በምሕረት አስቻለው
ነፍሰጡር ሴቶች የመገላገያ ጊዜያቸው ከመድረሱ ቀደም ብሎ የአጥሚትና የገንፎ እህል፣ ቅቤና ሌላም ሌላም የወላዶችን ሰውነት ይጠግናሉ የተባሉ ምግቦችን ማዘጋጀት ወግና ባህል ነው፡፡
ከዚህ አልፎ ወላድ ለሚጠይቁ እንግዶችም አቅም በፈቀደ የሚቀማመስ ይዘጋጃል፡፡
አራሶች የሚተኙበት ክፍል የተዘጋጋና ጨለምለም ያለ እንዲሆን መመረጡም እንግዳ አልነበረም፡፡ አራሶች በብዛት እየተመገቡ እንዲያርፉም ይደረጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የተወሰኑ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ አራሶች ከወለዱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ በቤት ውስጥም ሊጠይቃቸው የሚሔድን እንግዳ ከማስተናገድ አልፈው ተርፈው ጉድ ጉድ ሲሉ ሁሉ ያጋጥማል፡፡ የተወሰኑት ለውጡን መልካም ሲሉት፣ ሌሎቹ ደግሞ አይቀበሉትም፡፡
ሲስተር መሠረት ዓለማየሁ፣ አልወለደችም፤ በአዋላጅ ነርስነት ለሁለት ዓመታት ሠርታለች፡፡ አሁንም በየካቲት 12 ሆስፒታል በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ አራሶች የሚተኙበት ክፍል እንዲጨልም፣ ነፋስ እንዳይገባ በርና መስኮት እንዲዘጋጋ መደረጉ፣ በተለያየ መልኩ ጥሩ እንዳልሆነ ይሰማታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የአራሶች ወፍሮ ከአራስ ቤት ላለመውጣት፣ በበቂ ሁኔታ አለመመገባቸው በቂ እረፍት አለማድረጋቸው አይስማማትም፡፡
‹‹እንደ ዱሮው እናቶቻችን ሲያደርጉት እንደነበረው፣ አራሷ አርባ አምስት ቀን ሳይሞላት ከቤት ሳትወጣ ጨለማ ቤት ውስጥ ጭስ እየተጨሰ የምትታረስበት መንገድ ጥሩ የሚባል አይደለም፡፡ እንደ ዛሬው በወለዱ ማግሥት ተነሥቶ መሥራትም አይመረጥም፡፡ ይልቁንም አንዲት ወላድ ስትወልድ ብዙ ደም ስለሚፈስባት ያንን የሚተካ ምግብ እየወሰደች፣ በቂ እረፍትና እንቅስቃሴ እያደረገች እንድትታረስ የሚደረግበት መንገድ መልካም ነው እላለሁ፡፡››
ቀደም ካለው የወላጆች የመታረስ ሒደት የምግብ አዘጋጃጀቱ በተለየ መልኩ ጥሩ እንደሆነና፤ ትልቁ ነገርም ተመርጦ የሚዘጋጀው የምግብ ዓይነትም በሳይንሱ የሚደገፍና ለወላድ ጠቃሚ መሆኑን ሲስተር መሠረት ታሰምርበታለች፡፡ የወላድ እናቶች እንቅስቃሴ ተገድቦ እንዲሁ በተገኘው ሰዓት ሁሉ እንዲመገቡ መገደዳቸው አስፈላጊ እንደሆነም ታምንበታለች፡፡
ከኑሮ ሁኔታ ወይም የሰውነት ክብደት እጨምራለሁ ብሎ ከመፍራት አጥሚትና ገንፎ የመመገብ ነገር በአራሶች እየቀነሰ መምጣቱንም አስተውላለች፡፡ ወላጆች በየሁለት ሰዓቱ ሕፃናት ልጆቻቸውን ማጥባት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ በበቂ ሁኔታ ሲመገቡና ዕረፍት ሲያደርጉ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ነገር ግን ከዚህ ጋር በተወሰነ መልኩ የሚፃረር ነው፡፡
እሷም ወልዳ ከአራስ ቤት ወፍራ መውጣት አትፈልግም፡፡ ነገር ግን ተመጣጣኝ ንጥረ ነገር ያላቸውን ምግቦች በመለየት አማርጦ መመገብ፣ ምግብን በአግባቡ ተመግቦ በቂ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የሰውነት ክብደት መጨመር ሥጋት የሚሆንባቸው ወላድ እናቶች ሊያተኩሩበት የሚገባ ነገር እንደሆነ ታምናለች፡፡
በወለደች በጥቂት ቀን ውስጥ ወደ ቤቷ ልትጠይቃት ጎራ ስትል ራሷ ያስተናገደቻት፣ ልብስ ስታጥብ ያገኘቻትም ወላድ አለች፡፡ በሌላ በኩል ሁኔታው ሙሉ ለሙሉ ሳይቀየር እንደቀድሞ ሆኖ የተመለከተችበት አጋጣሚም እንዳለ ሲስተር መሠረት አጫውታናለች፡፡ በተለይም እናቶች ትክክለኛና ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ መሆን አለበት ብለው የሚያምኑት የቀድሞውን ስለሆነ በእናት ቤትና በእናት እጅ የሚታረሱ ወላዶች በአብዛኛው የሚታረሱት ከሞላ ጎደል በቀድሞው መንገድ ነው፡፡
‹‹አንዲት የጓደኛዬ ጓደኛ ወልዳ ትተኛለች፡፡ በፊት ልጅቷ ስምንት ቁጥር የሚባል ዓይነት ወገብ ነው የነበራት፡፡ እናም ላለመወፈር በጣም ትጥር ነበር፡፡ የታረሰችው እናቷ ቤት ቢሆንም እንድትመገብ የሚሰጧትን ምግብ ተመግቤያለሁ እያለች አብዛኛውን ጊዜ አልጋ ሥር ታደርግ ነበር፡፡ በመጨረሻም እንደተመኘችው ክብደት አልጨመረችም ወገቧም እንደፈለገችው ሆነላት፡፡ ነገር ግን መመገብ እንዳለባት ባለመመገቧ ታምማ ለአንድ ወር ተኛች፤›› በማለት ሙሉ ለሙሉ በመመገብ ረገድ ያለው የቀድሞ ሁኔታ ትክክል እንዳልሆነ በማሰብና ክብደት ላለመጨመር ብቻ መጠንቀቅ ጤናን ከአደጋ ላይ እንደሚጥል ትናገራለች፡፡
እሷ እንደምትለው፣ አራስ ቤት እንደ ዱሮ ዝም ብሎ ተተኝቶ የሚበላበት፣ እንደ አሁኑም ዘመናዊነት ተብሎ በቂ ምግብ፣ እረፍት የማይገኝበት ሳይሆን የወላዶችን፣ የተወለዱ ሕፃናትን ጤና ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ በቀድሞና በአሁኑ መካከል የሚደረግ ነገር ተገቢነት አለው፡፡
ሲስተር ብዙነሽ በኃይሉ፣ በአጠቃላይ ነርስነትና በአዋላጅ ነርስነት ለሠላሳ ሦስት ዓመታት በጅማ ጤና ጥበቃ፣ በጥቁር አንበሳና ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች ሠርተዋል፡፡ በቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥም አገልግለዋል፡፡ ወልደው፣ ከብደዋል፤ የልጅ ልጅም አይተዋል፡፡ ወላዶች ቀደም ባሉት ዓመታት በሚታረሱበት መንገድ ታርሰው አልፈዋል፡፡ የተወሰኑ ነገሮች ተለውጠው የሚስተዋልበትን ዛሬም እንደ አያትና እንደ ባለሙያም እየተመለከቱ ነው፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት በአራስነት ላይ ትልቅ ትኩረት ይደረግ እንደነበር፣ ይህ የሆነው ነፍሰ ጡር ሁለት ነፍስ በመሆኗ ለመጪው ትውልድም በደህና መቆም አለባት ከሚል እሳቤ የመነጨ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚያ ወቅት ክብደት መጨመር ትኩረት አይደረግበትም፡፡ አራሶች ያለውን፣ ቤት ያፈራውን በልተው ወደ ደጅ እንዲወጡ ይደረግ ነበር፡፡ እናቶች ‹‹ውሻ መስለሽ እንዳትወጪና ጎረቤት እንዳይወቅሰኝ›› ይሉ ነበር፡፡ ለእናትነት ለአራስ ቤት የሚሰጠው ክብርና እንክብካቤ ትልቅ በመሆኑ ሁሉም ያቅሙን ቋጥሮ ነው የሚጠይቀው፡፡ እንዲህ አስቦ የመጣን ጠያቂ ለማስደሰት ሲባል ደግሞ ተቋጥሮ ከመጣው ሁሉ አራሶች እንዲጎርሱ ይደረጋል፡፡››
የራሳቸውን ወቅታዊ ጤንነትና ቀጣይ እርግዝናንም ታሳቢ በማድረግ ወላድ እናቶች አመጣጥነው እንዲመገቡ በማሰብ በተለያየ መልኩ በባለሙያዎች እየተሰጠ ያለ ምክር ውጤት እያሳየ እንደሆነ ሲስተር ብዙነሽ ይናገራሉ፡፡ እንደ እሳቸው እይታ የዛሬ አራሶች (ወላዶች) ያገኙትን እንዳገኙ አይመገቡም፡፡ አመጋገባቸውን ለማመጣጠን የሰውነት ክብደታቸውን ከቁመናና ከዕድሜያቸው አኳያ መቆጣጠር ይፈልጋሉ፡፡ የትኛው እንቅስቃሴ ሊጠቅም ወይም ሊጎዳ እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ ሕፃን ልጃቸውን መንከባከብና ንጽሕናቸውን መጠበቅ ለወላዶች እንደማይከብድ ይህ እንቅስቃሴ ከአመጋገብ ጋር በተያያዘም ጠቀሜታ እንዳለው በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡
ወላዶች ይታረሱበት ከነበረው ከቀድሞ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ለወላዶች በተለይም ለእናቶች አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ መቀበል ቀላል ይሆናል? ስንል ለሲስተር ብዙነሽ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ምንም እንኳ ለውጦች ቢኖሩም የቀድሞው ነገር ዛሬም ስላለ ለረዥም ቀናት ከቤት ሳይወጣ ከአልጋ ሳይወረድ እንዲበላና እንዲጠጣ የሚፈልጉ እናቶች በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ይህ ሁሉ እንደ ቀድሞው ይሁን ማለታቸው ካለማወቅ የተነሣ በመሆኑ በሒደት እየተቀየሩ እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡
ከአርባ ዓመታት በላይ በአዋላጅ ነርስነት ያገለገሉት ሲስተር ኪሮስ ከበደ ደግሞ የወላዶች መታረስ ጥሩ ባህል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ወላዶች የሚተኙበት ክፍል ጨለምለም፣ እፍንፍን እንዲል የሚደረግበት ሁኔታ እንደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እየተቆጠረና እየቀረ መሆኑን ያምናሉ፡፡
እንደ እሳቸው አባባል መንቀሳቀስ አይብዛ፣ አድካሚ አይሁን እንጂ ማሕፀን ወደ ቦታው እንዲመለስ ስለሚረዳ ጥሩ ነው፡፡ አራሶች ግልጽ ቦታ ላይ እንዲተኙና አየር እንዲያገኙ ስለሚያደርግም እንደ በጎ የሚታይ ነው፡፡ በቂ እንቅልፍና እረፍት ያለማድረግ ግን እናቶችን ለአእምሮም፣ ለአካላዊም ሕመም ያጋልጣል፡፡


