Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር የሚተጉ

E-mail Print PDF
User Rating: / 5
PoorBest 

በጋዜጣው ሪፖርተር

በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በእነሱው የተመሠረቱ ድርጅቶች እያደረጉ ያለው ድጋፍ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ያገኘናቸውን ዶ/ር ኤልያስ ሲራጅ በቴምፕል ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢንዶክሪኖሎጂ እና የስኳር ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የስኳር ሕክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ዶ/ር ኤልያስ፣ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሚሠራውና በዶክተር እናውጋው መሐሪ መሪነት፣ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕክምና ባለሙያዎች አማካይነት በአሜሪካ በተመሠረተው ፒዩፕል ቱ ፒዩፕል የሕክምና ትምህርት ተወካይና የቦርድ አባል ሆነውም ይሠራሉ፡፡ እርሳቸውንና በፒዩፕል ቱ ፒዩፕል በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሚሠሩትና በዌስት ቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት፣ የአረጋውያን ሕክምናና ፓሊየቲቭ ኬር ባለሙያውን ዶ/ር አንተነህ ሀብቴን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዙርያ አወያይተናቸዋል፡፡

በአሜሪካ በሺዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች አሉ፡፡ በፒዩፕል ቱ ፒዩፕል ሥር ደግሞ ከ200 በላይ የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች የበኩላቸውን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የሚሰጡትን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከር ደግሞ ተቋሙ በአንድ ድርጅት፣ አባሎቹ ደግሞ በግለሰብም ደረጃ የበኩላቸውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር ኤልያስ እንደነገሩን በጤናው ዘርፍ የጀመሩትን እገዛ በማጠናከር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋኩልቲ የኢንዶክሪኖሎጂ ንዑስ ስፔሻላይዜሽን ሥልጠና ለማስጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል፡፡ ከሥራ ባልደረባቸው ዶ/ር አንተነህ ጋር በመሆንም ከዚህ ቀደም የተማሩበትን የጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፒዩፕል ቱ ፒዩፕል ጋር በትብብር የሚሠራበትን መንገድ ለማመቻቸትም ዩኒቨርሲቲውን ጐብኝተዋል፤ ተወያይተዋል፡፡

በሌላም በኩል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመቀሌ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከዚሁ ተቋም ጋር በጋራ አብሮ እንዲሠራ ለማስቻል የመግባቢያ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ በጤና ሳይንስ ኮሌጆቹ የንኡስ ስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሞች መከፈት ላይም የበኩላቸውን ለማገዝ እየሠሩ ነው፡፡

ዶ/ር አንተነህ በበኩላቸው፤ የጤና ክብካቤ (ሆስፒስና ፓሊየቲቭ) ከሕክምና ጋር ተጣምሮ እንዲሠራ ከፖሊሲ አውጭዎች ጋር አብሮ መሥራት፣ በሥልጠናና በአቅም ግንባታ ማጠናከር፣ በኤችአይቪ/ኤድስ ዙርያ ከሚሠሩ ጋር በመተባበር የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች በድረ ገጽና በርቀት ትምህርት የታገዘ ሞጁል ተዘጋጅቶላቸው በነፃ የሚሰለጥኑበት ሁኔታን ለማመቻቸት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁሉም ለሕይወት አስጊ በሆኑ ሕመሞችም ክብካቤውን አካትቶ የመሥራት አካሔድ እንዲጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያዩ በጤና ሳይንስ ኮሌጆች በካሪኩለም እንዲካተት በኋላም ክብካቤው ተፈጻሚ እንዲሆን መሥራትም ይገኝበታል፡፡

ሥራዎቻቸውን በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን ግን መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም፣ ችግሮች አሉባቸው፡፡ የተቀላፈጠና ወጥነት ያለው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በተቋም ደረጃ የሚሠራ አለመኖሩ አንድ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም የሥራ ድግግሞሽ ይታያል፡፡ በሌላም በኩል አዳዲስ ፕሮግራም ለማስጀመር እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ በመግባባትና ሥርዓተ ትምህርቱን በመቅረጽ ላይ ለሚገጥሙ ችግሮች ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሠሩ ነው፡፡

ከዲያስፖራው እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ተቋማት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖርም በጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ፋኩልቲዎች ራሱን ችሎ የሚሠራ አካል ሊኖር እንደሚገባ ይህንን በድረ ገጽም ዘላቂና ውጤታማ የሆነ እገዛን ማጠናከር እንደሚያስችልም ይጠቁማሉ፡፡

ከጤና ሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ አለ የሚሉት ችግር እንደሌለና በሁሉም አገራት ያሉ ሥርዓተ ትምህርቶችም የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚጠቅሱት ዶ/ር ኤልያስ፣ ሆኖም ግን መታሰብ ያለበትን አውስተዋል፡፡ ብዙ የጤና ሳይንስ ኮሌጆች መከፈታቸውና ብዛት ያላቸው ተማሪዎችም መሳተፋቸው ትልቅ እመርታ መሆኑን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከትምህርቱ ጥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ፣ የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን ለማሰልጠን በቂ መምህራን አሉ ወይ? ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ በተለያዩ ዘርፎች የሚካኑበት (ስፔሻላይዝድ የሚያደርጉበት) ፕሮግራም ተመቻችቷል ወይ? የሚሉት ላይ ትኩረት መስጠትም ይገባል፡፡

በፒዩፕል ቱ ፒዩፕል በኩል ለእነዚህ ምላሽ ለመስጠት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ሳይንስ ተቋማት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ ነው፡፡

በፒዩፕል ቱ ፒዩፕልም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በውጭ የሚኖሩ የጤና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የተማሩ የጤና ባለሙያዎች ወደ ውጭ ይወጣሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በተለያየ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያምናሉ፡፡ የኢኮኖሚ ምክንያት በሥራው መተማመን ላይ ክፍተት እንዳለ ማመን፣ እና ሌሎችንም የሚጠቅሱት ባለሙያዎቹ ዋናው ነገር የሕክምና ባለሙያዎች ስደትን ማስቆም የማይቻል መሆኑ ታምኖ በአገር ውስጥ ተረጋግተው እንዲሠሩ ለማስቻል ሳቢ ድባብ መፍጠር ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ፒዩፕል ቱ ፒዩፕል ዲያስፖራው የጤና ባለሙያ በኢትዮጵያ እገዛ ለማድረግ እንደሚፈልግ ያውቃል፡፡ የጤና ባለሙያዎችም ኢትዮጵያ መጥተው እየሠሩ ነው፡፡ ብዙ ተቋማትም እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው፡፡ ስለሆነም እንደድልድይ በመሆን ይህንን ኃይል በኢትዮጵያ እንዴት መጠቀም ይቻላል የሚለው ላይም እየሠራ ይገኛል፡፡