Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹የሕትመት ዋጋ ጭማሪው ከፕሬስ አፈና ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም››

E-mail Print PDF
User Rating: / 4
PoorBest 

ወይዘሮ ሙሉ ገብረ ሕይወት፣ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

ጋዜጦችንና ሚስጢራዊ ሕትመቶችን በማተም የሚታወቀው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ ነው፡፡ ከ85 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የማተሚያ ድርጅት ሰሞኑን በጋዜጦች የማሳተሚያ ዋጋ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በተለይ አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች የሚደጉማቸው አካል ባለመኖሩ የታወጀባቸውን የዋጋ ጭማሪ እየተቃወሙ ነው፡፡ በፕሬስ ነፃነት ላይ ያንዣበበ ከፍተኛ አደጋ መሆኑንም አሳታሚዎች እየተነጋገሩበት ይገኛሉ፡፡ ማተሚያ ድርጅቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩትና ከ37 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉወርቅ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሙሉወርቅ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት ድርጅቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ነው፡፡ ሳይታሰብ ለምን ከፍተኛ የማሳተሚያ ዋጋ ጭማሪ እንደተደረገና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የጋዜጣ ወረቀት የሚያስመጣው ከየት ነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- የጋዜጣ ወረቀት የምናስመጣባቸው አገሮች ይለያያሉ፡፡ የምንገዛው በጨረታ ነው፡፡ በግዢ መመርያዎች መሠረት ዝቅተኛ ዋጋ ያለውንና ጥራቱን የጠበቀ ወረቀት ከሚያቀርብልን አቅራቢ ነው የምንገዛው፡፡ አሁን በቅርቡ ከስዊድን አስመጥተናል፡፡ ከዚያ በፊት ለሁለት ጊዜያት ከሩሲያ አስመጥተናል፡፡ ከደቡብ ኮርያ፣ ከቻይናና ከተለያዩ አገሮችም እናስመጣለን፡፡ በአብዛኛው የምናወጣውን ጨረታ የሚያሸንፉት አገሮች እነዚህ ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- ላለፉት በርካታ ዓመታት የጋዜጣ ወረቀት የምታስመጡት ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከደቡብ ኮርያ፣ ከኢንዶኔዥያና ከመሳሰሉት አገሮች ነበር፡፡ አሁን ግን ከስዊድን አስመጥተናል ብላችኋል፡፡ አሁን ለምን ከስዊድን ልታስመጡ ፈለጋችሁ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ያወጣነውን ጨረታ ያሸነፈው የስዊድን አቅራቢ በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጨረታ እንዴት ነው የምታወጡት?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ጨረታ የምናወጣው በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ነው፡፡ በሔራልድ ጋዜጣ ተጫራቾችን እንጋብዛለን፤ ብዙ ተጫራቾች እንዲሳተፉ እንፈልጋለን፡፡ ተጫራቾች ካነሱም በድጋሚ ጨረታ እናወጣለን፡፡ በዚህ መሠረት የምናወጣውን መስፈርት የሚያሟላና የተሻለ ዋጋ የሚያቀርበውን ተጫራች እንመርጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ግዢ የሚፈጽመው በወኪሎች ነው ወይስ በራሱ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- የምናስመጣው ራሳችን ነን፤ ኤጀንት የለንም፡፡ የባንክ ኤልሲ የምንከፍተው ራሳችን ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም ገበያ የሚያሳየው የወረቀት ዋጋ መቀነሱን ነው፡፡ እናንተ ደግሞ በተገላቢጦሽ የማሳተሚያ ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራችኋል፡፡ ለምን?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- የጨመርነው ጭማሪ ከፍተኛ አይደለም፡፡ እኛ ወረቀቱን የምንገዛው በግልጽ ጨረታ እስከሆነ ድረስ የወረቀት ዋጋ ከቀነሰ እኛም የምንገዛው ይቀንሳል፡፡ አሁንም ያቀረብነው ወረቀት በዓለም ላይ ያሉ ወረቀት አቅራቢ ድርጅቶችን አወዳድረን፣ ቅናሽ ዋጋ የሰጠንንና ጥራት ያለው ወረቀት ካቀረበልን ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ላይ ያለው የወረቀት ዋጋ ቀደም ብሎ ከነበረው ዋጋ በእርግጠኝነት ቀንሷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዓለም በቴክኖሎጂ እያደገች ስለሆነ በተለይ ወረቀት የሚጠቀሙ የሕትመት ሚዲያዎች ወደ ኦንላይን እየተቀየሩ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ  የወረቀት ዋጋ እንዴት ሊጨምር ይችላል?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ትክክል ነህ፡፡ የወረቀት ተጠቃሚ ሚዲያዎች ወደ ኦንላይን በሚገቡበት ጊዜ የወረቀት አምራች ድርጅቶችም ይቀንሳሉ፡፡ ማምረት ያቆማሉ፡፡ እኛ ያለን መረጃ በርካታ የወረቀት አምራች ድርጅቶች እየተዘጉ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ሁለታችንም ያለን መረጃ የተለያየ ነው፡፡ በቅርቡም አዲስ ጨረታ እናወጣለን፡፡ ብዙ ተሳታፊዎች ከመጡና የወረቀት ዋጋ ከቀነሰ እኛም እንቀንሳለን፡፡ ከጨመረ ግን እኛም እንጨምራለን፡፡ በኢንተርኔት ያለው መረጃ የወረቀት ዋጋ ቀንሷል የሚል ከሆነ፣ በሚቀጥለው ጨረታ ላይ የማንቀንስበት ምክንያት የለም፡፡ ቀደም ብለን በገዛነው ላይ ግን ጭማሪ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ላይ የጋዜጣ ወረቀት ዋጋ እየቀነሰ ባለበት ጊዜ እናንተ ደግሞ  ከፍተኛ ዋጋ መጨመር የፈለጋችሁት ለምንድን ነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- በፊት ለምንገዛው ወረቀት እስከ ወደብ ድረስ ያለው የጭነት ማጓጓዣ ክፍያ ጨምሯል፡፡ አሁን ግን የፎብ (ፍሬት ኦን ቦርድ) ዋጋ 42 በመቶ እንድንከፍል ተደርገናል፡፡ በፊት በቶን 490 የአሜሪካ ዶላር ነበር፡፡ አሁን ግን 696 የአሜሪካ ዶላር ሆኗል፡፡ ይህ ማለት የጭነት ማጓጓዣው በቶን 206 ዶላር ጨምሯል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋ ሲጨምርባችሁ ለምን ሌላ አማራጭ አልተጠቀማችሁም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- በወቅቱ የነበረው የገበያ ዋጋ በመሆኑ ምንም አማራጭ አልነበረም፡፡ እንዲያውም አብዛኛዎቹ ተጫራቾች ሊያቀርቡልን አልቻሉም፡፡ በወቅቱ ጥሩ ሆኖ ያገኘነው ስዊድንን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጨረሻውን ግዢ የፈጸማችሁት መቼ ነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ትዕዛዝ ስንሰጥ ቀደም ብለን ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ዘንድ ለመድረስ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ስለሚፈጅ፡፡ ስለዚህ ቀደም ብለን ያዘዝነው ከአራት ወራት በፊት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዋጋ መጨመር ምክንያት የሆናችሁ የወረቀት ዋጋ ጨምሮ ሳይሆን፣ በሰሜን አፍሪካና በዓረቡ ዓለም እየታየ ያለውን ተቃውሞ በሚመለከት ጋዜጦች የሚዘግቡት ዘገባ ሕዝብን ሊያነሳሳ ይችላል በሚል ነው፡፡ በጋዜጦች ላይ የማሳተሚያ ዋጋን በመጨመር ከገበያ እንዲወጡ ለማድረግ በእጅ አዙር እናንተ ጫና እንድታደርጉ ከመንግሥት አካላት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ይሆናል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- የእኛ ድርጅት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ነው፡፡ ማንም ተጽዕኖ የሚያደርግብን አካል የለም፡፡ የምንሠራው ቢዝነስ ነው፡፡ አትራፊ እንደመሆናችን መጠን የምንሠራው ለማትረፍ ነው፡፡ ዋጋ ሲጨምርብን እንጨምራለን፤ ሲቀንስልን እንቀንሳለን፡፡ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አለን፡፡ እሱ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የዕለት ተዕለት ሥራ ውስጥ አይገባም፡፡  

ሪፖርተር፡- በሳምንት ስንት ጋዜጦችን ታትማላችሁ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- በየቀኑ ከሦስት በላይ ጋዜጦችን እናትማለን፡፡ ከመንግሥት ጋዜጦች ውጭ፡፡ በሳምንት ውስጥ እስከ 30 ጋዜጦችን እናትማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ብርሃንና ሰላም ቀደም ባሉትም ጊዜያት የወረቀት ዋጋ ጭማሪን በማስመልከት መጠነኛ የማሳተሚያ ዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሳታሚዎችም የነበረውን ጭማሪ ያለምንም ማንገራገር ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ አሁን ግን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ማለትም 50 በመቶ ዋጋ ጭማሪ አድርጋችኋል፡፡ በጣም አልበዛም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ከዚህም በፊት እስከ 40 በመቶ የጨመረበት ጊዜ ነበር፡፡ በጣምም የቀነሰነበትም ጊዜ ነበር፡፡ ብርሃንና ሰላም እንደ ፖሊሲ ነጋዴ ነው፡፡ እኛ የጨመርነውና በትክክል በወረቀት ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ አንድ አይደለም፡፡ አጠቃላይ የጨመረብን ወደ 70 በመቶ ነው፡፡ ሌላውን ወጪ እኛ ችለን የተወሰነውን ጨምረናል፡፡ የፎብ ዋጋ መጨመርና የዶላርና የብር ምጣኔ መለያየት (ዲቫሉዌሽን) በማሳተሚያ ዋጋ ላይ እንድንጨምር አስገድዶናል፡፡ ትክክለኛው የዲቫልዌሽን ለውጥ 22 በመቶ ቢሆንም፣ የጉምሩክ፣ የመርከብና ሌሎችም ተጽዕኖ ከ30 በመቶ በላይ እንዲጨምር ስለሚያደርገው ጭማሪውን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የመጨረሻው የብርና የዶላር ማስተካከያ (ዲቫሉዌሽን) የነበረው በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ጭማሪ ሳታደርጉ ቆይታችሁ አሁን እንድትጨምሩ ያስገደዳችሁ ምንድነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- በዚያን ጊዜ ያልጨመርነው ቀደም ብለን የገዛነው ክምችት ስለነበረን ነው፡፡ በወቅቱ ወረቀት የገዛንበት ጊዜ ስለነበር አልጨመርንም፡፡ ወደፊት ይጨምራል ብለን ደግሞ አንጨምርም፡፡ ክምችቱን የግድ መጨረስ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ጭማሪው እንደሚኖር ከአንድ ወር በፊት ጽፈን አሳውቀናቸዋል፡፡ በዲቫሉዌሽንና በወረቀት ጭማሪ ተጽዕኖ ምክንያት ጭማሪ እንደምናደርግ ቀድመን አሳውቀናል፡፡ ምን ያህል ይሆናል የሚለውን ማወቅ የምንችለው ወረቀቱ ከገባ በኋላ የጉምሩክ፣ የጭነቱና የመሳሰሉት ዋጋ ከተወሰነ በኋላ የምናውቀው ነው በሚል የጭማሪውን መጠን አልተናገርንም ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- በጻፋችሁልን ደብዳቤ ላይ መጠነኛ ጭማሪ እንደምታደርጉ ብትገልጹም የአሁኑ ጭማሪ ግን እጅግ በጣም የበዛና (50 በመቶ) የጋዜጦችን ዕድሜ የሚያሳጥር ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ለምን በቃላችሁ መሠረት መጠነኛ ጭማሪ አላደረጋችሁም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- በጻፍነው ደብዳቤ ላይ መጠነኛ የሚል ቃል አልጨመርንም፡፡ የጻፍነው ‹‹የወረቀት ዋጋ ጭማሪ ስለሚኖር የዋጋ ጭማሪ እንደምናደርግ እናስታውቃለን›› የሚል ነው፡፡ የዲቫሉዌሽን ሁኔታ ስለሚታወቅ ስለሱ አልጻፍንም፡፡ ጭማሪው ግን ብዙ አይደለም፡፡ የዲቫሉዌሽን ተጽዕኖው ብዙ ነው፡፡ ኤልሲ ስንከፍት በአጠቃላይ 30 በመቶ እንከፍላለን፡፡ ኤልሲ ስንከፍት ዶላር 16.3 ቢሆንና ጭነቱ ሲደርስ ግን 16.4 ከሆነ ክፍያ የሚፈጸመው በወቅቱ በነበረው ነው፡፡ የጭነትም፣ የጉምሩክም ሆነ ማንኛውንም ክፍያ የምንከፍለው በወቅቱ ባለው ምንዛሪ ልክ ነው፡፡ ኤልሲ ከፍተን ወረቀቱ ተመርቶ እስከሚመጣ ድረስ አራት ወራት ይፈጃል፡፡ በአራት ወራት ውስጥ ያለችው ትናንሿ ጭማሪ ትልቅ ተጽዕኖ አላት፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለጋዜጣ አሳታሚዎች በቅርቡ የላካችሁት ሌላው ደብዳቤ ደግሞ ‹‹በጋዜጣችሁ ላይ ድርጅታችንን ማስተዋወቅ ስለምንፈልግ የማስታወቂያ ዋጋችሁን ላኩልን›› ይላል፡፡ በደብዳቤው መሠረት ሲላክላችሁ ማስታወቂያ ለማውጣት ሳይሆን ጋዜጦች የሚያገኙትን የማስታወቂያ ገቢ ለመገመትና የማተሚያ ዋጋ ለመጨመር እንዲጠቅማችሁ ነው የተጠቀማችሁበት ተብሏል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሥነ ምግባርን የጠበቀ አካሄድ ነው ይላሉ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ይህ እንዴት እንደተገጣጠመ አላውቅም፡፡ ለዚህ ግን አይደለም፡፡ አንተ ግን የቤት ሥራህን ሠርተህ ነው የመጣኸው፡፡ እኛ ማስተዋወቅ የፈለግነው ነገር አለ፡፡ አንደኛ የአይኤስኦ ሠርቲፊኬሽን ባለቤት ስለሆንን፣ ሁለተኛ ባለፈው ጊዜ ባዘጋጀነው የልማት ድርጅቶች ዝግጅት ላይ ብርሃንና ሰላም ተሸልሞ ስለነበርና ለመጪው ዓመት ለምናዘጋጀው የአጀንዳ፣ የካላንደርና የተለያዩ ሥራዎችን በሚመለከት ከአሁኑ ማስተዋወቅ ስለነበረብን ነው ዋጋ የሰበሰብነው፡፡ ከሕትመት ዋጋ ጭማሪው ጋር ግን ምንም ግንኙነት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሬስ ውጤቶችን ለማፈን እንደመሣሪያ ከሚያገለግሉት መንገዶች አንዱ የሕትመት ዋጋን መጨመር ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ድጎማ በማይደረግላቸው የአገራችን የሕትመት ውጤቶች (በግል ጋዜጦች ላይ) ይህንን ያህል ጭማሪ ማድረጉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ፕሬሶቹን ማፈን አይሆንም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- የሕትመት ዋጋ ጭማሪው ከፕሬስ አፈና ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡ እኛ ነጋዴዎች ነን፡፡ የምናመጣው ወረቀት ዋጋ ከጨመረ ማንኛውም ነጋዴ እንደሚያደርገው መጨመራችን አይቀርም፡፡ እኛ እንደ ነጋዴ የውጭ ምንዛሪ ተመን በመቀየሩ ምክንያት ይህንን ያህል ጨምረናል ብለን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብርሃንና ሰላም በአንድ ጊዜ የጋዜጣ ወረቀት ሲያስገባ ለምን ያህል ጊዜ ይጠቀምበታል?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ከአምስት እስከ ስድስት ወር የሚጠቀምበትን በአንድ ጊዜ ያስገባል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የጨረታ አሸናፊው አገር ውል ከተዋዋለ በኋላ በመሀል የወረቀት ዋጋ ቢወደድ፣ የተጨመረውን ዋጋ የሚከፍለው ማነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- እኛ አንድ ጊዜ ተስማምተን ከተፈራረምን በኋላ በመሀል ለሚመጣው ጭማሪም ሆነ እኛ ከተዋዋልን በኋላ ዋጋ ቢቀነስ፤ የምንረጋው መጀመሪያ በተዋዋልንበት ነው፡፡ ይህንን ባንክም ይቆጣጠረዋል፡፡ ምክንያቱም ለውጭ ግዢ የውጭ ምንዛሪ ጠይቀናልና፡፡ ዋጋ ጨምሯል በሚል ምንዛሪም አንጠይቅም፣ ባንክም አይፈቅድም፡፡ ሌላው ወረቀት የምናስጭነው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ከሚገባባቸው አገሮች በራሱ መርከብ ነው፡፡ ስለዚህ መርከቡ በመሀል ዋጋ ጨምሮብኛል  የሚለው ነገር አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ላይ ለጋዜጣም ሆነ ሌሎች ለሕትመት የሚውሉ ወረቀቶችን በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡት ኢንዶኔዥያ፣ ህንድ፣ ሩሲያና ደቡብ ኮርያ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ከስዊድን ልትገዙ ቻላችሁ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- እኛ ሁሉንም እንጋብዛለን፤ የኢንዶኔዥያ ወረቀት ዋጋ ቅናሽ አላሳየም፡፡ ባወጣነው ጨረታም ላይ አልተሳተፈም፡፡ ደቡብ ኮርያና ሩሲያ ግን ተሳትፈዋል፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻው ጨረታችን የተሻለ ዋጋና የወረቀት ዓይነት የቀረበው ከስዊድን በመሆኑ ልንመርጠው ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕትመት ዋጋ የጨመራችሁት በሁሉም የሕትመት ወረቀቶች ላይ ነው?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- አይደለም፤ በጋዜጣ ወረቀት ላይ ብቻ ነው፡፡ ውድ የሆነውም የጋዜጣ ወረቀት ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው መጥቶ ‹‹እኔ የምፈልገው መጽሐፌ በጋዜጣ ወረቀት እንዲታተምልኝ ነው›› ቢል የሚከፍለው አሁን በተጨመረው ዋጋ ነው፡፡ በሌሎቹም ላይ እየጨመረ ነው፡፡ ከዲቫሉዌሽን በኋላ በሁሉም ዕቃዎች ላይ ጭማሪ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማተሚያ ቤቶች የሚጠቀሙበት ጥሬ ዕቃ በሙሉ ማለትም መቶ በመቶ የሚመጣው ከውጭ ነው፡፡ ወንጂ ያለውም የወረቀት ፋብሪካ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ በማምጣት ነው ወረቀት የሚያመርተው፡፡ ዋጋውም ከውጪዎቹ በላይ ውድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ጨረታ ላይ ምን ያህል አገሮች ይሳተፋሉ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- እንደ ሁኔታው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሰባት አገሮች ይሳተፋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሦስትና አራት አገሮች ይሳተፋሉ፡፡ ዝቅተኛው ግን ሦስት ነው፡፡ አምራች አገሮች በጨረታ ላይ አይካፈሉም፡፡ ለአከፋፋዮች ይሸጡና እኛ ከእነሱ ነው የምንገዛው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የማንበብ ባህል ሊያብብ ነው ሲባል ባለው የፖለቲካና የተለያዩ ተጽዕኖዎች ምክንያት የኋሊት እየሄደ በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች ቀርተዋል፡፡ እናንተ ባደረጋችሁት ያልተመጣጠነ ጭማሪ ምክንያት በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚታተሙት ወደ አንዴ እንደሚታጠፉ እያስታወቁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጋዜጦች ለማተሚያ ቤቱ በዓመት የሚያስገቡት ገቢ  እስከ 12 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ አንፃር ማተሚያ ቤቱ ባደረገው ዋጋ ላይ የሚያስበው ነገር የለም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- አሁን ያለውን ጭማሪ በቀጥታ አስልተን ወጪያችንን እንይ ካልን 70 በመቶ ደርሷል፡፡ ነገር ግን አሁን እያደረግን ያለነው ጭማሪ ጠቅላላውን አይደለም፡፡ ያደረግነው ጭማሪ 44 በመቶ ነው፡፡ ከ20 በመቶ በላይ ያለውን ድርጅቱ እንዲሸፍን አድርገናል፡፡ ይህንንም ያደረግነው ብክነትን በመቀነስ ላይ እንሠራለን ብለን ነው፡፡ የተወሰነውን ወጪ እንቀንሳለን ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ጠቅላላ ወጪያችንን በሙሉ ወደ ደንበኞቻችን አላስተላለፍንም፡፡ ይህ ነው የብርሃንና ሰላም ድርሻ የሚሆነው፡፡ ጭማሪው ከተነገረበት ቀን ጀምሮ እየተጠቀምን ያለነው በአዲሱ ወረቀት ነው፡፡ ሰሞኑን ከአሳታሚዎች ጋር ባደረግነው ውይይት ‹‹ጊዜ ይሰጠን›› ስላሉ የተወሰነች ጊዜ ሰጥተናል፡፡ ሌላውን ማየት ያለብን እንደ ቢዝነስ ነው፡፡ አሳታሚዎች ዲቫሉዌሽን መኖሩን እያወቁ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየከሰረ እንዲቀጥል አይፈልጉም፡፡ ይህም የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ነው፡፡ የመርከብ፣ የጉምሩክና የሌሎች ዋጋ ጭማሪዎችን ሳንጨምር በፎብ ላይ ብቻ የተጨመረብን ምን ያህል እንደሆነ ልናሳያቸው ተስማምተናል፡፡ ሌላው እኛ ያሉንን 900 ሠራተኞች ይዘናቸው ልንቀጥል እንፈልጋለን፡፡ እኛም በጣም በመጨነቅ አውጥተን አውርደን ነው ይህን ጭማሪ ያደረግነው፡፡ ይህ ያዋጣናል? አያዋጣንም? የሚለውን ሁሉ አይተን፣ ለደንበኞቻችን ምን ያህል ብንጨምር ሊያዋጣን ይችላል የሚለውን ሁሉ አይተን ነው ጭማሪውን ያደረግነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብርሃንና ሰላም አትራፊ የልማት ድርጅት በመሆኑ በቅርቡ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ አትራፊ ከሆነ ጋዜጦችም ለትርፉ መገኘት በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ጭማሪ ማድረግ የግድ ከሆነ ለምን መጠነኛ ጭማሪ አላደረገም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ማተሚያ ቤቱ ያተረፈው ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በነበረው የሥራ አፈጻጸም ቢሆንም፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘነው ትርፍ ከጋዜጦች የሕትመት ዋጋ ጭማሪ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- በዋጋ ጭማሪ ምክንያት ጋዜጦች አቅም አጥተው ቢዘጉ፣ የዜጎችን የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ማሳጣት አይሆንም?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- እኛ የምናየው ወይም የምንሠራው እንደ ነጋዴ ነው፡፡ ይህን ከመረጃ ነፃነቱ ሕግ፣ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከብሮድካስት ሕጉና ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር ያለውን ሁኔታ እናንተው የምትሄዱበት ይሆናል፡፡ በዚህ ዙርያ ላይ የእኔ መልስ መሆን ያለበት ወይም ማድረግ ያለብኝ እንደ ነጋዴ በመሆኑ ሌላ የምልህ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሥራዎችን በብቃትና በጥራት እየሠራ ነው ይላሉ?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- ችግሮች አይኖሩም አልልም፡፡ ቢሆንም ግን እየሠራን ነው፡፡ በጋዜጣ ከሆነ 90 በመቶ የሚሆኑት ጋዜጦች የሚታተሙት እኛ ጋ ነው፡፡ በዚያ በኩል ያለውን ገበያ በደንብ ይዘናል እንላለን፡፡ በመጽሐፍም ሆነ በሌላ የራሱ የሆነ ችግር ግን አለው፡፡ ወደ ሌላ አጀንዳ እንዳንሄድ እንጂ እኛ ዘንድ ባለው ችግር ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር የሚያሳትማቸው መጻሕፍት በሙሉ ወደ ውጭ ሄደዋል፡፡ ይህ ከአቅም ጋርም የተያያዘ ነገር ስላለው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ጋዜጦች የፈለጉትን ያህል (በብዛት) እንዳያሳትሙ ይከለከላሉ? የእሑድ ጋዜጣ ቅዳሜ ገብቶ መታተም ሲችል ዓርብ ካልገባ አይደርስም በማለት ታስገድዳላችሁ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ያሏችሁን የማተሚያ ማሽኖችን በአግባቡና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ባለመጠቀማችሁ መሆኑ ይነገራል፡፡

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- አሁን የፈተና ወቅት ስለሆነ አንዱን ማሽን ሙሉ በሙሉ ለፈተናው ለቀን፣ ለጋዜጦች በአንድ ማሽን ነው የምንጠቀመው፡፡ በዚህ ምክንያት ቀደም ብለው እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ትንሽ መጨናነቅ ያለው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በተለይ ቅዳሜ ላይ የመጨናነቅ ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን የሚፈታው ተጨማሪ መሣርያ በመግዛት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ብርሃንና ሰላም የመግዛት አቅም የለውም፡፡ አሁን ግን እዚህ ያሉትንም ችግሮች በመቅረፍ ወደ ውጭ እየሄዱ የሚታተሙትን መጻሕፍት (በተለይ የትምህርት ሚኒስቴርን) ለማስመለስ ፕሮጀክት ሠርተን እንዲፈቅድልን ለተቆጣጣሪው ኤጀንሲ አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሙሉ ቀለም (ከለር) ሕትመትን በሚመለከት ገጾችን ትወስናላችሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተለይ ቢጫ ቀለም ከአገር ውስጥ ስለሚገዛ የተሟላ ቀለም የለንም በማለት የአሳታሚውን ፍላጎት አትጠብቁም፡፡ ለምን?

ወ/ሮ ሙሉወርቅ
፡- እኛ በራሳችን ፍላጎት አንወስንም፡፡ አሳታሚዎች የፈለጉትን ያህል ነው የሚያሳትሙት፡፡ ግብዓቶቹን መቶ በመቶ የምናስመጣቸው ከውጪ ስለሆነ አንዳንድ ጊዜ ችግር አለ፡፡ ግን ያንን ለማጣጣም ይሞከራል፡፡ ቢጫ ቀለምን በተመለከተ እጥረት ሲያጋጥመን ማለትም ያዘዝነው ሲዘገይብን ከአገር ውስጥ እንገዛለን፡፡ ከአገር ውስጥ ገዛን ስንል ግን አገር ውስጥ የሚመረት ሳይሆን ከውጭ አስመጥተው ከሚሸጡ ላይ ነው፡፡ ሌላው የሙሉ ቀለም ሕትመትን ፍላጎት ያወቅነው አሁን ነው፡፡ ቀደም ብለን አውቀን ቢሆን ኖሮ ጥሬ ዕቃዎቹን ቀደም ብለን ማስመጣት እንችል ነበር፡፡ አሁን ግን አውቀነዋል፡፡ አቅርቦቱን በሙሉ አስተካክለን የሚፈለገውን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እጥረት ወይም ችግር አይፈጠርም ማለት አይደለም፡፡