Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ክቡር ሚኒስትር

E-mail Print PDF
User Rating: / 14
PoorBest 

የክቡር ሚኒስትሩ ሞባይል ስልክ ባልተለመደ ሁኔታ የጥሪ ጩኸት ያስተጋባው በመንፈቀ ሌሊት ነበር፡፡ ምን ተፈጥሮ ይሆን ብለው በድንጋጤ ተቻኩለው አነሱት፡፡ የተደወለውም ውጭ አገር ከሚኖር የልጅነትና የወጣትነት የቅርብ ጓደኛቸው ነበር]
    ሃሎ!
    ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር አውቃለሁ፤ ባልሆነ ሰዓት ደውያለሁ፡፡ የእናት ነገር ሆኖብኝ ነው፡፡ እናቴ ታማለች፡፡ አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ እሸፍናለሁ፤ እልካለሁ፡፡ ሹመቱን ተወውና የዱሮ ወዳጅነታችንን እይ፡፡ እባክህን ክቡር ሚኒስትር እንዳትሞትብኝ አንዴ ጧት ሒድና እናቴን እያት፡፡ መደረግ የሚገባውን ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ንገራቸው፡፡ እኔ አሁን አስፈላጊውን ገንዘብ ሁሉ እልካለሁ፡፡
    እሺ አይዞህ አትጨነቅ፡፡ በጧት እሔዳለሁ፡፡ ካስፈለገም እኔ ቤት አመጣቸዋለሁ፡፡ ያንተ እናት ብቻ አይደሉም የእኔም እናት ናቸው፡፡
    አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትር በጧት ሔደው ቤተሰቡን አነጋገሩ]
    እማማ እንዴት ናቸው? ወንድማችሁ ደውሎ ስለነገረኝ ነው የመጣሁት፡፡
    አሟታል ክቡር ሚኒስትር፤ በጣም አሟታል፡፡
    እንደዚህ እስኪታመሙ ድረስ የት ነበራችሁ? ለምን ሆስፒታል አልተወሰዱም?
    ክቡር ሚኒስትር መጀመርያ ትንሽ ሲያስላቸው ጉንፋን ነው ብለን ችላ አልነው፡፡ አንዳንዶቹ መጥፎ በሽታ ሊሆን ይችላል፤ አስመርምሯቸው ሲሉንም አልሰማናቸውም ችላ አልን፡፡
    እናንተ ችላ አላችሁ በሽታው ተባባሰ?
    አዎን ክቡር ሚኒስትር ተባባሰ፤ ከዛ አንድ ሁለት ሐኪሞች ስናማክር በሽታው አይድንም አደገኛ ነው አሉን፡፡ ያኔ ተስፋ ቆረጥንና ተውነው፡፡
    ሐኪሞቹ አይድንም ሲሏችሁ መርምረው ነው ሳይመረምሩ?
    ሁኔታውን ስንነግራቸው ካንሰር ነው ብለው ደመደሙ፡፡
    ሳይመረምሩ?
    ካንሰር እንደዛ ነው የሚያደርገው አሉን፡፡
    በሉ በሉ አሁን ጥሩ ሐኪሞች ወዳሉበት ሆስፒታል እንውሰዳቸው፡፡ እንሒድ መኪናዬ ውስጥ አስገቧቸው፡፡
[ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በሽተኛዋ እናት ሆስፒታል ሔዱ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ የመረጡት ሆስፒታል እሳቸውም፣ የበሽተኛዋ ልጅ፣ ዲያስፖራው ጓደኛም የሚያውቁት ዶክተር ጋ ነበር፡፡ በሚገባ የተደራጀና ባለሙያዎች ያሉበት ሆስፒታል ነው]
    እስቲ እንደተለመደው ላስቸግርህና ምርመራውን አቀላጥፍልን እባክህ፡፡
    የአንተ እናት ናቸው እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
    የወዳጃችን የጆኒ እናት ናቸው፡፡
    ውይ. .  . . .  . በቀደም አሜሪካ ተገናኝተን ለምን አልነገረኝም ታዲያ? የእኔ እናት አይደሉም እንዴ?
    ለእኔም ሌሊት ደውሎልኝ ነው፡፡
    ቅድሚያ ልስጣቸውና ይግቡ፡፡
[ገቡ ምርመራ ተጀመረ]
    እህ. .  . እንዴት ናቸው?
    ቆይ አትቸኩል ክቡር ሚኒስትር ገና ደም፣ ሽንት ነው የመረመርነው፡፡
    ደምና ሽንት ላይ ችግር አለ?
    የለም - ግን እስቲ ራጅ ልመርምር፡፡
    [ራጅም ተመረመረ] ውጤቱ እንዴት ነው?
    ይህም ብዙ ችግር የለበትም፡፡
    ታዲያ ካንሰር የተባሉት ለምንድን ነው ዶክተር?
    ማነው ካንሰር ያለው፡፡
    ሌሎች ሐኪሞች፡፡
    ካንሰር አይደለም በቀላሉ የሚድን ነው፡፡ ግን እርግጠኛ ለመሆን ሲቲ ስካን ላድርግ እስቲ ክቡር ሚኒስትር፡፡
    ጥሩ ነው ሁሉም ምርመራ ይደረግ፡፡ ሁሉንም እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡
[ሲቲ ስካን ተደረገ] በዚህ በኩልም ችግር የለም፡፡
    ታዲያ ምንድን ነው ችግራቸው?
    ቤተሰብ የጠቀመ መስሎት ያልሆነና አለርጂክ የሆነባቸውን ምግብ ይሰጣቸዋል፡፡ ኮሌስትሮልም አለ፡፡ የደም ግፊትም እየጀማመራቸው ነው፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜም ያልሆነ መድኃኒት ተሰጥቷቸዋል፡፡
    እና ይድናሉ?
    አዎን ይድናሉ፡፡ እንዲያውም ከመጀመርያው ተገቢ ምርመራ ቢደረግላቸው ኖሮ ምንም ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡ በቀላሉ የሚፈታ ችግር ነው፡፡
    እና አሁን ተስፋ አለ በለኛ - ጓደኛችን ጋ ልደውል እባክህ በጣም ተጨንቋል፡፡
    ደውልለት ካንሰር የሚባል የለም፡፡ አስጊ በሽታም አይደለም፡፡ እኔ ራሴ እከታተላቸዋለሁ፡፡ ሆስፒታል መተኛትም አያስፈልጋቸውም፡፡ መድኃኒት ልስጣቸውና ቤት ይሒዱ፡፡ ያልሆነ መድኃኒትና ያልሆነ ምግብ እንዳይሰጣቸው ግን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሙያ ወደሌላቸው ሐኪም ተብዬዎች ጋ እንዳይሔዱም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
    እና አሁን ይሒዱ ዶክተር?
[ቤተሰብ ደስ አለው፡፡ በሽተኛዋም ፈገግታ ጀመሩ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ከዶክተር ጋር ለሻይ ቡና ቆዩና በሽተኛዋንና ቤተሰቡን በመኪናቸው ላኩዋቸው፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ከዶክተሩ ጋር ቡና እየጠጡ ወሬ ጀመሩ]
    አመሰግናለሁ ዶክተር፡፡ ጓደኛችን እንዴት ተጨንቋል መሰለህ፣ እኩለ ሌሊት ነበር የደወለልኝ፡፡
    ክቡር ሚኒስትር ይዘሃቸው በመምጣትህ ልዩ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡
    እንዴ የሰው ልጅ ሕይወት አይደለም እንዴ? የሁላችንም እናት አይደሉም?
    እሱ እኮ ነው ደስ ያሰኘኝ፡፡ ሚኒስትር ስትባሉ ‹‹ልማታዊ›› እናት ናቸው? ወይስ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› እናት? ብላችሁ ጠይቃችሁና በኮሚቴ ተሰብስባችሁ በበላይ አካልም አጸድቃችሁ ውሳኔ የምትወስኑና ዕርምጃ የምትወስዱ ይመስለኝ ነበር፡፡
    ሃ. .  . .ሃ. .  . .ሃ ለካ ዶክተሮችም ትቀልዳላችሁ፡፡
    በጤናና በሕይወት አንቀልድም እንጂ ቀልዳቀልድማ እንወዳለንኮ፡፡
    የፖለቲካ ዶክተሮች ግን የሚቀልዱት በሁሉም ጉዳይ ነው፡፡
    ሚኒስትሮችም ጭምር ክቡር ሚኒስትር?
    ዶክተር ቀልደኛም ብቻ ሳትሆን አሽሙረኛም ነህ፡፡
    አሽሙር የቀጥተኛ ንግግር እጥረትና እጦት ውጤት ነው፡፡
    ሆ. .  .ሆ. .  . ባለቅኔም ጭምር ነህ ልበል?
    ቅኔም ከግልጽነት የመሸሽና ግልጽነትን የመፍራት ውጤት ነው፡፡
    ይኸውልህ አሁን አስቸኳይ ስብሰባ ስላለኝ ለምን ማታ አብረን ራት አንበላም ዶክተር?
    እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
    እኔ ቤት አንድ ሰዓት፡፡
    እመጣለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ለራት ተገናኙ፡፡ ጭውውቱ ከረር እያለ ሔደ]
    ኧረ ዶክተር ቅድም ሳልጠይቅህ ወንድምህ እንዴት ነው?
    ደህና ነው፡፡
    ምን እየሠራ ነው?
    ሪል ስቴት አለው፡፡ እ. . .  አለው ነው የሚባለው ነበረው?
    ሪል ስቴት?
    ሪል ስቴት!
    ከሆስፒታልህ ከሔድኩ ጀምሮ ሙሉ ቀን አንድ ሐሳብ ከአእምሮዬ አልወጣ አለ፡፡ ተገቢ ምርመራ ባለመደረጉ ምክንያትና በባለሙያዎች ባለመያዙ ምክንያት ሊፈወስ የሚችል ቀላል በሽታን ካንሰር ነው ተብሎ ቤተሰብ ሁሉ ተረበሸ፤ በሽተኛዋንም ተስፋ አስቆረጠ.  . . .
    እ. . .  ከመጀመርያው ምልክት ሲታይ ምርመራ ቢደረግና ክትትል ቢካሔድ ኖሮ፣ ባለሙያም ቢመረምር ኖሮ በቀላሉ የሚፈታ ነበር፡፡
    ሕዝብም የሕክምና ባለሙያዎች ነን ባዮች ከዚህ ሊማሩ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ተሳሳትኩ ዶክተር?
    አልተሳሳትክም፡፡ ነገር ግን ከዚህ መማር ያለበት ቤተሰብና ሐኪሞች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትና ፖለቲከኞችም ጭምር ናቸው፡፡
    መንግሥትና ፖለቲከኞች ደግሞ ምን አገባቸው?
    እያወራሁ ያለሁት ስለ አገር ጤና ነውኮ፡፡
    አልገባኝም ዶክተር፤
    ይኸውልህ ክቡር ሚኒስትር. .  . ልክ አንተ ከሆስፒታል ከወጣህ ጀምሮ የሴትየዋን ጤና መነሻ አድርገህ አስቀድሞ በሽተኛን ወደ ሆስፒታል አለመውሰድ፣ ተገቢ ምርመራ አለማድረግ፣ ባለሙያ ሐኪም አለመኖር፣ ያልሆነ ውጤት መናገር የሚያስከትለው አደጋ እያሳሰበህ እንደሆነ፣ እኔም በአገር ጉዳይ ላይ ተገቢ ምርመራ አለማድረግ፣ በቂ መረጃ አለመሰብሰብ፣ በባለሙያዎች አለመሥራትና ያልሆነ በሽታ አለ ማለት የአገርን ሕይወት እንዴት ከአደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ሲያሳስበኝ ዋለ፡፡
    ይህን ያህል ያሳሰበህ ምንድን ነው?
    ወንድሜ ሪል ስቴት አለው ብዬሃለሁ ክቡር ሚኒስትር?
    ነግረኸኛል አዎ ዶክተር፡፡
    ያጠፋ መቀጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ወንጀለኛም መቀጣት አለበት እላለሁ፡፡ ያጠፋንና ወንጀለኛን ተለማመጡ አልልም፡፡ አገርን ይጎዳልና፡፡ ነገር ግን. .  .. ነገር ግን. .  .
    ነገር ግን ምን?
    በወቅቱ ምርመራ ሳይደረግ ቀርቶ. . .  በወቅቱ ክትትልና ቁጥጥር ሳይደረግ ቀርቶ፣ በወቅቱ በባለሙያዎች ጥናትና ምርምር ሳይደረግ ቀርቶ፣ አንዱ ካንሰር ነው ስላለ ብቻ ‹‹ሪል ስቴት ካንሰር ነው›› ብሎ መጯጯህ ከሴትየዋ ሁኔታ ጋር ተያያዘብኝ፡፡ ይኸኛው የግለሰብ ጤና አጀንዳ ነው፡፡ እኔ የምለው የአገር ጤና አጀንዳ ነው፡፡
    እ. . . . ህ. . . ም. . .  የሪል ስቴት ሁኔታው ግን አሁን ተፈትቶ የለም እንዴ ዶክተር?
    አዎን ተፈቷል ክቡር ሚኒስትር፤ ግን ከመጀመርያው በቂ ምርመራ ሳይደረግ ሁሉም ተሰደቡ፤ ተወገዙ፡፡
    እ. .  .
    መወገዝ ብቻ አይደለም ከአገር እንዳትወጡ ተባሉ. .  ከጉዞም ታገዱ፡፡
    እ. .  .
    እነሱም ካንሰር ነው እንዳሏቸው በሽተኛ ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡
    እ. .  . .
    ኋላ በሚገባ ሲመረመሩ ሴትየዋ ካንሰር የለባቸውም፤ መኖር ይችላሉ እንደተባሉት እናት፤ እነሱም መሥራትና መቀጠል ይችላሉ፤ የሚያስቀጣም ከሆነ ይቀጣሉ ተብለዋል፡፡
    አዎን፡፡
    ይኸውልህ ከመጀመርያው መደማመጥና በባለሙያ ዓይን መረጃን መፈተሽና ማቅረብ፣ ሁኔታዎችንም መገምገሙ ቢኖር ኖሮ፣ አላስፈላጊ ፍርኀትና ጥርጣሬ በኅብረተሰቡ ዘንድ ባልተፈጠረም ነበር፡፡
    እና የኢትዮጵያ ጤና እንዲጠበቅ ራጅ አስነሧት እያልከን ነው?
    ማንም የመንደር መርፌ ወጊ ካንሰር ነው እያለ ከሚሰጠው ውሳኔ ሐኪሞች መጠንቀቅ እንዳለብን ሁሉ፣ እናንተ ፖለቲከኞችም ከምርመራ በፊት እስርና እግድ ከሚል ውሳኔ ተጠንቀቁ እያልኩ ነው፡፡
    እኮ ራጅ?
    ሲቲ ስካን!
[ራት ሲበሉ የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሙሉውን ጊዜ አብረው ባይቀመጡም የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤትና በሕግ ዙርያ የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀች ያለችው የቅርብ ዘመድ ውይይቱን ያዳምጡ ነበር፡፡ ዶክተር እንደሔደም ወዲያውኑ የቤተሰብ ውይይት ቀጠለ]
    እሺ ውድ ባለቤቴ ለመናገር የፈለግሽ ትመስያለሽ፡፡
    አዎን፡፡
    በያ ተናገሪ፡፡
    እኔ የምለው አሁን የሪል ስቴቱ ችግር በውይይትና በመግባባት መፈታቱን ወድጄዋለሁ፡፡ ግን ለምን ሁልጊዜ ውይይትና መግባባት አይቀድም? እናንተ በመጀመርያ ዕርዳታ ከማመን ይልቅ በአምቡላንስ የምታምኑት ለምንድን ነው?
    እስክንማር ድረስ ነው፡፡ አሁን ተምረናል፡፡ ስለተማርንም ነው በመወያየትና በመግባባት የተፈታው፡፡
    በውይይትና በመግባባት መፍትሔ የማግኘቱ ጉዳይ ለሪል ስቴት ችግር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለሁሉም ችግር ይሁን፡፡ በየቦታው እያለቀሰ ያለው ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ አወያዩት፤ አዳምጡት፡፡
    እኔም አንቺ ያየሽው እየታየኝ ነው፡፡
    ጥሩ ግን እስቲ ደግሞ ይህቺ ዘመዳችንን አዳምጣት፡፡ በሕግ የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀት ባለችበት ሁኔታ ብዙ ነገር እየታዘበች ናት፡፡
    ምንድን ነው የታዘብሽው? (ልጅቷን ጠየቋት)
    መጀመርያ ከሁለት ወር በፊት ለጥናት ያሰብኩት ርእስ ሌላ ነበር፤ አሁን ግን ቀይሬው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አትኩሬያለሁ፡፡
    የምን ወቅታዊ ጉዳይ?
    የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና የፍርድ ቤቶች ሚና ከሕግ አንፃር ምን መሆን አለበት በሚል ዙርያ፡፡
    አልገባኝም፡፡
    በባንክ ችግር ሲፈጠር ባንኩ የፍርድ ቤት ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ ለአገር ውስጥ ገቢም ይሰጠዋል፡፡ ለኪራይ ቤቶችም ይሰጠዋል፡፡ አሁንም የከተማው አስተዳደር ይህን ያህል እቀጣለሁ ብሎ ቅጣት የመወሰን ሥልጣን እንዳለው እየሰማን ነው፡፡
    እና. .  . .
    እናማ ክቡር ሚኒስትር የፍርድ ቤቶች ኃላፊነትና ሥልጣን እየተቆራረጠ ለመሥርያ ቤቶች እየተሰጠ በኋላ ፍርድ ቤት የሚባል ነገር ሳይታወቀን እንዳይጠፋ ነው፡፡
    በየፍርድ ቤቱ ከመጓተት ይልቅ በመግባባት እንፍታው ብሎ ነው አስተዳደሩ ይህን በጎ አካሔድ የመረጠው እንጂ፤ የፍርድ ቤትን ሥልጣን ለመቀማት ብሎ አይደለም፡፡
    ከባለሀብቱ ጋ በመግባባትና በገንዘብ ከፈታው ከራሱ ሠራተኞች ጋር ታዲያ ለምን በመግባባት አይፈታውም? 
    እነሱ በገንዘብ ይቀጡ ከተባለ ገንዘብ የላቸውማ፡፡
    ስለዚህ መነሻው ፍትሕ ሳይሆን ገንዘብ ነው ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
    እ. . .እ. . . እ. . .እንደዛ ማለት አይደለም፡፡
    ምን ማለትዎ ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
    ለነገሩ የሕግ ነገር ስለማላውቅ ምን ማለት እንደሆነ በሕግ አንፃር ለራሴም ግልጽ አይደለም፡፡ አንቺ ግን በአጭሩ ምን እያልሽ ነው?
    የፍትሕና የሕግ አካሔዱንም ዶክተሩ እንዳሉት አድርጉ እያልኩ ነው፡፡
    እኮ የፍትሕና የሕግ ሥርዓቱ ምን ያስፈልገዋል እያልሽ ነው?
    ሲቲ ስካን!