Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በመዘጋጀት ላይ ያለው የአፋር የቤተሰብ ሕግ ከሴቶች መብቶች አንጻር ሊኖረው የሚችለው ክፍተ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በጌታሁን ወርቁ

ሴቶች ያሏቸው መብቶች ከሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር እየተስተካከሉ በዝርዝር ሲሻሻሉ የቆዩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱና የስድስት ክልላዊ መንግሥታት የቤተሰብ ሕጎች በዚህ መሠረት ተሻሽለው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ በሶማሌ፣ በአፋርና በሐረሪ ክልሎች በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተካተተውና የሴቶችን እኩልነት ያላገናዘቡና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረሩ ድንጋጌዎችን የያዘው የቤተሰብ ሕግ ተፈፃሚነት ያለው ሲሆን፣ ሕጉን የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በሶስቱ ክልሎች የቤተሰብ ሕጉን የማሻሻል ሥራው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ከጸደቀ ከብዙ ዓመታት በኋላ ዘግይቶ ለመጀመሩ ምክንያቱ” መገመት ቢያስቸግርም፣ ክልሎቹ ካላቸው የባለሙያ እጥረትና ብዙ የእስልምና ተከታዮች የሚገኙባቸው በመሆኑ ከእምነት ጋር የሚኖረውን መጣረስ ለማለሳለስ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡ ጸሐፊው የሶማሌና የሐረሪ የቤተሰብ ሕግ እንደ አፋር ሁሉ በረቂቅ ሕጉ ላይ ውይይት እየተደረገ የነበረ መሆኑን ቢያውቅም፣ ሕጎቹ ወጥተው ሥራ ላይ ስለመሆናቸው ያደረገው ማጣራት አልተሳካለትም፡፡

ስለዚህ በዚህ ጽሁፍ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን የቤተሰብ ሕግ በተመለከተ ቀደም ሲል ከተደረጉ ውይይቶች የተነሱት አከራካሪ ነጥቦችን በማንሳት ሕጉ ሳይወጣ የዘገየበትን ምክንያት ለመጠቆም ሙከራ ተደርጓል፡፡ የቤተሰብ ሕጉን የማውጣት ጥያቄ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለክልሉ ምክር ቤት ባደረገው የሰብዓዊ መብቶች ግንዛቤ ሥልጠና ላይ የተነሳ ሲሆን፣ የሕጉ መውጣትም ለሴቶችና ለሕጻናት መብቶች መከበር የራሱ አስተዋጽኦ ስላለው “የዓለም የሴቶች ቀን” በሚከበርበት በዚህ ሳምንት ወቅታዊ እንዲሆን ታስቦ ተጽፏል፡፡ የሐረሪና የሶማሌ ክልሎች የቤተሰብ ሕጎቻቸውን ያላሻሻሉ ከሆነ እንደ ግብዓት ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በክልሉ የሚያደርጉትን የቅስቀሳ ስትራቴጂ ለማገዝ እንደሚረዳ ይታሰባል፡፡

በአፋር ክልል የተዘጋጀው ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ በአብዛኛው ከተሻሻለው የፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር የጋብቻ ዕድሜ፣ ጋብቻን ለመፈጸም መሰጠት ስላለበት ፈቃድ፣ የጋብቻ ውጤቶች፣ የቤተዘመድ ሽምግልና ሚና፣ የፍቺ ምክንያቶችና መሠል የሴቷን መብት የሚመለከቱ ነጥቦች ከፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ አቋም ተወስዶባቸው በረቂቁ እንዲካተቱ ተደርጓል:: ሆኖም በጋብቻ ላይ ጋብቻና ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት ስለመኖር የተያዘው አቋም አከራካሪና የሴቷን መብት በአግባቡ የሚጠብቅ አይደለም፡፡ በእነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ ከተደረጉት ውይይቶች ለመረዳት እንደተቻለው የክርክሩ ምንጭ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34 እና 78 የኃይማኖትና የባህል ሕጎች በቤተሰብና ግላዊ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ቢገልጽም፣ ገደቡን በግልጽ ባለማመልከቱ ነው፡፡ ሆኖም የሕገ መንግሥት የበላይነትንና ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ቦታ መሠረት ካደረግን የኃይማኖትና የባህል ሕጎች ተፈጻሚ የሚሆኑት የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች እስካልጣሱ ብቻ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91 “ባሕል ነክ ዓላማዎች” በሚል ርዕስ በንዑስ ቁጥር 1 “መንግሥት መሠረታዊ መብቶችንና ሰብዓዊ ከብርን፤ ዴሞክራሲንና ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ ባሕሎችንና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት” በሚል ደንግጓል:: ይህ ድንጋጌ መንግሥት እንዲጎለብቱ ሊረዳቸው የሚችለው ባህሎች ወይም ኃይማኖቶች ከመሠረታዊ መብቶችና ሰብዓዊ ክበር ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በጋብቻ ላይ ጋብቻ አንድ ወንድ ከሁለት በላይ ከሆኑ ሴቶች ጋር እኩል የማድረግ ውጤት ስላለው፣ ከእኩልነትና ከሰብዓዊ መብት ጋር መጋጨቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡

የፌዴራል ሸሪዓ ፍ/ቤቶችን አቋም ለማጠናከር የወጣው አዋጅ ቁጥር 188/1992 ዓ.ም. የሸሪዓ ፍ/ቤቶችን ሥልጣን በመለየት ሕጋዊ መሠረት ይስጥ እንጂ በሸሪዓ ፍ/ቤቶች ተፈጻሚ ስለሚሆነው መሠረታዊ ሕግ (Substantive law) ይዘት አልደነገገም፡፡ ከዚህ አንጻር በሙስሊም የዶግማ ት/ቤቶች መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ አስተሳሰቡ ግን ክልላዊ የቤተሰብ ሕጎችም ላይ ተጽዕኖ ማድረጉ ባለመቅረቱ ጉዳዩ አከራካሪነቱን አይተውም፡፡

በአፋር ክልል የቤተሰብ ሕግ በጋብቻ ላይ ጋብቻን በተመለከተ ሶስት የተለያዩ አቋሞች ተንጸባርቀዋል፡፡ እነዚህ ሐሳቦች የሴቷን መብት በመጠበቅ ረገድ አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ያሏቸው ሲሆን፣ ከሕግ አወጣጥ ሥርዓት (Law making process) አንፃርም የራሳቸው ክፍተት ይታይባቸዋል፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻን በማናቸውም ሁኔታ መከልከል ከተነሱት ሐሳቦች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ይህ አቋም በተሻሻሉት የቤተሰብ ሕጎች የተያዘ አቋም ነው፡፡ በረቂቅ ሕጉ ውይይት ወቅት ይህ አsም በአንዳንድ የምክር ቤት አባላትም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በጋብቻ ላይ ጋብቻን መከልከል የእኩልነት መርህን የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በተግባር ለሴቷ የሚፈቀድበት የኃይማኖትና የባህል መሠረት ባለመኖሩ መፈቀዱም ብዙ ማኅህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ስለሚያስከትል ይህ አቋም የሴቷን መብት ይጠብቃል፡፡ በአንዳንድ የሙስሊም ት/ቤቶች ሁለትና ከዚያ በላይ ሰዎችን በተመሳሳይ ጊዜ እኩል መውደድ ስለማይቻል በጋብቻ ላይ ጋብቻ ተከልክሏል የሚሉ አማኞችንም ሐሳብ በአግባቡ ያንፀባርቃል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በክልሉ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይም ሴቶችና የሴቶች ጉዳይ ተወካዮች ቀደም ሲል በጋብቻ ላይ ጋብቻ ይፈቀድ የነበረባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አሁን ባለመኖራቸው፣ በተግባር ያለ ገደብ የሚፈጸም በመሆኑና ከስነ ሕዝብና ልማት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከለከል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ሁለተኛው አቋም በጋብቻ ላይ ጋብቻን በመርህ ደረጃ ከልክሎ በልዩ ሁኔታ መፍቀድ ነው፡፡ ይህ አቋም አንዳንድ ሰዎች በማስታረቂያነት የሚያቀርቡት አማራጭ ነው፡፡ በጋብቻ ላይ ጋብቻን ከልክሎ የኃይማኖት መብት ከመርገጥ፣ ሙሉ በሙሉም ፈቅዶ የሴቶችን መብት ከመሸርሸር በልዩ ሁኔታ መፍቀዱን ይመክራሉ፡፡ ይህን ሐሳብ ለማጠናከር የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 550 በጋብቻ ላይ ጋብቻን ሲቀጣ በልዩ ሁኔታ በአንቀጽ 551 ኃይማኖታቸው የሚፈቅድላቸው ግለሰቦችን ነፃ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም በሸሪዓ ሕግ ጋብቻ መሥርተው ፍቺ በመደበኛ ፍ/ቤት ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑ ሴቶችን መብት ለመጠበቅ ልዩ ሁኔታው ጠቃሚ ነው የሚሉ አካላት አሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ሁለተኛዋን ሚስት ፍ/ቤት በንብረት ክፍፍል ጊዜ አላውቅሽም እንዳይላት መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ሆኖም ሙስሊም ማኅበረሰብ በብዛት በሚኖርበት ክልል ውስጥ የሙስሊም እሴትን (Islamic value) በልዩ ሁኔታ መደንገግ አብዛኛውን ሕዝብ በራሱ ክልል አናሳ (Minority) ማድረግ ነው የሚል ተቃውሞ ተነስቶበታል፡፡

በጋብቻ ላይ ጋብቻን በልዩ ሁኔታ መፍቀድ የሚደግፉ ሰዎች ያላገናዘቡት መሠረታዊ የሕገ መንግሥት ጽንስ ሐሳብ ያለ ይመስላል፡፡ ይኸውም መንግሥት በኃይማኖት፣ ኃይማኖት በመንግስሥት ጣልቃ እንዳይገባ መከልከሉ (Secularism) ነው፡፡ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሰረት የመንግሥት ኃይማኖት ባለመኖሩ ሕግ ሲወጣ፣ ፍ/ቤቶች ሲቋቋሙ፤ ዳኞች ሲሾሙ ወ.ዘ.ተ የአካባቢውን ነዋሪዎች ፍላጎትና መብት መሠረት ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአፋር የቤተሰብ ሕግ የክልሎቹን ነዋሪዎች ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ የክልሉ ነዋሪም ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ ኃይማኖት የሌለው፣ … ወዘተ ዓይነት ሰዎችን የሚያካትት መሆኑ ሊታመን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግሥት ም/ቤቶች የቤተሰብ ሕጉ ዝርዝር ድንጋጌን ከሸሪዓ ሕግ አንፃር ብቻ ሊየዩት አይገባም፡፡ ይህ ሲባል የሙስሊም ማኅበረሰብ የኃይማኖት መብት ያለ አግባብ ይገደባል ማለት አይደለም፡፡ የሸሪዓ ሕግን ተፈጻሚ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ስላለ በጋብቻ ላይ ጋብቻ በሸሪዓ ፍ/ቤቶች አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው በቃዲዎች እየተረጋገጠ ስለሚፈቀድ የኃይማኖትን መብት የሚቃረን አይሆንም፡፡ እንዲያውም በጋብቻ ላይ ጋብቻን በልዩ ሁኔታ በመፍቀድ መደበኛ ፍ/ቤቶች ጉዳዩን እንዲመለከቱት ማድረግ ነው የኃይማኖት መብት የሚጥሰው፡፡ የሸሪዓ ሕግ እውቀት የሌላቸው የመደበኛ ፍ/ቤት ዳኞች ልዩ ሁኔታው ስለመኖር አለመኖሩ እንዲመረምሩ መፍቀድ የኃይማኖት ጉዳይ ላይ እጃቸውን እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡ በጋብቻ ላይ ጋብቻን በቤተሰብ ሕጉ ከልክሎ በሸሪዓው ያለውን አፈጻጸም መቀጠል ግን የሕግ ሥርዓቱን ወጥነት ያከብራል፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ሙስሊም በሸሪዓ ሕጉ መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ቢፈጽም ወንጀል እንደማይሆንበት የወንጀል ሕጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡

ሦስተኛውና የአፋርን የቤተሰብ ሕግ የማሻሻል ኃላፊነት የተጣለበት ኮሚቴ የሚያንጸባርቀው አቋም በጋብቻ ላይ ጋብቻን በዝምታ ማለፍ የሚለውን ሲሆን፣ ይህ አቋም በጋብቻ ላይ ጋብቻን የሚፈቅድም የሚከለክልም ድንጋጌ አለመቀመጡን ይቀበላል፡፡ ለዚህ መነሻ የተለያዩ ምክንያቶች ቢገለጹም፣ ዋናው ነጥብ ግን ዝምታ በክልሉ ያሉትን የብዙኃን እሴት (Value) ለመቀበል ስለሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውጭ ጋብቻ የግለሰቦች ነፃነት መገለጫ በመሆኑ አግቡም፣ ሁለት-ሦስት አታግቡም ብሎ መደንገግ ተገቢ አይደለም የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ግለሰቦች ያለማግባት፣ አራትም የማግባት መብት ስላላቸው በጋብቻ ላይ ጋብቻ የግለሰቦች ነፃነት ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ጉዳይ የማይከለክሉት፣ የማይመክሩትም ነው (An issue which can neither be recommended nor prohibited) ይላሉ:: አንዳንድ የኃይማኖት አባቶችም የሸሪዓ ሕግ አራት ማግባትን በመፍቀድ በሩን ከፍቷል፣ ዝሙት አይኖርም፣ ሚስቶቹንም እኩል ያስተዳድር በማለት ደግሞ መልሶ ስለዘጋው በዝምታ እውቅና ቢሰጠው መልካም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሐረሪ ምክር ቤት ተደርጎ የነበረው ውይይት ይህን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡

ከላይ ከቀረቡት አማራጮች ሁሉ የሴቷን መብት እጅጉን የሚጎዳው ይህ አቋም ነው፡፡ በጋብቻ ላይ ጋብቻን በግልፅ አለመከልከል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሕግ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ በሕግ በግልጽ ያልተከለከለ ነገር እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ይህ አቋም በጋብቻ ላይ ጋብቻን ያለቅድመ ሁኔታ ስለሚፈቅድ ከእኩልነት መርህ ጋር የሚቃረን በመንግሥትና በኃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት (Secularism) የማይጠብቅና በተግባርም ሴቶች ለተለያዩ ጥቃቶች እንዲጋለጡ የሚፈቅድ ነው፡፡ በጋብቻ ላይ ጋብቻን በቤተሰብ ሕግ በዝምታ ማለፉ አሁን ከምንከተለው የፌዴራል ሥርዓት ጋርም ተያይዞ የአፈጻጸም ችግር የሚያስከትል ይሆናል፡፡ በክልሎች መካከል ባለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር (Socio-economic interaction) የአፋር ክልል ነዋሪዎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ተባብረው ሊሠሩ እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ በአፋር ክልል የሚቀረፀው የቤተሰብ ሕግ ተጋቢዎች በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል እውቅና ተሰጥቷቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚያስችል ሕግ ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉም የክልል /የፌዴራሉን ጨምሮ/ የቤተሰብ ሕጎች በጋብቻ ላይ ጋብቻ የከለከሉ ሲሆን፣ በሌላ ክልል የተፈጸሙ ጋብቻዎች እውቅና የሚሰጣቸው በጋብቻ ላይ ጋብቻ መከልከልን ጨምሮ ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ እንደሆነ በግልጽ ይደነግጋሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአፋር ክልል በጋብቻ ላይ ጋብቻ ቢፈቀድ በሌሎች ክልሎች እውቅና /ጥበቃ/ የማግኘት እጣው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

በተጨማሪም ሰዎች የኃይማኖትና የባህል ምክንያት (Justification) ሳይኖራቸው ከሌሎች ክልሎች እየመጡ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ለመፈጸምና በሕጉ ተጠቃሚ ለመሆን ማሰባቸው አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል በጋብቻ ላይ ጋብቻን በቤተሰብ ሕጉ ከልክሎ በሸሪዓ ያለውን አፈፃፀም መቀጠል በፌዴራሉ ሥርዓት መነሻነት የሚፈጠር ምንም ዓይነት ተግዳሮት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የሸሪዓ ሕግ ተመሳሳይ አስተምህሮና አፈፃፀሙ ይኖረዋል ተብሎ ስለሚታሰብ አፈፃፀም በየክልሉ የሚለያይ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ኃይማኖት ተፈጻሚ የሚሆነው  የቤተሰብ ሕግ ላይ በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈጸምን ከልክሎ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በእምነታቸው መሠረት በሸሪያ ሕግ መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ቢፈጽሙ፤ የሸሪያ ፍ/ቤቶችም አፈጻጸሙ ሸሪዓውን የተከተለ ስለመሆኑ ቁጥጥር ቡያደርጉ የተሻለ ይሆናል::

በአፋር ክልል የምክክር ውይይት ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት መኖርን  በተመለከተ የተነሳው ዋናው ችግር ለግንኙነቱ እውቅና መስጠት የጋብቻን ዋጋ የሚቀንስና ዝሙትን የሚያበረታታ ነው የሚል ሐሳብ ነው፡፡ በተጨማሪም ከእስልምና ኃይማኖት ጋር የሚጋጭና በብዛትም የማይዘወተር ነው በሚል ምክንያት እውቅናው እንዳይሰጥ ግለሰቦች ይከራከራሉ፡፡ ይህ አቋም በግንኙነቱ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶችን ለጥቃት የሚያጋልጥና ያለ ሕግ ማዕቀፍ የሚያስቀር ነው፡፡ ሰዎች በእንዲህ አይነት ግንኙነት በተለያዩ ምክንያቶች የሚገቡ ሲሆን፣ በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ሃቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ግንኙነቱ ያለና የሚኖር (Unavoidable) ነው፡፡ ለግንኙነቱ ዕውቅና አለመስጠት ማኅበራዊ ቀውስ ያመጣል፡፡ ሕግ አከራካሪ የሆነውን የሞራል እሴት (Moral value) ከመጠበቅ አልፎ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ነባራዊ “ችግሮችን” ሊገዛ ይገባል፡፡ በግንኙነቱ ልጆች እየተወለዱ፣ ንብረት እየተፈራ፣ ኅብረተሰቡ ተቀብሎት በአንድ ጣራ እስከ 10 ዓመትና ከዚያ በላይ እየኖሩ የሕግ እውቅናና ጥበቃ አለመስጠት ሕጉ ኅብረተሰቡን ያላገናዘበ (Society blind) እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የጋብቻን ዋጋ ለመጠበቅ የምክርና የቅስቀሳ ሥራን መሥራት እንጂ ለግንኙነቱ የሕግ እውቅና መከልከል መፍትሔ አይደለም፡፡ የእኛ ኃይማኖትና ባህል መገምገሚያ መሠረተ ሐሳቡ (Doctrine) ወይስ በተግባር ያለው እውነታ? አንዳንዶች እንደሚሉት የኅብረተሰቡን እውነታ የሚዘነጋ ሕግ ሕዝባዊ አይሆንም፡፡

ከዚህ በላይ የቀረቡት ሁለት አከራካሪ ነጥቦች በረቂቅ ሕጉ ውይይት ጊዜ በነበረው አቋም የሚፀድቁ ከሆነ /ማለትም በጋብቻ ላይ ጋብቻን መፍቀድ፣ ከጋብቻ ውጭ እንደ ባልና ሚስት መኖርን እውቅና አለመስጠት/ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች፤ ስምምነቶችና በሕገ መንግሥቱ ሴቶች የተረጋገጠላቸውን መብት የሚጥሱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሕግ ተፋልሶ (Legal fallacy) የሚያስከትሉ ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ ልማዳዊ አሠራሮችም ሆኑ ሕጎች ተፈፃሚነት እንዳይኖራቸው መታገል የሁሉም ግዴታ ሊሆን ስለሚገባ በዚህ ረገድ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ መንግሥስታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለጉዳዩ ተገቢ ቦታ ሊሰጡ ይገባል፡፡

የአፋር ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤትም የሴቶችና የሕጻናት መብቶችን እንዲከበሩ ያለውን ቁርጠኝነት ሊያሳይ ይገባል፡፡ ቀደም ሲል ም/ቤቱ ከፌዴራሉ የወንጀል ሕግ በተጨማሪ በክልሉ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የግርዛት ዓይነቶችን ወንጀል በማድረግ ቅጣቱን በማስፋት አዋጅ እንዳወጣ ሁሉ አሁንም የሴቶችን መብት የሚያከብር የቤተሰብ ሕግ እንዲጸድቅ ቁርጠኝነቱን ሊቀጥል ይገባል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ ግን የአፋር የቤተሰብ ሕግ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ከ16 ዓመታት በኃላ አለመውጣቱ የሴቶችና የሕጻናት መብት በአግባቡ ቦታ ያልተሰጣቸው መሆኑ ያሳያል፡፡ የክልሉ የቤተሰብ ሕግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር (ከሕዝቡ፤ ከሴቶች፤ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከኃይማኖት አባቶች) በቂ ውይይት ተደርጎበት ላለመውጣቱ አሳማኝ ምክንያት አልተገኘም፡፡ ስለዚህ የክልሉ ም/ቤት ለሴቶችና ለሕጻናት መብት የተሻለ ጥበቃ የሚሰጥ የቤተሰብ ሕግ በቅርቡ እንዲያወጣ በተጠቃሚዎች ስም ተማጽኖ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በ This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it ማግኘት ትችላላችሁ፡፡