህቱን ጠልፎ
በቀለሰው ጎጆ!
(ዳኜ አሰፋ፤ የአዳም ስሞታ፣ 2ዐዐ1)

****************
ይቺው ወርቅ ያንጥፉ
ይቺው ወርቅ ያንጥፉ ይቺው ባለቤቴ ዛሬ እንዲህ ዘምና ፍዳዬን ልታስቆጥረኝ ያኔ ክፉኛ ተጃጅላብኝ ነበር ነው የምላችሁ፡፡ የዚያን ለት ልብሷንና ጫማዋን ከገዛን በኋላ ላዳራችን ወደ አልቤርጎ ነበር የሔድነው፡፡ አልጋ ከያዝን በኋላ ዘበኛውን ወደ ዘመዶቻቸው ቤት ሸኝተን ለስላሳ መጠጥ አስመጥተን እየጠጣን ሳለን ሳልገዛው የረሳሁት እቃ ስለነበር ወደሱቅ ትቼያት ሄጄ ሳለሁ የሠራችሁ ሥራ ምን ጊዜም አይረሳኝም፡፡

የተከራየነው የሽቦ አልጋ የረገበ ወይም የተወጠረ መሆኑን ለመፈተሽ ያህል አንድ ሁለቱ በቁሜ እየወደቅሁበት ስንጋለልበት ለካስ ወርቅ ያንጥፉ አይታኝ ኖሯል፡፡ እኔ ሱቅ ደርሼ እስክመጣ ድረስ እኔ እንዳደረግሁት ለማድረግ ስትንደረደር ሔዳ አልጋው ላይ ስትወጣ ሽቦው አንጥሮ ከወለሉ ላይ ያነጥፋታል፡፡ ነፍስና ሥጋዋ በድንጋጤ ሲለያዩ ከወደቀችበት ተነሥታ፡ ‹‹የምን ሰይጣን ነው ገፍትሮ የጣለኝ›› ብላ ካልጋው ስር ባይኖቿ ስታፈላልግ ትልቅ ነጭ የሽንት ‹‹ፖፖ›› ታያለች፡፡ ‹‹ውይ ለካስ ይኸ ሰይጣን ኖሯል ካልጋው ስር ተቀምጦ አፈር ድሜ ያስጋጠኝ›› ትልና ፈርታ ከነክንብንቧ ከክፍሉ ጥግ ትቆማለች፡፡ ቀስ ብላ ወደ ፊት ለፊቷ ስታይ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ትልቅ መስታዋት መልሶ መልኳን ያሳያታል፡፡ እሷ ግን የራሷ መልክ መሆኑን ልብ ባለማለቷ ‹‹ወይ ጉዴ! የቤቷም ባለቤት ሁኔታዬን ቁመው እያዩኝ ናቸው ለካ›› በማለት ከቆመችበት እንባዋን ታፈሰዋለች፡፡

በዚህ ጭንቀት ላይ እያለች ከሱቅ ተመልሼ ስመጣ የኮካ ኮላ ጠርሙሶቹና ብርጭቆዎቹ በሙሉ ከሲሚንቶው ወለል ላይ ተከስክሰዋል፡፡ የድንጋጤ ውጋት ቀስፎ እንደያዘኝ ‹‹ወርቅ ያንጥፉ! ወርቅ ያንጥፉ!›› እያልኩ ወደ ክፍሉ ስገባ ከግድግዳ ጥግ ቆማ እየተንሰቀሰቀች ስታለቅስ አገኘኋት፡፡ ምን እንደ ሆነች ስጠይቃት አሁን ያጫወትኳችሁን ድርጊቷን ገለጸችልኝና የገመተችውና ያሰበችው ሁሉ እሷ እንዳለችው አለመሆኑን በጥሞና አስረድቼያት አረጋጋኋት፡፡
(አበራ ለማ፤ የማለዳ ስንቅ፣ 1980 ዓ.ም.)

**********************
ኔውትሮን
የኔውትሮን ቦምብ በጣም ከፍተኛ ራዲኤሽን የሚያስከትል እጅግ አረመኔያዊ ዓይነት የኑክሌየር መሣሪያ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሕንጻዎችና መኖሪያ ቤቶችን እጅግም ሳይነካ በሕያው ነገሮች ሁሉ ከፍተኛ እልቂት እንዲያደርስ የተፈለሰፈ መሣሪያ ነው፡፡ ከሌላ ዓይነት ራዲኤሽን ጋር ሲነጻጸር የኔትሮን ራዲኤሽን ኃይል በአሥር እጅ የበለጠ ነው፡፡ ኔውትሮኖች በሰው ልጅና በእንስሳት የአካል ክፍሎች ውስጥ ገብተው ሕዋሶችን ያፈርሳሉ፡፡ የኔውትሮን ራዲኤሽን አሰቃቂነቱ በቀጥታ በመግደሉ ብቻ ሳይሆን ሕያው ነፍሳትን በመመረዝ ለሚመጡት ትውልዶች ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት በኔውትሮን ራዲኤሽን የተመረዘ ሰው የኋላ ኋላ ይሞታል፤ ልጆች ቢወልድም ልጆቹ ይሞታሉ፤ ወይም አካለ ጎደሎዎች ይሆናሉ፡፡
(ሶሶሪኃ፤ኖቨስቲ አገልግሎት ማተሚያ ቤት፣1983)

****************
አውራ ጣት
አውራ ጣት ከሌሎቹ ጣቶች ተለይቶ አጠርና ወፈር ብሎ ከዳር የሚገኘው ይህ ጣት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አለው፡፡ ሌሎች ጣቶች ታጥፈውና ተሰብስበው አውራ ጣት ብቻውን ወደ ላይ ተቀስሮ ሲታይ፣ አዎንታዊ በጎ ትርጉም ይሰጣል፡፡ (በዋና መዲናችን ያለ አንድ የንግድ ተቋም ይህን ጣት “ዝ” ከሚል አንድ ሆሄ ጋር በንግድ ምልክትነት ተጠቅሞበታል፡፡ “ዝ” በጉራጊኛ ቋንቋ “ይኸው!” እንደማለት ነው፡፡) “ትክክል ነው”፣ “በርታ!”፣ “ጥሩ ነው.. በዚሁ ቀጥል!”፣ “ተስማምቼያለሁ”.. የሚሉ ትርጓሜዎች ይኖሩታል፤ ከላይ በተመለከተው ሁኔታ ስንጠቀምበት፡፡ በተቃራኒው አቅጣጫውን ለውጦ.. ከላይ ወደ ታች ሲዘቀዘቅ ደግሞ.. አሉታዊ ትርጉም ይሰጣል፡፡ “ተዘቅዘቅ!” የሚል፡፡    
(የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር፤ ብርታት፣ 2003)

****************
ከምሁራን አንደበት
•    የሌሎች ስህተቶች ተገንዝበው ራሳቸውን ከስህተት የሚያርቁ ሁሉ ከፀፀት ነፃ ናቸው፡፡
(ሬይሌመን)
•    ጨለማን ሲረግሙ ከመኖር አንዲት ቁራጭ ሻማ ፈልጐ መለኮስ ይበጃል፡፡
(ኮንፊሸስ)
•    የማንም ጥገኛ ሳትሆን ለመኖር ተጣጣር፡፡             (ሳሙኤል ጆንሰን)
•    ፍቅር የተፈጥሮ ሁለተኛ ፀሐይ ነው፡፡             (ጀርጅ ቻፕ ማን)
•    ያለ ጥረት ምንም ዓይነት ትልቅነት አይገኝም፡፡        (ኤመርሰን)
•    ከመጀመሪያ ሳቅ የመጨረሻ ፈገግታ ይሻላል፡፡         (ጆን ሬዲ)
•    የሚያናድደኝ ለእኔ መዋሸትህ ሳይሆን ከእንግዲህ ላምንህ አለመቻሌ ነው፡፡
(አሪስጣጣሊስ)
•    ሰውን የሚገድለው ሥራ ሳይሆን ጭንቀት ነው፤ ሥራ ጤንነት ሲሆን ጭንቀት ግን የዛገ ምላጭ ነው፡፡                    (ኤች ደብሊው ቢቸር)

****************
(የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ ዜና መጽሔት፣ 2003)

ሙያተኛ ሴት
በዚህ የሴቶች እኩልነትና ነፃነት በተከበረበት ጊዜም ላይ ቢሆን ወንነዶች ሙያ የታደሉ ሴቶችን ይናፍቃሉ፡፡ ይህ ማለት ሞያ ያላት ሴት ከሌሎች በበለጠ እንመርጣለን ማለት አይደለም፡፡ ባለሥራው ወንድ ሥራ ካላት፣ የራሷ ሐሳቦችና ተስፋዎች ካላት ሴት ጋር መሆንን ይመርጣል፡፡ ሆኖም የራሳቸው የሆነ ሥራ ያላቸው ሴቶቻችን ትንሽ ሞያ ያላቸው ቢሆኑም እንኳን ደስታችን ይጨምራል፡፡

እውነታው ወንዶች ከሴቶች እንክብካቤን ከመፈለጋቸው ላይ ነው፡፡ ወንዶች የሚያፈቅሯት ሴት እናቶቻችን፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ሲያደርጉልን የነበረውን ነገር እንድታደርግላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ቅቤ ስለመናጥና ልብስ ስለመስፋት እያወራን አይደለም፡፡ ምግብ በቤት ውስጥ እንዲበስልልንና ጥዋት ወደ ሥራ ስንሔድ አልጋው እንዲነጠፍልን ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡

ከሆዱ ውጭ ወደ ወንድ ልብ ለመዝለቅ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ ባለሥራ ወንድ ምግብ ቤቱ ውስጥ ቢዘጋጅለት ያበረታታል፡፡ ይህ ሁኔታ ፍቅረኛው ከራሷ ጊዜ ላይ ወስዳ ለሱ ምግብ በማብሰል እንክብካቤን እንደምታደርግ ያመለክተዋል፡፡ ሁሌም የታሸገ ምግብ ከመብላት ታድገሽዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታሽ እናቱ ሕፃን እያለ ስታደርግለት የነበረውን ነገር እንዲያስታውስ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ፍቅረኛው ባዘጋጀችለት ምግብ መንስኤነት የብርታት፣ የግልግልና የትዝታ ስሜት ያገኛል፡፡ ቤት ውስጥ የምታዘጋጂለት ምግብ ጓደኛሽን ወዳንቺ በጣም ያቀርበዋል፡፡
(ናኦሚ፤ የወንዶች ገመና፣ 2000)

****************
ከበር
ሜሪ ኩሪ “እጅግ ታላቋ ፖላንዳዊት” ተሰኘች

የዓለም ሴቶች ቀን “ማርች ኤይት”ን (የካቲት 29) 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የፖላንድ የታሪክ ቤተመዘክር፤ በኢንተርኔት ባካሔደው መጠይቅ በተሳታፊዎች ዘንድ የፖላንዷ ተወላጅ፣ ሜሪ ኩሪ እስክሎዶቭስካ፤ በአገሪቱ ታሪክ “እጅግ ታላቋ ፖላንዳዊት” መሰኘቷን ማስታወቁን ደቸቬሌ ዘገበ፡፡

የዘመናዊው ፊዚክስ እናት የምትባለው ሜሪ ኩሪ እስክሎዶቭስካ፣ እ.ኤ.አ. በ1867 ወደ ፓሪስ (ፈረንሳይ) ተጉዛ፣ በዚያም በ1895 ፒዬር ኩሪ የተባለውን ፈረንሳዊ አግብታለች፡፡ ሜሪ ኩሪ የፖሎኒዬም እና ሬዲየም ንጥሮችን በመነጠል፣ በተለይ ሬዲዬም፣ ለሕክምና አገልግሎት እንዲውል ያደረገች ሳይንቲስት ናት፡፡ በአቶም ጨረር (ራዲየሽን) ባደረገችው ምርምር እ.ኤ.አ. በ1903 በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ከተቀበለች በኋላ፣ በሥነ ቅመማ 2ኛ የኖቤል ሽልማት አግኝታለች፡፡ በመሆኑም ይኸው መቶኛ ዓመት፣ ዓለም አቀፍ የሥነ ቅመማ መታሰቢያ ዘመን በተሰኘው የዘንድሮው ዓመት እንዲታሰብ የፖላንድ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ደንግጓል፡፡ 

* *  * *  *  * * *
የ17 ዓመቱ ‹‹ሕፃን››

ጆርኒ ባላዊንግ የፊሊፕንስ ተወላጅና የ17 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ነገር ግን ዕድሜው ከአንድ ዓመት በታች የሆነ ሕፃን ያለውን ቁመት ያህል ያጠረ ነው፡፡ ወይም ቁመሩ ከ22 ጫማ አይበልጥም፡፡ በዓለም ውስጥ በጣም አጭር ሰው መሆኑም ተገልጿል፡፡

ጆርኒ ዕድሜው አንድ ዓመት ከሞላ በኋላ ዕድገቱን አቁሟል፡፡ በእግሩ ለመራመድ ቢሞክርም መቆም አይችልም፡፡ ጆርኒ ከወላጆቹና ከሦስት ታናናሽ ወንድሞች ጋር አብሮ እንደሚኖር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እናቱ ሚሲዝ ኮንሰፕሲዩን ‹‹ጆርኒ በየደቂቃው እንድንከባከበው ይፈልጋል፤ በድጋፍ መሔድ ይችላል፡፡ ሕመም ስለሚሰማው ግን መቆም አይችልም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡