በምሕረት ሞገስ
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለዲያስፖራው የቦንድ ሽያጭ ማቅረቡን በተመለከተ በካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ አዳራሽ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
ቁጥራቸው ከ100 የማያንሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ተሳትፈዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ጋዜጠኞችም ታድመው ነበር፡፡ ዲያስፖራው በቦንድ ሽያጭ ወለድ ላይ የዋጋ ማሻሻያ እንዲኖር፣ እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሣ ውይይቱ ቀጠለ፡፡ ከመድረኩ ከሚነሡት የቦንድ ሽያጭ አካሔድ ውይይቶች ወጣ ያለ አቤቱታ ከአንድ እድሉ ከተሰጣቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተሰማ፡፡
ብሶታቸውን ሲገልጹ ሲቃ እየተናነቃቸውና ስሜታቸውንም ከመቆጣጠር ውጭ ሆነው ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊው በሰጠችው የኢንቨስትመንት እድል መሠረት በአገሬ ለመሥራት ልጆቼንና ባለቤቴን 20 ዓመት ከኖርንበት አሜሪካ፤ ቤቨርሊሂልስ አፈናቅዬ፣ ንብረቶቼንና ልሠራ ባቀድኩበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ መሣርያዎችን በኮንቴነር አስጭኜ አገሬ ገባሁ፡፡ ኮንቴነሮቹን ከጅቡቲ ወደብ ለማንሣት ከሦስት ሳምንት በላይ እንደማይፈጅብኝ ገምቼ የነበረ ቢሆንም፣ ሊሳካ አልቻለም፡፡ በወደብ ላይ ከሦስት ወራት በላይ አስቆጠረ፡፡ በጅቡቲ መንግሥት በኩል ለወደብ ኪራይ በቀን 125 የአሜሪካ ዶላር ይከፈላል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ዕቃውን ለማስገባት አትችልም፤ ካስገባህም ከቀረጥ ነፃ አይሆንም ተብያለሁ፡፡ ያልገባሁበት ቢሮ የለም፡፡ ችግሩ አልተፈታም፡፡ ችግር ላይ ነኝ፡፡›› እያሉ ችግራቸውን ሲተነትኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ስብሰባው ሲያልቅ ግን እንደሚያነጋግሯቸው ገለጹላቸው፡፡
ስብሰባው ሲበተን ግለሰቡ ስለገጠማቸው ችግር ዝርዝር ጉዳይ እንዲነግሩን ጠይቀን በወቅቱ ጉዳዩ በሚድያ እንዲዘገብ እንደማይፈልጉ ችግሩ ሲፈታ ግን ፈቃደኛ እንደሚሆኑ ቃል ገቡልን፡፡
በወቅቱ ዕቃው መግባት እንደማይችል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተሰጠው የኢንቨስትመንት ዕድል መሠረት ከቀረጥ ነፃ መግባት ሲገባው ከቀረጥ ነፃ መግባት እንደማይችል፣ በመኪና ላይ የተገጠመው ተንቀሳቃሽ ወርክሾፕም ሆነ ሌሎቹ ዕቃዎች መግባት እንደማይችሉ ከገቡም 2.1 ሚሊዮን ብር ቀረጥ መክፈል እንዳለባቸው ተነግሯቸው ነበር፡፡
ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከኢንቨስትመንት ኤጀንሲ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ያስጫኗቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመናዊ መሣርያዎች በጅቡቲ ወደብ 5 ወር ከ20 ቀን ካስቆጠሩ በኋላ በጅቡቲ መንግሥትና በዚም ሺፒንግ ላይን በተደረገላቸው ቅናሽ 35 ሺሕ ዶላር የወደብ ኪራይ መክፈል ሲገባቸው 22 ሺሕ ዶላር ከፍለው፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ደግሞ ተጠይቀው የነበረ 2.1 ሚሊዮን ብር ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ስለተፈቀደላቸው ከሁለት ዓመት ውጣ ውረድ በኋላ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡
ቢሯቸው ከሚገኝበት ግቢ እንደደረስን ገለጻ የተደረገልን የኢንፎርሜሸን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፋሲሊቲዎች ላይ ነበር፡፡ ከኢንተርኔት፣ ከኔትወርኪንግና ከኮምፒውተር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሥራዎች የሚያከናውኑበት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀውና በመኪና ላይ የተገጠመው ተንቀሳቃሽ ወርክሾፕ፣ በየቢሮዎች ውስጥ የተገጠሙ የኢንፎርሜሸን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሣርያዎች ተገልጋዮቻቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ኢንጂነር እምሩ ደጉ ይባላሉ፡፡ በተወለዱበት ወሎ፤ ኡርጌሳ አካባቢ ለሰየሙት የኡርጌሳ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከእውቀታቸው ጋር ተያያዥነት ያላቸውንና በእጅጉ ከቴሌኮም ኢንዱስትሪው ጋር ተቀናጅተው ለአገር ጥቅም ይሰጣሉ ያሏቸውን፤ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የተከተሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሣርያዎች ኢትዮጵያ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸው ሥራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡
ለመንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለይ ደግሞ ለንግዱ ዘርፍና ለገንዘብ ተቋማት፣ ለሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች የሚያገለግልና መረጃን በማዕከላዊ መንገድ የሚያስተዳደር መሠረተ ልማት (Data Center Infrastructure) መዘርጋት፣ መረጃዎች በፍጥነት የሚፈለጉበት ቦታ እንዲደርሱ ማድረግና መረጃዎቹን ከጥፋት መጠበቅ የሚያስችል ለኢትዮጵያ ጠቃሚና ዓለም የደረሰበትን አዲስ ቴክኖሎጂ ለአገልግሎት ፈላጊው ለማድረስ መዘጋጀታቸውን ነግረውናል፡፡
ቴክኖሎጂው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልንም ሆነ የደኅንነት ሥራዎችን በቴክኖሎጂው ዘርፍ የአሜሪካው ከደረሰበት ለማድረስ የሚያስችልና የደኅንነት/የመረጃ ጥበቃ ዘዴዎችን በመጠቀምም መረጃዎች የሚፈለጉበት ቦታ ብቻ እንዲደርሱ ማድረግንም ያጠቃልላል፡፡
‹‹ብዙ ችግሮችን አልፌ ለሥራ በመብቃቴ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ ያልጠበቅሁት ፈተና ገጥሞኝ መስዋዕትነት ከፍያለሁ፡፡ እኔም ሆነ በቤተሰቦቼ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለን ኢትዮጵያ መጥተናል፤›› የሚሉት ኢንጂነር እምሩ፣ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም ባለመለመዱ ግንዛቤውን መፍጠር ዋና ኃላፊነታቸው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ መግባቱ በራሱ ስኬት መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡
ኢንጂነር እምሩ፣ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሲወስኑ የመጀመርያ ዓላማቸው በዩኒቨረሲቲዎች ውስጥ እውቀታቸውን ማስተላለፍ ቢሆንም፣ በተፈጠረው አጋጣሚ እስካሁን አለመጀመራቸውን፤ በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር ቅርበት ያላቸውን አካላት በማስተማርና በማሰልጠን እውቀታቸውን እንደሚያስተላልፉ፤ ዘርፉም በኢትዮጵያ እንዲታወቅና ሥራ ላይ እንዲውል እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያቸው ይዞት የመጣውን አዲስ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ በተግባር ማዋል፤ የንግዱንም ዘርፍ ሆነ የመንግሥት ተቋማትን በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሁም የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል፡፡
የኢንፎርሜሸን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ስነዳ (ዶክመንቴሽን)፣ የመረጃ አያያዝና አጠባበቅ፣ ንግድን ከአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እርስ በርስና ከተለያዩ ተቋማት ጋር መረብ በመዘርጋት (ኔትወርክ በማድረግ) ቀጣይነቱን ማረጋገጥና ሌሎችንም ተያያዥ መሠረተ ልማቶች እንደሚሠሩ የነገሩን ኢንጂነር እምሩ፣ በአሜሪካ ኢምፔሪያል ካፒታል በተባለ የገንዘብ ተቋምና በሌሎች ኩባንያዎች ሲያገለግሉ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢዝነስ ቴክኖሎጂ፣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንትና ኢኮኖሚክስ ዘርፍ ከካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሎሳንጀለስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከማይክሮሶፍት ኮርፖሬሽን፣ በማይክሮሶፍት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛውን የኢንጂነሪንግ ሰርተፍኬትም ተቀብለዋል፡፡


