በምሕረት አስቻለው
ከዕድሜውም ሆነ ከሕይወት ተሞክሮው አንጻር የተሠማራበት የንግድ መስክ የተለመደና ሌሎችም የሚሠሩበት ነው፡፡ ከስምንት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የቆዳ ውጤቶችን እያመረቱ ይሸጣሉ፡፡
የሚኪያስ ተሾመ የሥራ ድርሻ በአብዛኛው የቆዳ ምርቶቹን መሸጥ ነው፡፡
ምንም እንኳ የመሸጫ ቦታ ቢኖራቸውም እሱ ግን በተለየ መልኩ ለቅሶ ቤት፣ ሆስፒታል፣ ባንክ እዚህ እዚያ ብሎ ቦታ ሳይመርጥ የቆዳ ምርቶቹን በሔደበት ሁሉ ይዞ በመንቀሳቀስ ይሸጣል፡፡ እስከ አሁን ምርቶቹን ለመሸጥ አመቺ ሆኖ ያላገኘው ብቸኛ ቦታ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አመቺ ያልሆነው በጧቱ የጸሎት ሰዓት ብቻ ነው፡፡
‹‹ምሳ ልበላ የገባሁበት ቤት ከጐኔ ያለ ሰው ጋር ጨዋታ ይጀመራል፡፡ ከዚያ ምን እንደምሠራ ገልጬ እቃዎቼን አሳያለሁ፣ ከፈለገ እዚያው ወዲያው ይገዛል ካልሆነ አድራሻዬን ሰጥቼ በፈለገ ቀን የፈለገበት ቦታ ድረስ የፈለገው እቃ ይወሰድለታል፤›› የሚለው ሚኪያስ ዘወትር ሲንቀሳቀስ ምርቶቹን እንደሚይዝና ወደ ቤት ሲመለስ ጨርሶ እንደሚገባ አጫውቶናል፡፡
ከወንድም፣ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሻይ ቡና ሊሉ በተገኙበት ቤት ውስጥ ወይም በሌላ ተመሳሳይ አጋጣሚ ከያዛቸው የቆዳ ምርቶች ውስጥ ይሆናል ያለውን ለመሸጥ የሚጠቀምበትን አቀራረብ ወንድሞቹና ጓደኞቹ እንደ ነውር ይቆጥሩታል፡፡ ሚኪያስ ግን በእንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች እቃዎቹን ከመሸጥ ባሻገርም ስለተጠቀመ፣ በዚህ መልኩ የመሠረታቸው ግንኙነቶችም በተለያየ መልኩ ጠቅመውት ስለተመለከተ የእነሱ አስተያየት ብዙም አይረብሸውም፡፡ እነሱም ምን ያህል እንደተጠቀመ ስለተመለከቱ ዛሬ ላይ እንደ ቀድሞ ብዙም አይቃወሙትም፡፡
‹‹አታፍርም ወይ? ይሉኝ ነበር፡፡ በየሔድኩበት ቀረብ ብሎ ሰዎችን አግባብቶ መሸጥ ትንሽነት ራስንም ዝቅ ማድረግ ይመስላቸውም ነበር፡፡ ቢሆንም እኔ ጉዳዬን ከመፈጸም ወደ ኋላ አልልም፡፡ ኋላ ላይ አስረዳቸዋለሁ፤ ሊቀበሉም ላይቀበሉም የሚችሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ አሁን አሁን ግን እየተቀበሉኝ ነው፡፡ ብዙም በሚያስጨንቅ መልኩ ስላልሆነ ሰዎችን የምቀርበው ከማድነቅ ከመልካም አስተያየት ውጭ የገጠመኝ አሉታዊ ነገር የለም፡፡››
በምግብ ቤት ወይም በካፍቴሪያ ውስጥ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩት ተስተናጋጅ ያልሆኑ፤ የኑሮ ደረጃቸውም ከተስተናጋጁ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ የሆነ ሰዎች በመሆናቸው በተመሳሳይ ሁኔታ እንደነሱ ተስተናጋጅ የሆነው ሚኪያስ ጊዜና አጋጣሚን ለመጠቀም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለብዙዎች እንግዳና አስገራሚ ነው፡፡ አድናቆትንም አትርፎለታል፡፡
እንደ ሚኪያስ ገለጻ ጥቂት በማይባሉ ወጣቶች፣ የሚያሳፍረውን እንደ ክብር የሚያስከብረውን ነገር ደግሞ እንደ ነውር የመቁጠር አዝማሚያ ይታያል፡፡ ረዥም ሰዓትን ሥራ የለም በሚል እንዲሁ በከንቱ ከማሳለፍ ሳይንቁ ሥራን ከታች ከትንሹ መጀመር ያስፈልጋል፡፡
‹‹ለምሳሌ ማምረቻ ቦታ ኖሯቸው መሸጫ ቦታ የለንም የሚሉ አስተያየቶች በብዛት ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የኪራይ ወጪን ቀንሰው በተወሰነ ሰዓት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ከመሸጥ ይልቅ በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ግንኙነቶችን መፍጠርና ገበያን መፍጠር ይገባል፡፡ አንድ ቦታ ተወስኖ ለመሸጥ መሞከር ላይሳካ ይችላል፡፡ መንቀሳቀስ በተለያዩ አቅጣጫዎች መጓዝ ተጨማሪ እድሎችን ሁሉ ያመጣል፡፡››
ወጣትነት ሮጠው ትልቅ ነገር መሥራት የሚቻልበት የህይወትን አቅጣጫ የሚያስተካክሉበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለተለያዩ አደገኛ ባሕሪያት የሚጋለጡበት የዕድሜ ክልል እንደሆነ የሚናገረው ሚኪያስ ጊዜን በማይጠቅም ነገር ማጥፋትን፣ ያልተገቡ ድርጊቶችን መፈጸምን በመሳሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ አልፏል፡፡ በዚያ መንገድ ከጉዳትና ከኪሳራ ውጭ አንድም ጥቅም እንዳላገኘ ያስታውሳል፡፡
‹‹ጊዜን ማባከን፣ ጉልበትና ገንዘብን መጨረስ ነው፤ ተመሳሳይ ሕይወት በመሆኑም ድግምግሞሹ ያሰለቻል፡፡ ሱስም ቢሆን ይታክታል፡፡ ለጊዜው ደስታን የሚሰጥ፣ የሚያዘልቅም ይመስላል፤ ግን መጨረሻ የለውም፡፡›› በማለት ነገሮች የተሰናከሉባቸው፣ እድሎች የጠበቡባቸው ለሚመስላቸው ወጣቶች የተለያዩ ነገሮችን በመሞከር፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ትክክለኛውን መስመራቸውን ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራል፡፡
ዛሬ ላይ ትዳር መሥርቶ የሦስት ልጆች አባት መሆን ችሏል፡፡ መሥራት የጀመረው ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የተለያዩ እቃዎችን በማሻሻጥ ነበር፡፡ በማሻሻጥ በሚያገኘው ኮሚሽን ቤት ተከራይቶ በመውጣት ራሱን ችሎ መኖር ጀምሮ ነበር፡፡ ያኔ በወር ለቤት ኪራይ መቶ ብር ይከፍል የነበረ ሲሆን ራሱን ችሎ መኖር መጀመሩ ለቀጣይ ሕይወቱ ድፍረትና ብርታት እንደሰጠው ይናገራል፡፡
‹‹ልብስና ከውጭ የሚመጡ የተለያዩ እቃዎችን አሻሽጥ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ ያገኘሁትን ሰው እንዲህ ላድርግልህ፤ ይሄን ነገር ከዚያ ለኔ ይሄን ያህል ታስብልኛለህ እያልኩ ነበር ሥራዎችን የማገኘው፡፡››
የቆዳ ምርቶቹን ወደ ውጭ እየላከ ይሸጣል፡፡ አገር ውስጥም በተለያየ አቅጣጫ ደንበኞች አሉት፡፡ ሥራ መሥራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጠቀመው ከሰዎች ጋር ያለው መግባባት እና ግንኙነቱን ለሥራ በጠቀም ወደ ገንዘብ መቀየር መቻሉ እንደሆነ ይናገራል፡፡


