Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

E-mail Print PDF
User Rating: / 4
PoorBest 

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰሜን አሜሪካ ሕዝቦች እያንዳንዱን ሌሊት በአማካይ ከሰባት እስከ ሰባት ተኩል ሰዓት በእንቅልፍ ያሳልፋሉ፡፡ ይሁንና እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሌሊት ተኝተህ ሳለ ከ60 እስከ 90 በሚሆኑ ደቂቃዎች ውስጥ ደጋግሞ በሚመጣው በባለ ሕልም የእንቅልፍ ዑደት ውስጥ ታልፋለህ፡፡ በዚህ የእንቅልፍ ዑደት ውስጥ አንጎላችን በጣን ንቁ የሚሆን ሲሆን ተመራማሪዎች እንደሚያምኑት አንጎላችን በዚህ ጊዜ አንድ ዓይነት ራስን የመጠገን ሥራ እያከናወነ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ የእንቅልፍ ዑደት ሲስተጓጎልና እንቅልፍ ሲጠፋ ችግሮቹ ይጠራቀሙና በሰውነታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከት ይጀምራሉ፡፡ በተጨማሪም አንጎላችን ሥራውን እንዳያከናውን ሳንካ የሚገጥመው ሲሆን ይህ ደግሞ የንቃት ማነስና በርካታ አካላዊ ሕመሞችን ያስከትላል፡፡

እንደ ካፌይን ያሉ ንጥረ ነገሮች እንቅልፍ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁሙን ኬሚካላዊ ውሕድ ሥራውን እንደያከናውን ሊያግዱት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ሰውነታችን በቂ እንቅልፍ ሳያገኝ ከቀረ አንጎላችን ሳይታወቀን ለጥቂት ሴኮንዶች እንድናሸልብ የሚያደርግበት የራሱ አሠራር አለው፡፡ ዘ ቶሮንቶ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው ከሆነ ‹‹እየሠራህ ያለኸው ነገር ምንም ሆነ ምን፣ እንሕቅልፍ የተነፈገው አንጎልህ አለፍ አለፍ እያለ ቢያንስ ለአሥር ሴኮንድ ቢበዛ ደግሞ ከአንድ ደቂቃ ትንሽ ለሚበልጥ ጊዜ የመጀመርያውን ደረጃ እንቅልፍ (ሸለብታ) ይተኛል፡፡›› በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት መኪና እየነዳህ እያለህ ይህ ዓይነቱ እንቅልፍ ወሰደህ እንበል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ካለው ርዝመት የሚበልጥ ርቀት ትጓዛለህ፡፡ ሰውነትህ ለበሽታ መንስዔ የሆኑ ባክቴሪያዎችን የሚዋጉትን ቲ ሴሎች የሚያመርተው በእንቅልፍ ሰዓት በመሆኑ ሰውነትህን እንቅልፍ መንፈጉ በሽታ የመከላከል አቅምህንም ሊያዳክመው ይችላል፡፡ በተጨማሪም ሰውነታችን የምግብ ፍላጎታችን የተስተካከል እንዲሆን የሚያደርገውን ሌፕቲን የተባለ ሆርሞን የሚያመርተው በእንቅልፍ ላይ እያለን ነው፡፡ በእርግጥም ሰውነታችን ተገቢ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴና ምግብ የሚያስፈልገውን ያህል እንቅልፍም ያስፈልገዋል፡፡

(ንቁ!፣ ጥር 2011)
*******************
እሱና እነሱ
እንደ ኢያሪኮ ግንብ
ሴቶችን ይዞራል
ከመካከላቸው
የአንዷ ልብ ይወድቃል፤
አብረው ይተኙና
ብቻውን ይነሣል፡፡
ደግሞ ሌላ ግዳይ
ደግሞ ሌላ ምርኮ
ልብና ዓይኑን ልኮ
እንደ ገና
ሴቶችን ይከባል፤
መላልሶ ሲያንኳኳ
የአንዷ ልብ ይፈርሳል፡፡
እንዲህ እያደረገ
በምድር እየኖረ
ዐልጋ ላይ አደገ፡፡
ምን ይሻላል!
አንድ ሰው ለአንድ ነው
ቢሉትም እነርሱ፣
አንድን ሰው እንዴት ነው
ትለዋለች ነፍሱ፡፡
(ዳዊት ጸጋዬ፤ አርነት የወጡ ሐሳቦች፣ 2003)

*******************
ሕዝባዊ ተውኔት
ሕዝባዊ ተውኔት ትውፊታዊና ሥርዓተ አምልኳዊ ተውኔት እየተባለም ይጠራል፡፡ ከየአካባቢው ማኅበረሰብ ባህልና ታሪክ ላይ የሚመነጭ የተውኔት ዓይነት ነው፡፡ እንደሌሎቹ ተመድራኪ ሕዝባዊ ኪነጥበብ እንደ ሕዝባዊ ዘፈን፣ ሕዝባዊ ውዝዋዜና ሕዝባዊ መዝሙሮች ሁሉ በአፍሪካ አሁንም የተደናቂነት ሥፍራ አለው፡፡ የየአካባቢውን ታሪክና ባሕል መነሻ የሚያደርገው ሕዝባዊ ተውኔት ትውፊታዊና ሥርዓተ አምልኳዊ ክንዋኔዎች ዋና ግባቶች ናቸው፡፡ ሥርዓተ አምልኳዊ ተፈጥሮ ያለውን የባህላዊ ጋብቻ አተገባበር ከዚህ ላይ ብናነሳ ለሕዝባዊ ተውኔት ተጨባጭ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል፡፡ በብዙ ማኅበረሰብ የባሕላዊ ጋብቻ የሚከተሉትን ዋና ዋና ሒደቶች ያካትታል፡፡
1. መተጫጨት፣
2. የንብረት መዋጮን መገመት (ማጫ የመምታት) ሥነ ሥርዓት፣
3. የወንድ ሙሽራ ጥሎሽ አጣጣል፣
4. ለወንድ ሙሽራ ከነሚዜዎቹ የሚደረግ ግብዣ፣
5. የሴት ሙሽራ ከወላጆቿ ቤት ስንብት፣
6. የሙሽሮቹ ወደ ወንድ ቤት ጉዞ፣
7. በወንድ ቤት የሚደረግ ግብዣና የዳቦ ቆረሳ ሥርዓት፣
8. የጫጉላ ቤት ሥርዓት፣
9. የብርአምባር ሰበረልዎ ብሥራትና
10. የመልስና የቅልቅል (የግጥግጥ) ግብዣዎች ናቸው፡፡
በነዚህ ሁሉ የጋብቻ ክንዋኔዎች ወጥ ታሪክ፣ ቁርጥራጭ ግጭቶች፣ ዘፈኖች፣ ውዝዋዜዎች፣ ከትረካ ጋር የሚዛመዱ ገለፃዎች፣ ምርቃቶች፣ ውይይቶች፣ ቃለ ተውኔቶችና ሌሎች ተውኔታዊ አላባዎች ተካተው ይቀርባሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች ኢመደበኛ በሆነ መድረክ በአንድ ጊዜ ቀርበው ቢታዩ የሕዝባዊ ተውኔት ባሕርያትን በግልጽ ለመመልከት ይቻላል፡፡
(ፋንታሁን እንግዳ፤ ሥነ ፅሁፋዊ ሙዳዬ-ቃላት ከነማብራሪያቸው፣ 2003)

**********************
ቅን ፍርድ
ቅን ፍርድ አንዱ ለሌላው ሊያደርገው የሚገባ ቀዋሚ ነገር ነው፡፡ የሕግም፣ የመንፈስም ይህ ነው፡፡ በክብር መኖር ሌላውን አለመጉዳትና አንዱ ለሌላው ሊያደርግለት የሚገባውንም መፈጸም ነው፡፡
(ጁስቲንያን)

********
ብቸኝነት
ሰው ራሱን ሊሆን የሚችለው ብቻውን እስካለ ድረስ ነው፡፡ ብቸኝነትን ካልወደደ ግን ነጻነትን አይወድም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ነፃ ሊሆን የሚችለው ብቻውን እስካለ ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡
(ሾፐናዎር)

*********
ብልህ ሰው

ብልህ ሰው ጊዜውን ተከትሎ ጠባዩን ቢለዋውጥ ስህተት እንዳደረገ ሊቆጠርበት አይችልም፡፡
(ዲዮኒሴስ ካቶ)

*********
ለአንድ ሰው ጠባዩ በሌሎች መብት ጣልቃ ሳይገባ የራሱን ክብር እንዲጠብቅ የሚረዳው መሆን አለበት፡፡
(ቤከን)

***************

ገራገር
ያልተለመዱ ድርጊቶችን ያሳይ የነበረው በረኛ ለከንቲባነት

የቀድሞው የኰሎምቢያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ነው፡፡ በሜዳ ከሚያሳያቸው ያልተለመዱና ድፍረት የተሞላባቸው ድርጊቶች ውስጥ በቀላሉ በእጁ መያዝ የሚችላቸውን ኳሶች ተገልብጦ በእግሩ በመመለስ ይታወቃል፡፡

ሬኔ አል ሎኰ ሒጉታ በተለይ እ.ኤ.አ በ1995 በዌምብሌይ ስታዲየም ኰሎምቢያና እንግሊዝ በተጋጠሙ ጊዜ ተገልብጦ በእግሩ አድኗል፡፡ በዚህም ‹‹ስኰርፒዮን ኪክ›› (የጊንጥ ምት እንደማለት) የሚል የግሉን መጠሪያ አትርፏል፡፡

ወደ ተቃራኒ ጐል ክልል ኳስ እያንከባለለና ቅጣት ምት እየመታ ኰሎምቢያውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ ያዝናናው ሒጉታ ለከንቲባነት ምረጡኝ ማለቱን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ቢቢሲ የኰሎምቢያውን ዴይሊ ኤል ቲቶምፓ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በኰሎምቢያዋ የጐዊፒኒ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ ለመሆን 4,500 ድምፅ ቢያስፈልገውም ሒጉታ ግን 10,000 አገኛለሁ ብሎ እየተጠባበቀ ነው፡፡

ለ24 ዓመታት እግር ኳስ የተጫወተው ሒጉታ እ.ኤ.አ በ1990ቱ እና በ1994ቱ የዓለም ዋንጫ ለአገሩ ተሰልፏል፡፡ ሰዎችን በማገት ወንጀል ተሳትፏል በሚል ታስሮ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

*      *       *
የ23 ዓመቷ የዓለማችን ወጣት አያት
ሮማኒያዊቷ እንዳለችው ከሆነ፣ ‹‹በ23 ዓመቷ የዓለማችን ወጣት አያት ለመባል የበቃሁት የመጀመርያ ልጄን (ማፊያ) የወለድኩት በ12 ዓመቴ ነበር፡፡›› ግን ሴቶች ይሄን ባያደርጉ ብላም መክራለች፡፡

በ11 ዓመቷ ጎጆ የወጣችው ፊፍካ ያገባችው በሁለት ዓመት የሚበልጣትን የጌጣ ጌጥ ሻጩን ነበር፡፡ እንዲህ ለጋብቻ ያጣደፋትም አባቷ ከሌላ አካባቢ ለመጣ የመሬት ባለቤት ሊድራት መሆኑን በመረዳቷ፣ እርሱን ለማክሸፍ የወሰደችው ርምጃም ከ13 ዓመቱ ልጅ ቶሎ ማርገዝና መደበቅ ነበር፡፡ እናም የበኩር ልጇን ማፊን ስትወልድም ቤተሰቦቿ ተቀበሏት፡፡

እናቷም በ40 ዓመቷ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች፡፡ ፊፍካ ሁለተኛ ልጇን ኒኰላ ከዓመት በኋላ ደግማለች፡፡ ወጣቷ እናት ልጇን ማፊያ ትምህርት ቤት እንድትገባ ብታስገድዳትም፣ ከ6 ወራት በኋላ በ10 ዓመቷ በመውለዷ ፊፍካን አያት አድርጋታለች፡፡ ፊፍካ ‹‹አያት በመሆኔ ከማፊያ በበለጠ በጣም ደስተኛ ነኝ›› ማለቷን ዘ ሰን የተባለ ጋዜጣ ዘግቦታል፡፡ 

*      *       *
የንጉሣውያኑን ጋብቻ ለመዘከር የተሳሳተ ምስል ያተመው
በእንግሊዝ የልዑል ቻርለስና ልዕልት ዲያና ልጅ የሆነው ልዑል ዊልያም በመጪው ሳምንት ንጉሣዊ ጋብቻውን እንደሚፈጽም ይጠበቃል፡፡ ይህንን መነሻ ያደረገው የቻይና ኩባንያ ግን የልዑል ዊልያምን ምስል በማተም ፈንታ የወንድምየውን የልዑል ሔሪ ፎቶ ከዊልያም እጮኛ ከኬት ሚድልተን ጋር አጣምሮ ባመረ አጋጌጥ በመጠጫ ኩባያ ላይ አትሟል፡፡

ሮይተርስ እንዳስነበበው ከሆነ፣ ኩባንያው ሆን ብሎ ያደረገው ይሁን አሊያ በስህተት ስለመሆኑ ምንም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ጥንዶቹ በመጪው ሚያዝያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም. የሚጋቡ ሲሆን፣ እጮኛይቱን ከወደፊት ባሏ ወንድም ጋር አጣምሮ ያወጣው ኩባያን በተመለከተ መግለጫ ከመስጠት ታቅበዋል፡፡

ኩባንያው ጉዋን ደንግ ምስሎቹን ከየትኛውም ንጉሣዊ ቤተሰብ እንዳላገኘ ገልጾ ይልቁንም ለጥንዶቹ መታሰቢያነት ባማረ ጌጥ የተሠራውን መጠጫ ኩባያ ከወዲሁ በ9 ነጥብ 99 ፓውንድ እንዲገዙት ደንበኞቹን እየወተወተ ይገኛል፡፡