በምሕረት አስቻለው
ለአንድ ዓመት መንግሥታዊ ባልሆነ አንድ ድርጅት ዳይሬክተር ሆና ሠርታለች፡፡
ድርጅቱ ለኃላፊነት ቦታው ሴት መቅጠር ይፈልግ የነበረ ቢሆንም የመጀመርያዎቹ ሁለትና ሦስት ወራት ፈታኝ ሆኖባት ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ በባሕሪዋ በሰዎች ላይ ጫና መፍጠር የማትመርጥ ይልቁንም ነገሮችን በቀላሉ በመግባባትና በመቀራረብ ማስኬድ የምትፈልግ ዓይነት ሰው መሆኗ በወቅቱ ገጥሟት ለነበረው ችግር ምክንያት ነው፡፡
ወ/ት ኅላዊት በላይ ትባላለች፡፡ ‹‹በተፈጥሮዬ ሰዎች ላይ ግፊት ማድረግ አልፈልግም፤ አልችልምም፡፡ መጀመርያ አካባቢ ምንም ዓይነት ሥራዎችን ለማስፈጸም የምወስነውና ወደ ተግባር ለመግባት የምሞክረው ይመለከታቸዋል የምላቸውን በማወያየት ነበር፡፡ ነገር ግን ማንም በቁም ነገር እንደ አለቃ ሊቆጥሩኝ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ትንሽ ልጅ አምጥታችሁብን ማለት ጀምረው ነበር፡፡››
የኃላፊነት ደረጃዋን አለቅነቷን መቀበል የቸገራቸው፤ ይበልጥም አስቸግረዋት የነበሩት በሥሯ የነበሩ ሴት ሠራተኞች እንደነበሩ፤ ይህ የሆነው ሴት ስለሆነች ሳይሆን ሴት ልጅ በባሕሪዋ ጫና መፍጠር፣ ሰዎችን በኃይል መግፋት የማትፈልግ በመሆኑ፣ በእሷም የአመራር ዘዬ ይስተዋል የነበረው ይኸው ስለነበር እንደሆነ ይሰማታል፡፡ ከሁለትና ከሦስት ወራት ሁኔታዎችን ማጤን በኋላ በዚያ መልኩ ውሳኔዎችን ማስፈጸምና ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደማትችል ተረድታ ከውሳኔ ላይ ደረሰች፡፡
‹‹እንደዚህ እናድርግ፣ ይኼን ብናደርግ ይሻላል ብዬ ማነጋገር አቆምኩ፡፡ ይሆናል ያልኩትንና መሆን ያለበትን ወስኜ ውሳኔዬን ብቻ ማሳወቅ ጀመርኩ፡፡ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ኃይለኛ መሆን ጀመርኩ፡፡ ሥራውን በማይጎዳ አካሔድ ስቀየር እነሱም ተቀየሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ሥራውም በጥሩ መልክ መቀጠል ጀመረ፡፡ እወስናለሁ፤ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን አሳውቃለሁ፤›› ብላናለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዚያ ድርጅት ለቅቃ በሌላ ድርጅት ውስጥ ከሞላ ጎደል በኃላፊነት ደረጃ በመሥራት ላይ እንደሆነች ነግራናለች፡፡ ዛሬ ላይ ከዚያ የኃላፊነት ተሞክሮዋ የተማረችው በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች በሥራቸው ባሉ ሠራተኞች ተቀባይነት እንዲያገኙ፣ ውሳኔያቸው ተፈጻሚና ውጤታማ እንዲሆን ቀለል ያለ የአመራር ዘዬ ሳይሆን ገዥነትና የበላይነት የነገሠበት አመራር (authoritarian leadership style) መከተል እንዳለባቸው ነው፡፡
እንደ ኅላዊት አገላለጽ፣ ለሠራተኞች ብዙም ሥልጣን መስጠት ሥራዎች በአግባቡ እንዲሠሩ፣ አለቆችም ውጤታማ እንዲሆኑ አያደርግም፡፡ ኃላፊነትና የተወሰነ ሥልጣን መስጠት ውጤታማ ሆኖ ሊሠራ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር ብታምንም በልምዷ የተመለከተችው በተቃራኒ ያለውን ነው፡፡ ስለዚህም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች በውሳኔ ላይ ጠንካራ እንዲሆኑ ትመክራለች፡፡
ያነጋገርናት ሌላዋ ወጣት ደግሞ በአንድ የመንግሥት መሥርያ ቤት ውስጥ የውጭ ግንኙነት ኦፊሰር ነች፡፡ በኃላፊነት ደረጃ ስለሚገኙ ሴቶች የአመራር ሁኔታ ሁለት ነገሮችን፤ በሥራ አስኪያጅነት ደረጃ ያለውንና በማንኛውም ደረጃ ያሉ ሴቶችን የአመራር ብቃትና ተቀባይነት ለይቶ ማየት እንደሚያስፈልግ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ጥቂት የማይባሉ ሴት ሥራ አስኪያጆች በተለያዩ አጋጣሚዎች የቢሮ ስልክ አቃጭሎ ካነሡ ሥራ አስኪያጁን እንዲያገናኙ ይጠየቃሉ፡፡ ራሳቸው እንደሚሆኑ አይጠብቁም፡፡ ከቢሮ ውጪ በአካል ሲገኙም ተመሳሳይ ሁኔታ ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው መጀመርያውኑ ሰዎቹ ሥራ አስኪያጅ ብለው ሲሥሉ የሚሥሉት ወንድ እንጂ ሴት ስላልነበር ነው፡፡››
የሴትም ይሁን የወንድ አለቆች የአመራር ስኬት መሠረት የሚሆነው ለተቀመጡበት ቦታ ያላቸው ችሎታና ብቃት እንዲሁም ስብዕናቸው እንደሆነ ይሰማታል፡፡ በሥራቸው ባሉ ሠራተኞችና በእነሱ ደረጃ ባሉ ሌሎችም የሚኖራቸው ተቀባይነትም በዚያ መልኩ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን በተለየ ሁኔታ ሴት አለቆች በተወሰነ መልኩ ፈላጭ ቆራጭ የመሆን አዝማሚያ በብዛት እንደሚታይባቸው፤ በዚህም እንዳልተሳካላቸው መመልከቷን ገልጻልናለች፡፡
ቀደም ሲል ትሠራበት በነበረው መሥርያ ቤት የቅርብ አለቃዋ ሴት ነበረች፡፡ የምታምንበትን ነገር ለመናገርም ለማስፈጸምም ብቃት፣ ሥራ ላይ ጥሩ ትኩረት የነበራት በመሆኗ ከሷ በላይም ሆነ በታች ከነበሩ ሠራተኞች ጋር የነበራት ግነኙነት መልካም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዛሬ ላይም የቅርብ አለቃዋ ሴት ብትሆንም በችሎታና በአመራር የገጠማት ነገር የተለየ ነው፡፡ ‹‹ይህቺኛዋ አለቃዬ እንደ ብዙዎቹ ሴት አለቆች ምርጥ አለቃ የመሆን ከልክ ያለፈ ፍላጎት ያላት፣ ነገር ግን ምንም ዓይነት የአመራርነት ብቃት የሌላት ነች፡፡ ውሳኔ የምታስተላልፈው፣ ሥራ ለማሠራት የምትሞክረው በኃይልና በማስፈራራት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሆነው ሴት ስለሆነች ሳይሆን ለቦታው የሚመጥን ችሎታ ስለሌላት ነው፡፡ ጥሩ አለቃ መሆን መቻል የሚወሰነው ቦታው ወይም ሥራው የሚፈልገው ብቃት መኖርና በራስ መተማመን ላይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንዳንዶች በተፈጥሮ ጥሩ አለቃ መሆን የሚችሉ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሒደት በልምድ ጥሩ መሪነትን ይላበሳሉ፡፡››
በሌላ መልኩ ከሴቶች የመሪነት ችሎታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚሰማት የሴቶች ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው፡፡ እንደ እሷ አባባል ሴት ልጅ ከወንድ ጋር ስትነፃፀር በጣም ለስላሳ ነች፡፡ ያ ደግሞ በሚኖራት ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ይንፀባረቃል፡፡ እናም በሥራ ላይ ይህ ባሕርይ ሲንፀባረቅ እንደ ደካማነት ሲቆጠር፤ ሁኔታውንም ባልተገባ መልኩ ሌሎች የግል ፍላጎታቸውን ሊያሳኩበት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ይኽ ደግሞ በሴቶች የአመራር ዘዬ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ‹‹ብዙዎች በሚጠብቁትና በሚቀበሉት ኃይለኛ መሆንና ነገሮችን በኃይልና በትዕዛዝ ማስፈጸም ዓይነት አካሔድ ያመጣል፡፡ ነገር ግን ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ብዙ ሴት አለቆችንም አንዳይሳካላቸው ያደረገ ይመስለኛል፡፡››
ለሁለት ዓመታት በሠራበት ድርጅት ውስጥ ሥራ አስኪያጇ ሴት ነበረች፡፡ በአጋጣሚ ከሥሯ ከነበሩ ሠራተኞች ከጥቂቶች በቀር አብዛኞቹ ወንዶች ነበሩ፡፡ የአመራር ዘዬዋ አምባገነናዊ ቢሆንም ውጤታማ እንደሆነች ይናገራል፡፡
‹‹ብዙዎቻችን ወንዶች ስለሆንን አለቅነቴን ሊቀበሉት አይፈልጉም የሚል እሳቤ ያላት ይመስለኛል፡፡ ማንኛውንም ነገር የምትመለከተው ከዚያ አንፃር ነው፡፡ እንደ ፍላጎቷ የሚሰማትን የአመራር ዓይነት መከተል ብትችልም አምባገነን መሆን ያስኬዳል ብላ ስለምታምን ሳይሆን፣ እንደዚያ ካልሆንኩ የበላይነቴን አይቀበሉም የሚለውን አስተሳሰብ መነሻ አድርጋለች፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡››
በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ የተለያዩ አስተያየቶችን ወይም ጥያቄዎችን የእሷን ያመራር ብቃት ከጥያቄ ውስጥ እንደመክተት፤ ይህ ደግሞ ሴት ስለሆነች ብቻ እንደሚመስላት ይሰማዋል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ የምትለውን ነገር ከመቀበል፣ የምታስተላልፈውንም ትዕዛዝ ከመፈፀም በስተቀር ምንም ዓይነት ጥያቄ ማንሣት እንደማይቻል እንዳሳወቀቻቸው ነግሮናል፡፡
እሱን ጨምሮ በሌሎች ሠራተኞች በኩል የአመራር ብቃቷን በሚመለከት ስላለው ነገር ጠይቀነዋል፡፡ ‹‹ሁላችንም ማለት ይቻላል ትዕዛዟን እንቀበላለን፤ እንፈጽማለን፡፡ እሷ ግን ሠራተኞቹ ኃላፊነት ስለሚሰማንና ሥራችንን አውቀን ስለምንሠራ ሳይሆን ኃይለኛ በመሆኗ ብቻ ይመስላታል፤›› በማለት መልሶልናል፡፡


