(በናታን ዳዊት)
ከጥቂት ወራት በፊት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግሥት በ18 ዕቃዎች ላይ የዋጋ ተመን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ አብዛኛውን ሸማቾች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እፎይታ ሰጥቶ ነበር፡፡
እየቆየ ሲሄድ ግን ከሥጋ፣ በመጠኑም ቢሆን በቢራና በለስላሳ መጠጦች ላይ ካለሆነ በስተቀር ዋጋ የተተመነላቸው አብዛኛዎቹ ምርቶች ወደ ቀድሞ ዋጋቸው እየተመለሱ ሲሆን፣ የሸማቹን መጠነኛ ተስፋ ወደ ማጨለም ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እንዳውም አንዳንዶቹ ምርቶች ተወደደ ተብሎ ከነበረበት ጊዜ የበለጠ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩም ነው፡፡
የዋጋ ጭማሪው ወደ ቀደመው ዋጋ ሸቀጦችን መመለሳቸው ብቻ ሳይሆን መሠታዊ የዋጋ ተመን ከተተመነላቸውና መሠረታዊ ከሚባሉት ምርቶች ውስጥ እንደዘይትና ስኳር የመሳሰሉ ምርቶችን እንደልብ ማግኘት ያልተቻለበት ደረጀ ላይ ተደርሷል፡፡
ይህ ያልተረጋጋ የግብይት ስርዓት ሸማቹን እያማረረ ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መከተሉ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ማድረጉም አልቀረም፡፡
በአንድ ሌትር ቤኒዚን ላይ 1 ብር ከ79 ሣንቲም የጨመረበት ጊዜ ያልነበርና የወቅቱ የነዳጅ ጭማሪ አራተኛው በመሆኑ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የነዳጅ ጭማሪ ተደረገ ሲባል ቀድሞ የሚታየው በግብይት ውስጥ ተጽዕኖ ማሳደሩ ነው፡፡ በእርግጥም የነዳጅ ዋጋ መጨመር በእያንዳንዱ ምርትና አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲንርና የዋጋ ግሽበቱም በዚያው ልክ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በወቅታዊው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆኑ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በተለይ በተወሰኑ ምርቶች ላይ የተጣለው የዋጋ ገደብ እየተጣሰ ከመምጣቱ ጋር ተደምሮ የዋጋ ግሽበቱ አሳሳቢም እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በእርግጥ የነዳጅ ጭማሪው መንስኤ በዓለም ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ የማሻቀብ ምክንያት ዋነኛ የነዳጅ አምራች በሆኑ አገሮች ውስጥ የተቀሰቀሱት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ ይህ የሕዝብ ነውጥ ደግሞ ቀጣይ የማይሆንና አንድ ቦታ ላይ ሊቆም እንደሚችል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ከዚህ አንጻር መንግሥት የኑሮ ውድነትን የበለጠ ሊያባብስ የሚችለውን እንዲህ ዓይነቱ የነዳጅ ጭማሪ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አንዳንድ መስተካክሎችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ከወቅታዊው የነዳጅ ጭማሪ ጋር በተያያዘ እየተሰነዘሩ ያሉ አስተያየቶችም እንደሚያመለክቱት፣ ቢያንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረ ያልተጠበቀ ክስተት የነዳጅ ጭማሪ ሲደረግ፣ ጊዜያዊ የሆነው ክስተት ብዙ ነገር እንዳያበላሽ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ውስጥ እስከ 45 በመቶ ለነዳጅ የሚከፈለውን ታክስ መቀነስ ወይም ማስቀረት ጥሩ አማራጭ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በነዳጅ ላይ የሚጣለው ታክስ መቀነስ ወይም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ማስቀረት የዋጋ ማስተካከያ ተደርጐለት ለጥቂት ጊዜ ቢሰራበት እንደገና እያንሰራራ ያለውን የዋጋ እድገት በማረጋጋት ሸማቹን መታደግ ይቻላል፡፡
የሰሞኑ የነደጅ ዋጋ ጭማሪ እንደተለመደው በእጅጉ የሚጐዳው አነስተኛ ገቢ ያላቸውንና ደሞዝተኛውን ስለመሆኑ አይጠረጠርም፡፡
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የተወሰነ የደሞወዝ ጭማሪ ያገኙ ሠራተኞች የነዳጅ ጭማሪው በሚያስከትለው ተፅዕኖ የተደረገላቸውን ጭማሪ መልሶ ሊወስድባቸውም ይችላል፡፡ በሌሎች ዜጐች ላይም መጠኑ ይለያይ እንጂ ጫና ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ተደራራቢ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በተለይም እንደ ነዳጅ ያሉ ጭማሪዎች የሚያደርሱትን ተጽዕኖ ለማስቀረት መንግሥት በነዳጅ ላይ ታክስ በመቀነስ ሸማቹን ሊታደግ ይገባል፡፡
ችግሩ ዓለም አቀፍ ቢሆንም ለዜጐች ከአቅም በላይ ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ የኑሮ ውድነትን ሊያባብሱ የሚችሉ ከፍተኛ የነዳጅ ጭማሪዎችን የሚያስከትሉትን ችግር ለማለዘብ አገራዊ መፍትሔዎች የግድ ይላሉ፡፡


