Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የኤርትራ ተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በየማነ ናግሽ

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ረፋድ አካባቢ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ‹‹በኤርትራ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የስትራቴጂ ለውጥ ማድረጉን›› በተመለከተ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ፣ በምሳ ሰዓት አዲስ አበባ ወደሚገኘው ገነት ሆቴል ጎራ ስል በአካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ ጥብቅ የሆነ የፀጥታ ክትትልና ፍተሻ ተመለከትኩና ስለሁኔታው የሆቴሉን ሠራተኞች ከመጠየቄ በፊት፣ ከአራት ዓመትና ከሁለት ዓመት በፊት የተደረጉትን የኤርትራ ተቃዋሚዎች ጉባዔዎች አስታወሰኝ፡፡ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ከመድረሴ በፊትም፣ ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ፣ ቃለ መጠይቅ ሳደርግለት ‹‹ሻዕቢያ የሚገባው ብቸኛ ቋንቋ ጠመንጃ ነው›› ያለኝን ወጣት ያሲን መሐመድ አብደላ (የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ) ተመለከትኩኝ፡፡ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ስብሰባ በሆቴሉ እየተካሄደ መሆኑንም ገመትኩኝ፡፡ ‹‹የኤርትራ ሠራዊት የመዋጋት ሞራል የለውም፤ እናቱና አባቱ በእስርና በረሃብ እየማቀቁ፣ ወንድሞቹ ከትምህርት ቤት ተመንጥረው ወደ ውትድርና እየተወሰዱ እያየ ለምን ብሎ ይዋጋል?›› በማለት በኤርትራ ስለነበረው ወቅታዊ ሁኔታ የተናገረውን አስታውሼ አዋራሁት፡፡ ለያሲን በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገሮች ተባብሰዋል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ወደ ውትድርና በገፍ የሚወሰድ ወጣት የለም፡፡ ወጣቱ ቀደም ብሎ ወደ ውትድርና ውስጥ ተገፍትሮ ገብቷል፤ ወይም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ ሱዳንና የመሳሰሉ ጎረቤት አገሮች በአጋጣሚ የማለፍ ወይም ወደ ባህር ማዶ የመውጣት መልካም ዕድል ገጥሞት ይሆናል፡፡

በሶማሊያ አካባቢ የነበረው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግሥት ትኩረት በኢትዮጵያ ወታደሮች በኋላ የተበታተነው አክራሪ እስላማዊ ቡድንን በመደገፍ ላይ ነበር፡፡ በአንዳንዶቹ እንደ ‹‹የውክልና ጦርነት›› ተደርጎ የተተነተነው ይህ የሶማሊያ ጦርነት ጊዜ ከመግዛት ውጪ ሌላ ጥቅም አላስገኘላቸውም ለፕሬዚዳንቱ፡፡ በእርግጥም እስካሁን ተግባራዊ ባይሆንም የኤርትራ ፕሬዚዳንትና መንግሥታቸው በሶማሊያና በጂቡቲ ባደረጓቸው ሕገወጥ ጣልቃ ገብነቶች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ወታደራዊ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

ያሲን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን አደረግኩት ስላለው የአቋም ለውጥም ድሮም ‹‹የዘገየ ነው›› ከማለት ውጭ የሚለው አልነበረውም፡፡ የኢትዮጵያ የፀጥታና የደኅንነት ጉዳይ ኤርትራ ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር እጅግ የተቆራኘ መሆኑን አምርሮ በመናገር፡፡ የኤርትራ ተቃዋሚዎች በዚሁ ስብሰባ በውጭ አገር ፓርላማ የሚያቋቁሙበትን ሁኔታና የኤርትራ መንግሥትን የሚቃወሙ ሠልፎችና እንቅስቃሴዎችን የሚያካሂዱበትን ለማመቻቸት ከኤርትራ ሲቪክ ማኅበራትና የሃይማኖት አባቶች ጋር እየመከሩበት መሆናቸውን ነበር የገለጸልን፡፡  ከስድስት ወራት በፊት የኤርትራ ሕዝባዊ ጉባዔ ለማካሄድ እንዲያስችል የተቋቋመው ይህ አመቻች ኮሚቴ 53 አባላትን ያቀፈ ሲሆን፣ 11 አባል ፓርቲዎች ያሉት የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ኪዳንን (ጥምረት) ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ የሚገኙ ሲቪክ ማኅበራትን ያቀፈ ነው፡፡

የኮሚሽኑን መቋቋም በተመለከተ ከስድስት ወራት በፊት በሒልተን ሆቴል ተገኝተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ከሰጡት የጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት መካከል የነበሩት ተቀማጭነታቸው በስዊድን የሆነው አቶ ሳላሕ ሰባሕ፣ የዚሁ ዋና ኮሚሽን አባል በመሆን በዕለቱ ከነበሩት መካከል ሲሆኑ፣ የኤርትራ መንግሥት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወሳኝ ምዕራፍ እየያዘ መሆኑን ነው የገለጹልን፡፡   

የስትራቴጂው ለውጥ ለአስመራና ለአዲስ አበባ ተቃዋሚዎች?
ሰሞኑን የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ያሟሟቁት በኤርትራ ላይ ተደረገ የተባለው የስትራቴጂ ለውጥ፣ በኢትዮጵያም ‹‹የዴሞክራሲና የብዙኃን ሥርዓት አብቅቶለታል›› ብለው ለሚታገሉ ተቃዋሚዎች በወቅቱ በሰሜን አፍሪካ የተጀመረው አመፅ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት የሕዝቡን ትኩረት ለማስቀየር ነው ቢሉትም፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ግን ተስፋ ሰንቀውበታል፡፡ እንደ መድረክ የመሳሰሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ነውጠኞች›› ተብለው እጅግ እየተገለሉና እየተጥላሉ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ኢሕአዴግ በተጭበረበረ ምርጫ በያዘው ሥልጣን ላይ አመፅ እንዳይነሳበት ከፍተኛ ስጋት ላይ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ጭቆናና ድህነት በሰሜን አፍሪካ አገሮች ውስጥ ካለው የባሰ ነው፤›› የሚል አቋም ያላቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች፣ ‹‹ንግግሩ የማስቀየስ ስልት ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?›› የሚል ጥያቄ የሚያነሱት የኤርትራ መንግሥት የሚከተለው ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ ላለፉት አሥር ዓመታት የቆየና የተለመደ ነው ከሚል አመክንዮ በመነሳት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግን ‹‹መከላከሉ ሰልችቶናል፣ አንድ ቀን ሊከሽፍብንም ይችላል›› በሚል እሳቤ መንግሥታቸው ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሊሸጋገር እንደሚችል ዝተዋል፡፡

በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት፣ መሣሪያ አንስተው የኢትዮጵያ መንግሥትን በትጥቅ ትግል እየፈተኑ ያሉትን ዓማፂዎች በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ የሽብር ሥራዎች እየፈጸመ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ይከሳል፡፡ ከዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ መንግሥት ላይ ላለፉት አሥር ዓመታት ሲከተለው የቆየው በአመዛኙ በመከላከል ላይ የተመሠረተው የውጭ ፖሊሲው ከወዲሁ እንደማያዋጣ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚናገሩት፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በኤርትራ በሚገኘው አሸባሪ የሚለው የአመራር ቡድን ላይ ጠንካራ ዕርምጃ የማይወስድ ከሆነም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተናጠል የራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዕርምጃ ለመውሰድ ዝቷል፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት የአቋምና የስትራቴጂ ለውጥ የሚያደንቁ በኢትዮጵያ የሚደገፉ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ ይህንን የስትራቴጂ ለውጥ ተከትለው ነው በአሁኑ ወቅት ስለ አገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ እየመከሩ ያሉት፡፡

መጋቢት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ ስለ ኒው ዮርክ ጉብኝታቸው አስመልክተው የነበረ ቢሆንም፣ መግለጫው ፖለቲካ ፖለቲካ የሸተተው በኤርትራ ላይ ተደረገ ስለተባለው የአቋም ለውጥ ሲነገር ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ሳምንት በፊት በግልጽ ከጋዜጠኞች ያልቀረበው ነገር ግን ‹‹በኢትዮጵያ የእነ ግብፅና ሊቢያ ዓይነት ነውጥ ሊነሳ ይችላል ወይ?›› በሚል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ የጉዳዩ ጭብጥ (አንኳር) ያደረጉት የኤርትራን መንግሥት (ሻዕቢያ) ዕቅድ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ለነውጥ የተመቻቸ ሁኔታ የለም፤ የሚሞክሩ አይኖሩም ማለት ግን አይቻልም፤›› ያሉዋቸውን አንዳንድ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፣ ከሻዕቢያ አዲስ አበባን ባግዳድ ለማድረግ ተነድፎ የተሰጣቸውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይቦዝኑ አስረግጠው በመናገር፣ በኤርትራ መንግሥት ላይ የአቋም ለውጥ ማድረጋቸውን ያበሰሩት ነበር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ተጠናክሮ የቀረበው፡፡ በእርግጥም ጉዳዩ ታስቦበት መሆኑን የሚያመላክተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ መንግሥት ላይ አለኝ የሚለውን አዲስ መረጃ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማሳወቁን፣ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ያሰበበት መሆኑን ነው፡፡

አቶ ሳላሕ ኤርትራ ውስጥ ስላለው ሁኔታ መጨረሻው ምን እንደሚሆን አስጨንቋቸው ሐሳብ ውስጥ ገብተው ነበር ስለስብሰባው የሚናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ በሰጣቸው የማስፈራሪያ መግለጫዎች ግን ደስተኛ ይመስላሉ፡፡ ‹‹እናንተም ተባበሩን እንጂ፣ አንድ እኮ ነን፡፡ የእኛ ችግር ብቻ አይደለም፣ የእናንተም ነው፡፡ አብረን ተባብረን ነው መለወጥ የምንችለው፡፡ የኢሳያስ መንግሥት ኤርትራን እያጠፋት ነው ያለው፡፡ ይህ እርኩስ ቡድን ሳይጠፋ ልማትም ሰላምን አይታሰብም፤›› ነበር ያሉት እጅግ በተጨናነቀ መንፈስ፡፡ አቶ ሳላሕ፣ ‹‹ብሔራዊ ኮንፈረንሱን›› በተመለከተ ከስድስት ወራት በፊት፣ የዚህ ጉባዔ መሳካት ለኤርትራ ሕዝብ ወደ ትልቅ ምዕራፍ እንደመድረስ ነበር የቆጠሩት፡፡ ‹‹የሚያስጨንቀን አስመራ ውስጥ ያለው ቡድን የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎት እንዳይሔድ ነው፤›› ያሉትን አሁንም በድጋሚ አጽንኦት ይሰጡበታል፡፡

ተስፈኛው ኮሚሽን?
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች የሚያነሱት የኤርትራ መንግሥት አባሎቻቸውን በማዋከብና በማሰር ድርጊቶች ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕገ መንግሥታዊ የመቃወም መብት በመርህም ደረጃ በኤርትራ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ነፃ ፕሬስ፣ ሕገ መንግሥት፣ ዴሞክራሲ የሚሉት አገላለጾች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንደ ቅብጠት የሚታዩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በተለያዩ የውስጥና የውጭ ችግሮች እየተፈተነ የሚንገዳገድ የፕሬስ ነፃነት፣ የመረጃ ፍሰት፣ የመናገርና የመደራጀት መብቶችም ለኤርትራ አፈ ታሪክ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ከኤርትራ ውጪ የሚንቀሳቀሱ የኤርትራ ተቃዋሚ ቡድኖችም፣ ከኤርትራ መጠን የሰፋ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት፣ የታሪክ ንክኪና አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ የመቀናጀት ዜናቸውን ሰምተው ሳይጨርሱ የመበታተናቸውን ወሬ ቢያዳምጡ የሚገርም አልነበረም፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ሕዝባዊ ብሔራዊ ጉባዔ ለማካሔድ እየተንቀሳቀሰ ያለው የተቃውሞ አካል ግን በተቃዋሚ ቡድኖች ብቻ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በብዛት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሑራንና ተጽዕኖ ይፈጥራሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን ግለሰቦች ያካተተ ነው፡፡ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ዳንኤል ተወልደ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከመጋቢት 6 እስከ 12 ቀን 2003 ዓ.ም. በቆየው በዚሁ ሁለተኛ ስብሰባው ኮሚሽኑ የእስካሁን እንቅስቃሴውን ገምግሟል፤ የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ አፅድቋል፤ የፖለቲካ ሚኒፌስቶውንም ተነጋግሮበታል፡፡   

በመጪው ዓመት መጀመርያ ወራት አካባቢ አንዲመሠረት ዕቅድ ስለተያዘበት አገራዊ ሸንጎም ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የሸንጎው አባላት ቁጥር፣ ማንነትና ቅርፅ ላይም ተነጋግረውበታል፡፡ ከስምንት በላይ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ የኤርትራ ድርጅቶች ወደ አንድ የጋራ ጥምረት እንዲመጡ ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በኤርትራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ትግል እንዲካሄድ የተስማሙት እነዚህ ወገኖች፣ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ጭቆናን አሜን ብሎ የሚቀበል አይደለም፤ አመፅ ለማካሄድም ቢሆን ተማሪ አይደለም፤›› በማለት የኤርትራ ወታደሮች ግን በአገራቸው ምን እየሆነ ተረድተውና አውቀው ወገኖቻቸውን ከመግደል እንዲቆጠቡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ወጣት ዳንኤል ይገልጻል፡፡

ኤርትራ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከትም የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ወዳጆች የነበሩት ሙባረክንና የመሳሰሉ ፕሬዚዳንቶች ሥልጣናቸውን በሕዝባዊ ዓመጽ መልቀቅ ትልቅ ትምህርት መሆኑንና ይህም በኤርትራ የማይቀር መሆኑን ነው ተስፋ በማድረግ የሚናገረው፡፡