በናታን ዳዊት
ከዓመታት በፊት በእድሜ ከፍ የሚሉ ጐልማሶችና ወይዛዝርት፣ ወይም አዛውንቶች “በእኛ ጊዜ” እያሉ የሚጠቅሱትን ዘመን ከአሁን ጋር እያነፃፀሩ “ድሮ ቀረ” የሚሉት አንደበታቸው አንዳንዴ ያናድደኛል፤ አንዳንዴ ደግሞ ያስገርመኝም ነበር፡፡
የንዴቴ ምንጭ እነርሱ አሳለፍን በሚሉት ጊዜ ሁሉ ነገር መልካም፣ ሁሉ ነገር ጥጋብ አድርገው ይህንን ጊዜ ደግሞ ዘመነ ችጋር አድርገው የሚመለከቱ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ አግራሞቴ ደግሞ “ያኔ አንድ ሙክት በአምስት ብር ገዝተን ቆዳውን በሶስት ብር እንሸጠው ነበር፡፡ አንድ ጣባ ክትፎ በአንድ ብር ይበላ ነበር፣ የሚለውና ሌሎች በርካታ ማነፃፀሪያቸው ከወቅቱ ጋር ስናስተያየው ልዩነቱ ለማመን የሚቸግር መሆኑ ነው፡፡
በእርግጥ የዛን ወቅትና አሁን ባለንበት ዘመን መካከል ያለው የገንዘብ የመግዛት አቅም ልዩነት ቢኖረውም፣ ለዚህ ትውልድ አንድ ክትፎ አንድ ብር ይሸጥ ነበር ሲባል ማስገረሙ አልቀረም፡፡ ትራንስፖርት እንደልብ ባልነበረበት ዘመን ዛሬ ለአጭር የታክሲ ጉዞ የሚከፈለው አንድ ብር ከ15 ሣንቲም “በእነርሱ ጊዜ” 15 ሣንቲም ብቻ ነበር ሲባልም ሊገርም ይችላል፡፡ በዋጋ ደረጃ ሌሎችም ብዙ አስገራሚ የሚሆኑብን አጋጣሚዎችን ስንሰማ ቆይተናል፡፡ “የበዚያን ዘመን” ሰዎች አንደበትን አሁን ላይ ሆኜ ስመለከተው ግን እንደቀደሙት አዛውንቶች ወይዛዝርትና ጐልማሶች እድሜ ላይ ሳንደርስ፤ ገና በሰላሳዎቹ እድሜ ላይ ሆነን ከዓመታት በፊት የነበረውን የገበያ አሁን ካለው ጋር ሲነጻፀር “የዛሬ አምስት ዓመት እኮ አንድ ኪሎ ስኳር ይህንን ያህል ነበር የምንገዛው” እንዲህ የተባለውን እቃ ደግሞ ሲሸመት የነበረው በዚህን ያህል ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ያህል ገባ ማለት መጀመራቸውን ለራሴም ይገርመኛል፡፡
ሌላውን ነገር ትተን ከአምስት አመት በፊት እኔ ትዳር በመሰረትኩበት ጊዜ አካባቢ ያለውን የገበያ ዋጋ ከአሁን ጋር ሳነጻጽረው ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረውን ገበያ ለማስታወስ ከባለቤቴ ጋር ወደ ገበያ ወጥተን የወር አስቤዛ በምን ያህል እንገዛ እንደነበር ሳሰላ እኔም ድሮ ቀረ ወደሚለው ወግ መግባት መጀመሬን አረጋግጦልኛል፡፡ ይህም “በዚያ ዘመን ሰዎች” ላይ የነበረኝን አመለካከት እንዳለዝብ አድርጐኛል፡፡
ከቤተሰቦቼ ጋር ከአምስት አመት በፊት ገበያ ወጥቼ አስቤዛ ስናደርግ እያንዳንዱን ዕቃ በምን ያህል ብር እንገዛ እንደነበርም የተወሰኑትን አስታወሰን፡፡ በዚያን ወቅት ሦስት ሊትር እሽግ ዘይት በ23 ብር ገዝተናል፡፡ ስኳር ተወደደ ተብሎ ስድስት ብር፣ አንድ ኪሎ ሩዝ ስድስት ብር፣ ቡና ከ25 - 30 ብር ሸምተናል፡፡ አሁን ደግሞ ሦስት ሌትር ዘይት ከ120 ብር በላይ ደረሰ፡፡ ስኳር ከተገኘ 14 ብር ይገዛል፡፡ በጥቁር ገበያ እስከ 20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
በትራንስፖርት ወጪም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ በአምስት አመት በፊት በነበረ ዋጋ በግሌ ቢሮ ለመሄድና ለመመለስ አምስት ብር ይበቃኝ ነበር፡፡ አሁን በአስር ብር ደርሶ ለመመለስ አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ ጭማሪ ሲደረግ ግን የእኔም ሆነ የሌሎች ሸማቾች ወርሃዊ ገቢያቸው በወራት ልዩነት የሚገሰግሰውን የዋጋ ጭማሪ መወዳደር የሚችል አይደለም፡፡
ስለዚህ በአምስት አመት ውስጥ የትራንስፖርት ዋጋ እጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ በዚህም ከቤቴ መስራያ ቤቴ ድረስ ላለው የደርሶ መልስ ጉዞ በወር 150 ብር ይፈጅብኝ የነበረው አሁን 300 ብር ደርሷል፡፡
ከቢሮ ውጭ የሚደረግ ጉዞዎች ሲታከሉበት ደግሞ የትራንስፖርት ወጪው ወደ አንድ ሺሕ ብር ሊጠጋ መሆኑ ነው፡፡
ለአስቤዛ፣ ለትራንስፖርት፣ ለማብሰያ ለሚወጣ ነዳጅ፣ ለምግብ፣ ለአልባሳት ግዢ፣ የሚወጣው ወጪ በእጥፍ እንደጨመረ የራሴው ልምድ ያስረዳኛል፡፡
በአምስት ዓመት ውስጥ የዚህን ያህል ልዩነት ከታየ በቀጣዩ አምስት ዓመት ሊመጣ የሚችለው ሲታሰብ ያስፈራል፡፡
የዋጋ ንረቱ ያልነካካው ቦታ የለም፡፡ ዛሬ አንድ ብር እየገዛነው ያለው ዳቦ ከአምስት ዓመት በፊት ከ50 ሣንቲም ያነሰ ነበር፡፡ ያኔ አንዳንድ ዳቦ ቤቶች ባለ 20 ባለ 50 የሚሸጡት ዳቦ ነበራቸው፤ አሁን ይህ የለም፡፡ የ20 እና የ50 ሣንቲም ዳቦ ከጠፋ ሦስት ዓመት አልፎታል፡፡ ይህንንም እንደ ታሪክ ማውራት ጀምረናል፡፡
ደረቅ እንጀራም እንዲሁ 50 ሣንቲም፣ 75 ሣንቲም፣ 1.25 ብር፣ 1.50 ብር እያለ ዛሬ 2.50 ብር እስከ 3.00 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑንም አንዘንጋ፡፡
አዲስ ቤት ሰሪ ከአምስት ዓመት በፊት በ120 ብር የገዛው ሲሚንቶ አሁን 400 ብር የመድረሱ ነገር በነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን ያህል የዋጋ ለውጥ እንዳለ ያሰየናል፡፡ የሌሎችን የአገልግሎትና የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ብናክልበት ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ እየተከመረ ያለው የዋጋ እድገት ጭንቅላት ሊያሳምም ይችላል፡፡
ይህ ጉዞ ወደየት እየተጓዘ እንደሆነ ባይታወቅም ሁላችንም እየኖርን ነው፡፡ ሰው ብርቱ! ሸማች ብርቱ፡፡


