Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹የማኅበረሰብ ተጠያቂነት ትክክለኛ ዓላማ የሐኪሙን ሥራ ለማክበርና የታካሚውን መብት ለማስጠበቅ ነው›› ዶክተር መንግሥቱ አስናቀ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

ዶክተር መንግሥቱ አስናቀ በፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ኃላፊ ናቸው፡፡ የተወለዱት፣ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በአዲስ አበባ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ (ጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በሕክምና የመጀመሪያና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋካሊቲ በፐብሊክ ሔልዝ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በሥራ ዓለምም በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በሕክምና፣ በፕሮግራምና በጤና መምሪያ ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአለርት ሆስፒታል የሳምባ ነቀርሳ፣ የሥጋ ደዌ በሽታና በሐዋሳ ደግሞ የሕፃናት የጤና ፕሮግራሞች አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ አጠቃላዩን የሕክምና አገልግሎት አስመልክቶ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሕክምና አገልግሎት ጫና እንዳይበዛበት ለማድረግ ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- የሕክምናው አገልግሎት የተቃና እንዲሆን ወይም ከጫና የፀዳ ለማድረግ ከተፈለገ በሽታዎችን በመከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ የመከላከሉንም ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ በእያንዳንዱ ቀበሌ ሁለት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ተመድበዋል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች በአብዛኛው የመከላከል፣ የጤና ማጎልበትና የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ሥራዎችን እያከናወኑ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የክትባት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በጤና ጣቢያ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የጤና ድርጅቶች ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የክትባት አገልግሎት በቀበሌ ደረጃ መሰጠት ተጀምሯል፡፡ በጤና ጣቢያ ተይዞ የነበረው ሥራ በመስፋፋቱ በእያንዳንዱ የጤና ኬላ ላይ እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መረዳት የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር በመከላከሉ ላይ የሚከናወነው ሥራ ካልተስፋፋ የሕክምና አገልግሎቱ ጫና ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት መከላከል ካልተቻለ በርካታ ሰዎች ይታመማሉ፡፡ ከታመሙ ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋማት ለመምጣት ይገደዳሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታም በሕክምና ተቋማት ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ለተቋማቱ ለዓመት እንዲበቃ ተመጥኖ የቀረበው ግብዓት ከጊዜው በፊት ያልቃል፡፡ በዚህም የተነሳ ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያዎችንና መድኃኒቶችን በሽተኛው ከግል ድርጅቶች ገዝቶ እንዲያመጣ ይገደዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የጤና ተቋማት የራሳቸውን ገቢ ለራሳቸው መተዳደሪያ እንዲያውሉት የሚያስችል ራስን በራስ የማስተዳደር (ኦቶኖመስ) እስከተሰጣቸው ድረስ የአቅርቦት ችግሮቻቸው ለምን አልተፈቱም?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- ተቋማቱ የራሳቸውን ገቢ የጤናውን ዘርፍ ጥራት ለማሻሻል እንዲያውሉት በመደረጉ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት እናያቸው የነበሩ መድኃኒቶች እጥረት ማለትም ከውጭ ግዙ፣ እዚህ የለም የሚባሉ ነገሮች እየቀሩ ነው፡፡ በአንዳንድ የመድኃኒት ዓይነቶች ላይ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አንዳንድ ተቋማት ካሁን በፊት የሌላቸውን የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን መግዛት ችለዋል፡፡ ይህንንም በማሟላታቸው በሽተኛውን ውጭ ሄደህ መድኃኒት ግዛ፣ የላብራቶሪ ምርመራ አድርግ፣ ወዘተ ማለታቸውን እየተው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ ሆስፒታሎች የተገነቡት ለበሽተኞች ምቹ በሆነ ሁኔታ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- አንድ ሆስፒታል ሲገነባ ለበሽተኛው ምቹ መሆን አለበት፡፡ በሸክም የሚመጣ በሽተኛ ደረጃ መውጣት የለበትም፡፡ በአሳንሰር ወይም በተሽከርካሪ መኝታ እየተገፋ ሊወጣ የሚችልበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ብዙዎቹ ሆስፒታሎች  ይህን ዘዴ ተከትለው የተገነቡ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለሌላ ሥራዎች በተጀመሩ ቦታዎች ላይ ሆስፒታል ያስፈልጋል ስለተባለ ብቻ በቅጥልጥል እየተገነቡ ሆስፒታሎች መጋዘን የሚመስሉበት ጊዜ አለ፡፡ ብዙዎቹ በመጀመሪያ ሲሠሩ የሚታሰበው የግልጋሎት መጠንና ከ15 ዓመት በኋላ ስናስባቸው ያለው ግልጋሎት መጠን አይመጣጠንም፡፡ በቀድሞ ጊዜ የተገነቡት ሆስፒታሎች ንድፋቸው እንኳን አንድ ዓይነት አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሚሠሩት የጤና ጣቢያዎች ግን ዲዛይናቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ወደ ተለያዩ ክፍሎች የሚያመሩ ኮሪደሮች፣ የመመዝገቢያ ቦታዎችና የሕክምና መገልገያ ክፍሎች ሁሉ አንድ ዓይነትና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የጤና ድርጅቶችን የሚያይና የሚፈቅድ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ በመቋቋሙ ነው፡፡ የዳይሬክቶሬቱ የሥራ አቅጣጫ የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ሲገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ይከታተላል፡፡

ሪፖርተር፡- በባለሙያ በማዋለድ ወይም በባለሙያ በታገዘ የማዋለድ አገልግሎት አነስተኛ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል አዳዲስ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከሚከናወኑትም ሥራዎች መካከል አንደኛውና ዋናው የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጡ አዋላጅ ነርሶች በብዛት የሚሠለጥኑበት ሁኔታ መኖሩ ይገኝበታል፡፡ ችግሩ በማዋለድ አገልግሎት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የሌላውም ሕክምና ባለሙያ ቁጥር ከአገልግሎት ፈላጊው ኅብረተሰብ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ ለስንት ሕዝብ የሚለው የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት ሲታይ ቁጥሩ አናሳ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የባለሙያ ፍልሰት አለ፡፡ ፍልሰቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከመንግሥት ተቋም ወደ ግል ሕክምና ተቋም የመፍለሱ ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ ይህም ሁኔታ በሕክምናው ላይ የተወሰነ ችግር ያሳድራል፡፡

ሪፖርተር፡- በአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና (ኢመርጀንሲ) የሚሰጡ ዕርዳታዎች ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና በአብዛኛው ሕይወትን ለመታደግ የሚያስችል አስቸኳይ ሕክምና መስጠት ማለት ነው፡፡ ተጎጂውን ከደረሰበት ችግር በቅድሚያ ማላቀቅ ወይም ደም እየፈሰሰ የመጣውን በቅድሚያ የሚፈሰውን ደም እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደሙ በመፍሰሱ ምክንያት ሌላ ችግር ከመጣ ተከታታይ የሆነ ሕክምና እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ በቅድሚያ ግን የሚፈሰው ደም መቆም አለበት፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ከመኪና ወይም ከእሳት አደጋዎች ጋር ቢያያዝ ሕክምናው የሚጀመረው የተጎዳው ሰው ወይም በሽተኛው ከወደቀበት ወይም ከተገኘበት ሥፍራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የመኪና አደጋ ይደርስና ተጎጂዎች በአግባቡ ወደ ጤና ተቋማት ስለማይጓጓዙ ለበለጠ አደጋ ይዳረጋሉ፡፡ በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ማለት አደጋ ከደረሰ ወይም ችግር ካጋጠመ በኋላ የሚቀጥለውን ሕክምና እስከሚያገኝ መርዳት ነው፡፡ ለዚህም እውን መሆን ከአምቡላንስ ጋር የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን የሚታየው አምቡላንሱ ከሾፌሩ በስተቀር ምንም ዓይነት ባለሙያ ሳያስከትል ተጎጂውን ሰው ወደ ሕክምና ተቋም ሲያጓጉዝ ነው፡፡ መሆን ያለበት ግን አምቡላንስ ውስጥ ኦክሲጂን፣ ግሉኮዝና ሌሎችንም አስፈላጊ መድኃኒቶች ከነሙሉ መገልገያ መሣሪያዎችና ባለሙያዎች ጋር መኖር እንዳለባቸው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ክፍል ምን ዓይነት የሕክምና መሣሪያዎች ሊኖሩ ይገባል?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- ላይፍ ሴቪንግ (ሕይወት አድን) የሆኑ እንደ ትንፋሽ የመሳሰሉ ነገሮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የደም ዝውውርን ማስተካከል የሚችሉና በተለያዩ የመንቀሳቀሻ አካላት ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ መጠገን የሚቻልበት ሁኔታ መመቻቸት ይገባዋል፡፡ ትንፋሽ ሲባል ኦክስጅን መስጠት ብቻ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ዘዴ ትንፋሽ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የልብ ምት ድንገት ሊቆም ይችላል፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ማስነሳት የሚችሉ መሣሪያዎች ሊኖሩት ግድ ይላል፡፡ ወይም ለትንፋሽና ለልብ ምት ሊያገለግሉ የሚችሉ የተለያዩ መሣሪያዎችና የሠለጠነ ባለሙያ ሊኖረው ይገባል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና አገልገሎት መስጠት የሚችል የሠለጠነ ባለሙያ መኖር አለበት፡፡ በዚህ በኩል ብዙ ባለሙያዎች የሉንም፡፡ የተወሰኑ ናቸው ያሉት፡፡ ሁሉም ባለሙያ ሲማር በተወሰነ ነገር ይሠለጥናል፡፡ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ ሕክምና ላይ የሚመደብ ባለሙያ የበለጠ ሥልጠና ማግኘት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ድንገተኛ አደጋ የደረሰበት ሰው ሕክምና ተቋም ከደረሰ በኋላ ፈጣን የሆነ አገልግሎት ሲያገኝ አይታይም፡፡

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- የተጎዳ ሰው ወደ ሕክምና ተቋም ሲደርስ በፍጥነትና በቅድሚያ ሕክምና አያገኝም እየተባለ ይነገራል፡፡ እንደ አንድ ባለሙያ ስናስበው ግን  ሕሙማን በተራ ወረፋ ይዘው እየጠበቁ ነው፡፡ ምናልባት ፊታችን ላይ አንዳንድ ጊዜ ስንፈነከት ደም በአንዴ ነው በብዛት ፍስስ የሚለው፡፡ ይህም የሚሆነበት ምክንያት በፊታችን ዙሪያ ትናንሽ የደም ስሮች ስላሉ ነው፡፡ እንደ ሕክምና ባለሙያ ሲታይ ግን ተፈነካክቶ ደሙ ከፊቱ ላይ ፈስሶ ከሚታየው ተጎጂ የበለጠ የልብ ምቱ ለቀነሰበትና ሕይወቱ ለአደጋ ለተጋለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ በመጀመሪያ ደረጃ ቅድሚያ የሚያስፈለገው ሰው የትኛው ነው ተብሎ ይለያል፡፡ በኢመርጀንሲ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ ከሚመጡት ሕሙማን መካከል ምንም ዓይነት ደም በፊቱ ላይ ሳይታይ አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልገው በሽተኛ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕሙማን ተራ ሲገቡ የሚደረግ ነገር ቢኖር ማንነው ቅድሚያ የሚያስፈልገው የሚለው ነው፡፡ ተራ ቀድሞ ስለመጣ ብቻ አገልግሎቱን በቅድሚያ ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ በኋላ ዘግይቶ የመጣው በሽተኛ ለሞት የሚያጣጥር ከሆነ ቅድሚያ ሊያገኝ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና ባለሙያዎች የማኅበረሰብ ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- የማኅበረሰብ ተጠያቂነት ገደብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ሁላችንም እንደ ባለሙያ ሥነ ምግባር አለን፡፡ ለሥነ ምግባሩ ተገዢዎች ነን፡፡ አንድ ባለሙያ ሥነ ምግባሩን በአግባቡ ካልፈጸመ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሐኪም ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ተመርቆ ሁሌም ሐኪም ነው ተብሎ መቀጠል የለበትም፡፡ በየጊዜውና በየወቅቱ ራሱን መሻሻል ይኖርበታል፡፡ የተለወጡ ነገሮች ምንድናቸው? የሚለውን ማየት መቻል አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በየጊዜው በሙያው የጥራት ማረጋገጫ ሊኖረው ይገባል፡፡ የጥራት ማረጋገጫ የመስጠቱ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡ ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በዚህም በኩል የሙያ ማኅበራት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ የሙያ ማኅበራት የባለሙያውን መብት ማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡን ወይም የኅብረተሰቡን የጤንነት መብት ማስጠበቅ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የማኅበረሰብ ተጠያቂነትን በተሳሳተ መልኩ የሚተረጉሙ ወገኖች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሐኪሙን ለማሳጣት ተደርጎ የሚወሰድበትም ጊዜ አለ፡፡ የማኅበረሰብ ተጠያቂነት ትክክለኛው ዓላማ የሐኪሙን ሥራ ለማክበርና የታካሚውን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ ሐኪሙ ድንገት ሲያጠፋ አጥፍተሃል እንዲባል፣ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ (ታካሚው) ደግሞ መብቱ ያልሆነውን ነገር ሲጠይቅ አይሆንም እንዲባል ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የማኅበረሰብ ተጠያቂነት የሐኪሙ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆን አለበት፡፡ ኅብረተሰቡም መብትና ግዴታውን እንዲያውቅ፣ ሐኪሙም የበሽተኛውን ወይም የደንበኛውን መብትና ግዴታ ጠብቆ እንዲሠራ ያደርጋል፡፡ የማኅበረሰብ ተጠያቂነት ካለ እኮ ጥሩ የሥራ ዕውቅና ያስገኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ የሕክምና ባለሙያ እስከ 40 በሽተኞች አይቶ ወይም ሦስት አራት ቀዶ ሕክምና ሲሠራ አድሮ፣ በማግስቱ ለምን ሌላ በሽተኛ አላየህም ወይም አላከምክም ተብሎ ግፊት ሊደረግበት አይገባም፡፡ ግፊት ተደርጎበት ሲሠራ ምናልባት በድካሙ ምክንያት ስህተት ሊፈጽም ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- አንድ ሐኪም በቀን ስንት ሕሙማንን ማየት አለበት?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- ይህን ያህል ለማለት ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም በሽታዎች ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ ለክትትል የመጣን በሽተኛ ለአሥር ደቂቃ ያህል አነጋግሮና አንዳንድ የሚለኩ ነገሮች ካሉ ተለክቶ ሊሄድ ይችላል፡፡ አዲስ በሽተኛ ደግሞ 30 ደቂቃ ግፋ ቢል ደግሞ አንድ ሰዓት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ማየት አለብህ ተብሎ በኮታ ከተሰጠው ችግር አለበት፡፡ ባለው ሰዓት የተሰጠውን ኮታ ለማሟላት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የአገልግሎት ጥራት ሊጓደል ወይም ሊበላሽ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፈራል ለምን አስፈለገ?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- ሪፈራል ያስፈለገው በሽተኛው በመጀመሪያ የታየበት የሕክምና ተቋም ውስጥ ችግሩን ሊያይለት ወይም መፍትሔ ሊሰጠው የሚችል ባለሙያ፣ እንዲሁም የላብራቶሪና ሌሎች የመመርመሪያ መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ነው፡፡ በተረፈ ሕክምናውንና መፍትሔውን ታች ወይም መጀመሪያ የታየበት ቦታ ላይ ማግኘት እየቻለ ወደላይ የሚሄድ ከሆነ ላይ ባለው ባለሙያ ላይ መጨናነቅ ይፈጥራል፡፡ የመጨናነቁ ሁኔታ ደግሞ የአገልግሎት ጥራትን ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ያዳክመዋል፡፡ ስለሆነም በጤና ኬላ ላይ አገልገሎቱ ሲሰጥ ጤና ጣቢያ ላይ ያለው መጨናነቅ ይወገዳል፡፡ ጤና ጣቢያው ደግሞ እንደዚሁ ከሠራ በሆስፒታል ደረጃ ያለው መጨናነቅ ይከስማል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች ሕሙማኑን በቅን ልቦና ማገልገል ሲገባቸው ሲበሳጩና ሲነጫነጩ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ያሉበት የሕክምና ተቋም ለሥራ ምቹ ባለመሆኑ ነው? ወይስ በሥራ ጫና ሳቢያ ነው?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- የባለሙያ ተነሳሽነት በሚታይበት ጊዜ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንደኛውና ትልቁ ነገር የተለያዩ የሥራ አቅርቦቶች ተሟልተው መገኘት የሥራ ተነሳሽነትን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ለተነሳሽነት ማነስ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው በሥራ አካባቢ ላይ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች በበቂ ሁኔታ ተሟልተው አለመገኘት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛ የሥራ መደራረብ ይኖራል፡፡ ማንም በሽተኛ መድኃኒት ውጭ ሄደህ ግዛ መባልን አይፈልግም፡፡ በሕክምና ተቋሙ ውስጥ መድኃኒቱ ሳይኖር ቀርቶ ግን ውጭ ሄደህ ግዛ ሲባል መጀመሪያ የሚያማርረው ሐኪሙን ነው፡፡ መድኃኒት በተቋሙ ውስጥ አለመኖሩ የሐኪሙ ኃላፊነት አይደለም፡፡ በጤናው ዘርፍ ሥርዓት ውስጥ ያሉት አካላት ይህንን ክፍተት ማሟላት ነበረባቸው፡፡ ይህ ባለመሟላቱ ምክንያት መጀመሪያ የሚወቀሰው ፊት ለፊት የሚገኘው ሐኪሙ ነው፡፡ የሕክምና ሥራ ደግሞ የቡድን ሥራ ነው፡፡ የቡድን ሥራ ሲባልም በራፍ ላይ ጥበቃ ሥራ ላይ ካለው ሰው ጀምሮ እስከ ዋናው ሥራ አስፈጻሚ ወይም የበላይ ኃላፊ እስከሆነው ሰው ድረስ ይጠቃለላል፡፡ በቡድን ሥራው በደንብ ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሐኪም የተፈለገውን ያህል እውቀት፣ ክህሎትና ችሎታ ቢኖረው የቡድን ሥራው ካልተሳካ ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ሕክምና ተቋማት የሚያስከፍሉት ገንዘብ የታካሚዎችን አቅም ያገናዘበ አይደለም ስለሚባለውስ?

ዶ/ር መንግሥቱ
፡- በዚህ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የኅብረተሰብ ተጠያቂነት መኖር ካለበት እንቅስቃሴ ውስጥ አንዱ ይኼ ነው፡፡ አንድ የሕክምና ተቋም ለትርፍ የተቋቋመ ቢሆንም ትርፍ ያገኘው ተገልጋዩን ኅብረተሰብ አስደስቶና አርክቶ ነው? ወይስ አራቁቶ ነው? የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የሚያሳዩት የመንግሥት የሕክምና ተቋማትም ማንነው የሚያገለግሉት ተብሎ ቢታይ፣ ደሃ ነው የተባለው ሰው አገልግሎቱን አያገኝም፡፡ ተቋማቱ አነስተኛ ዋጋ ቢያስከፍሉም ይህንኑ ዋጋ መሸፈን የማይችል ደሃ መኖሩን መዘንጋት አይገባም፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ፀበልና ሌላም ፈውስ አገኝበታለሁ ብሎ ወደሚያምንበት ሥፍራ ይሄዳል፡፡ ዜጎች ማኅበራዊ ኢንሹራንስ መግባት አለባቸው የሚባለው እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ነው፡፡ ሁሉም የግል ሕክምና ተቋማት በሕክምና ባለሙያዎች ነው የሚመሩት ለማለት አያስደፍርም፡፡ አብዛኛዎቹ ከሕክምና ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ባለንብረት የሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም በሕክምናው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ተጽእኖ የሚያሳድረውም አላስፈላጊ የሆኑ ላብራቶሪዎችን፣ አልትራ ሳውንድንና ሌሎችንም ምርመራዎች ሐኪሙ እንዲያዝ በማድረግ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ገቢ ለማግኘት ሲሉ ነው፡፡ ባለቤቱ ገቢውን ነው የሚያየው፡፡ በሕክምና ባለሙያ ባለቤትነት በሚመራ የግል የሕክምና ተቋማትና ከሕክምና ዘርፍ ውጭ በሆነ ግለሰብ ባለቤትነት በሚመሩ የግል የሕክምና ተቋማት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ባለቤቱ የሕክምና ሙያ ካለው አንድን በሽተኛ ገንዘብ እስከሌለው ድረስ በነፃ ሊያክመው ይችላል፡፡ ባለቤቱ የሕክምና ባለሙያ ካልሆነ ግን ገቢውንና ትርፉን ብቻ ስለሚያሰላ በነፃ የመርዳቱን ሁኔታ ቦታ አይሰጠውም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያም ወደዚሁ የገባው የሕክምና ዘርፍ አትራፊ ነው ብሎ በማመኑ እንጂ ለማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ላበርክት ብሎ አይደለምና፡፡