Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የየመኑ መሪ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሥልጣን አስረክባለሁ አሉ

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

ከወራት በላይ የፈጀው በየመን ዋና ከተማ ላይ በተለይም በሰነዓ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የተቀሰቀሰውን አመፅ ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ በዚህ ዓመት ማለቂያ ግድም ሥልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ቢገቡም፣ ተቃዋሚዎች ግን ባፋጣኝ ሥልጣን ለቀቀው ይሂዱ በሚለው አቋማቸው አንደፀኑ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ሲል ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ይህንን ከሥልጣን የመልቀቂያ የጊዜ ሰሌዳ ውድቅ አድርገው የቆዩት ፕሬዚዳንት ሳላህ፣ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙና የጦር ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑ ግለሰቦች ለሕዝባዊ አመጹ ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹ በኋላ ግን በአቋማቸው መጽናት አልቻሉም እየተባለ ነው፡፡

በየመን የተቀሰቀሰው አመፅ ከወር በላይ ቢቆይም፣ ባለፈው ዓርብ የተፈጠረው ጉዳይ ግን ብዙዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንት ሳላህን እንዲከዱ ምክንያት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በዕለቱ የመንግሥት አልሞ ተኳሾች በሠልፈኞቹ ላይ ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፣ በጥቃቱም 40 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል፡፡

ከሕንፃዎች አናት ላይ በመሆን አመፅኞቹ ላይ ተኩስ የከፈቱት የመንግሥት የጥበቃ ኃይሎች ድርጊት በአገር ውስጥ ያሉ የጐሳ መሪዎችን፣ የኃይማኖት መሪዎችንና የሠራዊቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ማስቆጣቱ ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል የፈረንሳይ መንግሥትም እንዲሁ ለአመጹ ያለውን ድጋፍ እንዲገልጽ ያደረገው ይኸው የዓርብ ቀኑ ግጭት እንደሆነ ሲነገር፣ የፈረንሳይ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አላን ዡፒ የፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ ከሥልጣን መውረጃ ጊዜ እየቀረበ ነው፤ ይህም አይቀሬ ነው ሲሉ ለሕዝባዊ አመጹ የመንግሥታቸውን ይፋዊ ድጋፍን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የዓርቡ የመንግሥት ዕርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ፣ የፕሬዚዳንት ሳላህ የቅርብ ወዳጅና የአገሪቱ አንደኛ ብረት ለበስ ክፍለ ጦር መሪ የሆኑትን ሜጀር ጄኔራል አሊ ሞህሰን አል አህማርን ያስከፋ መሆኑን ግን ብዙዎቹ ዘገባዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ሜጀር ጄኔራሉ የመን ካሏት ጠንካራ የጦር መሪዎች መካከል እጅግ የሚፈሩና የሚከበሩ ሲሆን፣ የዚህ ሰው ክህደትን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሳላህ ሥልጣን የመልቀቅ አዝማሚያ እያሳዩ መሆናቸው በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡

ሰኞ የጄኔራሉ ጦር ኃይል አባላት የአገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ባንክ በቁጥጥር ሥር ያዋሉ መሆኑ ከሥፍራው ሲገለጽ፣ ሰውየው ከእግዲህ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሠልፈኞች ላይ ጉዳት ማድረስ እንደማይችሉ ሊያቁ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል በፕሬዚዳንት ሳላህ ልጅ የሚመራ የመንግሥት ታማኝ ጦር የቤተ መንግሥቱን ደቡባዊ አቅጣጫ በመያዝ በተጠንቀቅ እንዳለ በመግልጽ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ያሰጋል የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች በርክተዋል፡፡ ትላንት ቀትር ግድም ደግሞ 40 የሚደርሱ የየመን የፓርላማ አባላት ከሥልጣን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታትና በካናዳ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች የሚገኙ አምባሳደሮችም እንዲሁ ፕሬዚዳንቱን በመክዳት ለሕዝባዊ አመጽ ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ አንዳንድ ዘገባዎች ፕሬዚዳንት ሳላህ የጄኔራሉን ክህደት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማለት፣ ‹ለጦር ኃይሉ ሥልጣን አላስረክብም› ብለው በይፋ ቢናገሩም፣ ከጄኔራሉ ጋር የውስጥ ለውስጥ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ደርሰንበታል ሲሉ ዘግበዋል፡፡

የአሜሪካን የፀረ ሽብርተኝነት አጋር የየመን ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ ሥልጣን የመቆያ ዕድሜያቸው ከ48 ሰዓታት እንደማይበልጥ ግን የአካባቢው የፖለቲካ ተኝታኞች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡